Monday, 28 January 2019 00:00

በሜክሲኮ አምና ብቻ ከ33 ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ከአደገኛ ዕጽ ዝውውርና ከተደራጀ ውንብድና ጋር የተያያዙ የወንጀል ድርጊቶች በከፍተኛ ሁኔታ በተባባሱባት ሜክሲኮ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2018 ብቻ 33 ሺህ 341 ሰዎች መገደላቸውንና ይህ ቁጥር በአገሪቱ ታሪክ እጅግ ከፍተኛው እንደሆነ ተዘግቧል፡፡
በሜክሲኮ በአመቱ የግድያ ወንጀሎች ከተፈጸሙባቸው ሰዎች መካከል 861 ሴቶች እንደሆኑ  የአገር ውስጥ ሚኒስቴር ሰሞኑን ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ የዘገበው ዴችዌሌ፤ አዲሱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አንድሬስ ማኑኤል ሎፔዝ ኦርፓራዶር፣ ወንጀልን የሚከላከል ልዩ ብሄራዊ የጦር ሃይል በማቋቋም ሂደት ላይ እንደሚገኙ መነገሩን አመልክቷል፡፡
በአገሪቱ በአመቱ ግድያ የተፈጸመባቸው ሰዎች ብዛት ከአንድ አመት በፊት ከነበረው የ15.5 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ያስታወሰው ዘገባው፤ የተደራጀ ውንብድናና ወንጀል በከፍተኛ ሁኔታ ተባብሶ መቀጠሉን ገልጧል፡፡ የሜክሲኮ መንግስት እ.ኤ.አ ከ2006 አንስቶ በአደንዛዥ ዕጽ ዝውውርና ንግድ በተሰማሩ የተደራጁ ወንጀለኞች ላይ ወታደራዊ ዘመቻ እያከናወነ እንደሚገኝ ያወሳው ዘገባው፤ ከዚያ ጊዜ አንስቶም ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና የህግ አስፈጻሚ አካላትን ጨምሮ ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን አመልክቷል፡፡ በሜክሲኮ የግድያ ሰለባዎች ከሚሆኑት ሰዎች መካከል ጋዜጠኞች እንደሚገኙበትና ባለፈው አመት ብቻ በአገሪቱ 9 ጋዜጠኞች በወንጀለኞች መገደላቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
በሜክሲኮ የተደራጀ የወንጀል ድርጊት ከሚፈጽሙት ወንጀለኞች መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ለህግ ቀርበው ቅጣት እንደማይጣልባቸውና የህግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ ከፍተኛ ክፍተት እንዳለ የጠቆመው ዘገባው፤ በተለይ በአደንዛዥ ዕጽ ነጋዴዎች መካከል የሚደረገው ግጭት በርካታ ዜጎችን ለግድያ እየዳረገ መሆኑን በመጥቀስ ፣በ2017 የአገሪቱ መንግስት ከመሰል ግድያዎች ጋር የተያያዘ እንደሆነ የተነገረለትን የ250 ሰዎች አጽም ያለበት የጅምላ መቃብር እንዳገኘም  አክሎ ገልጧል፡፡

Read 1061 times