Monday, 28 January 2019 00:00

“ሃይማኖትና መንግስት መለያየት አለባቸው” ማለት የጋራ ጉዳይ የላቸውም ማለት ነው?

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(0 votes)

 ብዙ ጊዜ “ሃይማኖትና መንግስት መለያየት አለባቸው” የሚለው አባባል ተደጋግሞ ሲነገር እንሰማለን፡፡ ግን ይህ ሃሳብ ትርጉሙ ምንድነው? ይህ ሃሳብ መስተጋባት የጀመረው ከመቼ ጀምሮ ነው? በዚያ ወቅት ይህ ጥያቄ ለምን ተነሳ? እነማን ናቸው ጥያቄውን ያነሱት? በሀገራችን ሃይማኖትና መንግስት የነበራቸው ግንኙነት ምን ይመስላል? ‘መንግስት ጥበቃ በሚያደርግለት ሃይማኖት’ እና ‘በመንግስታዊ ሃይማኖት’ መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው? መንግስት ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ስርዓትን ሳይሸራርፍ ተግባራዊ እያደረገ ለሃይማኖቶች ጥበቃ ማድረግ ይቻለዋል? ለእነዚህና መሰል ጥያቄዎች መልስ የሚሆን ሃሳብ ማቅረብና ሃይማኖትና መንግስት መለያየታቸው ለሀገራችን ምን ጉዳት፣ ምን ጥቅም እንደሚያስገኝ የመወያያ አጀንዳ መጫር የዚህ ጽሁፍ ማጠንጠኛ ነው፡፡
በምዕራባውያን ሀገሮች ቀደም ባሉት ዘመናት ቤተ ክርስቲያንና መንግስት (church and state) ቅርርብ ነበራቸው፡፡ ለዚህም ነው በ17ኛው እና በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን “መንግስትና ቤተ ክርስቲያን ይለያዩ” ይባል የነበረው፡፡ ቤተ ክርስቲያንና መንግስት (church and state) ይለያዩ የሚለው የምዕራባውያን የዴሞክራሲ ንድፈ ሃሳብ የመጣው ደግሞ ያኔ ረጅም እጅ የነበራት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በመንግስት አስተዳደር ውስጥ የነበራትን የጣልቃ ገብነት ሚና ለመከላከል ታስቦ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል፡፡
በ17ኛው እና በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ ምዕራባውያን የዓለማዊነት ስርዓት አራማጆች (secularists) የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ጉልበት በማዳከም የቤተ ክርስቲያኗን የበላይነት ለማክሰም ችለዋል፡፡ በርግጥ የሃይማኖት መስፋፋት በተለይም የፕሮቴስታንት እምነት መከሰት በዚያ ወቅት በህብረተሰቡ ውስጥ ስር ሰዶ ይታይ ለነበረው ቁማር፣ አስማት፣ አባይ ጠንቋይ፣ ዛር፣… ለመሳሰሉ ማህበራዊ እንከኖች መጥፋት የበኩሉን አስተዋጽዖ ማድረጉን ምዕራባውያን የንድፈ ሃሳብ ተንታኞች ይናገራሉ።
በሌላ በኩል የሃይማኖት ደብሮች ከመንግስት የአስተዳደር መዋቅር መነጠላቸው፣ ሃይማኖት በህዝብ አስተዳደር ውስጥ የሚኖረውን የበላይነት ያስቀራል፡፡ በሀገራችን ህዝብን በማስተዳደር ሂደት ሃይማኖትና መንግስት አንድ ጊዜ ጠበቅ፣ ሌላ ጊዜ ላላ የሚል የመተጋገዝም የጣልቃ-ገብነትም ግንኙነት ነበራቸው፡፡ አሁንም ድንበሩን ጠብቆ ከሁሉም እምነቶች ጋር መንግስት የጠበቀ ግንኙነት ሊኖረው ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በ17ኛው እና በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩት የአውሮፓ የዴሞክራሲያዊ ንድፈ ሃሳብ አራማጆችም ቢሆኑ ሃይማኖትንና መንግስትን ሙሉ ለሙሉ የማለያየት ህልም አልነበራቸውም፡፡ ፍላጎታቸው በወቅቱ የበላይና ገናና የነበረቺው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የበላይነት እንዳይኖር ማድረግ ነበር፡፡
መንግስት ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ስርዓትን ሳይሸራርፍ ተግባራዊ እያደረገ፣ “ለሃይማኖቶች ጥበቃ ማድረግ” ይቻለዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በዚህ ረገድ በዓለም ላይ ያሉ ተመሳሳይ ሁኔታዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ለአብነት ያህል እንግሊዛውያን በተለያዩ ድንጋጌዎችና በሕግ አወጣጥ ስርዓታቸው ውስጥ መንግስት የክርስትና ሃይማኖትን ከተንኮልና ከሃሜት የመጠበቅ ግዴታ እንዳለበት ድንጋጌዎችን አስቀምጠዋል፡፡ እስራኤላውያን የኦርቶዶክስ መንፈሳዊ ስርዓት እየሩሳሌምን በመሳሰሉ የሀገሪቱ አካባቢዎች ጥበቃ እንዲደረግለት የተለያዩ መንግስታዊ መመሪያዎችን አስቀምጠዋል፡፡ ጣሊያን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ የሚያስችል ውስብስብ ስርዓት አላት፡፡ አየር ላንድና ሌሎች የአውሮፓ ሀገሮች እንዲሁ ካቶሊካዊ ማንነትን ለመጠበቅ የሚያስችል ድንጋጌ በሕገ መንግስታቸው ላይ አስፍረዋል፡፡
በእኛም ሀገር መንግስት በሀገሪቱ ባሉ ሃይማኖቶች መካከል ልዩነት ሳያደርግ ሊጠብቃቸው ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህንን በተመለከተ በህገ መንግስታችን በአንቀጽ 91/1 ላይ “መንግስት… ህገ መንግስቱን የማይቃረኑ ባህሎችና ልማዶች በእኩልነት እንዲጎለብቱና እንዲያድጉ የመርዳት ኃላፊነት አለበት” ይላል፡፡ (እዚህ ላይ “ባህሎችና ልማዶች” የሚለው ሀረግ በውስጡ ሃይማኖትን እንደሚያካትት ይታመናል) መንግስት በሀገሪቱ ያሉ ሃይማኖቶችን ልዩነት ሳያደርግ እንደሚጠብቃቸው ሁሉ በሀገሪቱ ያሉ ሃይማኖቶችም የዜጎችን ሰብእና ለማነጽ ተግተው የመስራት ሃላፊነት እንዳለባቸው ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል፡፡
በኛ ሀገር “ሃይማኖት የግል ጉዳይ ነው፣ ዴሞክራሲን በአግባቡ ተግባራዊ ለማድረግ የሕዝብ አስተዳደር ከሃይማኖት መራቅ አለበት” ተብሎ በዚሁ መንፈስ እየተሄደበት ቢሆንም፤ የተመኘነው ዴሞክራሲ ግን በሚፈለገው መጠን እውን ሲሆን አልታየም፡፡ ምዕራባውያን ራሳቸው ሲፈልጉ ጣልቃ እየገቡ፣ ሲያሻቸው ያሻቸውን እያደረጉ ሀገሮቻቸውን እየመሩ በታዳጊ ሀገሮች “መንግስትና ሃይማኖት አይተጋገዙ፣ መንግስትና ሃይማኖት የየራሳቸውን ማህበረሰባዊ ኃላፊነት አይወጡ፣…” ማለት ውድቀታችንን ከመመኘት ውጪ ሌላ ትርጉም የሚሰጠው ሆኖ አይታየኝም፡፡
በርግጥ ሃይማኖት በሕዝብ አስተዳደር ጉዳይ ውስጥ ሊኖረው የሚገባውን ሚና በተመለከተ ከዴሞክራሲ ንድፈ ሀሳብም ይሁን ከዴሞክራሲ አተገባበር አኳያ በምሁራንና በሊቃውንት መካከል ገና ሙሉ ለሙሉ ስምምነት የተደረሰበት ጉዳይ አደለም፡፡ ይሁን እንጂ፤ ሃይማኖት በሕብረተሰብ አጠቃላይ ሕይወት ውስጥ በግንባር ቀደምነት የሚጫወታቸው ወሳኝ ሚናዎች የሉትም የሚል ሰው የሚኖር አይመስለኝም!
ወደ ኋላ መለስ ብለን ታሪካችንን እንይ፡፡ በጥንት ዘመን እነ ኢዛና የክርስትና ሃይማኖትን ከተቀበሉበት ጊዜ ጀምሮ እስከ 1966ቱ አብዮት ፍንዳታ ድረስ ቤተክርስቲያንና መንግስት አንድ ላይ ይሰሩ ነበር፡፡ ቤተክርስቲያኗ ሲሶ መንግስት ሆና ሀገር ታስተዳድር ነበር፡፡ ምእምናኗን መልካም ስነ ምግባርና ግብረ-ገብነት ታስተምር ነበር፡፡ የ1966ቱ አብዮት ሲፈነዳ መንግስትና ሃይማኖት ተፋቱ፡፡ መፋታት ብቻ ሳይሆን፤ (በተለይ ኦርቶዶክስ) ሃይማኖትን ከቤተ መንግስት ቅጥር ግቢ አባረው፣ ንብረቷን ሁሉ ወርሰው እንድትዳከም አስፈላጊውን ጊዜና ጉልበት አባክነዋል - ደርጎች!
ከ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የካቶሊክ ክርስትና እምነት በፖርቺጊዞች አማካይነት ወደ ኢትዮጵያ መግባት ለዘመናት በቆየቺው ኦርቶዶክስ ክርስትና ውስጥ መከፋፈልን ፈጠረ፡፡ በተለይም በእየሱስ “ልደት፣ ቅብዓት እና ውህደት” ዙሪያ ልዩነቶች ማቆጥቆጣቸው ቤተክርስቲያኗን ጤና ነሳት፡፡ የቤተክርስቲያኗ ችግር ውስጥ መግባትና መዳከም ደግሞ ለዘመነ መሳፍንት መፈጠር ምክንያት ሆነ። ቤተክርስቲያኗ ከመንግስት አስተዳደር እጇን በማንሳቷ ሃይ ባይ ጠፍቶ፣ ንጉሰ ነገስት መሾም አቅቶ፣ ሁሉም በየአምባው ነግሶ፣ ዘመነ መሳፍንት ለአንድ መቶ ዓመታት ስርዓት ሆኖ ሰነበተ፡፡
የቋራው ካሳ ኃይሉ (አፄ ቴዎድሮስ) መጥቶ ማዕከላዊ መንግስት መስርቶ ንጉሰ ነገስት መሆን የቻለው የተከፋፈለቺውን ቤተክርስቲያን በማዋሃድ የኦርቶዶክስ ተዋህዶን ሃይማኖት በማጠናከሩ ነበር፡፡ የሚገርመው ነገር አፄ ቴዎድሮስ ራሱ ከስልጣን የወረደበት ዋነኛው ምክንያት ደግሞ ከቤተ ክርስቲያኗ ጋር በመጣላቱ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ “ተው የምትሄድበት መንገድ ትክክል አይደለም” አለቺው፡፡ ቴዎድሮስ አልሰማም አለ፡፡ ቀሳውስቱን “ራሱን ታጣቂ፣ ወገቡን ሰባቂ…” እያለ ከመዝለፍ አልፎ በአንድ ቤተ  ክርስቲያን ምን ያህል የሰው ኃይል ሊኖር እንደሚገባ ደንግጎ፣ ቤተ ክርስቲያኗ የምትመራበትን ስርዓት አበጃለሁ በማለቱ ጠቡ ከፍ እያለ መጣ፡፡
ቴዎድሮስ ከቤተ ክርስቲያኗ ጋር ሲቃቃር ወደ ሽንፈት መንደርደሩን በመጨረሻዋ ሰዓት ላይ በነበረበት ወቅት ለእንግሊዙ ጄኔራል ናፒር በጻፈው ደብዳቤ፤ “ያገሬ ሰው ገብር፣ ስራት ግባ ብየ ብለው እምቢ ብሎ ተጣላኝ፡፡ እናንተ ግን በስራት በተገዛ ሰው አቸነፋችሁኝ፡፡ … ያገሬ ሰው የፈረንጅ ሃይማኖት ይዟል፣ ሰልሟል እያለ አስሩን ምክንያት ይሰጠኝ ነበረ፡፡ እኔ ከከፋሁበት እግዚአብሔር መልካሙን ይስጠው…” ብሎ ጸጸቱን ገልፆ ነበር፡፡
እንደ ክርስትና ሁሉ እስልምናም በሀገሪቱ ፖለቲካና የመንግስት አስተዳደር ውስጥ ሚና ነበረው፡፡ ሙስሊሞች በሚበዙባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች ህዝበ ሙስሊሙ ይተዳደር የነበረው በቃዲዎች ነበር፡፡ ቃዲዎቹ በሸሪዓ ህግ መሰረት ጋብቻና ፍቺን ከማስፈጸም በተጨማሪ በህዝበ ሙስሊሙ ማህበራዊ ህይወት ውስጥ የአድራጊ ፈጣሪነት ሚና ነበራቸው፡፡ የተጣሉትን ያስታርቃሉ፡፡ በሀብት ክፍፍል የተፈጠረን ጠብ ይዳኛሉ፡፡ ማህበራዊ ቀውስ እንዳይፈጠር፣ ባለፀጋዎች ሰደቃ እንዲያወጡ፣ ዘካ እንዲሰጡ ያደርጉ ነበር፡፡ ተሰሚነት ነበራቸው፡፡ እንደ ጦልሓ ሐጂ ዓይነት የእስልምና ሃይማኖት መሪዎች ደግሞ የማስታረቅም፣ የመዋጋትም፣ የመምራትም ሚና እንደነበራቸው ታሪክ የመዘገበው ሀቅ ነው፡፡
ከ1966ቱ አብዮት ፍንዳታ ወዲህ ሁለቱም አብራሃማዊ ቤተ እምነቶች መንግስትን የመደገፍ ሚናቸውን አጡ፡፡ የቄስ ት/ቤቶች እየተዳከሙ እንዲሄዱ ተደረጉ፡፡ የቁርዓን ት/ቤቶችና መድረሳዎች እንዲዘጉ ተደረጉ፡፡ የስነ ምግባርና የግብረ-ገብነት ትምህርት ቆመ፡፡
ለ27 ዓመታት የዘለቀው ኢህአዴግ መራሹ መንግስት፣ የደርግን ፈለግ ተከትሎ ቄስ ት/ቤትንና መድረሳዎችን ዘግቶ፣ የስነ ዜጋና የስነ ምግባር ትምህርት (Civics and Ethical Education) አስተምራለሁ ብሎ፣ ስርዓተ ትምህርት ቢቀርጽም፤ ስነ ምግባር የሌላቸው “የግብረ-ገብነት” መምህራን፣ ምን እንደሚያስተምሩ፣ ለምን እንደሚያስተምሩ እንኳ አልገባቸውም ነበርና ያመጡት ለውጥ በተጨባጭ አልታየም፡፡
እነዚህ ሁለት መንግስታት የወሰዷቸው እርምጃዎች ውጤቱ፣ ዛሬ ከአባ ገዳ ላይ ማይክራፎን የሚቀማ ትውልድ እንዲፈጠር አደረገ፡፡ ውጤቱ ፈሪሀ እግዚአብሔር ጠፍቶ፣ በደቦ ፍርድ በአደባባይ ሰው ገድሎ፣ ዘቅዝቆ መስቀልን አስከተለ፡፡ ውጤቱ ወላጆቹን የማይፈራ፣ አስተማሪዎቹን የማያከብር ትውልድ ገንኖ እንዲወጣ አደረገ፡፡ ውጤቱ በሀገሪቱ ሙስና እንዲስፋፋ፣ ታክስ ማጭበርበር እንዲበራከት፣ ኮንትሮባንድ የላቀ ስፍራ እንዲኖረው አደረገ፡፡
ከሁሉ በፊት የመንግስት ኃላፊነት፣ ዜጎችን ስለ “ዜግነት” ማስተማር እንጂ ስለ “ስነ ምግባር” ማስተማር እንዳልሆነ መታወቅ አለበት፡፡ “ስነ ምግባር እና ግብረ-ገብነትን” ማስተማር የእምነት ተቋማት ስራና ኃላፊነት ነው፡፡ በሌላ በኩል (መጋቤ ሐዲስ እንደሚሉት)፤ ቤተ ክርስቲያንና መስጊዶች ስነ ምግባርና ግብረ-ገብነትን ማስተማር ትተው፣ አእምሮ ማልማታን ዘንግተው፣ መንግስት ልማት ሲል አካፋና ዶማ አንስተው፣ ልማት እንሰራለን ብለው መነሳታቸውም ትክክል አይደለም፡፡
በዚህ ወቅት በየአካባቢው ለተነሱት የደቦ ፍርድ፣ ረብሻ፣ ዝርፊያ፣ ሁከት፣ የንብረት ውድመት፣… መፍትሄው ኮማንድ ፖስት ማቋቋም አይደለም፡፡ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ አዋጅ መሰል መግለጫ ማስተጋባትም በየአካባቢው የተለኮሰውን እሳት ሊያጠፋው አልቻለም፡፡ መፍትሄው ይሄ አይደለም፡፡ መፍትሄው ይሄ ቢሆን ኖሮ ውጤቱ ይታይ ነበር፡፡ መፍትሄው በሃይማኖት ተቋማት መዳፍ ውስጥ እንደሆነ ይታየኛል፡፡ ይኸውም፡- መስጊዶች በየሳምንቱ ጁምዓ (ዓርብ) ከሶላት በፊት በሚደረገው ኹጥባ (ሣምንታዊ መግለጫ) አማካይነት በመላ ሀገሪቱ ባሉ ሁሉም መስጊዶች “ይህንን አድርጉ፣ ያንን አታድርጉ” የሚል መንፈሳዊ መልእክት በቁርአንና በሐዲስ ጥቅሶች ታጅቦ ቢነገር፣ የህዝበ ሙስሊሙ ልብ ውስጥ ፈሪሀ አላህ አድሮ ከጥፋት እንደሚታቀብ አምናለሁ፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ፤ በሀገሪቱ ባሉ ሁሉም ቤተ ክርስቲያናት በሰንበት ቀን (በየሳምንቱ ዕሑድ) በሚደረግ የስብከት ፕሮግራም ላይ እየተፈጸመ ያለው ሁከትና ብጥብጥ እንዲቆም በመንፈሳዊ አባቶች አማካይነት ቢነገርና መንፈሳዊ አባቶች መጥፎ ተግባርን ቢገዝቱ፣ ነውረኛ ተግባር ሁሉ ቁልፉን እንደተጫኑት ቧንቧ ቀጥ ብሎ እንደሚደርቅ ጥርጥር የለውም፡፡
ሁለቱ አብርሃማዊ የእምነት ተቋማት በዘመቻ መልክ ይህንን ተግባር ለአንድ ወር ምዕምናኖቻቸውን ቢገስጹና ቢያስተምሩ ሁሉም ነገር ስለሚረግብ፣ ቀሪውን ስራ የመንግስት የጸጥታና የደህንነት ተቋማት ሊሰሩት ይችላሉ። ከቁጥጥር ውጪም ሊሆን አይችልም። ወደ ሰማይ የጓነው የሁከት አቧራ ወደ መሬት ይወርዳል፡፡ ማዕበሉ ሰክኖ ሰላማዊ ገጽታ ይኖረዋል፡፡
በዚህ ረገድ አንድ አብነታዊ ምሳሌ ላንሳ። በቱርክ  አንዳች ሀገራዊ ጉዳይ በተነሳ ጊዜ የተነሳውን ጉዳይ ማዕከል ያደረጉ መንፈሳዊ መልእክቶች በማዕከል ደረጃ ተዘጋጅተው በጁምዓ ኹጥባ አማካይነት ለምእመናኑ እንዲተላለፍ ለሁሉም መስጂዶች የሚላክ መሆኑን በቱርክ ከሰባት ዓመታት በላይ የኖረው ወንድሜ አጫውቶኛል፡፡ መስጊዶች መልእክቱን እንዳስተላለፉ ስጋት የነበረው ሀገራዊ ጉዳይ መስመር አንደሚይዝም ነግሮኛል፡፡
ቀደም ባሉት ዘመናት በፖለቲከኞች መካከል ጠብና ኩርፊያ ሲፈጠር የሚያስታርቁት የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የጎሣ መሪዎች ነበሩ፡፡ ዛሬ ዛሬ ደግሞ በቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ መሪዎች መካከል ያለን ጠብ የሚያስታርቁት ፖለቲከኞች ሆነዋል፡፡ በመስጊድ ያለን መከፋፈልና መናቆር የሚያበርዱት ፖለቲከኞች ሆነዋል - የተገላቢጦሽ!
እንዲህ ያለው ሁኔታ የሚያሳየው የስነ ምግባር ጉድለትና የሞራል ዝቅጠት፣ የሃይማኖት ተቋማቱን ግንቦች ጭምር ደርምሶ ከባድ ጉዳት ማድረሱን ነው፡፡ እንዲህ ያለው ሁኔታ የሚያሳየው ከአንድነት ይልቅ መለያየት፣ ከመከባበር ይልቅ መዘላለፍ፣ በሙስና መንቀዝና መዝረፍ፣… በቤተ-እምነቶች ውስጥ ጭምር መባባሱን ነው። ይህ ደግሞ እንደ ሀገር የመቀጠላችንን ጉዳይ አሳሳቢ እያደረገው ነው፡፡
እንደ እምነት ተቋማት ሁሉ የመንግስት ተቋማት፣ የሙስናና የንቅዘት ማዕከላት ሆነዋል። መንግስት በብዙ አስፈሪና አስደንጋጭ አንቀፆች የተሞላ ህግ ማውጣት ብቻ ሳይሆን የሞት ቅጣትን ቢደነግግ እንኳ የሚሰማው ያለ አይመስለኝም፡፡ በአንዳንድ የዐረብ ሀገራት በስርቆት የቀኝ እጁን የተቆረጠ ሰው፣ የግራ እጁን ሲያስደግም ይታያል፡፡ በእኛም ሀገር በሙስና የተጠረጠሩ ሰዎች ተይዘው ለፍርድ መቅረባቸው ጧት ማታ በመገናኛ ብዙሃን እየተነገረ፣ ሙስና እየባሰ እንጂ እየቀነሰ መሆኑ አይታይም፡፡
በሀገሪቱ ስንት ሺህ ቤተ ክርስቲያናት፣ መስጊዶችና የፀሎት ቤቶች አሉ? በበኩሌ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሊሆኑ እንደሚችሉ አስባለሁ፡፡ በእነዚህ ተቋማት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የሃይማኖት አባቶች፣ ሰባኪዎች፣ ዑስታዞች፣ ዳዒዎች፣ ፓስተሮች፣… ሊኖሩ እንደሚችሉም እገምታለሁ፡፡ እነዚህ አንጋፋዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን አስተሳሰብ መቀየር ያቅታቸዋል የሚል እምነት የለኝም። ይችላሉ! ለዚህ አባባሌ ተጨባጭ ምሳሌ ማቅረብ እችላለሁ፡፡ በ1990ዎቹ በሀገሪቱ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ስርጭት ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ ነበር፡፡ ቤተ እምነቶች ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው ማስተማር ሲጀምሩ፣ በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ዙሪያ የተሻለ ግንዛቤ ተፈጠረ፡፡ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ስርጭትም በተጨባጭ  መሻሻል አሳየ፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ እነዚህ ቤተ እምነቶች የሙስናን አስከፊነት በማስተማር፣ አምርረው በመኮነንና በማውገዝ ሀገሪቱን እንደ ጋንግሪን እየገዘገዘ ያለውን ሙስና መዋጋት ቢጀምሩ፣ የላቀ ውጤት ሊያስመዘግቡ እንደሚችሉ አስባለሁ። በተመሳሳይ ሁኔታ እነዚህ ቤተ እምነቶች ሙስናን የሚጸየፍ፣ መልካም ስነ ምግባርን የተላበሰ፣ ግብረ-ገባዊ ሰብእና ያለው ትውልድን ለማፍራት በህጻናት ላይ ቢሰሩ፣ ከዓመታት በኋላ ሀገሪቱ ምን ዓይነት ዜጎች ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት ሊቅነትን የሚጠይቅ አይሆንም፡፡
ሙስና ማህበራዊ ነቀርሳ ነው፡፡ ሙስና ሀገርን በቁሟ የሚያቆነቁንና ባዶዋን የሚያስቀር ካንሰር ነው፡፡ የዜጎች የስነ ምግባር ጉድለትና የሞራል መላሸቅ ከባድ ማህበራዊ ኪሳራን ያስከትላል። ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ገደማ ማህበረሰብን ከማነጽ ርቀው የነበሩ ቤተ ክርስቲያን፣ መስጊድና ቤተ ፀሎቶች እነዚህን የሀገር መቅሰፍቶች ለማስወገድ ዘመቻውን በራሳቸው ቅጥር ግቢና አፀድ ውስጥ መጀመር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ አረም ተጭኖባቸው የነበሩት የቄስ ት/ቤቶች እና የቁርኣን መማሪያ መድረሳዎች እንዲያንሰራሩ ሊደረጉ ይገባል፡፡ በዚህም በሃይማኖት ተቋማትና በመንግስት መካከል ያለን መተጋገዝ ማጠናከር ይቻላል፡፡ “ሃይማኖትና መንግስት የተለያዩ ናቸው” የሚለው አስተሳሰብ ይህንን ማድረግን አይከለክልም!
ብዙዎቻችን እንደምንገነዘበው መልካም ስነ ምግባር ያለው ሰው ሁከት አይፈጥርም፡፡ በጎ ስነ ምግባር ያለው ሰው ለመገዳደል፣ ለጭቅጭቅና ለጠብ አይጋበዝም፡፡ ስነ ምግባር ያለው ሰው ለቅሚያ፣ ለዝርፊያና ለስርቆት አይሰማራም። የሞራል ልዕልና ያለው ሰው ታላላቆቹን ያከብራል፡፡ መምህራኖቹን ይሰማል፡፡ ለመንፈስ አባቶቹ ይታዘዛል፡፡ ለማህበራዊ ድንጋጌዎች ይገዛል፡፡ የመንግስትን ህግና ስርዓት ያከብራል፡፡
በብዙዎች ዘንድ በእንግዳ ተቀባይነታቸውና ፈጣሪን በመፍራት የሚታወቁት ኢትዮጵያውያን፤ ዘራፊዎች፣ ነፍሰ ገዳዮች፣ ጨፍጫፊዎች፣ አግላዮች፣… አይደሉም፡፡ ይህ እውነት ነበር። ዛሬ ዛሬ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የምንሰማው ዜና ግን ኢትዮጵያውያን መሬት በሚያንቀጠቅጥ የሁከትና የብጥብጥ ተግባር መሰማራታቸውን ነው፡፡ ኮንትሮባንዲስት፣ ሙሰኛ፣ ዘራፊ፣… መሆናቸውን ነው፡፡ እንዲህ ያለው የሁከትና የብጥብጥ ዜና ትዝብትን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያንን በአስቀያሚነታቸው ከሚታወቁት አለመቻቻል፣ ግድያ፣ ዘረኛነትና አግላይነት ጋር ተቆራኝተው እንዲታዩ የሚያደርግ መልእክት የሚያስተላልፍ መሆኑን ጭምር ነው፡፡
ይህ ወቅት ኢትዮጵያውያን ወደ ራሳችን ውስጥ ማየት ግድ ይለናል የሚል እምነት አለኝ። እንደ ኢትዮጵያዊ የመጣንበትን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሕይወታችንንና ውስጣዊ ሰብእናችንን መፈተሽ ይጠበቅብናል የሚል ተጨማሪ ሃሳብም አለኝ፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ ማንነታችን አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ እናም፤ የሀገራችንን መልካም ስም፣ ክብርና ዝና ወደ ነበረበት ሥፍራ የማስመለስና እንደገና የማደራጀት እምነት፣ ኃይልና ድፍረት ሊኖረን ይገባል፡፡
ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ ያፈረስናቸውን ተቋማት (ማለትም፤ ቄስ ት/ቤትና መድረሳዎችን) መልሰን መገንባት ይጠበቅብናል። ቤተ እምነቶቻችንም ለዘመናት ሲያደርጉት እንደነበረው ሁሉ አእምሮን ለማልማት በርትተው መስራት ይጠበቅባቸዋል።
በመጨረሻም በጽሁፌ ርእስ ላይ ላነሳሁት ጥያቄ፣ መልስ ልስጥና ጽሁፌን ልቋጭ፡፡ “ሃይማኖትና መንግስት መለያየት አለባቸው” ማለት “መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፤ ሃይማኖትም በመንግስት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም” ማለት ነው፡፡ ይሄ ማለት ግን መንግስትና ሃይማኖት የጋራ ጉዳይ የላቸውም ማለት አይደለም፡፡ “የጋራ ህዝብ” እስካላቸው ድረስ የጋራ ጉዳይም ይኖራቸዋል፡፡ ሁለታቸውም በየራሳቸው አፀድ ውስጥ ሆነው፣ ድንበር ሳይጥሱ፣ ወሰን ሳይሻገሩ በመተባበርና በመተጋገዝ መንፈስ “ለጋራ ህዝባቸው” የሚጠቅም ሥራቸውን ማከናወን ይችላሉ፡፡
ከአዘጋጁ፡-ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1084 times