Monday, 28 January 2019 00:00

ቃለ ምልልስ “ኢትዮጵያ ገዥ ሳይሆን መሪ አግኝታለች”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 • የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ቁልፍ ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?
       • የኢትዮጵያ ለውጥ በምስራቅ አፍሪካ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?

     ከፍተኛ የሥነ ትምህርት ባለሙያ ቢሆኑም ይበልጥ የሚታወቁት በፖለቲከኛነታቸው ነው፡፡ የመኢአድ  ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን ያገለገሉ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል አይደሉም፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለ16 ዓመታት በተለያዩ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የሰሩት አቶ አሰፋ ሃብተወልድ፤ ሰፊ ጊዜያቸውን በምስራቅ አፍሪካ ጂኦፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ጥናትና ምርምር በማድረግ እንደሚያሳልፉ ይናገራሉ፡፡ ለመሆኑ ምሥራቅ አፍሪካ ምን ዓይነት ቀጠና ነው? ለኢትዮጵያ ያለው በረከትና ተግዳሮት ምንድን ነው? በጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ መንግስት እየተካሄደ ያለው የለውጥ ሂደት በቀጠናው ላይ ምን አንደምታ ይኖረዋል? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከአቶ አሰፋ ሃብተወልድ ጋር ተከታዩን ቃል ምልልስ አድርጓል፡፡


    የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናን እንዴት ይገልጹታል?
የምስራቅ አፍሪካ አካባቢ በብዙ ችግር የተተበተበ ነው፡፡ በአካባቢው ሁለት ዓይነት እረፍት የለሽ ተቀናቃኝ ሁኔታዎች አሉ። ይህ ደግሞ ይበልጥ ኢትዮጵያን ነው የሚመለከተው። በኢትዮጵያ ላይ አንደኛ ታሪካዊ ተቀናቃኞች፤ ሁለተኛ ደግሞ ተፈጥሮአዊ ተቀናቃኞች አሉባት። ታሪካዊ ተቀናቃኝ የምንላቸው ሰፊና ረጅም ታሪክ ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህ በታሪክና በባህል የሚቀናቀኗት ናቸው። ተፈጥሮአዊ ተቀናቃኞቿ ደግሞ በሃብት የሚቀናቀኑ ናቸው፡፡ ሁለቱ ተመጋጋቢ ሆነው ነው እስካሁን የዘለቁት። በንጉሡ ዘመን ፖይንት 4 የሚባል የአሜሪካ መንግስት አማካሪ ቡድን፣ ይሄን ጉዳይ ይፋ አድርጎ፣ ንጉሱም ስትራቴጂካዊ ለውጦችንና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን እንዲያፈላልጉ ነግረዋቸው ነበር፡፡ በወቅቱ ንጉሱ መፍትሄው ምንድን ነው ብለው ሲጠይቁ፤ የፖይንት 4 ኤክስፐርቶች ያቀረቡላቸው መፍትሄ፤ 1ኛ ሃገሩን ፈፅሞ ዲሞክራሲያዊ ማድረግ የሚል ነው፡፡ እሳቸው የመጀመርያውን መፍትሄ ሳይቀበሉ፣ ወታደሩን ብቻ ለማዘመን ሞክረዋል፡፡ ዲሞክራሲውን በተመለከተ “እኛን ህዝባችን ይወደናል፤ ይሄን ተዉት” ነው ያሏቸው፡፡ ለዲሞክራሲ ምንም የሰሩት ስራ ባለመኖሩ፣ በመጨረሻ ባጠናከሩት ወታደር ከስልጣን ተወገዱ፡፡ ይሄው የዲሞክራሲ ችግር ደርግንም ለውድቀት ዳረገው፡፡ ይሄው ችግር ቀጥሎ ኢህአዴግንም በውስጥ አርበኞች ገለበጠው፡፡ አሁን በውስጡ ለውጥ የተደረገበት ኢህአዴግ ነው በስልጣን ላይ ያለው፡፡ ይሄ ለውጥ ደግሞ ባልተረጋጋው የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ውስጥ መምጣቱ ብዙ ትርጉም አለው፡፡ በአሁኑ ወቅት በምስራቅ አፍሪካ ከዶ/ር ዐቢይ በስተቀር በሙሉ ያሉት አምባገነን መሪዎች ናቸው፡፡ ጅቡቲ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማልያ… ሁሉም አምባገነን ናቸው። ኬንያም ያለው አምባገነን መሪ ነው፡፡ በጎሳ ላይ የተመሰረተ አምባገነንነት አለ በኬንያ፡፡ ምርጫቸው በጎሳ የበላይነት የተመሰረተ ነው። ይህ እስከሆነ ድረስ መሪው ዲሞክራሲያዊ አይደለም፡፡ አንድ ሃገር በግለሰብ፣ በቡድን፣ በቤተሰብ፤ በአምባገነንነት የምትያዝ ከሆነ፣ ያቺ ሃገር ብቻ ሳትሆን ዙሪያው በሙሉ ይረበሻል፡፡ ምስራቅ አፍሪካም ከዚህ አንፃር የአምባገነኖች አካባቢ ነው፡፡ ምስራቅ አፍሪካ በቀጣይም የመረጋጋት እድሉ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ምናልባት በኢትዮጵያ የመጣው ዓይነት ለውጥ በሁሉም አገሮች ተፈጥሮ፣ የየሃገራቱ መሪዎች ተባብረው ከሰሩ ለውጥ ሊመጣ ይችላል፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ብቻቸውን በአካባቢው የሚኖራቸው ድርሻ፣ የሌሎቹ ለውጥ ከሌለበት አነስተኛ ነው የሚሆነው፡፡ እኔ፤ የዶ/ር ዐቢይን ጥረት በእጅጉ አደንቃለሁ፡፡
ከአምባገነንነት ሌላ በምስራቅ አፍሪካ ያሉ ስጋቶች ምንድን ናቸው?
ሌላው የሃይማኖት ጉዳይ ነው፡፡ ምስራቅ አፍሪካ፤ የመካከለኛው ምስራቅ አካል መሆኑን መገንዘብ አለብን፡፡ ከዚህ አንፃር በመካከለኛው ምስራቅ ያለው የሃይማኖት አክራሪነት፣ አንዱ የቀጠናው ችግር ነው፡፡ ክርስትናና እስልምና በአክራሪነት የሚንቀሳቀሱበት ቀጠና ነው። ክርስትና አክራሪ አይደለም የሚል ክርክር ይነሳል፡፡ ይሄ ግን ተቀባይነት የሌለው ነው። ክርስትና በሚስፋፋበት ጊዜ ወይም ራሱን ከሌሎች ለመከላከል የሚወስደው እርምጃ ጠንካራ ይሆናል፤ ያን ጊዜ ሌሎችን ችሎ መቀበል አይፈልግም፡፡ ግጭቱ የሚመጣው እዚህ ላይ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ምስራቅ አፍሪካ ላይ ከሌላው ዓለም በበለጠ የሃይማኖት አክራሪነት አለ። አክራሪነቱ ደግሞ በውጪ ገንዘብ ይደገፋል። ይሄ ቀጠናውን አደገኛ ከሚያደርጉት አንዱ ነው፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ ሃይማኖቶች በሙሉ ሊበራል ናቸው፡፡ ሌላውን መቻል ወይም መቻቻል አለ ማለት ነው፡፡ ምስራቅ አፍሪካ ግን ሊበራል አይደለም፡፡ ሌላውን ለመቻል የተዘጋጁ አይደሉም፤ ሃይማኖቶች፡፡ ይሄ የሆነው ደግሞ እውቀት ባለመኖሩ ነው፡፡ የሳይንስና የፍልስፍና እውቀቶች የሉም፡፡ ይሄን አክራሪነት ሊፈታው የሚችለው ህግም ስርአትም ሳይሆን የሳይንስና የፍልስፍና እውቀት መስፋፋት ነው፡፡
በምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ሃይማኖትን ይመራዋል ወይም ደግሞ ፖለቲካ በሃይማኖት ተፅዕኖ ስር ይመራል፡፡ እውነታው ይሄ ነው። በሃይማኖቶች ተፅዕኖ ስር ሆኖ ይመራል።  በሃይማኖቶች፣ በጎሳ፣ በዘር ተፅዕኖ ስር ሆኖ ሃገር የሚመራ ፖለቲካ፤ ምንጊዜም ጤነኛ ፖለቲካ አይሆንም፡፡ በጎሳ አስተሳሰብ ስር ሆኖ ሃገር የመራው የኢትዮጵያ ፖለቲካ፤ ለዚህ አንዱ ምሳሌ ነው፡፡ የዚህ አይነቱ አመራር ደግሞ ኢ-ዲሞክራሲያዊ ነው፡፡ ለዚህ ነው ዲሞክራሲ በቃል እንጂ በተግባር የለም እያልን ሁላችንም የምንተቸው፡፡ ሌላው የምስራቅ አፍሪካ ችግር፣ ፖለቲከኞች ፈጠን ብለው ዘር ውስጥ፣ ጎሳ ወይም ቡድንና ግለሰብ እጅ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ይሄ በሚሆንበት ጊዜ ሃገር ለመምራት የሚያስፈልገው የዲሞክራሲ ፍሬ ነገር አይኖርም፡፡
ለምሳሌ ሃይማኖትን ብንወስድ፣ ሃይማኖት የተጫነው ፖለቲከኛ ከሆነ ለራሱ ሃይማኖት ያደላል፡፡ በዘርም ሲሆን በአፉ ዲሞክራሲ ቢልም የመጨረሻ ምሽጉ ዘሩ ነውና ለዘሩ ያደላል። ለራሱ ወገን ያደላል፡፡ ለምሳሌ ደርግ ለራሱ አባላት፣ ኢህአዴግም በተመሳሳይ በሁሉም ነገር ለራሱ አባላት ሲያደላ ነበር፡፡ ለዚህ ነው “እኔ አልተጠቀምኩም” የሚለው የሰፊው ህዝብ ድምፅ እዚህም እዚያም የሚሰማው፡፡ ይሄ ድምፅ ደግሞ ዲሞክራሲ የአፍ እንጂ የተግባር እንዳልነበረ ያረጋግጥልናል፡፡
ሌላው የምስራቅ አፍሪካ ትልቁ ችግርና ለወደፊትም አደገኛ የሚሆነው፣ ምስራቅ አፍሪካ የንግድ መስመር እንዲሁም የነዳጅ መገኛና ማስተላለፊያ መንገድ በመሆኑ፣ የሃብታም ሃገሮች ፍላጎት እዚህ አካባቢ ላይ ከፍተኛ ነው፡፡ ሃብታሞቹ ይሄን አካባቢ ለመሻማት ሲሉ ወይ አንድን ጎሳ አሊያም፣ ቡድን ይይዛሉ ወይም በስልጣን ላይ ያለውን የፖለቲካ ኃይል ያጠምዳሉ፡፡ ከዚህ ካለፈም የጦር ሰፈር ይገዛሉ። አካባቢው ከእነሱ እጅ የወጣ ከመሰላቸው ደግሞ እዚህም እዚያም መረጋጋት እንዳይኖር ያደርጋሉ። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ እጅ ወጥታ ወደ ሶቪየት ህብረት ስታደላ፣ ሶቪየት ህብረትም አሜሪካም የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር ሲሻኮቱ፣ ኢትዮጵያ በመሃል እሳት ነው የነደደባት፡፡ አሜሪካ አመፀኞችን ታስታጥቃለች፤ ሶቪየት ከመንግስት ወግና መሳሪያ ታቀርባለች፤ በመሃል በኢትዮጵያውያን መሃል እሳት ይነድ ነበር፡፡ ሃገሪቷም በዚህ ልትዳከም ችላለች፡፡ በርካታ የመጠላለፊያ መንገዶች ያሉበት ቀጠና ነው፤ ምስራቅ አፍሪካ።
ሌላው የስልጣን ጥመኝነት ነው፡፡ ቡድኖች “ከስልጣን ተገፍቻለሁ፤ የኔ ጎሳ ተገፍቷል” በሚል ቂመኛና ተጋጭ የሚሆኑበት፣ አስቸጋሪ የፖለቲካ ስሪት ያለው ቀጠና ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ሌላው ትልቁ ችግር፤ አንዱ መንግስት፣ የአንዱን ሃገር መንግስት ተቀናቃኞች (አማፂዎች) የሚያጠናክር፣ የሚያደራጅ ሆኖ ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ መንግስት፤ የኤርትራ መንግስት አማፂዎችን ያደራጅ፤ ይደግፍ፤ ያስታጥቅ ነበር፡፡ የኤርትራ መንግስትም ተመሳሳዩን ያደርግ ነበር፡፡ ይሄ የቀጠናው የረጅም ጊዜ በሽታ ነው፡፡ እኔ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስሰራ፣ በዚህ ጉዳይ በርካታ መረጃዎችን ለማሰባሰብ ሞክሬ ነበር፡፡ ለምሳሌ ሶማሊያ በኢትዮጵያ ላይ ሰፊ የተቀናቃኝነት መንፈስ ነበራት፡፡ በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያን ተቀናቃኞች ሃብት ጭምር ሰጥታ ታሰለጥን ነበር፡፡ ለምሳሌ እነ ኦጋዴን ነፃ አውጪ፣ እነ ሶማሌ አቦ ይጠቀሳሉ፡፡ ሶማሊያ ኢትዮጵያን ለመውጋት ሞክራ ነበር፤ በወቅቱ ግን ተሸነፈች። ስትሸነፍ ደርግ በሶማሊያ ላይ በርካታ የትጥቅ ተፋላሚዎችን አሰልጥኖባታል፡፡ በዚያም ሶማሊያ ተንኮታክታ ለዛሬው ችግር በቅታለች። ደቡብ ሱዳንና ሱዳንም በተመሳሳይ፡፡ ኤርትራ እንድትገነጠል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካደረጉት መካከል የተፈጥሮ ተቀናቃኞቻችን፣ ሱዳንና ግብፅ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው፡፡ አካባቢው እንዲህ ያለው መጠላለፍ ያለበት ነው፡፡ ይሄ አካባቢ ግጭት አልባ ነው፡፡ እረፍት በማጣቱ ምክንያት ደግሞ ዜጎቹ እየተሰደዱ ያለቁበት ቀጠና ነው፡፡ አብዛኛው ወደ አውሮፓ፣ መካከለኛው ምስራቅ የሚሄደው ስደተኛ ከኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ ነው፡፡ ይሄ ለምን ሆነ? የህዝብ ቁጥሩ ያለ ገደብ ይጨምራል፤ በዚያው ልክ ሰርቶ የሚበላበት የተረጋጋ አካባቢ የለውም፡፡ የህዝብ ቁጥር መጨመር ሃብት ነው የሚሉ ኮሚኒስቶች አሉ፡፡ ይሄን የሚሉት ህዝብን ለጦርነት ስለሚጠቀሙበት ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ሃገሮች ግን የህዝብ ቁጥር መጥነው፣ ዜጋውን ባለ ሙሉ መብትና የሃብት ተጠቃሚ ማድረግ ላይ ነው የሚያተኩሩት፡፡
የጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ መንግስት ዋነኛ ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው ይላሉ?
ዶ/ር ዐቢይ አሁን የሚጋፈጡት ትልቁ ችግር፤ የህዝብ ቁጥሩ ከፍተኛ መሆን ነው፡፡ ይሄን  እንደ ህንድና ቻይና በማስተማርም ሆነ ህግ በማውጣት መግታት ያስፈልጋል፡፡ በቂ ሃብት በሌለበት የህዝብ ቁጥር መጨመሩ ለከፍተኛ ቀውስ ነው የሚዳርገን፡፡ በቀጣይ የህዝብ ቁጥር በእቅድ ካልተመራ እኮ ሲስተሙ በማይመለስ ሁኔታ ይዛባል፡፡ ሌላው ለዶ/ር ዐቢይ ፈተና የሚሆንባቸው በገጠር ተምሮ፣ ያለ ስራ የተቀመጠው ወጣት ነው፡፡ ይሄ ያለፉት መሪዎች የተከተሉት የስነ ህዝብ ፖሊሲ የፈጠረው ራስ ምታት ነው፡፡ ይሄ ችግር ደግሞ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የምስራቅ አፍሪካ ሃገሮችም ነው፡፡ ሃብት በሰፊው እንዲትረፈረፍ ካልተደረገ ዲሞክራሲ ይመጣል ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው። ለምሳሌ ሳውዲ አረቢያ ዲሞክራሲ የለም ግን ሃብት የተትረፈረፈ ነው፡፡ አሁን ሳውዲ አረቢያ ከፈለገች በቀላሉ ዲሞክራሲያዊ ሃገር መሆን ትችላለች፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ላለ ሃገር ግን ዲሞክራሲ ቢኖር፣ ነገ የዳቦ ጥያቄ ይከተላል፡፡ በዚህ የተነሳ መረጋጋት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። የዶ/ር ዐቢይ መልካምነት እጅግ የሚደነቅ ነው፡፡ ስለ ዲሞክራሲና ስነ ህዝብ ያላቸው አረዳድም ጠንካራ ነው፡፡ ነገር ግን ባለፉት አመታት የተገነባው የጎሳ ፖለቲካና የህዝብ ቁጥር ያለ ገደብ መጨመር ከፍተኛ ፈተና ነው የሚሆንባቸው፡፡ የብሔር ፖለቲካ ለኢትዮጵያ መርዝ ነው፡፡ በአካባቢውም ሃያል እንዳትሆን ወደ ኋላ ከሚጎትታት አንዱ፣ ይሄ የብሔር መከፋፈል ነው፡፡ የብሔረሰብ ፖለቲካ ከአገር ግንባታ አንፃር የአፍራሽነት ሚናው ያመዝናል፡፡
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ያላትን ተሰሚነት ለማሳደግ ምን ማድረግ ይጠበቅባታል?
በኢትዮጵያ የተደረገው ለውጥ ደም አፋሳሽ አለመሆኑ ጥሩ ነገር ነው፡፡ ዶ/ር ዐቢይ በዚህ ረገድ ታሪክ የሚያደንቃቸው የዲሞክራሲና የለውጥ ሻምፒዮና ናቸው፡፡ በምስራቅ አፍሪካ አሁን ባለው ሁኔታ ስጋት የለብንም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ምናልባት እሳቸው ለዲሞክራሲ ቀና ስለሆኑ ሁሉንም ነገር በቀናነት ለመመልከት ፈልገው ይሆናል፡፡ ነገር ግን ምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚገባ ቀጠና ነው፡፡ የተጀመረው የዲሞክራሲ ጉዞ ወደ ኋላ መመለስ በማይችልበት አቅምና ፍጥነት ነው ወደፊት መቀጠል ያለበት፡፡ ቀጣዩን ምርጫ ፍፁም ማድረግ ከተቻለ ደግሞ ሃገሪቱ የበለጠ ወደፊት መሻገርና ልዕለ ኃያል መሆን ትችላለች፡፡ ኢትዮጵያ በአካባቢው ያላት ወሳኝ ሚና ሊረጋገጥ የሚችለው በተቃና ዲሞክራሲያዊ አካሄድ ነው። በዚህ ዲሞክራሲያዊ አካሄድ ውስጥ ደግሞ ከእንግዲህ ኢትዮጵያ የማንንም ጎረቤት ሃገር ደፈጣ ተዋጊ መደገፍ የለባትም፡፡ በስሜትም በተግባርም የማንኛውንም ሃገር ደፈጣ ተዋጊ መርዳት አይገባትም፡፡ ኢትዮጵያ ሁለት አይነት ተፃራሪ ኃይሎች አሏት ካልን፣የኢትዮጵያ መንግስት ዘወትር በፕሮፌሽናል የጦር ሰራዊት ግንባታ ላይ ማተኮር አለበት፡፡ ስደተኛ መቀበሉ ማስተናገዱ ተገቢ ነው፤ ነገር ግን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በዚያው ልክ በሃገሪቱ በጎሳ፣ በብሄር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ መደራጀት እንዲቀር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እንዲህ ያለው አደረጃጀት በከፍተኛ መጠን እያደገ ካለው የህዝብ ቁጥር ጋር ተደማምሮ፣ ከፍተኛ የሀብት ሽሚያ ውስጥ ነው የሚከተን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በምንም አይነት የሃብት ሽሚያ እንዳይኖር መስራት ያስፈልጋል፡፡ እውቀት በሃገሪቱ ሰፊውን ቦታ እንዲይዝ የተለያዩ ስልቶችን ነድፎ መስራት ወሳኝ ነው፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ይሄን አሁንም እየሞከሩ ነው፡፡ ነገር ግን የበለጠ ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ ያልተማረ ሰው በበዛ ቁጥር ስሜት ነው ሰፊውን ቦታ የሚይዘው፡፡ እውቀት ከስሜት እንዲበልጥ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ ለፖለቲካ መረጋጋት ቁልፉ፤ ስሜት ለእውቀት ቦታውን እንዲለቅ ማድረግ ነው፡፡ ሌላው የፖለቲካ መረጋጋትን የሚያመጣው የበቂ ምግብ መኖር ነው፡፡ በዚህ ረገድ የዶ/ር ዐቢይ መንግስት ጥሩ እቅድ ሊያወጣ ይገባዋል፡፡ በሌላ በኩል፤ በገጠር የበአላት ቀን ተቀንሰው፣ ገበሬው በስራ የተጠመደ መሆን አለበት፡፡ የገጠር ከተማ ምስረታ መጠናከር ይኖርበታል፡፡ ለዚህ አዳዲስ እቅድ ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ አዳዲስ እቅዶችን አውጥቶ መስራት፣ ለፖለቲካው መረጋጋት ወሳኝ ነው፡፡
እኔ በግሌ የእስካሁኑን የዶ/ር ዐቢይ አካሄድ አደንቃለሁ፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ከታዩ የአስተሳሰብ አብዮታዊ መሪ፤ የመጀመሪያው ናቸው ብል ማጋነን አይደለም፡፡ ትክክለኛ የመሪነት እውቀት፣ ብቃት፣ ቅንነት ያላቸው መሪ ናቸው፡፡ ዐቢይ በተፈጥሮና በተመም ህዝባዊ መሪ የሆነ ሰው ነው ግን ከላይ የጠቀስኳቸው ጉዳዮች ፈተና ሊሆኑባቸው ይችላል፡፡ ለዚህ አዳዲስ ስልትና ጥበብ መጠቀም ያስፈልጋል። የጎሳ ፖለቲካው፣ ድህነቱ፣ የህዝብ ቁጥሩ መጨመር፣ የእውቀት እጥረት ናቸው፤ ለዶ/ር ዐቢይ አመራር ቀጣይ ፈተና የሚሆኑባቸው። ሃብትና እውቀት ወሳኝ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠሩ የደፈጣ ተዋጊዎች፣ በዋናነት የወጣቱን ድህነትና እውቀት ማነስ ተጠቅመው ነው፣ ከጎናቸው አሰልፈው ሲዋጉ የነበረው፡፡
ዶ/ር ዐቢይ ወደ ሥልጣን በመጡ ማግስት ከምስራቅ አፍሪካ አገራት ጋር ወዳጅነት አጠናክረዋል፡፡ ይሄ ፋይዳው እንዴት ይገለጻል?
ዶ/ር ዐቢይ በመጀመሪያ በራሳቸውም በድርጅታቸውም በጓዶቻቸውም በህዝቡም ድጋፍ ጭምር በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ አካሂደዋል፡፡ አንድ መሪ ለሃገሩ በሚሰራበት ጊዜ የውስጡን ጉዳይ ብቻ ካየ፣ ከውጪ ያለው ሴራ ደግሞ ሌላ አደጋ ይሆንበታል፡፡ ከዚህ አንፃር ጠ/ሚኒስትሩ በወቅቱ በምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ያደረጉት የወዳጅነት ጉብኝት በእጅጉ ስትራቴጂካዊና ጠቃሚ ነበር፡፡ በዋናነት አዲስ ወደ ስልጣን በመጣው በእሳቸው አመራር ላይ ያለን ጥርጣሬ አስወግደው፣ በጎረቤቶቻቸው የታመኑ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡ የውጪውን የአደጋ ስጋት በዚህ መልኩ ማስቀረት ብቻ ሳይሆን በግል የዲፕሎማሲ ብቃታቸውም ታማኝ ወዳጅነትንና አጋርነትን አግኝተዋል። በዚህ መልኩ የጎረቤት ስጋትን ከቀነሱ በኋላ በውስጥ ጉዳይ መጠመዳቸው ተገቢ አካሄድ ነው፡፡ ይሄ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ስራ ነው። በደርግና በኢህአዴግ ዘመን እኮ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር በጥርጣሬና በጠላትነት እስከመተያየት ደርሳለች፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራ፣ ኢትዮጵያና ሶማልያን መመልከት ይቻላል። ስለዚህ ዶ/ር ዐቢይ በዙሪያቸው ታማኝ ወዳጆችን ለማብዛት መንቀሳቀሳቸው የአንድ በሳል መሪ ተግባር ተደርጎ ነው መወሰድ አለበት፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ይሄን በማድረጋቸው ሚዛናቸውን ጠብቀው፣ በሃገር ውስጥ ያላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አስችሏቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ምንጊዜም የሰላም የስበት ማዕከል ናት፤ለወደፊትም መሆን አለባት፡፡
ሶማሊያ፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ በፌዴሬሽን ሊዋሃዱ ይችላሉ ብለው ያምናሉ?
ዶ/ር ዐቢይ ይሄን ማሰባቸው በእውነቱ ተገቢ ነው፡፡ ሊደነቅም የሚገባ ነው፡፡ ሃሳቡ በደንብ እንዲበለፅግ መደረግ አለበት፡፡ የምስራቅ አፍሪካ ህብረት ወይም ውህደት ሃሳብ፤ በየጊዜው መኮትኮት፣ ውሃ መጠጣት አለበት፡፡ ከውጪ ሃገራት ጣልቃ ገብነት መጠበቅ አለበት፡፡ ጉዳዩ የመሪዎችን እውቀትና ቀናነት ይጠይቃል። ከዚህ አንፃር በዶ/ር ዐቢይ ሙሉ ለሙሉ መተማመን አለኝ፡፡ ከኤርትራ ጋር የተጀመረው ስምምነት ጥሩ ነው፤ ነገር ግን የህውሓት እና የኤርትራ መንግስት፣ የጫካ ፀብ አንድ መቋጫ እስካላገኘ ድረስ ስጋት የተለየው አይሆንም። ኤርትራም የኢትዮጵያን ዘላቂ ወዳጅነት የምትፈልግ ከሆነ አንዱን ወደብ ማስረከብ አለባት፡፡ በምትኩ ከኢትዮጵያ የምትፈልገውን ነገር መቀበል ትችላለች፡፡ በኤርትራም ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረው አይነት ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ መፈጠር አለበት፡፡ የምስራቅ አፍሪካ ትልቁ ችግር የህዝብ አይደለም፤የገዥዎች ነው። ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ ዛሬ ገዥ ሳይሆን መሪ አግኝታለች፡፡ ህዝባዊ መሪ ኢትዮጵያ አግኝታለች፡፡ ይሄ ህዝባዊ መሪነት በክልል፣ በዞንና በወረዳ ደረጃም መውረድ አለበት። ህዝባዊ መሪዎች በየደረጃው መፈጠር አለባቸው፡፡ ህዝባዊ መሪ ህዝብ ያገለግላል እንጂ ህዝብን አይዘርፍም፤ አይቀጥፍም አይዋሽም፡፡ ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ድረስ ህዝባዊ መሪ አግኝታ አታውቅም ነበር፡፡ ምናልባት አፄ ምኒልክን መጥቀስ ይቻል ይሆናል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ለኔ ህዝባዊ መሪ ሆነው የመጡት ዶ/ር ዐቢይ ናቸው፡፡ ህዝባዊ መሪዎች በዓለም ላይ ጥቂት ናቸው፡፡ ለምሳሌ፡- ማንዴላን ጋንዲን መጥቀስ ይቻላል፡፡
እርስዎ የሚመሩት ድርድር (በገዢውና ተቃዋሚዎች መካከል) ተጀምሮ ነበር፡፡ ምን ውጤት አመጣ? አሁን የተጀመረውስ ምን ይመስላል?
ድርድር ሁሌም መደረግ አለበት፡፡ በሚነሱ ችግሮች ላይ ሁሉ ድርድር አስፈላጊ ነው። ውይይትና ድርድር፤ የችግሮች ማቃለያ ዘዴ ነው፡፡ በጦርነት ምንም አይነት መፍትሄ አይመጣም፡፡ እንደውም ችግሮችን መኮትኮት ነው፡፡ በኛ ሃገር ሁኔታ ፖለቲከኞች፣ ከዚህ በኋላ በድርድርና በውይይት ችግሮችን ሁሉ መፍታት አለባቸው፡፡ በሀገሪቱም ከጥር 2009 ጀምሮ ድርድር ተካሂዶ ነበር፡፡ ሰፊ ክርክሮች በድርድሩ ይነሱ ነበር፡፡ መንግስት ችግሩን እንዲረዳና ኋላ ላይ ላደረጋቸው ለውጦች ግብአት እንዲሆነው ድርድሩ ጠቃሚ ነበር፡፡ የመንግስት ሰዎች ከእልህ ወጥተው እንዲሰክኑና የሃገሪቱን ጉዳይ በፅሞና አስበው ወደ መፍትሄ እንዲገቡ፣ ድርድሩ መልካም አስተዋፅኦ ነበረው። አሁን የተጀመረው ድርድርም፣ ከዚህ አንፃር ጥሩ ውጤት እንዲያመጣ፣ ሁሉም የራሱን አስተዋፅኦ ማድረግ አለበት፡፡ የአለም ትልልቅ ጦርነቶች የመጨረሻ መፍትሄዎቻቸው ድርድር ነበር። በአሁኑ ወቅት የማይደራደር ፖለቲከኛ፤ አምባገነንነትን የሚያልም ነው፡፡ በዚያው ልክ ለድርድር ልቡ ክፍት የሆነ ፖለቲከኛ፤ ራሱን ለህዝባዊ መሪነት እንደሚያዘጋጅ አድርጌ ነው የምቆጥረው፡፡ ድርድር በገዢውና በተቃዋሚ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን በተቃዋሚ  ፓርቲዎች መካከልም  ያስፈልጋል፡፡
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ቀጣዩን አገራዊ ምርጫ ማካሄድ የሚቻል ይመስልዎታል?
አሁን ባለው ሁኔታ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም፡፡ ከተደረገም ኢህአዴግ ብቻ ነው ተጠቃሚ የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም ሌሎቹ ድርጅቶች የፓርቲ ጽ/ቤቶቻቸውን በየቦታው ከፍተው ለምርጫው መድረስ አይችሉም። በሌላ በኩል፤ መረጋጋት ሳይኖር አመቺ የሆነ ምርጫ ማካሄድ ፈፅሞ አይቻልም፡፡ ምርጫ ማካሄድ የሚቻለው ሰማዩም ምድሩም ሰላማዊ በሆነበት ሁኔታ ነው፡፡ ዲሞክራሲ ችግር አይችልም፤ በመረጋጋት ውስጥ እንጂ በግርግር ውስጥ አይገነባም፡፡ ስለዚህ ሁሉም ፓርቲዎች ተወያይተው፣ የመረጋጋትና የሽግግር ጊዜ በስምምነት መወሰን አለባቸው፡፡ በዚያ ጊዜ ውስጥ መረጋጋት ላይ ተሰርቶ፣ ለምርጫ መዘጋጀት ይቻላል፡፡
ሃገርን እንዴት ወደ ሰላምና መረጋጋት ማምጣት ይቻላል ይላሉ?
አንደኛ፤ የዘርና ብሄር አስተሳሰብን በዜግነት አስተሳሰብ መተካት ያስፈልጋል፡፡ የዘር ሃሳብን ማስወገድ አስፈላጊ ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ የውሸት ታሪክን ማስወገድ ተገቢ ነው፡፡ ሲቪክ ተቋማት ህዝቡን ስለ ዲሞክራሲ ማስተማር አለባቸው። የዘር ፖለቲካን ሳይሆን የህዝብን አንድነትና የዲሞክራሲን ምንነት የሚያስተምሩ ሲቪክ ተቋማት መፈጠር አለባቸው፡፡ ደቡብ አፍሪካን ያረጋጋው እኮ 3500 የሚደርሱ የሲቪክ ተቋማት ትምህርት ነው፡፡ የሲቪክ ተቋማት ሚና በቀላሉ መታየት የለበትም፡፡ እውቀት በሰፊው መንሰራፋት አለበት፡፡ ስሜት ቦታ ማጣት አለበት፡፡ ምክንያታዊነት ማበብ አለበት፡፡ ይህ እንዲሆን የሲቪክ ተቋማት አስተምህሮ ሚና በቀላሉ የሚታይ አይሆንም፡፡ ቋንቋዎች እውቀት ተሸካሚ መሆን አለባቸው፡፡ ብሔረሰብና መደብ አልባ መሆን አለባቸው፡፡ ምክንያቱም ቋንቋ አብሮ የሚወለድ ሳይሆን የሚለመድ ነው፡፡ ስለዚህ ቋንቋ የእውቀት ተሸካሚ እንጂ የብሔር መበየኛ መሆን የለበትም፡፡ ኢትዮጵያ አረብኛ ቋንቋ ያስፈልጋታል፡፡ አረብኛ ብታውቅ ሃብት ነው የሚሆናት፡፡ በዚህ በኩልም መታሰብ አለበት፡፡

Read 6448 times