Saturday, 12 January 2019 14:41

ያሬዳዊው ሥልጣኔ

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(1 Vote)

  ክፍል-፭ የተአምራዊነት አሻራዎች በኢትዮጵያ ፖለቲካና ኪነ ጥበብ ውስጥ
             
     በክፍል ፬ ፅሁፌ የብህትውና አሻራ ያረፈባቸውን የጥንት፣ የመካከለኛውና የአሁን ዘመን የሥነ ፅሁፍ፣ የስዕል፣ የኪነ ህንፃና የሙዚቃ ሥራዎች ተመልክተናል፡፡ ብህትውና ለተአምራዊ መገለጥ የሚያበቃ መንገድ ሲሆን፣ ተአምራዊነት ደግሞ ለብህትውና ትክክለኛነት ማረጋገጫ ሆኖ ያገለግላል። በመሆኑም፣ ብህትውናና ተአምራዊነት ለየብቻቸው መቆም የማይችሉና አንዱ የሌላውን ታሪክ ተሸካሚ ናቸው፡፡  እናም በዛሬው ፅሁፌ ላይ ከብህትውና ጋር የተአምራዊነት አሻራ ያረፈባቸውን የሀገራችንን ታሪክ፣ ፖለቲካና ኪነ ጥበብ እንመለከታለን፡፡
ተአምራዊነት (Mysticism) የሜታፊዚካል ፅንሰ ሐሳብ ሲሆን፣ በዋነኛነት የሚመለከተውም የመንስኤ - ውጤት ፅንሰ ሐሳብን (Concept of Cause and Effect) ነው፡፡ ይህ ፅንሰ ሐሳብ በቦታ የተለያዩ እና በጊዜ የተከታተሉ ሁለት ክስተቶች እንዴትና ማን እንዳያያያዛቸው የሚገልፅ ነው፡፡
‹‹ክስተቶች እንዴት ነው የሚያያዙት?›› የሚለውን እንቆቅልሽ ለመፍታት እስከ ዛሬ ድረሰ የሰው ልጅ ሦስት መልሶችን ሲያቀርብ ቆይቷል፤ አንድም ‹‹አጋጣሚ ነው›› በማለት፣ አሊያም ‹‹መለኮታዊ›› (Mystical) በማድረግ፣ ወይም ደግሞ ‹‹የተፈጥሮ ህግ ነው›› በማለት፡፡ ሳይንሱ ‹‹የተፈጥሮ ህግ ነው›› የሚለውን ሲደግፍ፣ ሃይማኖትና ባህላዊ ማህበረሰቦች ደግሞ ‹‹መለኮታዊ ነው›› የሚለውን ሐሳብ ያራምዳሉ፡፡ በዚህ ፅሁፍ የምንመለከተውም የክስተቶች መያያዝን በተመለከተ ‹‹መለኮታዊ›› የሚያደርገውን የተአምራዊነት ተረክ ነው፡፡
‹‹የክስተቶች መያያዝ መለኮታዊ ነው›› የሚሉ ወገኖች፤ ‹‹መንስኤ››ን የማይታወቅና የሰው ልጅ አእምሮ መረዳት የማይችለው  አድርገው ያስቡታል። በዚህም የተነሳ የሰው ልጅ ክስተቶችን አሜን ብሎ ከመቀበል ውጭ ሊለውጣቸውም ሆነ ሊቆጣጠራቸው አይችልም፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ የተአምራዊነት አስተሳሰብ በኢትዮጵያውያን ስነ ልቦና ውስጥ ብቻ ሳይሆን በኪነ ህንፃችን፣ በኪነ ጥበባችን፣ በታሪክ አተራረካችንና በፖለቲካችንም ውስጥ ይንፀባረቃል፡፡
ኪነ ህንፃ
የኪነ ህንፃ ጥበብ በኢትዮጵያ በጣም የቆየ ሲሆን፣ በሁለቱም ዘመን ሥልጣኔዎች - በአክሱምና በያሬዳዊው ሥልጣኔ - አብቦ የታየ ነው፡፡ በአክሱም ሥልጣኔ ዘመን የነበረው ኪነ ህንፃ ዓለማዊ ይዘት የነበረው ሲሆን፣ ጥበቡም የተገለፀው በዋነኛነት በሐውልትና በቤተ መንግስት ግንባታ ነው፡፡
በሌላ በኩል፣ በያሬዳዊው ሥልጣኔ ዘመን የኪነ ህንፃ ጥበብ መንፈሳዊ ይዘት የነበረው ሲሆን፣ ጥበቡም ገዳማትንና አብያተ ክርስትያናትን በማነፅ ላይ ብቻ ተወስኖ ነበር፡፡ በያሬዳዊው ሥልጣኔ ዘመን የኪነ ህንፃ ጥበብ መንፈሳዊ አገልግሎት ላይ ብቻ መወሰኑ የኪነ ህንፃ ጥበባችን የብህትውና አሻራ ተሸካሚ መሆኑን ሲያሳይ፣ ኪነ ህንፃዎቹ የሚገነቡበት ቦታ በሰው ልጅ ዕውቀት አለመወሰኑ ደግሞ ኪነ ህንፃችን ላይ የታተመውን የተአምራዊነት አሻራ ይገልፃል፡፡
የአክሱም ሐውልቶች ያረፉበት ቦታ ለምን እንደተመረጠ ባይታወቅም፣ በያሬዳዊው ሥልጣኔ ዘመን ግን የኪነ ህንፃ ቦታዎች የሚመረጡት ተአምራዊ በሆነ ‹‹ራዕይ›› ነው፡፡ ማንኛውም አስገራሚ የኪነ ህንፃ ጥበብ ያረፈባቸውን የጥንትና የመካከለኛው ዘመን ገዳማትና አብያተ ክርስትያናት የተሰሩበት ቦታ ለምን እንደተመረጠ ብትጠይቁ፣ ተአምራዊ ከሆነው ራዕይ በስተቀር ሌላ መልስ ማግኘት አይቻልም፡፡
ለምሳሌ፣ በ6ኛው ክ/ዘመን፣ በአፄ ገብረ መስቀል ዘመን የተሰራው የደብረ ዳሞ ገዳም ታሪክን ስንመለከት፣ አቡነ አረጋዊ ገዳም ለመመስረት ቦታ እየፈለጉ ሳለ ትልቅ ዘንዶ እላያቸው ላይ ተጠምጥሞ፣ ዙሪያውን ገደል ከሆነው የደብረ ዳሞ አፋፍ ላይ እንዳደረሳቸው ይነገራል፡፡ በ12ኛው ክ/ዘመን ከአንድ ዲንጋይ ተፈልፍለው የተሰሩት የላሊበላ አብያተ ክርስትያናት ኪነ ህንፃም እንዲሁ የተአምራዊነት ተረክ ተሸካሚዎች ናቸው፡፡
ሙዚቃ
በሙዚቃችን ውስጥ የተአምራዊነት አሻራን የምናገኘው በዋነኛነት በያሬድ አነሳስ ውስጥ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ለኢትዮጵያ ሙዚቃም ግዕዝ፣ ዕዝልና አራራይ የተባሉ የዜማ ቅኝቶችን ያመነጨ፣ እንዲሁም ዜማ ወደ ፅሁፍ የሚቀየርበትን ምልክት የፈጠረ ባለውለታችን ነው፡፡ ሆኖም ግን፣ ያሬድ እንዴት እነዚህን ነገሮች ሊያመነጭ ቻለ ለሚለው ጥያቄ መልሱ ‹‹በተአምራዊነት›› ተሸፍኗል። ተአምራዊው ተረክም፣ ‹‹ያሬድ ዜማዎቹን ያፈለቀው ከራሱ ሐሳብና ህሊና ሳይሆን፣ ከሰማይ በተላኩ ሦስት ወፎች አማካኝነት ወደ ሰማይ አርጎ ዜማውን ከመላዕክት በመስማቱ ነው›› የሚል ነው፡፡
ሥነ ፅሁፍ
የሀገራችን የጥንትና የመካከለኛው ዘመን ሥነ ፅሁፎች በዋነኛነት ገድላትን፣ ቅዱሳን መፃህፍትን፣ ፍትሐ ነገስትን፣ የህክምና፣ የምክርና የተግሳፅ መፃህፍትን፣ ዜና መዋዕሎችንና የቀኖና መፃህፍትን ያካተተ ነው፡፡ ከእነዚህ መፃህፍት ውስጥ አብዛኛዎቹ በተአምራዊነት ተረኮች የተሞሉ ናቸው፡፡ በእነዚህ የተአምራዊነት ተረኮች ውስጥ የሰው ልጅ ነፃ ፈቃድና የማሰብ ኃይል የተደፈጠጠ ሲሆን፣ ሰዎቹ በሚደረግላቸው መለኮታዊ ተአምራት ግን ከተፈጥሮ ህግ ውጭ በሆነ መንገድ ከደዌ ሲፈወሱ፣ ከፈተና ሲያመልጡ፣ ከአደጋ ሲጠበቁ፣ ሞትን ድል አድርገው ሲነሱ፣ ወደ ሰማይ ሲያርጉ፣ በደመና ላይ ሲሄዱ፣ እውነት ሲገለጥላቸው ይታያል፡፡ ይህ የተአምራዊነት አሻራ አሁን ላይ በሚታተሙ መፃህፍት ላይ ሳይቀር ይስተዋላል፡፡
ታሪክ
የተአምራዊነት ተረኮች በአንድ ማህበረሰብ ላይ የሚያሳርፉት ተፅዕኖ በኪነ ህንፃ፣ በሙዚቃውና በሥነ ፅሁፉ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በታሪክ አተራረኩ ላይ ጭምር ነው፡፡ ይሄም በዋነኛነት በዜና መዋዕሎቻችን ላይ የሚታይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሥነ ፅሁፍ ውስጥ የታሪክ ማስረጃ ሆነው ከሚቀርቡ መፃህፍት ውስጥ ዋነኛዎቹ የነገስታት ዜና መዋዕሎች ናቸው፡፡ ዜና መዋዕሎቹ የነገስታቱን አነሳስ፣ ንግስና፣ የጦር ሜዳ ውሎ፣ የህዝብ አስተዳደርና የውጭ የዲፕሎማሲ ግንኙነቶችን በተመለከተ የሰፈረባቸው መዛግብት ናቸው፡፡
ሆኖም ግን ዜና መዋዕሎቹ ‹‹መንስኤን›› የሚያብራሩበት መንገድ በተአምራዊነት የተሞላ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ የአፄ ቴዎድሮስን ወታደራዊ ጀግንነት ‹‹ፍካሬ እየሱስ››ን በማምጣት ‹‹ተአምራዊ›› ሲያደርጉት፣ የአድዋ ድል መንስኤን ደግሞ ‹‹በጦርነቱ ለተሳተፉ መላዕክት›› ይሰጡታል። ኢትዮጵያዊ አእምሮ ሁለት ክስተቶች እንዴት አመክኖያዊ በሆነ ግዴታ (logical necessity) እንደሚተሳሰሩ ስለማናውቅ፣ ብዙ ጊዜ አያያዡን ‹‹ተአምራዊ›› እናደርገዋለን። ለዚህም ነው ገብረ ህይወት ባይከዳኝ፤ ‹‹የእኛ ህዝብ ‹‹አንድ ንጉስ ይሄንንና ያንን አድርጎ በራሱ ጥረትና ብልሃት ነገሰ›› ከሚሏቸው ይልቅ፣ ‹‹በእንዲህ ያለ መለኮታዊ እርዳታ ነገሰ›› ተብሎ ቢነገራቸው ይመርጣሉ›› ያለው፡፡
ፖለቲካ
በኪነ ህንፃችን፣ በሥነ ፅሁፎቻችን፣ በሙዚቃችንና በታሪክ አተራረካችን የተሸከምነው የተአምራዊነት አሻራ በወቅታዊ የሀገራችን ፖለቲካ ላይም አሻራው በግልፅ ይታያል፡፡ ከዚህ በፊት ‹‹ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድን በተአምራዊነት ተረክ›› በሚለው ፅሁፌ ላይ (አዲስ አድማስ፣ ሐምሌ 21፣ 2010) የወቅቱ የሀገራችን ምሁራን፣ የኪነ ጥበብ ሰዎች፣ ሚዲያዎች፣ ህዝቡና የሃይማኖት ሰባኪያን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ‹‹ከእግዚአብሔር የተሰጡን መሪ ናቸው›› በማለት እንዴት የተአምራዊነት ተረክ እያላበሷቸው እንደሆነ ማስነበቤ ይታወሳል፡፡
ባጠቃላይ፣ እንደነዚህ ዓይነት የተአምራዊነት ተረኮች ያሬዳዊው ሥልጣኔ ላይ ሁለት ተፅዕኖዎችን አምጥቶበታል፡፡ የመጀመሪያው፣ የተአምራዊነት ተረኮች ከተፈጥሮ ህግ ውጭ የሆኑ ተረኮችን ሰብስቦ ስለሚይዝ ሰው ከመንስኤ ይልቅ ‹‹ውጤት›› ላይ ብቻ እንዲያተኩር አድርጓል፡፡ ‹‹መንስኤ›› ሳይታወቅ ደግሞ ምንም ዓይነት ሳይንሳዊ ዕውቀትን ማመንጨት አይቻልም፡፡ ይሄም፣ ሥልጣኔው ተፈጥሮ ላይ ትኩረት እንዳያደርግ፣ የተፈጥሯዊ ክስተቶችን መንስኤ እንዳያጠናና ተፈጥሮ ላይ ዕውቀት በማመንጨት ተፈጥሮን መቆጣጠር እንዳይችል አድርጎታል፡፡
ሁለተኛው፣ የተአምራዊነት ተረኮች ሰው ሰራሽ ህግንና የማህበራዊ ተቋማትን ሚና ስለሚያንኳስስ በህግ የበላይነት የሚያምንና በማህበራዊ ተቋማቱም የሚተማመን ማህበረሰብ እንዳይፈጠር አድርጓል። ይሄም፣ ያሬዳዊው ሥልጣኔ የራሱን የማህበራዊና የሥነ መንግስት እሳቤዎችን እንዳያፈልቅ፣ እንዲሁም የሀገርና የዘመናዊ ተቋማት ግንባታ በጊዜ እንዳይጀምር አድርጎታል፡፡
በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ ያሬዳዊው ሥልጣኔ በኋለኛው ዘመኑ ላይ ዘመናዊ ተቋማትን ለመኮረጅ፣ ሳይንሳዊ ዕውቀትንና ቴክኖሎጂን ለመለመን የምዕራባውያንን ደጅ መጥናት ግዴታው ሆኗል። በክፍል-6 ፅሁፌ ብህትውናና ተአምራዊነት ላይ የቆመው ያሬዳዊው ሥልጣኔ፣ በኋለኛው ዘመኑ ላይ ከዘመናዊነት ጋር የገጠመውን የሥልጣን ግብግብ እንመለከታለን፡፡
ከአዘጋጁ፡- ብሩህ ዓለምነህ፤ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ሲሆን “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” ደራሲ ነው፡፡ በኢ-ሜይል አድራሻው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 495 times