Monday, 28 January 2019 00:00

በኢትዮ ኤርትራ የድንበር ንግድ ስምምነት ድርድር ሊደረግ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በግማሽ አመት ብቻ 52 ሰራተኞች ስራቸውን ለቀዋል
           
     ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ የጠረፍ ንግድ አሰራርን ለማሻሻል የሚያስችል ሰነድ መዘጋጀቱና በኢትዮ - ኤርትራ ድንበር ላይ የድንበር ንግድ ስምምነት ድርድር ሊካሄድ መሆኑ ተገለፀ፡፡
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ፈትለወርቅ ከትናንት በስቲያ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት የ2011 ዓ.ም የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ እንደተናገሩት፤ በኢትዮ ኤርትራ ድንበር ላይ እየተካሄደ ያለውን የንግድ ሁኔታ በማጥናትና ይህንኑ ሁኔታ የሚገልጽ ሪፖርት በማዘጋጀት፣ ለድንበር ንግድ ስምምነት ድርድሩ ግብአት እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል፡፡ ከኤርትራ ጋር ስለሚደረገው የድንበር ንግድ፤ ረቂቅ ስምምነት ተዘጋጅቶ በቴክኒክ ኮሚቴ ደረጃ በሚመሩት ኮሚቴዎች ቀርቦ፣ የመጨረሻ ቅርፁን በማስያዝ ለኤርትራ ወገን እንዲላክ መግባባት ላይ መደረሱንም ወ/ሮ ፈትለወርቅ ተናግረዋል፡፡
በዘንድሮው ዓመት የተገኘው የውጪ ንግድ ገቢ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ135.82 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ ማሳየቱንና በበጀት ዓመቱ 6 ወራት 1.21 ቢሊዮን  ዶላር ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡
የቅባት እህሎች፣ የጥራጥሬ ሰብሎች፣ የተፈጥሮ ሙጫና እጣን፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ ጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ ስጋና ወተት፣ ጫትና የኮንስትራክሽን ግብአቶች በወጪ ንግድ ዘርፉ የውጪ ምንዛሪ ያስገኙ ምርቶች ሲሆኑ ጫትና ታንታለም ከተያዘላቸው ዕቅድ በላይ አፈፃፀም ያስመዘገቡና ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ያስገኙ የውጪ ምርቶች መሆናቸው በሪፖርቱ ላይ ተገልጿል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ለታየው የወጪ ንግድ ገቢ ማነስ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ተብለው ከተዘረዘሩት ጉዳዮች መካከል ህገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድን መቆጣጠርና መግታት አለመቻል፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የነበሩ ሀገራዊ የፀጥታ ችግሮች በገዥዎች ዘንድ ስጋት በመፍጠራቸው፣ የምርት ግዥ እንቅስቃሴ በመቀዛቀዙና የተሻለ ዋጋ የሚከፍሉ ገበያዎች በማፈላለግና ትስስር በፍጠር ረገድ የተሰራው ስራ በቂ ባለመሆኑ ነው ተብሏል፡፡
በበጀት ዓመቱ በስራ ላይ ያሉ ሁለት አዋጆች (በንግድ ምዝገባና ፈቃድና በካፒታል ሊዝ) ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በመለየት የማሻሻያ ሃሳብ ቀርቧል፡፡
በረቂቅ ደረጃ የሚገኙ 3 አዋጆች ማለትም፡- የአስገዳጅ ደረጃዎች ማስፈፀሚያ ረቂቅ አዋጅና የህጋዊ ስነልክ ረቂቅ አዋጅ ተጠናቀው ለካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስቴር ጽ/ቤት መላካቸውና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን አዋጅ ቁጥር 551/1999 ማሻሻያ ተጠናቆ ለጠቅላይ ዐቃቤ ህግ መላኩ ተገልጿል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሁለት ደንቦች (የምግብና መጠጥ ኢንስቲቲዩት፣ የኢትዮጵያ ፋርማሲዩቲካል ማቋቋሚያ ደንቦች መዘጋጀታቸው) በሪፖርቱ ላይ ተገልጿል፡፡
በ2011 በጀት ግማሽ ዓመት ብቻ 52 ሰራተኞች በተለያዩ ምክንያቶች ስራ መልቀቃቸውን ያመለከተው ሪፖርቱ፤ ባለው የደሞዝ ስኬል ዝቅተኛነትና ከስራው ባህርይ አስቸጋሪነት ምክንያት በሚኒስቴር መ/ቤቱ ከፍተኛ የሆነ የሰራተኛ ፍልሰት መኖሩን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

Read 1214 times