Saturday, 12 January 2019 14:44

የሥነ - ግጥም ቋንቋና ዘይቤ

Written by  ደረጄ በላይነህ
Rate this item
(3 votes)

 እንደ እንዝርት በሚሾር ስሜት፣ ከፍ ባለ የምናብ ዓለም ዘልቆ ነገሮችን በጥሞና ማየትና ማሳየት ነው - ግጥም፡፡ ገጠመኞችን እንደገና ማላመጥ፣ የሀሳብ ጎጆ ውስጥ ሌላ ነፍስ ዘርቶ፣ ሳቅና እንባ እያጣቀሱ መትከንም ነው!
ምናልባትም በትክክል ዘወትራዊውን ዐይን አንስቶ፣ በጥልቀት እየቆፈሩ፣ የቁሥልን ደም ማጣፈጥ፣ የደስታን ምዕራፎች መቧጠጥ ነው፡፡ በሙዚቃ ክንፎች፣ በቃላት ሰራዊት፣ ሕይወትን እንደ ገብስ ፈትጎ፣ አበጥሮና ነቅሶ በሚጥም ቃና ማጣጣም ነው - ግጥም!
ገጣሚነትም የዚሁ የእውነት ቁና ቅፅበታዊ ዘርፉ ነው፡፡ በውበት ደን መሀል፤ የቃላት ፋስ ይዞ ውበትን መመልመል፣ መከርከምና ማሳመርም!
ግጥም በራሱ ፍልስፍና አይደለም፡፡ ስብከትና ስነ ዕውቀትም አይሆንም፡፡ ይልቅስ ገጠመኞችን ፈልፍሎ፣ በሌላ ቀለም፣ በሌላ ምናብ፣ ሌላ ውበት ሰጥቶ ለተገጣሚው ተዐምር መፍጠር ነው!! ስለ ግጥም ስናወሳ፤ የግጥም ቋንቋ ዋና ጉዳይ ነው የሚሉ ጠቢባን ቁጥር ጥቂት አይደለም፡፡ ለምሳሌ ሮበርት ፍሮስትን የመሰለ ገጣሚና የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር፤ ይህንን ነገር በእጅጉ ያሰምርበታል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ግጥም ቋንቋው ቢመጥቅ፣ ዘይቤው ቢያሰክር መልካም ነው፡፡ ባይሆንም ግን ቋንቋው ሰማይ ስላላረገ ጥሩ ግጥም አይኖርም ማለት አይደለም ብለው ይሞግታሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አሜሪካዊው የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰርና ፀሐፊ ሎረንስ ፔሪኔ ይገኙበታል፡፡ እንደሳቸው አባባል፤ ሀሳብ ብቻውን ግጥም አይሆንም፡፡ ቋንቋ ብቻም ግጥም አይፈጥርም፡፡ ይልቅስ ሀሳቦችን በወጉ መደርደር፣ የስንኞችን ውቅር ማሳመር፣ ምትና ሙዚቃን ቦታ መስጠትና ሌሎችም ናቸው ግጥምን የሚፈጥሩት፡፡
ይሁንና ብዙ የቋንቋና የስነ ፅሁፍ ምሁራን፣ የገጣሚው ቋንቋ ምናባዊ ምጥቀት ያለው፣ ህልማዊና በፈጠራ ዐይኖች ጉልህነት የደረጀ ሲሆን ይመቻቸዋል፡፡ በቋንቋ አጠቃቀምም ዘመናዊ ዘይቤን አሊያም ጥንታዊ ዘይቤን መከተል ይችላል። ከህልማዊና ከእውናዊ፤ ከዘመናዊና ከጥንታዊ የቱን መምረጥ እንዳለበትና የቱ እንደሚስማማው ገጣሚው ራሱ ያውቃል፡፡
እዚህ ላይ ቃላትን ያለ ቦታቸው መደንጎር፣ ያለ አገባባቸው ማንጠልጠል… ለሀሳቡም ለውበቱም ሸክምና እንቅፋት መሆኑን መግለፁ ነው፡፡ ስለዚህ ገጣሚው ለራሱ ዐውድ የሚስማማና የሚጥመውን፣ ሀሳቡንና ህልሙን የሚያጎላለትን መምረጥ - ለጣዕምም ለዜማም፣ ለነፍስም እርካታ ይሰጣል፡፡
በተለይ የተሰለቹ ቃላትን መጠቀም በእጅጉ ውድቀትና ዝቅታ መሆኑን በርካታ የስነ ግጥም ተንታኞች ይመክራሉ፡፡ ከሁሉ በላይ የቋንቋ አጠቃቀሙና የቃላት ምርጫ መነሻ ፍላጎትና መድረሻ ግብ እንዳለው፣ ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለበትም፡፡
ስለ ቋንቋ አጠቃቀም ሥናነሳ፤ የቃላት ምርጫችን እንደየ ጉዳያችንና የጽሑፍ ዐላማችን ይለያያል፡፡ ስለዚህም አንድ ሳይንቲስትና ገጣሚ ምርጫቸው በእጅጉ ይራራቃል፡፡ ለምሳሌ ሳይንቲስቱ የሚጠቀምባቸው ቃላት ዐላማ፣ ሀሳብን ማስተላለፍ ስለሆነ፣ እንደ ገጣሚው የአደራደርና የውበት ምርጫ አያባትለውም፡፡ በማያሻማ ሁኔታ ያለተደራቢ መልዕክት፣ ያለ አጫፋሪ ስሜት፣ በቀጥታ ለመረጃ ተቀባዩ እንዲደርስ ያደርጋልና መንገዱ ለየቅል ነው፡፡
የገጣሚ ፍላጎት በጥቂትና የተመረጡ ቃላት፣ በተዋበ አሰኛኘትና የሙዚቃ ምት ስሜት እየቃኘ፤ በምናብ ዓለም ውስጥ ያሉን የሕይወት መልኮች አሸብርቆ ማቅረብ ነው፡፡ ስለ ሳይንቲስቱና ገጣሚው ልዩነት ስናነሳ፣ ለምሳሌ “ሰልፈረስ” የሚለውን ቃል በምሳሌነት በመጥቀስ አንድ የስነ ግጥም ምሁር እንዲህ ይላሉ፡- ገጣሚ ይህን ቃል ሲጠቀም በተለዋጭ ፍካሬዎቹ እሳት፣ ጅን፣ ጢስ፣ ቁጣ፣ ሲዖል ወዘተ እያለ ሊተረትረውና ከበርካታ ጉዳዮች ጋር ቋጥሮ ሊያጦዘው ወይም ሊያቀዘቅዘው ይችላል፡፡
በሌላ በኩል ግን ሳይንቲስቱ ያለ ምንም አሻሚ ፍካሬ “ሰልፈረስ” ሲል፤ የሰልፈር ንጥረ ነገርን ያዋሃደ ኬሚካል ማለቱ ነው፡፡ በቃ ሌላ ሻንጣ፣ ሌላ ኪስና ጓዳ የለውም፡፡ በቁጥርና በቀመር ሁሉ ይቀመጣል “H2SO” - ፍካሬም ሆኑ አጫፋሪ ሃሳቦች አያጅቡትም፡፡
ለገጣሚው ግን አጃቢ ሃሳቦች፣ የጦዙ ፍካሬዎች እንደ ዕለት ሲሳይ፣ እንደ ምድረበዳ መና ናቸው፡፡ በአንድ ምት የታጨቁ፣ ብዙና ብዙ የሚዘረዘሩ የብር ኖቶችም ያህል ዋጋ አላቸው - በብዙ አገባብና ዐውድ ይጠበብባቸዋል፡፡ ለዚህም ገጣሚው የቃላት ቱጃር መሆን አለበት ይላሉ፡፡ ይሁንና እንደ ዘበት የቃላት ቱጃር፣ የዘይቤ ባለጠጋ መሆን አይቻልም፡፡ የሥነ ግጥም ተመራማሪና ፀሐፊ የሆኑት ኤክስ ጄ. ኬኔዲና አጋራቸው ለዚህ ምክር አላቸው፡፡ ቃላት ከሰማይ አይወርዱም፤ ወይም ከሜዳ አይታፈሱም፣ ይልቅስ መዝገበ ቃላትንና የተለያዩ የጥበብ መጻሕፍትን በማንበብ ይመጣሉ የሚል እምነት አላቸው፡፡
እኔ ደግሞ የቃላት ኃይልና ምትሃታዊ ዘይቤ ተቀብዖ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህንን በቃላት ልዕቀት፣ በዘይቤ ሞገድ እንዲጠበብ የቱ መጽሐፍ አስተምሯል? ማንስ የሰቀለውን ጉልላት ደርሶ ከላዩ ላይ ቆንጥሮ መካፈል ችሏል? በዚህ ሀሳብ ከሚስማሙት ጋር እስማማለሁ።
ታዲያ የቃላትን ፍች በቅጡ ከመገንዘብ ጋር ከቃላቱ ጋር የተቆራኙ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ ፈርጀ ብዙ ፍቺዎችንም ልብ ማለት ያሻል የሚሉ አሉ፡፡ ስለ ቃላት ፍቺ ስናነሳ ሁለት መደበኛ ፍቺዎች አሉ፡፡ አንደኛው፤ እማሬያዊ ፍቺ ሲሆን ሁለተኛው፤ ፍካሬያዊ ፍቺ ነው፡፡ ይህንን በሚመለከት ዮሐንስ አድማሱ እንዲህ ይላል፡-
የአንድ ቃል ፍቺ በብዙ ስልት ሊጠብ፣ ሊሰፋ፣ ሊሻሻል፣ ሊወሰን ይችላል፡፡ ለዚህ ሁሉ መሰረቱ ግን የቃል መደበኛ ፍቺ ነው፣ የአንድ ቃል መደበኛ ፍቺ በሁለት ሊከፈል ይችላል፡፡
ሀ) የቃሉ ጥሬ ወይም ዝርው ፍቺ
ለ) የቃሉ ዘይቤ ፍቺ - በእንግሊዝኛው “ኮነቴሽን” ይሉታል፡፡ ይህን “ፍካሬ” ብዬዋለሁ፡፡
ዮሐንስ የጠቀሳቸው ፍቺዎች ለገጣሚ በየዐይነቱ የሚጠቅሙና የሚጠበብባቸው ናቸው፡፡ በተለይ ፍካሬያዊ ፍቺዎችን ብዙ የሀገራችንና የሌሎች አገራት ገጣሚያንም ላቅ ላለ የጥበብ ሥራና ለተለየ ፍካሬ ይገለገሉባቸዋል፡፡
ለምሳሌ “ኮከብ” የሚለው ቃል - በእማሬያዊ ፍቺ የተንጣለለ ሰማይ ላይ ሆኖ ብርሃን የሚተፋ፣ ውብ የብርሃን ምንጭ ሲሆን በፍካሬያዊ ፍቺው ግን የላቀ ሥራ የሰራ፣ ከአቻዎቹ በጥበብ፣ በችሎታ በልቀት የበለጠ ልንለው እንችላለን፡፡ ይሄኔ የምናብ እንጎቻዎቻችንን ደምሮ አነባበሮ ያደርጋቸውና የተደራሲን ነፍስ ያጠግባል፡፡
ለዘይቤ አጠቃቀምን ስናይ፣ ዘይቤዎች ስዕላችንን ከፍ አድርገው ጎን ለጎን ከቃላት አጠቃቀም ምናባችንን ያጎሉታል፡፡ በተለይ ሰውኛ ዘይቤ፣ ለዋጭ ዘይቤ፣ ተነፃፃሪ ዘይቤ፣ ከፍ ያለውን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡
ታሪክንና ሥነ - ፅሑፍን በማጠቀስና ያለፈውን ዕውቀት ጨልፎ ካሁኑ ጋር በማንፀር ጥበብን ከፍ ለማድረግ ንቡር ጠቃሽ ፍቱን መድሃኒት ነው፡፡ ሙዚቃን፣ ታሪክን ሥነ - ፅሑፍን ወዘተ ከቀደመው ዘመን ወደ አዲሱ ዘመን እያሻገረ ያስደምማል። ይህ የዘይቤ ዐይነት ደግሞ ሎረንስ ፔሪኔ በሦስት ይከፍሉታል፡፡
Biblical allusion መፅሐፍ ቅዱስ ጠቃሽ
Historic allusion ታሪክ ጠቃሽ
Literary allusion ሥነ ፅሑፍ ጠቃሽ
ይህ የዘይቤ ዓይነት በመጽሐፍ ቅዱስ ወይም በታሪክ የምናውቃቸውን ሰዎ፣ ቦታዎች፣ ግጥሞች እያነፀሩ ላሁኑ የጥበብ ሥራችን ጉልህነትና ውበት ይጨምሩለታል፡፡ ከሥነ ጽሑፋችን “ሰብለወንጌልና በዛብህን” እንደማሳያ መጥቀስ እንችላለን፡፡
ዘይቤዎቹ የግጥም የልብ ትርታ፣ የነፍስ ሙዚቃ፣ በልብ የሚታተም አሻራ አቅላሚዎች ናቸው ክልን የሀገራችንን ግጥች መዳሰስ ያስፈልገናል። ገጣሚዎቻችንም ከፊሉ በሀሳብ ልዕቀት፣ ሌሎቹ በአሰኛነት፣ ስልት፣ የቀሩት ደግሞ በቃላታቸው ፈጥጥነት፣ በዘይቤአቸው ፈርጣማነት ይማርካሉና ጥቂቱን መጠቃቀስና ማየት ያስፈልጋል፡፡ እነዚህን የቀጣዮቹ ጽሑፎች ውላማ እናድርጋቸው፡፡
ግን አንድ ነገር ልናገር በተለይ ንቡር ጠቃሽ ዘይቤን ስንጠቀም ልጓም ሊኖረን ይገባል፡፡ I.A Richards እንደሚሉት፤ “የምሁራዊ ጣሪያ ላይ የተንጠለጠለ እንዳይሆንና ከአንባቢያችን እንዳንተጣጣ ልክ ይኑረን፤ ሲበዛ ማር ይመራል” ብለው እንዳይተርቱብን ሰብሰብ እንበል!

Read 941 times