Print this page
Saturday, 12 January 2019 14:55

ቡሃሪ ለናይጀሪያ አለመረጋጋት ጋዳፊን ተጠያቂ አድርገዋል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ናይጀሪያ በ2018 ብቻ ከነዳጅ ዝርፊያ 2.8 ቢ. ዶላር አጥታለች

    ናይጀሪያን ከኢኮኖሚያዊ ቀውስና ከአለመረጋጋት ለማውጣት አልቻሉም በሚል ትችት የሚሰነዘርባቸው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሙሀመድ ቡሃሪ፣ ናይጀሪያን ላለመረጋጋት የዳረጓት ሟቹ የሊቢያ መሪ ሙአመር ጋዳፊ ናቸው ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ናይጀሪያ የሽብርተኞች መናኸሪያ የሆነቺው በጋዳፊና በአጋሮቻቸው ሴራ ምክንያት ነው ያሉት ቡሃሪ፤ ከሊቢያ ሰርገው የገቡ የጋዳፊ ግብረ አበሮች አገሬን እያመሷት ይገኛሉ ሲሉ መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ናይጀሪያን በሽብር እያተራመሷት የሚገኙት የራሷ ዜጎች የሆኑ የቦኮ ሃራም አሸባሪዎችና ታጣቂዎች መሆናቸው የሚታወቅ ቢሆንም፣ ቡሃሪ ግን የአገሬ ገበሬዎች በታሪካቸው ከአርጩሜ በላይ ታጥቀው አያውቁም፤ ኤኬ አርባ ሰባት ታጥቀው ናይጀሪያን የሚያምሷትና አለመረጋጋት ውስጥ የዘፈቋት ሰርጎ ገብ የጋዳፊ ቅጥረኞች ናቸው ሲሉ ወንጅለዋል፡፡
ጋዳፊ በህይወት በነበሩበት ጊዜ ናይጀሪያውያንን ብቻ ሳይሆን የማሊ፣ የቡርኪናፋሶ፣ የኒጀርና የቻድ ዜጎችን እየመለመሉ ጦርነት ሲያስተምሩ ኖረዋል ያሉት ቡሃሪ፤ የጋዳፊን ሞት ተከትሎ ከአገራቸው የፈረጠጡት እነዚህ ሰልጣኞች ወደ ናይጀሪያና ወደ ሌሎች አገራት ዘልቀው በመግባት የሽብር ጥቃቶችን ማካሄዳቸውን ቀጥለዋል ብለዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ፣ ናይጀሪያ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2018 ብቻ ከነዳጅ ጋር በተያያዘ ዝርፊያ 2.8 ቢሊዮን ዶላር ማጣቷን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማስታወቁን ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምዕራብ አፍሪካና የሳህል ቀጠና ቢሮ ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ባለፉት 12 ወራት ጊዜ ውስጥ በአገሪቱ የነዳጅ ሃብት ላይ ከፍተኛ ዝርፊያ የተፈጸመ ሲሆን የባህር ላይ ዝርፊያም ተባብሶ ቀጥሏል፡፡

Read 3101 times
Administrator

Latest from Administrator