Saturday, 26 January 2019 15:21

የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች ፋብሪካ በኢትዮጵያ ሊነባ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(3 votes)

 ተቀማጭነቱን በቻይና አድርጐ፣ በህክምና መገልገያ መሳሪያዎች ምርትና ሽያጭ፣ በህክምና ዘርፍ ምርምሮች አለም አቀፍ እውቅና ያለው ዋንፎ ካምፓኒ፤ የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች ማምረቻ ፋብሪካውን በኢትዮጵያ ሊያቋቁም ነው፡፡ ፋብሪካው በቂሊንጦ ፋርማሲ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ውስጥ የሚሰራ ሲሆን እ.ኤ.አ አቆጣጠር በ2020 ግንባታው ተጠናቆ ወደ ምርት እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
ቻይናዊው ዋንፎ ካምፓኒ ዴልታ ኢንስትሩመንት ቴክኖሎጂ፣ EZM እና RE4 ኢምፖርት ኤክስፖርት ከተባሉ አገር በቀል አጋሮቹ ጋር በትብብር ለሚያቋቋመው ለዚሁ ፋብሪካ ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ በጀት መመደቡንና የፋብሪካው ስራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ስራ በሚጀምርበት ወቅት ምርቶቹን ወደተለያዩ የአፍሪካ አገራት በብዛት ለማዳረስ እንደሚያስችል ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያን የህክምና መሳሪያዎች ማኑፋክቸሪንግ እምብርት ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንደሆነ የገለፀው ዋንፎ ካምፓኒ፤ ይህም ለአገሪቱ የስራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሏል፡፡
ትናንት በሸራተን አዲስ ሆቴል በተካሄደው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተነገረው፤ ዋንፎ ካምፓኒ ከሶስቱ አገር በቀል አጋሮቹ ጋር በመሆን በአፍሪካ እጅግ ተፈላጊ የሆነውን የወባ፣ የኤችአይቪ ኤድስ እና የእርግዝና ምርመራ ማድረጊያ የህክምና መሳሪያዎችን ሌሎች መገልገያ ቁሳቁሶችን ለማምረት የሚያስችለውን ፋብሪካ በአገራችን ያቋቁማል፡፡ ፋብሪካው በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ግንባታው ተጠናቆ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ እንደሚባና ለፋብሪካ ማቋቋሚያው ከተያዘው በጀት 3 ሚሊየን ዶላር የሚሆነው ለፋብሪካ ግንባታው እንደሚውል ተገልጿል፡፡

Read 4042 times