Saturday, 12 January 2019 14:50

መርሴድስ በአመቱ 2.31 ሚሊዮን መኪኖችን በመሸጥ ቀዳሚነትን ይዟል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  በቻይና የመኪኖች ሽያጭ በ20 አመታት ለመጀመሪያ ጊዜ ቀንሷል

    ታዋቂው የጀርመን የመኪና አምራች ኩባንያ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2018 ብቻ 2.31 ሚሊዮን መኪኖችን በመሸጥ ከአለማችን ኩባንያዎች ቀዳሚነትን መያዙን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ላለፉት ሶስት ተከታታይ አመታት በመኪና ሽያጭ ቀዳሚው የአለማችን ኩባንያ ሆኖ የዘለቀው የጀርመኑ መርሴድስ ቤንዝ፤ በአመቱ ከፍተኛ የሽያጭ ክብረወሰን ማስመዝገቡን የጠቆመው ዘገባ፣ በቻይና ብቻ ሽያጩ በ11 በመቶ ማደጉን አመልክቷል፡፡
ቢኤምደብሊው፣ አውዲና መርሴድስ ቤንዝ እጅግ ዘመናዊ የቅንጦት መኪኖችን በብዛት በመሸጥ ለአስርት አመታት ተፎካካሪ ሆነው መዝለቃቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ በአመቱ 245 ሺህ 240 መኪኖችን የሸጠው የአሜሪካው ቴስላም ከኩባንያዎቹ ተርታ እየተሰለፈ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ፣ በአለማችን ትልቁ የመኪኖች ገበያ እንደሆነች በሚነገርላት ቻይና የመኪኖች ሽያጭ ከሃያ አመታት በኋላ በ2018 ለመጀመሪያ ጊዜ የ6 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን የዘገበው ቢቢሲ፤ በቻይና ገበያ በአመቱ 22.7 ሚሊዮን መኪኖች ብቻ መሸጣቸውን ገልጧል፡፡
ለቻይና የመኪና ሽያጭ ቅናሽ በምክንያትነት ከተጠቀሱት ጉዳዮች መካከል የአገሪቱ ኢኮኖሚ መቀዛቀዝ በአለማችን የመኪና አምራች ኩባንያዎች ላይ ተጽዕኖ መፍጠሩ ይገኝበታል ያለው ዘገባው፤ ፎርድ፣ ቮልስዋገን፣ ጃጓርና ላንድሮቨርን ጨምሮ ታላላቅ የውጭ አገራት የመኪና አምራች ኩባንያዎች በቻይና ገበያ ያስመዘገቡት የአመቱ ሽያጭ መቀነስ ማሳየቱን አመልክቷል፡፡

Read 1143 times Last modified on Saturday, 12 January 2019 14:54