Saturday, 12 January 2019 14:43

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(0 votes)

 “መማርና ማወቅ ህይወትን የምናቀልልበት፣ አዲስ ነገር የምንፈጥርበት፣ የነገሮችን ተፈጥሮ መርምረንና አገናዝበን ምክንያታዊ ለመሆን የምንበቃበት፣ ራሳችንንም አለምንም የምንረዳበት፣ ስሜታችንን የምንገራበት፣ አስተዋይና ርህሩህ ሆነን ሰብዓዊ ፀጋ የምንጎናፀፍበት አቋራጭ መንገድ ካልሆነ ፋይዳው ምንድን ነው?---”
       
     ሰውየው በገነት መኖር ናፈቀ፡፡ ከሃጢአት ለመራቅ እጅና እግሩን ቆረጠ፡፡ ላለማየትና ላለመስማት አይኖቹን አጠፋ፤ ጆሮውን አደነቆረ፡፡ ላለመናገር ምላሱን ቆረጠ፡፡ ጠረንና ሽታ እንዳይፈታተኑት አፍንጫውን ደፈነ፡፡ መተንፈስ ሲያቅተው ሞተ። ሰማይ ቤት ደርሶ የገነትን በር አንኳኳ፡፡ “በኑሮ ያልተፈተነ አይገባም” አሉት፡፡ ያልጠበቀው ነበርና ተበሳጨ፡፡ የገሃነብን በር አንኳኳ፡፡ ተመሳሳይ መልስ ተሰጠው፡፡ “የማይሳሳት ያልነበረና ያልኖረ ብቻ ነው” ብለው ደረገሙበት፡፡ መልሰው  ወደ ምድር ወረወሩት፡፡ ይኸው እስከ ዛሬ አለ፡፡ ወደፊትም ይኖራል፡፡ … የትና እንዴት? ብለህ ከጠየቅህ ህፃናቱ ይነግሩሃል፡፡
***
ሰው እንደ ሰው፣ ሰው እንደ ሃሳብ የሚኖረው በስሜት ህዋሳቶቹ ነው፡፡ ይበላል ይጠጣል፣ ያያል ያዳምጣል፣ ያሸታል ይቀምሳል፣ ይዳስሳል አካልና አእምሮው ከነሱ ጋር ያድጋል፡፡ አእምሮው ሲያድግ በነሱ በኩል የሚተላለፍለትን መልዕክት ይተረጉማል - ጥቁር ነው፣ ነጭ ነው፤ ትልቅ ነው፣ ትንሽ ነው፤ ይጮሃል አይጮህም፤ ጣፋጭ ነው፣ መራራ ነው፤ ደስ ያሰኛል፣ ይሰነፍጣል፤ ያቃጥላል፣ ይቀዘቅዛል እያለ፡፡ ነጩን ጥቁር፣ ትልቁን ትንሽ ማድረግ ወይም መራራውን ማጣፈጥ ሲፈልግ ያስሳል፣ ይመራመራል፣ ያገናዝባል፡፡ እየለየና እያወቀ ሲሄድ አካባቢውን ይቀይራል፣ አካባቢው ሲቀየር ሰውየውና ሃሳቡም ይለወጣሉ፡፡
ሃሳብ ዓላማችንን፣ ጊዜያችንንና ኑሯችንን ለውጦአል፡፡ እግርና እጅ ባይኖርህ መኪና ወይም ጋሪ ትነዳለህ፡፡ በድምፅህ ታዛቸዋለህ፡፡ መናገር ባትችል የተገጠመልህ መሳሪያ ሃሳብህን ይተረጉምላቸዋል። አለማየትና አለመስማትም አያደናቅፍህም፡፡ ስልጣኔ ያግዝሃል፡፡ መፃፍ ቢያስቸግርህ ጠቃሚ ሃሳቦችህ አይባክኑም፡፡ ፕሮፌሰር ሃውኪንግ ዓለምን የሚያንቀጠቅጡ ሃሳቦቹን የሚገልፀው በቴክኖሎጂ ነበር፡፡ ዘመኑ ሃሳብና አእምሮ፣ ዕውቀትና ቴክኖሎጂ፣ ሳይንስና ግኝት፣ ጥበብና ፈጠራ የተቆራኙ መሆናቸው የተረጋገጠበት ነው፡፡ አውቃለሁ ማለት ወሬ፣ ተምሬአለሁ ማለት ወረቀት አይደለም። ንገረኝና ልወቅህ ቀርቶ አሳየኝና ልመንህ፣ ስራና ልመስክርልህ ሆኗል፡፡ ጥያቄው፡- “እጅ ከምን?” የሚል ነው፡፡ በዚህ ዘመን “ጅቡ መጣ ዝም በሉ” እያልን ልጆቻችንን ብንዋሻቸው ራሳችንን ማስገመት ነው፡፡ ሊስቁ ወይም ‹እስኪ አሳዩን› ሊሉ ይችላሉ፡፡ በደንብ ስለማናውቀው የዳይኖሰር ባህሪ እንኳ ከኛ የተሻለ ያውቃሉ፡፡
ወዳጄ፡- አለማወቅና አለማገናዘብ ነገር ያበላሻል… እንደ ሰሞኑ ነፋስ፡፡ ለነገሩ አምናም፤ ካችአምናም፣ ከዛም በፊት እንደዛ ነበር፤ዛፎች ተነቃቅለዋል፣ ቤቶች ፈርሰዋል፣ ጀልባዎች ተገልብጠዋል፡፡ ማንኛውም ነገር ከልክ ካለፈ ጉዳት አለው፡፡ አንዳንድ ፀሐፊዎች ኃይለኛ ነፋስን ከድንቁርናና ከስሜት ጋር ያመሳስሉታል፡፡ … “ፅፈዋል አሉ፣ በየመናፈሻው ሁሉ። አበቦችን አትቅጠፉ፣ ለምለሙን ሳር አትርገጡ እያሉ፡፡ … ግን ምን ዋጋ አለው? ነፋስ እንደሁ አያነበው (Though it is written on the sign board, Do Not Pluck The Blossom; It is useless against the wind, it cannot read)”… በማለት፡፡
ወዳጄ፡- ነፋስና እንስሳት ቢያጠፉ ‹ጥፋት› የምንለው እኛ እንጂ እነሱ አይደሉም፡፡ ለነሱ ተፈጥሯቸው ነው፡፡ አያነቡማ!!... አንብበን የማይገባን ወይም ጨርሶ የማናነብ፣ እናውቃለን እያልን የምናጠፋ እኛ ነን፡፡ ለንባብ፣ ለንባብ ሌላው ቢቀር አስርቱ ትዕዛዛትና የቅዱስ ቁርዓንን ጥቅሶች ብቻ ማንበብ በህግና በስርዓት፣ በሰላም በፍቅርና በመረዳዳት ለመኖር በቂ ነበር፡፡ ኢማኑኤል ካንት እንዲህ ሲል ጽፏል፡-
 “Education does not make a man good; it only makes him clever, usually for mischief. Instinct and feeling are more trustworthy than reason” (ምንም እንኳ አንዳንዶች ባይስማሙበትም … )
ወዳጄ፡- መማርና ማወቅ ህይወትን የምናቀልልበት፣ አዲስ ነገር የምንፈጥርበት፣ የነገሮችን ተፈጥሮ መርምረንና አገናዝበን ምክንያታዊ ለመሆን የምንበቃበት፣ ራሳችንንም አለምንም የምንረዳበት፣ ስሜታችንን የምንገራበት፣ አስተዋይና ርህሩህ ሆነን ሰብዓዊ ፀጋ የምንጎናፀፍበት አቋራጭ መንገድ ካልሆነ ፋይዳው ምንድን ነው? ሆዳችንን ለመሙላት እንደምንመገበው ምግብ ከጥቅሙ የሚወገደው ይበዛል፡፡ የዕውቀት ብርሃን ከተሾምንበት ጥቁር ቀሚስ ዘልቆ ሲበራ ካልታየ ውስጣችን ጨለማ ነው፡፡ ባትሪያችን የጎረሰው ሃይል የማያመነጭ፣ የሞተ ድንጋይ ነው፡፡ እንደገና ሊሞላ (Recharge ሊደረግ) ግድ ይላል፡፡ አለበለዚያ … በድህነታችን ላይ ብክነት ሲጨመርበት በራስ ላይ ከሚፈረድ ሞት አይተናነስም፡፡
ወዳጄ፡- እኔ እንደሚገባኝ አገራችን ውስጥ ውስጡን ስትፈርስ የነበረችው በግለሰቦች ጥረት ብቻ ሳይሆን እንደ ስርዓት በተቋም ደረጃ ነው፡፡ አገር ለመገንባትም፣ የዴሞክራሲ፣ የፍትህ፣ የነፃነትና የብልፅግና ልማትንም ለማሳካት እንደ ስርዓት በተቋም ደረጃ ካልሆነ በጥቂት ግለሰቦች ልፋትና ድካም ዕውን አይሆንም፡፡ ወይም ረዥም ጊዜ መራራ ትግልና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መጋፈጥ ግድ ነው። ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን በአጭር ጊዜ መገንባት መቻል ከጀብደኝነት የራቁ፣ በሞራል የታነፁ፣ ራሳቸውንና ህዝባቸውን የሚያከብሩ፣ በአዕምሮ ብስለት የላቁ፣ ደፋር ወጣቶችን አሰልጥኖ የትግሉ አጋር ለማድረግ አቋራጭ ይሆናል፡፡
ወዳጄ፡-ከነፋስ ጀርባ ላይ አትወርድም እንዴ? አትበለኝና ማርጋሬት ሚቸል፣ ቦብ ዲለንና ሌሎች እንደሚሉት፤ መሆን የሚገባው ነገር ሳይሆን---ሃሳብ ሲባክን፣ ድምፅ ሳይሰማ ሲቀር ነፋስ ወሰደው፣ ነፋስ በተነው መባሉ የተለመደ ነው፡፡ ካልተሳሳትኩ ሚካኤል ሌርሞንቶቭ እንዲህ ሲል ጽፎልናል፡-
All the bells are tolling,
But the gale wind takes them away,
No one hears.
   ደወሎቹ ይጮሃሉ፡-
   እሪ! ኡኡ! … እያሉ፣
  በሃይለኛው ነፋስ ውስጥ
መች ይኖራል መደማመጥ!
***
ወደ ተረታችን እንመለስ፡- ከሰማይ የተወረወረው ሰውዬ፤ ምድር ላይ እንዳለና ወደፊትም እንደሚኖር ተጨዋውተናል፡፡ ያለበትን ቦታ የሚያውቁት ህፃናት መሆናቸውንም ጠቁመናል፡፡ ምክንያቱም ሰውየውን የምናገኘው በተረት መጽሐፋቸው ውስጥ ስለሆነ ነው፡፡ አንዳንዶቹ “አያ ድቡልቡሌ” ይሉታል፡፡ ከሰማይ ሲወርድ የወደቀው ውሃ ውስጥ ነው የሚሉ ደግሞ “አያ ቆሪጥ” ብለው ይጠሩታል፡፡ … የተረት ነገር ሲነሳ ይቺ ‹ግጥም› ትዝ አለችኝ፡-
አባትሽ ተረት ነው፣
አንቺም እንቆቅልሽ
ትላንትና ሄዷል
ነገን ምን ዐውቅልሽ፣.
ዛሬ ለኔ ሁኚ
ፀሃዬ `ባክሽ፡፡
በነገራችን ላይ “… the growing citizen must be taught obedience to the law, else a state is impossible” ያለውን ታስታውሳለህ? “Young men are easily deceived, for they are quick to hope” ያለው ሰውዬ ራሱ ነው፡፡ … ሄምሎክ ተግቶ ራሱን ያጠፋው ሊቅ …. ማነው?
ሠላም!!

Read 702 times