Saturday, 19 January 2019 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(7 votes)


            “መንግስትነት ንግስና አይደለም”
             

     በጥንት ዘመን ነው፡፡ ሰውየው ቀኑን የሚያሳልፈው መጽሐፍ ሲያነብና ሲደግም፣ ሲደጉሥ፣ ሲጠርዝና ሲፅፍ ነው፡፡ አስማተኛ፣ መጽሃፍ ገላጭ፣ ኮከብ ቆጣሪ፣ ጋኔል ጠሪ፣ ጠጠር ጣይ፣ ጠንቋይ፣ ደብተራ እያሉ ያወሩበታል፡፡ ነቃ ያሉት ደግሞ ‹ሊቅ› ይሉታል፡፡
የአገሪቱ የበላይ ቧለሟሎችና የእምነት አጋፋሪዎች ሰውየውን አይወዱትም፡፡ ችሎታቸውን የሚያሳንስባቸው ስለመሰላቸው አሴሩበት፡፡ በንጉሱ ዕልፍኝም ሆነው፡- “ህዝቡ የሚያዳምጠው እሱን ነው፤ ለአልጋህ ያሰጋሃል፡፡” በማለት አሰማምረው መሰከሩበት፡፡ ንጉሡም እንዲታሰር አዘዘና ተያዘ፡፡ የከተማው ወሬ ግን ባሰ፡፡ … “ሰይጣን በሱ ተመስሎ እንጂ እሱ አይደለም የታሰረው፣ በዚህ ሲያገድም፣ በዚያ ሲያልፍ አይተነዋል፣ በዓይጥ ተመስሎ ከእስር ቤቱ እየሾለከ ይወጣል ወዘተ… ወዘተ ተባለ። ሰውየው ይኸን ሲሰማ በአገሬውና በሹማምንቱ ጅልነት እየተገረመ ይስቃል፡፡ ዘበኞቹ ደግሞ … “አንድ ነገር ቢኖረው ነው፣ የታሰረ ሰው ይከፋል፣ ይተክዛል እንጂ እንዴት ይስቃል?” እያሉ ተሸበሩ፡፡ ነገሩ ሲገን ንጉሡን አሳሰበውና “ስቀሉት!” ብሎ ፈረደበት። ሊሰቅሉት በወንበሩ ላይ እንዳቆሙት፣ ወታደሩ ገመዱን አንገቱ ላይ ለማጥለቅ እጁ ተንቀጠቀጠ። ሰውየውም … “አይዞህ! የምሞት እንዳይመስልህ፤ ነገ እንገናኛለን” አለው፡፡ ወታደሩም የሚወራውን ያውቃልና ሰይጣን መሆን አለበት ብሎ በመደናገጥ እየጮኸ ፈረጠጠ፡፡ ሌላ ወታደር ቢመጣም ያው ሆነ።
ራቅ ብሎ ተቀምጦ የነበረው ንጉሥ፤ ግራ እየተጋባ ወደ ሰውየው ቀርቦ …
“ከዕውቀትህ አካፍለኝና የፈለግኸውን ሰጥቼህ ወዳሻህ ትሄዳለህ” አለው፡፡
ሰውየውም … “ድግምት ስላለኝ፣ ሞት አይቀርበኝም፡፡ የተናገርከውን የምትፈፅም ከሆነ አንተንም እንደ‘ኔ አደርግሃለሁ፡፡” በማለት ተስማማና እንግዳ የሆኑ ቃላቶችን እንዲያጉተመትም  አስጠናው፡፡ ንጉሱም ደስ እያለው ለተሰበሰበው ህዝብ “ሟች” አለመሆኑን ለማሳየት፣ በሰውየው ምትክ ወንበሩ ላይ ቆመ፡፡ ሰውየውም ገመዱን አንገቱ ላይ አጥልቆ ሸመቀቀና ወንበሩን በፍጥነት ከስሩ አሸሸው፡፡ … ከዛስ?
***
አንዳንድ ሊቃውንት “ገሃነም ማለት ሌሎች ሰዎች ናቸው፡፡ (Hell is other people)” ይላሉ። አያን ራንድ፡- “ሰብአዊነትን አከብራለሁ፤ ሰዎችን እወዳለሁ፡፡ ነገር ግን አንድ ሳምንት ከሌሎች ሰዎች ጋር ቢዘጋብኝ አብዳለሁ” ብላ ነበር፡፡
“እየተመራመርክና እያወቅህ ስትመጣ የህይወትን ምስጢር ትረዳለህ፡፡ … ያ… ደግሞ ወደ ማታሸንፈው ጦርነት ውስጥ ያስገባሃል፡፡ (“The more you read, the more you know; the more you know, the more you understand life. The more you understand life, it puts you in a war that you cannot win”) በማለት የፃፈልን ደግሞ ጀምስ ሚሽነር ነው - ‹ዘ ፋየርስ ኦቭ ስፕሪንግ› በሚለው መፅሃፉ፡፡
ታላቁ ሾፐን ሃወርም በበኩሉ ይህንኑ ጉዳይ … “ሰው እያወቀ ሲመጣ በጥልቅ ያስባል። በማሰቡም የሚያተርፈው መከራን ነው፡፡ (The more distinctly a man knows-the more intelligent he is, the more pain he has; the man who is gifted with genius suffers most of all.”) በማለት ያረጋግጥልናል፡፡
ወዳጄ፡- ዛሬ የጥምቀት በዓል እየተከበረ ነው። መጥምቁ ዮሐንስ … “ከኔ በኋላ የሚመጣ … እሱ በእሳት ያጠምቃችኋል” ማለቱን ታውቃለህ? … አትፍራ፡፡ እኔ እንደገባኝ ነዳጅ አርከፍክፎ፣ ክብሪት ጭሮ ያነዳችኋል ማለቱ ሳይሆን እውነቱን ይነግራችኋል ለማለት ነው፡፡ እኔም ጥቅስ ባበዛብህ አይግረምህ፡፡ … ጥምቀት ነዋ!! … እንኳን አደረሰህ!!
ወዳጄ፡- ዓለምን የቀየሯት ስልጣኔያችንን የሰጡን ጥቂት ሰዎች ናቸው፡፡ እነሱ፡- በመከራቸው የሚስቁ፣ በራሳቸው የሚጨክኑ፣ ታላቁን ተራራ እንድንወጣ የሚያግዙን … እነሱ ክቡር ናቸው፡፡ በተመሳቀለ ኑሮ፣ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ውስጥ የማይንገጫገጩ፣ ዓይተው የማያዩ፣ ዐውቀው የማያውቁ የሚመስሉ፣ እያሉ የሌሉ፣ በሌሉበት ደግሞ ያሉ እነሱ ህያው ናቸው፡፡ በጥቅም የማይደለሉ፣ ለማንም የማያዳሉ፣ ማወቅ ፍዳ የሆነባቸው … እነሱ ናቸው የለውጥ አባቶች፡፡ እኛ ግን ብዙ ይቀረናል፡፡ … ታላቁ ፀሐፊ ኸርነስት ሄሚንግዌይ እንዲህ ፅፏል፡-
“If people bring so much courage to the world, the world has to kill them, to break them. It kills the very good and the very gentle and the very brave impartially”
ወዳጄ፡- ሰው ለህሊናው ካልኖረ፣ ለስርዓትና ለህግ ካልተገዛ ኋላቀር ይባላል፡፡ ኋላቀርነት አለመሰልጠን ነው፡፡ ባደጉና ራሳቸውን በቻሉ ሐገሮች ባህል ማለት ስልጣኔ፣ ስልጣኔ ማለትም የዘመናዊነት ባህል ነው። በሌላ አነጋገር “ዴሞክራሲ” ወይም ራስን በራስ የማስተዳደር ዘይቤ እንደ ማለት ይሆናል፡፡ ስርዓቱ፡- ዜጎች እንደ ‹ዜጋ› ስለሃገር፣ እንደ ግለሰብ ስለ ስራቸው፣ ስለ ቤተሰባቸውና ስለሌሎች ብዙ ነገሮች በነፃነት የሚያስቡበትና የሚፈልጉትን የሚሆኑበት ልማድ ነው፡፡ መንግስት ደግሞ የተሻለ ሃሳብና ጉልበት (energy) ኖሯቸው፣ የበለጠ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ሌሎች ግለሰቦችና ድርጅቶች እስኪዘጋጁ ድረስ ጎንበስ ቀና ብሎ፣ በቀናነት በማገልገል ህግና ደንብ የሚያስፈፅም ተቋም ነው፡፡ መንግስትነት ንግስና አይደለም፡፡
ለዚህ ነው፡- ታላላቅ ሳይንቲስቶች፣ የፈጠራና የጥበብ ሰዎች የሚወለዱት፤ ህዝባቸውንና አገራቸውንም ታላቅ የሚያደርጉት፡፡ ስልጣኔ አያስቀናም ወዳጄ?
***
 ወደ ተረታችን እንመለስ፡- በቅዠት የተተበተበው ህዝብና በቅናት የበገኑት ቧለማሎች፤ ሰውየው በሃሰት እንዲከሰስ ማድረጋቸውን፣ ንጉሱም ስቅላት እንደፈረደበት፣ ሰውየው ደግሞ የአእምሮውን ኃይል ተጠቅሞ ከሞት ለመዳን እንደዘየደ ተጨዋውተናል። ንጉሡም ዕውቀቱን ቢያካፍለው የፈለገውን ሰጥቶት እንደሚሸኘው ቃል በመግባቱ ሰውየው ‹ሞት የሚያርቅ› ድግምት አስጠንቶት፣ ‹ሟች› አለመሆኑንም ለሚገዛው ህዝብ ለማሳየት፣ በሰውየው ምትክ ወንበሩ ላይ እንደቆመና ገመዱን እንዳጠለቀ፣ ሸምቀቆውም እንደጠበቀ፣ አውርተናል፡፡ በዚያው ቅጽበት ሰውየው ንጉሱ የቆመበትን ወንበር ከስሩ በመሳቡ ንጉሡ ተንጠለጠለ፡፡
አፍታም ሳይቆይ ትንፋሹ ተቋርጦ ሞተ፡፡ ሰውየውም ወንበሩ ላይ ቆመና ጮክ ብሎ፤ “ከዛሬ ጀምሮ …” በማለት መናገር ሲጀምር አደባባዩን የሞላው ህዝብ እያጨበጨበ “… ንጉሣችን አንተ ነህ!” በማለት ሰገደ፡፡ ሰውየው ማለት የፈለገው ግን ሌላ ነበር፡፡ … እስኪ ገምት፡፡
ሠላም!!

Read 9824 times