Saturday, 19 January 2019 00:00

የሎሚ ገበያ

Written by  ፊያሜታ
Rate this item
(9 votes)

  አሥራ ሦስት ብር ከሰባ አምስት ሳንቲም!...
’በቂ ነው’ ሲል አሰበ፡፡ ፈጣሪ ይሁን እስካለና የአዲሳባ ኮበሌ ፍቅር እስከሻተው ድረስ፣ ይህ ገንዘብ በአንድ ቀን እጥፍ ይሆንለታል፡፡
ንጋትን በመናፈቅ ሲገላበጥ ነው ያደረው። ሌሊቱን እንቅልፍ ሸሽቶት ነው ያነጋው፡፡ ዘገምተኛው ሌሊት እንደ ምንም ሲገባደድ የተከራያትን ጠባብ ክፍል ዘግቶ በተስፋ ተሞልቶ ከግቢው ወጣ፡፡
’ከንጋቱ 11 ሰዓት ከ15 ደቂቃ’ አለችው፤ ከኪሱ ያወጣት ማሰሪያ አልባ የእጅ ሰዓቱ፡፡ ተስፋ አድርጓል። ፈጣሪ ይሁን ካለ ይህንን ገንዘብ እጥፍ ያደርገዋል፡፡
የመንደሩን ኮረኮንች መንገድ ነጠቅ ነጠቅ እያለ በመራመድ ጨርሶ ዋናው አስፓልት ላይ ደረሰ። ከመገናኛ አቅጣጫ አራት ኪሎን አቋርጠው ወደ አውቶቡስ ተራ የሚወነጨፉ የንጋት ታክሲዎችን ተመለከተ፡፡ ወደ አገር ቤት የሚጓዙ መንገደኞችን ይዘው ወደ አውቶቡስ ተራ ይከንፋሉ፡፡
«አውቶቡስ ተራ?...» ሲል ጠየቀ፣ ስትበር መጥታ ከፊቱ ወደቆመችው ታክሲ እያየ። ወደዚያው ናት። በመንገደኛና በሻንጣ የተጣበበችው ታክሲ ውስጥ ገብቶ ተቀመጠ፡፡ መንገደኞችን ሲያይ አንዳች ስሜት ተፈጠረበት። እነዚህ ሁሉ የነገውን የጥምቀት በዓል አገር ቤት ለማሳለፍ የታደሉ ይሆናሉ ሲል አሰበ፡፡ አገር ቤት ታወሰው፡፡
የጥምቀት ድምቀት ታሰበው። እንጀራ ፍለጋ ከአገር ቤት ወጥቶ ከአዲስ አበባ ምድር ከተቀላቀለበት ጊዜ አንስቶ ዓመት በዓል ሲመጣ ልቡ ይሸበራል፡፡ የአገር ቤት ትዝታው ገንፍሎ ይወጣና ይተናነቀዋል፡፡ ከዓመታት በፊት ያሳለፋቸውን የጥምቀት ትዝታዎች እያሰበ ይተክዛል፡፡ ታቦታቱ ወደ ጥምቀተ ባህሩ ሲወርዱ ከእኩያዎቹ ጋር «ሃይ ሎጋ» እያለ ታቦታቱን ያጅብ ነበር... ዛሬ የንጋት መንገደኞችን ያጅባል፡፡
አትክልት ተራ አካባቢ ሲደርስ ሂሳቡን ከፍሎ ከታክሲዋ በመውረድ ማልዶ ተነስቶ ገበያውን ካጥለቀለቀው ሸማች ጋር ተቀላቀለ፡፡ የሕዝቡ ትጋት አስገረመው፡፡ ህዝቡ ገና ሳይጠባ ወደ ገበያ አቅንቶ የሚፈልገውን ይሸምታል፡፡ የአትክልት ተራ ገበያ የሚቆመው ገና ዶሮ ሳይጮህ ነው፡፡
መጥረጊያና መወልወያ እያዞረ ያፈራትን ገንዘብ በግርግር መሐል እንዳይነጠቅ በመስጋት ራሱን ከሌባ እየጠበቀ፣ ዞር ዞር እያለ ገበያውን መቃኘት ቀጠለ፡፡
ሎሚ ሊገዛ ነው የመጣው፡፡ ተስፋውን የጣለው ሎሚ ላይ ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የሎሚ መወደድ ጎልቶ የታየው በዚህች ንጋት ነው፡፡
ተከራክሮ በደህና ዋጋ የሸመተውን ሎሚ በፌስታል ቋጥሮ ከገበያው ወጣ፡፡
ያንጠለጠለው ሎሚ ዝም ብሎ ሎሚ አይደለም።
ሕይወቱን በመጠኑም ቢሆን የሚቀይርለት ሎሚ ነው፡፡ ድንገት በዓይን ፍቅር የተለከፉ ወጣቶችን የተደበቀ ስሜት ይፋ የሚያወጣ፣ ከእጃቸው ተወርውሮ ጡት ላይ በማረፍ የፍቅር ተማፅኖን የሚገልጽ ሎሚ ነው የተሸከመው፡፡
ቀኑን እንደ በፊቱ መጥረጊያና መወልወያ ይዞ በመዞር ሳይሆን የሎሚውን ዋጋ ሲተምን ነው ያሳለፈው፡፡
የአራዳው ጊዮርጊስ በሕዝበ ክርስቲያን ታጅቦ፣ የሰማዕታት ሐውልትን አልፎ ወደ ጃንሜዳ እያቀና ነው፡፡ ጃንሜዳ በሰው ተጥለቅልቋል፡፡ ሴቶች ለጥምቀት ያሉትን ለብሰው አምሮባቸው ይታያሉ። እዚህም እዚያም ክብ እየሰሩ ይጨፍራሉ።
መዘምራኑ ያሸበሽባሉ፡፡ የሃርሞኒካው፣ የመዝሙሩ፣ የባህላዊ ሙዚቃው ድምጽ በአንድ ተቀይጦ ይወርዳል።
 ጃንሜዳ ቀውጢ ሆኗል፡፡
«ሎሚ... አለች ሎሚ» ይላል እሱ - ከተከመረው ሎሚ አጠገብ ቆሞ፡፡ አላፊ አግዳሚውን ይቃኛል፡፡ ሰብሰብ ብለው እየተሳሳቁ የሚመጡትን ወጣቶችን አሻግሮ ይመለከታል፡፡
’መቼም ከእነዚህ ሁሉ አንደኛው ዓይኑን ባንዷ ቆንጆ ላይ ይጥላል’ ሲል ያስባል፡፡
’ምን አስፈራው?’ ይላል፡፡ ’ሎሚ እንደሆነ ሞልቷል። ገዝቶ መወርወር ነው መፍትሄው’ ይላል ለራሱ፡፡
«ሎሚ...ምርጥ ሎሚ» ይላል ወደ ወጣቶቹ እያየ።
እነሱ ግን አይሰሙትም፡፡
እየተቃለዱ ባጠገቡ ያልፋሉ፡፡
ጨፋሪዎች እየተተራመሱ ሲያልፉ ሎሚዎቹን ይረጋግጧቸዋል፡፡
አላፊ አግዳሚውን በስስት ሲመለከት ይቆይና ዓይኖቹን ቁልቁል ወደ ሎሚዎቹ ይልካቸዋል።
አንዳቸውም አልጐደሉም፡፡
ከትከሻው አውርዶ ያስቀመጣቸው  ቦታ አለቀቁም፡፡
«ሎሚ... አለ ሎሚ...»
ድምጹ መስለል ጀምሯል። ታቦታቱ ወደ ማደሪያቸው ገብተው ቢጠናቀቁም ሴቱ ወንዱ የክቱን ለብሶ ከዚያ እዚያ ይላል፡፡
«ሎሚ... ምርጥ ሎሚ» አለ፤ አለፍ ብሎ ብቻውን የቆመውን መነጽር የሰካ ቀላ ያለ ወጣት እየተመለከተ። ፍቅር ፈላጊ መስሎ ታየው። ምናልባት አንዷን ዓይቶ ቀልቡን ነስቶት ፈዞ ይሆናል ሲል አሰበ፡፡
«አትፍዘዝ... መፍትሔው ይኼውልህ» ሊለው አስቦ ፈራና ተወው፡፡
«ሎሚ...ሎ...»
አለ አሻግሮ ወጣቱን እየተመለከተ።
ወጣቱ ወደ እሱ አቅጣጫ ሲመጣ በማየቱ ደስታ ተሰማው፡፡
ወጣቱ አጐንብሶ ሎሚዎቹን ሲነካካ ቆይቶ ቀና አለ፡፡
«ምረጥ... ግዴለም ዋጋ እንስማማለን» አለ ሎሚ ሻጩ፡፡
ወዲያው ግን...
«ብርቱካን የለህም?»
የሚለውን የወጣቱን ድምጽ ሰማ፡፡
ጃንሜዳ በሕዝብ ተጥለቅልቋል፡፡
ከዚህ ስፍር ቁጥር ከሌለው ሕዝብ መካከል ግን ሎሚ ፍለጋ ወደ እሱ ጐራ የሚል አልገጠመውም፡፡
«ሎሚ... ምርጥ ሎሚ» የሚለው ድምጹ ብቻ ሳይሆን ሕዝቡም መቀነስ ይዟል፡፡
እየመሸ ነው፡፡
ከበው ከሚዘፍኑት ወጣቶች መካከል የወጣው ነጭ በነጭ የለበሰ ጎልማሳ፣ አልቃሻ ሕፃን አስከትሎ ወደ ሎሚው ተጠጋ፡፡
«ይሄው...ሎሚ... ምርጥ ሎሚ...» አለ ጎልማሳውን በስስት እየተመለከተ፡፡
«ስንት ስንት ነው?» ጠየቀ ጎልማሳው፤ በጣቱ ሎሚዎቹን እየነካካ እንዳጐነበሰ፡፡
የመጀመሪያውን ሎሚ ጠያቂ እያየ ዝም አለ።  
’በቃ- የአዲስ አበባ ወጣት ሎሚ መወርወር የሚጀምረው እንዲህ ሲመሽ ነው’ ማለት ነው ሲል እያሰበ ነበር፡፡
’ከአሁን በኋላ ሎሚ ፈላጊዎች ወደ እኔ መጉረፍ ይጀምራሉ’ አለ፡፡ ወጣቶች የእሱን ሎሚ ፍለጋ ሲጋፉ ታየው፡፡ በጃንሜዳ ሰማይ ላይ ሎሚዎች እንደ ቀስት ሲወረወሩ... .ጡት ላይ ሲነጥሩ... ጡት ተሻግረው ልብ ሲደቁ ታየው፡፡
«ስንት ስንት ነው?» ደግሞ ጠየቀ ጎልማሳው።
ከበስተኋላው የቆመው ሕፃን ለቅሶውን አጠናክሮ ቀጠለ፡፡ ጎልማሳው ሎሚዎቹን ትቶ ፊቱን ወደ ሕፃኑ አዞረ፡፡
«አይዞህ ባቢዬ... አሁን ይሻልሃል...» አባበለው፡፡
ሕፃኑ ግን ማልቀሱን ቀጠለ፡፡ ከሰዓታት በፊት የበላው ምግብ ስላልተስማማው ሽቅብ ሊለው ነው፡፡
«አይዞህ... አሁን ይሻልሃል...
ከዚህ ሎሚ ስትመጥበት ይሻልሃል-»
የሕፃኑ ለቅሶ ጨመረ፡፡
«በቃ... በቃ... የምን ለቅሶ ነው!?...
ሎሚው ያሽልሃል» እያለ ሎሚ ያማርጣል፡፡
«ሎሚ አልወድም!... ይመረኛል!... እምቢ!... ያንን ነው የምፈልገው!... ያንን ግዛልኝ...» አለ ልጁ፤ ወደ ቀኝ አቅጣጫ እየጠቆመ፡፡
ሎሚ ሻጩ የልጁን እጅ ተከትሎ አሻግሮ ተመለከተ፡፡
’ጀላቲ’ የምትሸጠው ሴት፣ በገዢ ተጨናንቃለች፡፡

Read 2806 times