Saturday, 19 January 2019 00:00

ያሬዳዊው ሥልጣኔ

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(1 Vote)

 ክፍል- ፮ ተ አምራዊነት፣ ብህትውናና ዘመናዊነት
               
      የኢትዮጵያውያንን ባህል፣ ስነ ልቦና፣ ሥነ ምግባር፣ ታሪክ፣ ኪነ ጥበብና እምነት ከቀረፁት ነገሮች ውስጥ ዋናዎቹ ተአምራዊነትና ብህትውና ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለት ፅንሰ ሐሳቦች ኢትዮጵያውያን ስለ ዓለም ያላቸውን አመለካከትና ስለ መንስኤ ፅንሰ ሐሳብ (Concept of Cause) ያላቸውን መረዳት የወሰኑ ናቸው፡፡ በመሆኑም፣ ከኢትዮጵያውያን ሁለንተናዊ ማንነትና ሀገር ግንባታ ጀርባ እነዚህ ሁለት ፅንሰ ሐሳቦች አሉ፡፡
ይህ ተአምራዊነትና ብህትውና ላይ የተመሰረተው ሁለንተናዊ የማንነትና የሀገር ግንባታ ግን ከ17ኛው ክ/ዘ ጀምሮ የተለያዩ ተግዳሮቶች ገጥሞታል፤ ተግዳሮቶቹም የመጡት ከኢትዮጵያውያን ፈላስፎች፣ የታሪክ ፀሐፊያንና ከዘመናዊነት አራማጅ ምሁራን ነው፡፡ ከፈላስፎችና ከታሪክ ባለሙያዎች የመጡትን ተግዳሮቶች ለክፍል 7 እና 8 ፅሁፋችን እናቆየውና በዚህ ርዕስ ሥር የምንመለከተው በተአምራዊ - ብህትውና (Ascetic-Mysticism) እና በዘመናዊነት መካከል ያለውን የሥልጣን ግብግብ ነው፡፡
ተአምራዊነትና ዘመናዊነት
ተአምራዊነት በዋነኛነት የሚመለከተው ‹‹የመንስኤ - ውጤት›› ግንኙነትን (cause-effect relationship) እንደሆነ ቀደም ባሉት ፅሁፎቼ ገልጫለሁ፡፡ በአውሮፓ የመካከለኛውን ዘመን በመተካት በ15ኛው ክ/ዘ የመጣው ዘመናዊው ዓለም ግልፅ ካደረጋቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ፣ የአንድ ሀገር ህዝብ የዕድገት ዕጣ ፈንታው ከሚወሰንባቸው ነገሮች ውስጥ ዋነኛው ስለ ‹‹መንስኤ›› ያለው መረዳት (Concept of Cause) ነው፡፡ በመካከለኛው ዘመን ስለ ‹‹መንስኤ›› ያለው መረዳት ‹‹ተአምራዊነትና ሚስጥራዊነት›› ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡ ይሄም ግንዛቤ ‹‹አካላዊ ክስተቶች ኢ-አካላዊ መንስኤ አላቸው›› ከሚል ድምዳሜ የሚነሳ ነው፡፡ በዚህ ‹‹የተአምራዊነት›› ግንዛቤ ውስጥ ለዘመናት ከኖሩ ህዝቦች ውስጥ እኛ ኢትዮጵያውያንም እንገኝበታለን።
በዚህም የተነሳ የእኛ ህዝብ ከድሮ ጀምሮ ‹‹አካላዊ ክስተቶች ኢ-አካላዊ መንስኤ አላቸው›› በሚል ድምዳሜ ህይወቱን ሲመራ ኖሯል፡፡ ይሄም ማለት ‹‹አካላዊ ክስተቶች (ለምሳሌ - ህይወትና ሞት፣ ከበሽታ መዳን፣ ሐብትና ድህነት፣ ዝናብና ጎርፍ፣ ድርቅና ረሃብ፣ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች፣ ሹመትና ንግስና …ሁሉ) መንስኤያቸው ከመንስኤ - ውጤት ዝምድና (cause and effect relationship) ውጭ የሆነ መለኮታዊ ተአምራት ነው›› የሚል ድምዳሜ ነው፡፡
‹‹መንስኤው እኛ ከምንረዳው በላይ የሆነ መለኮታዊ ተአምራት ነው›› የሚለው ድምዳሜ ከእምነት በስተቀር ማረጋገጫ የለውም፤ ልክ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የሚታየው ነገር ከማይታየው እንደመጣ በእምነት እናምናለን›› እንዳለው፡፡ በዚህ ድምዳሜ ውስጥ ‹‹እኛ የምናቀው ውጤቱን እንጂ መንስኤውን አይደለም›› የሚል አስተሳሰብ አለ፡፡ እናም መንስኤው በሰው ልጅ አእምሮ የማይታወቅ ሚስጥራዊ ነው፡፡
በመሆኑም፣ የ‹‹ተአምራዊነት›› አስተሳሰብ የሚያውቀው በተጨባጭ የሚያየውን ውጤት (effect) እንጂ በጊዜና በቦታ የራቀውን መንስኤ ወይም ደግሞ በረቂቅነት ያለውን መንስኤ (cause) አይደለም፡፡ በዚህም የተነሳ፣ ነጋድራስ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ እንዳለው፣ የእኛ ህዝብ መንስኤን የመረዳት አቅምም ሆነ ፍላጎት እንዳይኖረው ሆኗል። በሌላ አነጋገር፣ ከድሮ ጀምሮ የተቀረፅንበት የ‹‹ተአምራዊነት›› አስተሳሰብ፣ መንስኤን የማወቅ ፍላጎትና አቅም እንዳይኖረን አድርጎናል፡፡ በዚህም የተነሳ፣ መንስኤን የመረዳት ስንፍናችንን መልሰን በ‹‹ተአምራዊነትና በሚስጥራዊነት›› እንሸፍነዋለን፡፡ ‹‹ተአምራዊ ማብራሪያ›› (Mystical justification) የተማረውን ካልተማረው፣ አዋቂውን ካላዋቂው መለየት ስለማይችል፣ ለዕውቀት መትጋትን አያበረታታም፡፡
ዘመናዊው ዓለም የመጣው፣ መካከለኛው ዘመን ሲመራበት የነበረውን ‹‹ተአምራዊነት›› ላይ የተንጠለጠለውን ‹‹የመንስኤ ፅንሰ ሐሳብ›› በመቃረን ነው፡፡ ይሄም አዲስ ‹‹የመንስኤ ፅንሰ ሐሳብ››፤ ‹‹እግዚአብሔር ዓለምን ፈጥሮ በራሱ ህግጋት እንዲመራ ትቶታል እንጂ በእያንዳንዷ ተፈጥሯዊ ክስተት ውስጥ ጣልቃ አይገባም፡፡ በመሆኑም፣ ዩኒቨርሱ ሜካኒካዊ በሆነ የመንስኤ - ውጤት ህግ የሚመራ ነው›› የሚል ነው፡፡ በዚህም፣ ዘመናዊው ዓለም ‹‹ማንኛውም ክስተት መንስኤ አለው፤ መንስኤውም በሰው ልጅ አእምሮ መታወቅ ይችላል›› የሚል አዲስ ግንዛቤ ይዞ መጣ፡፡ እንግሊዛዊው ፈላስፋ ፍራንሲስ ቤከንም (1561-1626)፤ ይሄንን ሐሳብ በማቀንቀን ወደፊት ወጣ፡፡
‹‹መንስኤ›› ሳይታወቅ ዕውቀትን ማመንጨት አይቻልም፡፡ የዕውቀት ምንጭ ‹‹መንስኤን›› ማወቅ እንጂ ‹‹ውጤትን›› መመልከት አይደለም፡፡ መንስኤን ‹‹በተአምራዊነት›› አስደግፈው ሲያብራሩ የነበሩ ህዝቦች በታሪካቸው ተጠቃሽ የሆነ ዕውቀት ማመንጨት ስላልቻሉ ተፈጥሮ ሰልጥኖባቸዋል፤ መንስኤን ‹‹በአመክንዮ›› ማብራራት በቻሉ ህዝቦችም ለመገዛት ተገደዋል፡፡ ያሬዳዊው ሥልጣኔ በ1500 ዓመታት ዕድሜው ውስጥ ሳይንሳዊ ዕውቀትን ማመንጨት ያልቻለውና ከአፄ ቴዎድሮስ ጀምሮ የመጡ ነገስታት፣ ዕውቀት ልመና የፈረንጅ ደጅ ሲጠኑ የነበሩት፣ እንዲሁም ሀገራችን በቅኝ ገዥዋ ጣሊያን ልትደፈር የቻለችው ያሬዳዊው ሥልጣኔ ስለ መንስኤ የነበረውን መረዳት ከተአምራዊነት ማላቀቅ ስላልቻለ ነበር፡፡
‹‹ማንኛውም ክስተት መንስኤ አለው፤ መንስኤውም በሰው ልጅ አእምሮ መታወቅ ይችላል›› የሚለው አውሮፓዊው አዲስ ግንዛቤ ለሳይንስ መወለድ ምክንያት ሆኗል፡፡ በዚህም፣ አውሮፓውያን ‹‹የተአምራዊነት›› ተረኮቻቸውን ወደ ጎን በመተው፣ ተመራማሪዎቻቸውን ተፈጥሮን እንዲያጠኑ በየመስኩ ማሰማራት ጀመሩ፡፡ የእኛ ሊቃውንት ዓለም እንዳያሳስታቸው ከዓለም ሲሸሹ፣ አውሮፓውያኑ ግን ተፈጥሮን ለማጥናት ወደ ዓለም ይሄዱ ነበር፡፡ በዚህ በአዲሱ ግንዛቤም፣ ሰው ‹‹እኔ የእግዜር አምሳል ነኝ›› እያለ ከዓለም ተነጥሎ ዓለምን በራሱ ተምኔት ማብራራቱ ቀረና እሱ ራሱ የሚጠና የዓለም አካል ሆነ፡፡ በዚህም፣ አመክንዮ ተአምራዊነትን ሊጋፈጥ ተነሳ፡፡
ብህትውናና ዘመናዊነት
ዘመናዊነት ከቀየራቸው የመካከለኛው ዘመን አስተሳሰቦች ውስጥ አንዱ የሰው ልጅ ስለ ራሱ አካል፣ ችሎታና ነፃ ፍቃድ ያለውን አመለካከት ነው። ብህትውና በነፍስና በስጋ፣ በመንፈሳዊ ህይወትና በዓለማዊ ህይወት፣ በእግዜርና በተፈጥሮ መካከል ቅራኔን በመፍጠር፣ ለሰው ልጅ አካል፣ ችሎታ፣ ዓለማዊ ህይወትና ለተፈጥሮ ዝቅተኛ አመለካከት እንዲኖረን አድርጓል፡፡ ዘመናዊነት የመጣው ይሄንን ብህትውናዊ አመለካከት በመቃረን ነው፡፡
ብህትውና ዓለምን መካድ ሲሆን፣ ዘመናዊነት ግን ዓለምን መቀበል ነው፡፡ ብህትውና ከዓለም መነጠል ሲሆን፣ ዘመናዊነት ግን በዓለም መኖር ነው፡፡ ብህትውና በዚህ ዓለም መከፋት ሲሆን፣ ዘመናዊነት ግን በዚህ ዓለም ተስፋ ማድረግ ነው፡፡ ብህትውና መንፈሳዊው ዓለም ላይ ማተኮር ሲሆን፣ ዘመናዊነት ግን በዚኸኛው ዓለም ላይ ማተኮር ነው፡፡ ብህትውና በሌላኛው ዓለም ላይ ያለውን መንግስተ ሰማያት መናፈቅ ሲሆን፣ ዘመናዊነት ግን መንግስተ ሰማያትን በዚህ ዓለም ላይ ለመፍጠር ማለም ነው፡፡
ብህትውና አካልን መጠየፍና ማጎሳቆል ሲሆን፣ ዘመናዊነት ግን አካልን መውደድና መንከባከብ ነው። ብህትውና ፍላጎትን መከልከል ሲሆን፣ ዘመናዊነት ግን ፍላጎትን መከተል ነው፡፡ ብህትውና ስሜትን ማፈን ሲሆን፣ ዘመናዊነት ግን በስሜት ደስታን መፍጠር ነው፡፡ ብህትውና ከዓለም ጋር መጣላት ሲሆን፣ ዘመናዊነት ግን ከዓለም ጋር መታረቅ ነው፡፡ ብህትውና በነፍስና በስጋ መካከል ቅራኔን መፍጠር ሲሆን፣ ዘመናዊነት ግን የዚህ ቅራኔ መፈታት ነው፡፡
ለማጠቃለል፣ ብህትውና (ተአምራዊነት) እና ዘመናዊነት ጎን ለጎን መኖር የሚችሉ ሐሳቦች አይደሉም፤ የአንዱ መኖር የሌላውን ህልውና ይጋፋል። በመሆኑም፣ ዘመናዊነት የመጣው የተአምራዊነትና የብህትውና አስተሳሰቦችን በመቃረንና እነሱን የሚተካ ሌላ አማራጭ ሐሳብ በማምጣት ነው፡፡ የተአምራዊነትና የብህትውና አስተሳሰቦች ላይ እንደዚህ ዓይነት ተግዳሮት መምጣት የጀመረው ደግሞ ከዘመነ ትንሳኤ (Renaissance) ጀምሮ ነው፡፡
በመሆኑም፣ በተለያዩ ዘመናት ላይ በተለያዩ ሀገራት ሲቀነቀኑ የነበሩት የዘመናዊነት ፕሮጀክቶች የተአምራዊነትና የብህትውና አስተሳሰቦችን በመቃረን የተነሱ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ሀገራት ውስጥ አንደኛዋ ደግሞ ኢትዮጵያ ነች፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ፣ ያሬዳዊው ሥልጣኔ የተመሰረተበትን የተአምራዊነትና የብህትውና አስተሳሰቦችን የሚቃረን ሐሳብ መምጣት የጀመረው ከ17ኛው ክ/ዘ ጀምሮ ነው፡፡ በዚህ ተገዳዳሪ ሐሳብ ውስጥ በየዘመናቱ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ፈላስፎች፣ የታሪክ ባለሙያዎችና የዘመናዊነት አቀንቃኞች ተሳትፈዋል። በክፍል-7 ፅሁፌ ዘርዓያዕቆብን፣ ወልደ ሕይወትን፣ ዶ/ር እጓለንና ዶ/ር ዳኛቸውን እየጠቀስን ያሬዳዊው ሥልጣኔ ከኢትዮጵያውያን ፈላስፎች የተነሳበትን ተግዳሮት እንመለከታለን፡፡

Read 936 times