Saturday, 19 January 2019 00:00

በሕልውና ላይ መቀለድና መቆመር ቢቀርብን ይሻላል

Written by  ዮሃስ ሰ
Rate this item
(2 votes)


 • የኢንዱስትሪ ፓርኮች ስኬታማ ካልሆኑና የተመራቂ ተማሪዎች የስራ እጦትን ለማቃለል ካልበቁ፣ አገሪቱ ከቀውስ የማምለጫ ፋታ ማግኘቷ ያጠራጥራል። ለጊዜው፣ የግል ኢንቨስትመንት የሚያስፋፋና የስራ እድልን ሊፈጥር የሚችል ሌላ ምን ተስፋ አለ? ምንም!
 • ታዲያ፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚታይ የግል ኢንቨስትመንት ጅምር የሚያናጋ የሰላም እጦት ሳያንስ ተጨማሪ አደናቃፊ ቅስቀሳ ሲካሄድ በዝምታ ማየት ይገባል? (በዩኤንዲፒ እና በአይኤልኦ ግፊት፣ በሰራተኛ ማህበራት የሚካሄድ ቅስቀሳ በዚህ ከቀጠለ መጨረሻው አያምርም)።
 • “የኢንዱስትሪ ፓርኮች የራሳቸውን ኤሌክትሪክ እንዲያመነጩ” ተብሎ ሲነገር መስማትም ያስደነግጣል። በኤሌክትሪክ እጥረትና መቆራረጥ ሲሰናከሉ፣ እንደ ቀላል ችግር ቸል ማለት፣ መዘዙ ክፉ ነው። ጭራሽ፣ ከፀሐይና ከነፋስ ኤሌክትሪክ እንዲያመነጩ ማሰብ ደግሞ፣.... ነገሩን ሁሉ የሚያሰናክል፣ የተስፋ ጭላንጭሉንም የሚያዳፍን ይሆናል።
 • “የኢትዮጵያ ከተሞች በፋብሪካና በግንባታ ብዛት ተጥለቀለቁ” ብሎ የሚያማርርና የሚያወግዝ ባለስልጣንና የመንግስት ሚዲያ፣ ምሁርና ኤንጂኦ ሲበራከት፣.... በሰው ኑሮና በአገር ሕልውና ላይ ክፉኛ እየተቀለደ ነው።
 • በፋብሪካና በግንባታ እጥረት ሳቢያ፣ ተቃውሰው የሚተራመሱና የሚፈርሱ አገራትን ነው እያየን ያለነው። የኢትዮጵያ እጣ ፋንታ በእጃችን ነው። በፋብሪካና በግንባታ እድገት ተጨናንቆ የሚፈርስ አገር አልታየም።
 • ካልሆኑና የተመራቂ ተማሪዎች የስራ እጦትን ለማቃለል ካልበቁ፣ አገሪቱ ከቀውስ የማምለጫ ፋታ ማግኘቷ ያጠራጥራል። ለጊዜው፣ የግል ኢንቨስትመንት የሚያስፋፋና የስራ እድልን ሊፈጥር የሚችል ሌላ ምን ተስፋ አለ? ምንም!
 
            ዮሃንስ ሰ


    መንግስት፣ ባለፉት ዓመታት እንዲሁ በኢኮኖሚና በሕልውና ላይ እየቀለደ፣ ራሱ ተሳክሮ አገሬውን አቃውሷል። የዚህ አገር ፈተና በዝቷል። በአንድ በኩል፣ በብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካና በዘረኝነት ቀውስ ከትርምስ የመዳን ፋታና መፍትሄ አጥታ እንዳትበታተን ያሰጋል። በሌላ በኩል ደግሞ፣... ኢንቨስትመንት ከጅምሩ ተሰናክሎ፣ ስራ አጥነት ተባብሶ፣ የኢኮኖሚ ቀውስ ከድጥ ወደ ማጡ ተወሳስቦ፣ የዜጎች ኑሮ  ተናግቶ አገር እንዳትተራመስ ያስፈራል።
አሁን፣ የኢኮኖሚ ቀውሱን ለማረጋጋትና የስራ አጥነት ችግር እንዳይባባስ ለመከላከል፣ አገሪቱ ከቀሯት ጥቂት ተስፋዎች መካከል አንዱ፣ “የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተስፋ” ነው። የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ካልተሳኩ፣.... አደጋው ብዙ ነው።
የመንግስት ኢንቨስትመንትና ቢዝነስ፣.... የጊዜ ጉዳይ እንጂ፣ ዞሮ ዞሮ፣ በድሃ አገር  ሃብት በአብዛኛው በኪሳራና በብክነት ከማጥፋት ያለፈ ውጤት እንደማያመጣ፣ የደርግ ዘመን ታሪክ ብቻ ሳይሆን ያለፉት አስር አመታት ሙከራዎችም ይመሰክራሉ። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግን፣ ለየት ይላሉ።
አንደኛ ነገር፣ በግል ኢንቨስትመንት የሚቋቋሙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች አሉ። የስኬት ጅምርም እያሳዩ ነው። ሁለተኛ ነገር፣ በመንግስት ወጪ የሚቋቋሙ የኢንዱስትሪ ፓርኮችም ቢሆኑ፣ የፓርኮቹ ግንባታ በግል ኩባንያ ሲከናወን፣ የሃብት ብክነት ይቀንሳል። በተለይ ደግሞ፣ በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ አምራች ፋብሪካዎች እየተከፈቱ ያሉት በግል ኢንቨስትመንት ነው። በሌላ አነጋገር፣ መንግስት፣ እንዳሻውና በዘፈቀደ፣ በእንዝህላልነትና በግድየለሸነት፣ የድሃ አገር ሃብትን በገፍ የማባከን እድል አያገኝም። በዚያው ልክ ደግሞ፣ የግል ኢንቨስትመንት የሚድግበት፣ ምርታማና ትርፋማም የሚሆንበት እድል ይሰፋል። ሃብት ይፈጥራል (ነባር ሃብትን በማባከን ሳይሆን አዲስ ሃብትን በማፍራት)። የስራ እድልንም ይከፍታል። በአጭሩ፣ ለጊዜውም ቢሆን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንደቀዳሚ የኢኮኖሚ ተስፋዎች ሊታዩ ይችላሉ።
የአገሪቱን ኢኮኖሚ አቃውሶ የዜጎችን ኑሮ ያናጋ መንግስት፣ ይህንን ተስፋ የሚያደበዝዝ ጥፋት ለመፈፀም ይቅርና፣ ይህንን ተስፋ በቸልታ ለማየትም እንኳ መድፈር የለበትም። የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ቸል ማለት ፈፅሞ አያዋጣም። አሁን፣ የግል ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋትና የስራ እድልን ለመፍጠር የሚችል ሌላ ምን ተስፋ አለ? ምንም! የኢንዱስትሪ ፓርኮች በማናቸውም ምክንያት ከተሰናከሉ፣ የአገር ተስፋ ይዳፈናል። ይህንን በቅጡ ካልተገነዘብን፣ አገራችን ምንኛ ከባድ ፈተና ውስጥ እንደገባችና አሁን ያለንበት ዘመን ምንኛ ቀውስን የሚያባብስና ለትርምስ ያቆበቆበ ዘመን እንደሆነ አላወቅንም ማለት ነው። ብናውቅና ብናገናዝብ አይሻለንም?
ለምሳሌ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮቹና በውስጡ የሚከፈቱ የግል ፋብሪካዎች፣ በኤሌክትሪክ እጥረት እንዲሰናከሉ መፍቀድ፣ መዘዙ ብዙ ነው። የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ፣ የግል ኢንቨስትመንትን ለማፋጠንና የስራ እድል ለመክፈት ካልቻሉ፣... የተመራቂ ተማሪዎችን የስራ እጦት በትንሹም ቢሆን ለማቃለል (ቢያንስ ቢያንስ የስራ አጥነት ተባብሶ እንዳይፈነዳ ለመከላከል ካልበቁ)፣ አገሪቱ መውጪያ ከሌለው ቀውስ የማምለጥ ፋታ ማግኘቷ ያጠራጥራል።
የኢትዮጵያ ችግር፣ የግንባታና የፋብሪካ ብዛት ነው?
ሐሙስ የኢትዮጵያ ሬድዮ ያሰራጨው ቀዳሚ ዜና፣ የኢትዮጵያ ከተሞችን ያስቸገረና ነዋሪዎችን ያሰቃየ “ችግር”፣ ላይ ያተኮረ ነው። በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች ውስጥ፣... “ለኢንዱስትሪና ለምርት፣ ለመኖሪያና ለቢሮ፣ ለሱቅና ለገበያ ግንባታ የሚውለው ቦታ በዛ” ብሎ የሚያማርርና የሚያወግዝ ነው ዜናው።
እንደ ዘገባውና እንደ ባለስልጣናት ገለፃ ከሆነ፣ 30 በመቶ ያህሉ የከተማ ቦታ፣... የእፅዋት ግዛት መሆን አለበት። ሌላ 30 በመቶ ደግሞ፣ ለመንገድ እና ክፍት ቦታ ሊሆን ይገባዋል ብለዋል። የቀረው 40 በመቶ የከተማ ቦታ ብቻ ነው፣ ለመኖሪያና ለስራ፣ ለቢሮና ለገበያ፣ እና ለሌሎች ግንባታዎች መሰጠት ያለበት ብለዋል - ባለስልጣናቱም ጋዜጠኛውም።... አሁን ግን ለእፅዋት በቂ ቦታ አልተሰጠም፣ “ለክፍት ቦታም” በቂ ቦታ አልተሰጠም። የኢትዮጵያ ከተሞች በግንባታ እየተወረሩ ነው በማለትም አውግዘዋል። ይሄው ነው የኢትዮጵያ ከተሞች ችግር?
ቀዳሚ ዋና ዜና ሆኖ መቅረቡ ያነሰ ይመስል፣... የተሰጠው የጊዜ ርዝመትም ያስገርማል። የአገር ውስጥና የውጭ ዜናዎችን ለመዘርዘር 28 ደቂቃዎችን የመደበው የኢትዮጵያ ሬድዮ፣ 14ቱን ደቂቃ የፈጀው፣ “ግንባታና ፋብሪካ በዛ” ብሎ ለማማረርና ለማውገዝ፣ ከዚያም “መኪኖችና ፋብሪካዎች አየርን ይበክላሉ” ብሎ ለመኮነን ነው። አስቂኙ ነገር ምንድነው?... የኢትዮጵያ ከተሞች በግንባታ ብዛት ተሰቃይተዋል መባሉ ብቻ አይደለም አስገራሚው ነገር። በፋብሪካዎችና በመኪኖች ብዛት አየሩ የተበከለባቸው ደግሞ የአፍጋኒስታን ከተሞች ናቸው ብሏል የኢትዮጵያ ሬድዮ ዜና። ሰፊ ጊዜ የተሰጣቸውና ከ28 ደቂቃ የዜና ሰዓት ውስጥ ግማሹን የፈጁት የእለቱ ዜናዎች እነዚሁ ናቸው - የኢትዮጵያ ሬድዮ የሐሙስ ዜናዎች።
ለዜናዎች የሚሰጠው የጊዜ ስፋት፣ ትርጉም እንዳለው የተቋሙ ባለሙያዎች ሊጠፋቸው አይገባም። ትርጉሙም፣ የኢትዮጵያ ከተሞች በግንባታ ብዛት መሰቃየታቸውና የአፍጋኒስታን ከተሞች ደግሞ በፋብሪካና በመኪና ብዛት መቸገራቸው የእለቱ ትልልቅ ጉዳዮቻችን ናቸው እንደማለት ነው። የአፍጋኒስታን ፋብሪካ? የትኛው ፋብሪካ? በድህነትም፣ በፋብሪካ እጦትም፣... ከኢትዮጵያ የማይሻል አገርኮ ነው። የኢትዮጵያ ሬድዮ ግን፣ “በፋብሪካ ምክንያት የአፍጋኒስታን አየር ተበከለ” የሚል እንቶፈንቶ ወሬ ትልቅ ጉዳያችን መሆን እንዳለበት ይሰብካል። እንቶፈንቶ ነው! ከፋብሪካ ለመራቅና ከመኪና ጋር ለመጣላት፣ ኋላቀር የችጋር ኑሮ ውስጥ መንከላወስ የናፈቀው ሰው፣... (የፋብሪካ እጦትና የመኪና እጥረት ተመራጭ ከሆነ)፣ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣት ወይም ወደ አፍጋኒስታን ከመሄድ የተሻለ አማራጭ ብዙም አያገኝም።
ለኢትዮጵያ ሬዲዮ ማብራሪያ ሲናገሩ የነበሩት የአገራችን ባለስልጣናት ግን፣ ስለሌላ አገር የሚያወሩ ይመስላል። የኢትዮጵያ ከተሞች በፋብሪካ ተቸግረዋል ባይ ናቸው። “ፋብሪካ ቸገረን” ሳይሆን፣ በዝቶብን “በፋብሪካ ተቸገርን” ብለው ሲናገሩ፣ ለማመን ይከብዳል። የትኛው ፕላኔት ውስጥ ነው የሚኖሩት ያስብላል። በከተሞች አካባቢ ብዙ ኢንዱስትሪዎች የተገነቡ መሆናቸው አለመታደል እንደሆነ ተናግረዋል - አንደኛው ባለስልጣን። የትኛው ኢንዱስትሪ? ኢንዱስትሪ የራቃትና የስራ እድል የጠፋባት፣ ድህነትና ስደት የበረከተባት፣ ኢትዮጵያ የተሰኘችውን አገር የማያውቋት ነው የሚመስሉት።
የኢትዮጵያ ሬድዮ ስለ የትኛው አገር እየዘገበ ይሆን? ስለ ኢትዮጵያ ከሆነ ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ከተሞች በግንባታ ብዛት ተጨናንቀው፣ በቢሮ ፎቆችና በአፓርትመንቶች፣ በፋብሪካዎችና በግዙፍ የገበያ ሕንፃዎች ተጥለቅልቀው፣ ነዋሪዎች ተሰቃዩ እያለ ከሆነም፣ ወደፊት ስንት ዓመታት በምናብ ተጉዞ ስለ የትኛው መጪ ዘመን ይሆን የሚነግረን?
አዲስ አበባ ናት በግንባታ የተጨናነቀችው? በመኖሪያ ቤት እጦት የሚሰቃዩ ከ900 ሺ በላይ ነዋሪዎች፣ ኮንዶሚኒዬም ለማግኘት ተመዝግበው የሚጠባበቁባት፣... በ3ሺ ብር የወር ኪራይ መፀዳጃ ቤት አልባ አንዲት ክፍል እንጂ ከዚያ በላይ የማይገኝባት ከተማ፣ “የ150ሺ ኮንዶሚኒዬም ቤቶች ግንባታ ዘንድሮ ይጠናቀቃል” እየተባለ ከአምስት አመት በላይ በባዶ ዘመን የሚቆጠርባት አገር ውስጥ፣... “የኢትዮጵያ ከተሞች በግንባታ ተጥለቀለቁ” እያለ የሚያማርር ባለስልጣን መኖሩ፣ የኑሮ ላይ ቀልድ አይደለምን? “እነ ቻይና በግንባታና በፋብሪካ ብዛት ከፍተኛ ችግር ላይ ወድቀዋል” እያለ ከቻይና የግንባታና የፋብሪካ እድገት እንድንድን የሚሰብክ ባለስልጣንስ? እና ደግሞ፣ ይህንን ነው እንደ እውቀት የሚቆጥሩት። የግንባታና የፋብሪካ እድገትን መመኘት ግን፣ የእውቀት ችግር፣ የግንዛቤ እጥረት ነው ይላሉ። ወይ ቀልድ!
አለም ሁሉ የሚናወጠው፣... የአፍሪካና የአረብ አገራት ብቻ ሳይሆኑ፣ የደቡብ አሜሪካ አገራትም ጭምር፣... ከቅርብ አመታት ወዲህ ደግሞ በእንግሊዝና በፈረንሳይ እንደምናየው፣ አገር ምድሩ፣ እዚህም እዚያም፣ በኢኮኖሚ ቀውስ የሚናጉት፣ በብጥብጥና በአመፅ፣ በጦርነትና በስደት የሚተራመሱት፣... ግንባታና ፋብሪካ በዝቶ ነው? የፋብሪካ ጭስና የመኪና ጉዞ ሰለቸን ብለው ነው? ከተሞች ውስጥ ጥቅጥቅ ጫካና አረንጓዴ ፓርክ በማጣታቸው ነው? በዚህ ምክንያት ነው፣ በርካታ አገራት ሲተራመሱና ሲፈራርሱ፣ ሚሊዮኖች ከኑሮ ተፈናቅለው በአገር አልባነት ሲሰደዱና ሲሞቱ የምናየው?
ሰዎች፣... ኧረ በሰው ኑሮና በአገር ሕልውና ላይ መቀለድ ነውር እንደሆነ እንገንዘብ። በሕልውና ላይ ከመጫወትና ከመቆመር የከፋ ጥፋትስ ምን አለ?         
የበዛውስ ሌላ ነው! በኑሮና በሕልውና ላይ መቀለድ ነው የበዛው!
አዎ፣ በሕልውና ላይ መቀለድ፣ መጫወትና መቆመር፣.... በጣም ተለምዷል። የትምህርት ፍኖተ ካርታ፣ በእውቀት ላይ ይቀልዳል። የድሮው ትምህርት እውቀት ላይ ያተኮረ ነው በማለት ያወግዛል - ለእውቀት በቂ ትኩረት አይሰጥም ከማለት ይልቅ። ትንሽ ትኩረት መሰጠቱም እንደጥፋት ተቆጥሯል -ለእውቀት ቅንጣት ትኩረት መሰጠት የለበትም በሚል ጠማማ ቅኝት።
ኢኮኖሚ ላይ፣ “ፋብሪካ አልተስፋፋም፣ ኢንዱስትሪ አላደገም” ብሎ ፋብሪካዎችን የሚያበራክት፣ ኢንዱስትሪን የሚያስመነድግ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ፣.... ጥቂት ፋብሪካዎች መኖራቸውንም እንደአለመታደል ሲቆጠርና ሲሰበክ እንሰማለን።
በቂ የአስፋልት መንገድ አልተሰራም፣ አብዛኛው ነዋሪ በመኪና ትራንስፖርት እጥረት ተቸግሯል” ብሎ መፍትሄ እንደመፈለግ፣ መንገድ መዝጋት ነው የተለመደው። ጭራሽ፣ ጥቂት የአስፋልት መንገድና ጥቂት መኪና መኖራቸውም እንደ እርግማን ተቆጠረና፣ ከመኪና እንቅስቃሴ የሚገላግል ነፃ አውጪ መጣሁላችሁ ብሎ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሲያውጅ ሰማን። አስፋልት መንገዶችን ዘግቶ፣ “ከተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ነፃ” የሚል መፈክር ዘርግቶ ሲያስጨፍርም አየን።
አዎ፣ መሳከር የበዛበት የቀውስ ዘመን ነው። አንዳንዶቹ አገራት ለይቶላቸው፣ እንዳልነበሩ እየሆኑ ነው። በየጊዜውም ተጨማሪ አገራት በአመፅና በብጥብጥ፣ ከሕልውና ለመውጣት ወደ ትርምስ እየተቀላቀሉ ነው። ኢትዮጵያም፣ ባለፉት አመታት፣ ወደዚያው ነው ስትጠጋ የቆየችው። አይበቃንም?
በነገራችን ላይ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፣ የአካባቢ ጥበቃ መሥሪያ ቤትን  ማፍረሳቸው ትልቅ ቁም ነገር ነው፡፡ ከላይ የተገለጸውን ዓይነት የተሳከረ አስተያየት የሚሰጡ ባለሥልጣናትንም ማቆየት አያስፈልግም፡፡ አይጠቅሙምና፡፡  

Read 1871 times