Saturday, 19 January 2019 00:00

የአዴፓ እና የህወሓት መሪዎች እርቅ - በፖለቲከኞች ዕይታ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 እርቅ የፈጸሙበት ጉዳይ አለመታወቁ እያነጋገረ ነው


    ሰሞኑን በሃይማኖት አባቶች አሸማጋይነት የአማራና የትግራይ ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች እርቅ የፈጸሙ ሲሆን ጉዳዩ ያልተገለፀ ስምምነትም ተፈራርመዋል፡፡ የህወሓት ሊቀ መንበር ዶ/ር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤልም ሆኑ የብአዴን ም/ሊቀመንበር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፤ በሁለቱ ክልሎች መሃከል በጥርጣሬ የመተያየት አዝማሚያ መፈጠሩን ጠቁመው፣ ይህም የሆነው በራሳቸው በፖለቲከኞቹ ስህተት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
“ህዝብ አልተጋጨም አልተጣላም፤ ችግሩ ያለው እኛ ጋ ነው” ያሉት የክልሎቹ መሪዎች፤ ”እኛ ፖለቲከኞች የሚጠበቅብንን ባለመስራታችን ለዚህ አሳዛኝ የታሪክ ምዕራፍ በቅተናል” ብለዋል፡፡
ሁለቱ መሪዎች ለእርቅና ስምምነቱ ፈቃደኛ ሆነው እርቅ በማውረዳቸው የሽምግልና ቡድኑ  ምስጋና ያቀረበላቸው ሲሆን ፖለቲከኞች ችግሮቻቸውን በእርቅ መፍታት መጀመራቸው የአገሪቱ ፖለቲካ እየተለወጠ መምጣቱን ጠቋሚ ነው ሲሉ  አስተያየት የሰጡ ወገኖች አሉ፡፡     
አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው ፖለቲከኞችና ምሁራን ደግሞ በዚህ አይስማሙም፡፡ ያልተግባቡት በምን እንደሆነ ባልተገለጸበት ሁኔታ የመሪዎቹ እርቅ መፍጠር ውጤት ያመጣል ብለው እንደማያምኑ ይገልጻሉ፡፡    
በዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር የሆኑት ዶ/ር ቴዎድሮስ፤ በሁለቱ መሪዎች መካከል የተደረሰው ስምምነት በምን ጉዳይ ነው የሚለው በግልፅ ለህዝብ ይፋ አለመደረጉ ጥርጣሬዎች እንዲቀጥሉ በር ከፋች ነው፤ ከዚህ ቀደምም እንዲህ ዓይነት ድርድር ተደርጎ አልሰመረም ብለዋል - ከአንድ አመት በፊት በጠገዴ ጉዳይ የተደረገውን ስምምነትና እርቅ በማስታወስ፡፡  
“አሁን የተደረገው ቁስሉን የመጠገን እንጂ በሽታውን ከስር መሰረቱ ማከም አይደለም” የሚሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ፤ “ማን ነው የታረቀው? በምን ጉዳይስ ነው የታረቀው? የሚለው መልስ የለውም” ይላሉ፡፡
የዶ/ር ቴዎድሮስን ሃሳብ የሚጋሩት የአረና ትግራይ ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ ጎይቶም ፀጋዬ በበኩላቸው፤ በመጀመሪያ ለግጭት የዳረጋቸው ጉዳይ ምንድን ነው? በምን መልኩ ፈትተውት ነው የታረቁት? ሲሉ ይጠይቃሉ። የግጭቱና ያለመግባባቱ ምክንያት ባልተገለፀበትና በምን ሁኔታስ እርቁ እንደተቋጨ ባልታወቀበት ሁኔታ ሁለቱ መሪዎች መጨባበጣቸው ከሚዲያ ፍጆታ ባለፈ  ውጤት ያመጣል የሚል እምነት እንደሌላቸው ይናገራሉ፡፡
በሁለቱም በኩል የግዛት (መሬት) ይገባኛል ጥያቄ ባለበትና ምላሽ ባልተሰጠበት፤ የተፈናቀሉ ወገኖች መፍትሄ ባላገኙበት፤ በሁለቱም ወገን ያሉ የፖለቲካ ልሂቃን ፅንፍ ይዘው ባሉበት ሁኔታ የተደረገው እርቅ ምን ዓይነት ነው? ሲሉ ጉዳዩ ለሳቸውም ግራ አጋቢ እንደሆነ አቶ ጎይቶም ይገልፃሉ፡፡ “እኔ እስከሚገባኝ ድረስ የፀባቸው መነሻ የስልጣን ሽኩቻ ነው” የሚሉት አቶ ጎይቶም፤አሁን ያደረጉት እርቅ እንግዲህ በስልጣን ሽኩቻ አንጣላም የሚል ከሆነም የእርቁ ስምምነት በግልፅ ተነግሮ ህዝብ ከመደነጋገር  መውጣት አለበት ብለዋል፡፡ የተፈጠረው አለመግባባት ግን በህዝብ መሃከል አለመሆኑን አቶ ጎይቶም ያሰምሩበታል፡፡
በሁለቱ አካላት መካከል ያለውን ችግር በንግግርና በእርቅ ለመፍታት መሞከሩ መልካም መሆኑን የገለጸው ወጣቱ ፖለቲከኛና ጦማሪ ዮናታን ተስፋዬ፤ ችግሩ ግን ሁለቱ አካላት ብቻ ከሚፈቱት በላይ ሆኗል የሚል እምነት እንዳለው ይገልጻል፡፡ በዚህ እርቅ ውስጥ በወልቃይትና ራያ እንዲሁም ሌሎች አካባቢ ያሉ የፖለቲካ ልሂቃን ቢካተቱ ቢያንስ ወደ መፍትሔው መድረስ ይቻል ነበር የሚለው ዮናታን፤የሁለቱ አካላት ዋነኛ ግጭት የመሬት ሳይሆን የፖለቲካ ቁጭት ነው ይላል፡፡
በአሁኑ ወቅት ህዝቡን ከማንም በላይ ማንቀሳቀስ የሚችሉት አክቲቪስቶች ለጉዳዩ ቀና አመለካከት ከሌላቸው መሪዎቹ ምንም ያህል ቀና ቢሆኑም ዋጋ የለውም የሚለው ዮናታን፤ ለዚህ መፍትሔው እነዚህ ተጽእኖ ፈጣሪ አካላትን በጨዋታው ማሳተፍ ነው ብሎ እንደሚያምን ተናግሯል፡፡  
ሁለቱ የፖለቲካ ሃይሎች ባለፉት 28 አመታት እጅና ጓንት ሆነው ሲሰሩ የኖሩ መሆናቸውን የጠቀሱት የአብን  የህዝብ  ግንኙነት ሃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለ በበኩላቸው፤ ከዚህ አንፃር የአዴፓ ወይም የአብን ሳይሆን የህዝቡ ጥያቄ ሳይመለስ የመሪዎቹ መጨባበጥ መሬት ላይ ያለውን ሃቅ አይቀይረውም ብለዋል፡፡ ዋነኛው የአማራ ህዝብ ጥያቄ የፖለቲካ ውሣኔ የተወሰደበት ታሪካዊ ርስቱ እንዲመለስለት ነው የሚሉት አቶ ክርስቲያን፤ ሁለቱ መሪዎች እነዚህን ጥያቄዎች የት አድርሰዋቸው ነው የተስማሙት ሲሉ የስምምነቱ ፍሬ ሃሳብ በግልጽ መቀመጥ እንዳለበት ያመለክታሉ፡፡    
የአረና ሊቀ መንበር አቶ አብርሃ ደስታ ግን የተለየ ሃሳብ ነው ያላቸው፡፡ “ሁለቱ አካላት አስቀድሞም ቢሆን ለጦርነት የተዘጋጁ መስለው የሚቀርቡት ህዝብን ለማታለል ነው፤ ህዝብ ሰግቶ ከእነሱ ጋር እንዲቆም፣ የህዝብ ተቃውሞ ወደ እነሱ እንዳይዞር ነው እንጂ ብአዴንና ህወሓት አብረው እንደሚሠሩ አስቀድሞም ይታወቃል” ያሉት አቶ አብርሃ፤ወትሮም ቢሆን ያን ያህል አለመግባባት በድርጅቶቹ መሃከል አለመኖሩን ይናገራሉ፡፡ “መሪዎቹ ለፖለቲካ ፍጆታ እየተጣሉ ቢታረቁም በአማራና በትግራይ ህዝብ መካከል መቼውንም ግጭት አይኖርም፤ ሠላም ይሠፍናል” ብለዋል አቶ አብርሃ፡፡
በሁለቱ ክልሎች መካከል ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት በዋናነት ሁለቱ አካላት ብቻ ሳይሆኑ ጉዳዩ ይመለከተኛል የሚሉ የፖለቲካ ልሂቃን፣ አክቲቪስቶች እንዲሁም ህዝቡ የተሳተፉበት ውይይትና መግባባት ተደርጐ ነው እርቅ መከናወን ያለበት የሚሉት የዩኒቨርሲቲ መምህሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ፤ በአጠቃላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ነው ብሔራዊ እርቅ መፈጠር ያለበት ብለው እንደሚያምኑ ይገልጻሉ፡፡   
“ወደ ትክክለኛው መፍትሄ እንሂድ ከተባለ የምንጣላው መሬት ስለጠበበን ሳይሆን በስልጣን ሽኩቻ ስለሆነ ዋነኛ መግባባቱ መፈጠር ያለበትም በስልጣን ሽኩቻው ጉዳይ ነው” ይላሉ፤ዶ/ር ቴዎድሮስ፡፡
በመጀሪያ ገለልተኛ የሆነ የመፍትሄና እውነት አፈላላጊ ኮሚሽን ተቋቁሞ ምርመራና ማጣራት ተደርጎ በሚያቀርበው ሪፖርት ላይ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ተሰባስበው መክረው ከተስማሙ በኋላ ነው እርቅ የሚሰምረው የሚሉት አቶ ክርስቲያን በበኩላቸው፤ለብሔራዊ እርቅም መደላደል የሚሆነው በመጀመሪያ የፍትህ መስፈን ነው ብለዋል፡፡
የሁለቱ ክልል ርዕሰ መስተዳደሮች ከእርቁ በኋላ በጋራ በሰጡት መግለጫ ላይ ሁለቱም ከእንግዲህ ለሰላም እንሰራለን ብለዋል፡፡ ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል፤ “በኛ በኩል የሚጀመር ግጭትም ሆነ የሚተኮስ ጥይት የለም” ሲሉ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው፤ “ለሰላም እሰራለሁ ይሄ ቃሌ ነው፤ባህርዳር ስሄድም አይቀየርም” ብለዋል፡፡  

Read 3294 times