Monday, 28 January 2019 00:00

ዘመናዊው ሥነ-ጥበብና ፍልስፍና

Written by  መኮንን ማንደፍሮ
Rate this item
(5 votes)

 ክፍል ሁለት
በቀዳሚው ክፍል በዘመናዊው ሥነ-ጥበብ ጐልተው በወጡ ንቅናቄዎች ሥነ-ጥበባዊ አስተምህሮና በኤግዚስቴንሻሊዝስም ፍልስፍና ውስጥ የሚገኙትን ተዛማጅ ፅንሰ-ሐሳቦች ለመዳሰስ ሞክሬ ነበር፡፡ ይህ ተከታይ ክፍልም በዚሁ ርእሰ ጉዳይ ላይ አትኩሮቱን ያደረገ ነው።
4. ፉቢዝም (Fauvism)
ፉቢዝም በሃያኛው ክፍለ ዘመን ፈረንሳይ ውስጥ የተነሳ፣ ከጥንታዊው የሥነ-ጥበብ የአሠራር መንገዶችና ፅንሰ-ሐሳቦች በማፈንገጥ፣አዲስ የሥነ-ጥበብ አቅጣጫን ያስተዋወቀ የሥነ-ጥበብ ንቅናቄ ነው፡፡ የዚህ ንቅናቄ ዋናው መስራች ፈረንሳዊው ሠዓሊ ሄንሪ ማቲስ ነው፡፡ የፉቢዎች (Fauves) ሥነ-ጥበብ ዐቢይ ጭብጥ፤ እንደ ኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍና ሁሉ የሰው ልጅ ህልውናዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ናቸው፡፡ በተጨማሪም ቅፅበታዊ ስሜትን (spontaneity) እና እውነተኛ ውስጣዊ ስሜትን (sincerity) እንደ ዐቢይ የሥነ-ጥበብ መርህ የሚጠቀሙ ናቸው፡፡ የዚህ ንቅናቄ ዋና አቀንቃኝ ሠዓሊዎች የሥዕል ሥራዎች ውስጥ ከወትሮው የተለየ የቀለም አጠቃቀም ምርጫ ይንፀባረቃል፡፡ በሥዕል ሥራዎቻቸው ውስጥ የሚጠቀሙት ደማቅ ቀለማትን ሲሆን ቀለማቱም የገሀዱን ዓለም ትክክለኛ ገፅታ የማይወክሉ ናቸው፡፡ ፉቢስቶች የሥነ-ጥበብ ሥራዎቻቸው ውስጥ ከወትሮው በተለየ መንገድ ቀለማትን የሚጠቀሙት ግላዊ ውስጣዊ ስሜታቸውንና እሳቤያቸውን ለማንፀባረቅ ነው፡፡ ለዚህ ሐሳብ ዋቢ የሚሆኑት የማቲስ የሥነ-ጥበብ ሥራዎች ናቸው፡፡ ማቲስ ፖርትሬት ዊዝ ግሪን ስትራይፕ (Portrait with Green Stripe) በሚለው የሥዕል ሥራው ላይ የተለየ የአሠራር መንገድና የቀለም አጠቃቀም ይታይበታል፡፡ ሠዓሊው እዚህ ሥራው ላይ የምናገኛትን ሴት የፊት ገፅ፣ በገሀዱ ዓለም ከምናስተውለው የቀለም አይነት ፍፁም ባፈነገጠ ቀለም ነው የሣለው፡፡ የገፀ-ባሕሪዋ የግራ ፊት ገፅ፣ ሐምራዊ ቀለም የተቀባ ሲሆን የቀኙ ደግም ወይባ ቀለም የተቀባ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ አፍንጫዋና የቀኝ ዐይኗ ዙሪያ አረንጓዴ ቀለም የተቀባ ሲሆን የራስ ፀጉሯ ደግሞ ጥቁር ሰማያዊ ቀለም የተቀባ ነው፡፡  
5. ሱሪያሊዝም(Surrealism)
ሱሪያሊዝም በ1920ዎቹ እና 1930ዎቹ እ.ኤ.አ. አውሮፓ ውስጥ በሠፊው ተስፋፍቶ የነበረ ፈረንሳይ ውስጥ የተነሳ የሥነ-ጥበብና የሥነ-ጽሑፍ ንቅናቄ ሲሆን መሠረታዊ መርሆዎቹ የተዋቀሩት ታዋቂው ፈረንሳዊው ገጣሚ እንድሬ ብሬቶን በ 1924 እ.ኤ.አ. ባወጣው ነጋሪ (manifesto) አማካኝነት ነው። ብሪቶን ይህን የሥነ-ጥበብና ሥነ-ጽሑፍ መሠረታዊ መርሆች ያዘጋጀው የኦስትሪያዊውን የሥነ-ልቦና ሊቅ ሲግመንድ ፍሩድ፣ የሥነ-ልቦና ትንተና ዘዴ (psychoanalytic theory) መሠረት አድርጐ ሲሆን፣ ይህን አስተምህሮ ተንተርሶ  የተሠራ የሥነ-ጥበብና ሥነ-ጽሑፍ ሥራ፣ የአስተምህሮው ዐቢይ ፅንሰ-ሐሳቦች የሆኑትን ምናባዊነት (imagination)፣ ሕልም (dream) እና ነፃ ሕሊናዊ ስሜትን (free association) መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡ ብራቶን ሱሪያሊዝምን “ግልዕ የሆነ አእምሮአዊ ግብታዊነትን (Pure psychic automatism) መሠረት አድርጐ በንግግር ወይም በጽሑፍ  የሚገለፅ፣ የአንድ ግለሰብ እውነተኛ እሳቤ ሂደት ነው” ብሎ ይተረጉመዋል፡፡ ብሪቶን፤ ጸሐፊዎች ነፃ በሆነ መንገድ ድንገት የመጣላቸውንና የተሰማቸውን እሳቤ እንዲጽፉ የሚያበረታታ አቋም አለው፡፡  ይህ አይነቱን የአጻጻፍ ሂደት ግብታዊ (automatic writing) ይለዋል፡፡
በሥነ-ጥበቡ ዘርፍ ንቅናቄውን ካስፋፉ ሠዓሊዎች መካከል ስፔናዊው ሠዓሊ ሳልቫዶር ዳሊ ዋናው ሲሆን ማርክ አርነስት እና ጆኦን ሚሮም ተጠቃሽ ሠዓሊያን ናቸው፡፡
ሱሪያሊዝም ውስጥ የሚገኙ ዐቢይ ሥነ-ጥበባዊ ፅንሰ-ሐሳቦች፣ በከፊል ንቁ ከሆነው የሰው ልጅ አእምሮ (subconscious mind) ምናባዊ እሳቤዎች (fantasies) በአእምሮአዊ መታወክ (insanity) እና በሚዛናዊ  አስተሳሰብ (sanity) መካከል ያለውን አእምሮአዊ ሁኔታና በሕልም ውስጥ እንደሚስተዋሉ ተጨባጭነት የሌላቸው ትዕይንቶች ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡
 የሱሪያሊዝም ሥነ-ጥበብ ንቅናቄ መሠረታዊ እሳቤዎች የተገለፁባቸው የታወቁ የሥነ-ጥበብ ሥራዎች የዳሊ ዘ ፕርሲስተንስ ኦፍ ሚሞሪ (The Persistence of Memory) እና አፕሬሺን ኦን ፌስ ኤንድ ፍሩት ዲሽ ኦን ኤ ቢች (Apparition  on Face and Fruit Dish on a Beach)፣  የሚሮ ዘ በርዝ ኦፍ ዘ ወርልድ (The Birt of the world)  እና ዶግ ባርኪንግ አት ዘ ሙን (Dog Barking at the Moon) የሚሰኙት ናቸው፡፡
ኤግዚስቴንሻሊዝምና ሱሪያሊዝም የሰው ልጅን የምክንያታዊ አእምሮ የበላይነትና የገነት ሚና የሚነቅሱ (anti-rationalists) ናቸው፡፡ ኤግዚስቴንሻሊስቶች የሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ ውስጣዊ ስሜቱን በመጨቆን፣ የአእምሮአዊ እውቀቱን ሚና ብቻ እውቅና በመስጠት፣ አጠቃላይ ኑሮውን ለመምራት የሚያደርገውን ጥረት አበክረው ይነቅሳሉ። ምክንያታዊ ፍልስፍናዊ  እሳቤ (reason) ብቸኛውና የመጀመሪያው ዓለምን የምንረዳበት መንገድ አይደለም ይላሉ፡፡ በተመሳሳይ መልኩ፤ የሱሪያሊዝም ሥነ-ጥበብና ሥነ ጽሑፍ አቀንቃኞችም፣ የሰው ልጅ አእምሮአዊ አመክንዮውን ብቻ በመከተል፣ ከኢ-ምክንያታዊው የአእምሮው ክፍል ለሚመነጩ ተፈጥሮአዊ ፍላጎቶቹ ትኩረት መንፈጉን በፅኑ ይተቻሉ፡፡
6. አብስትራክት ኤክስፕረሺኒዝም (Abstract Expressionism)  
አብስትራክት ኤክስፕረሺኒዝም በምድረ አሜሪካ ኒዮርክ ከተማ ውስጥ በ1940ዎቹ እ.ኤ.አ የተነሳ በሥነ-ጥበቡ ዘርፍ ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት የነበረው ንቅናቄ ነው፡፡ ይህ ንቅናቄ ከዘመናዊዉ የሥነ-ጥበብ ንቅናቄዎች መካከል በጣም ተጠቃሽ የነበረና ከኢግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍናዊ እሳቤ ጋር በእጅጉ የሚቀራረቡ መሠረታዊ መርሆችን የያዘ ንቅናቄ ነው፡፡  ግለሰባዊ ነፃነት (freedom) እና ለራስ እውነተኛ መሆን (authenticity) የአብስትራክት ኤክስፕረሺኒዝም ሥነ-ጥበብ ንቅናቄ መሠረታዊ መርህ የሆኑ ዐቢይ የኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍና ፅንሰ-ሐሳቦች ናቸው፡፡ እንደ ዋናው የኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍና አቀንቃኝ ሳርተር እሳቤ፤ ማንኛውም ግለሰብ ፍፁም ሉአላዊ ስለሆነ የራሱን ግንዛቤ መሠረት አድርጐ የሕይወት ትርጉሙንና ሥነ-ምግባራዊና ሥነ-ውበታዊ እሴቶቹን ፈጥሮ የመኖር ሥልጣንና ኃላፊነት አለው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ አብስትራክት ኤክስፕረሺኒስቶች ግላዊ ነፃ ምናባቸውንና እሳቤያቸውን ተጠቅመው ጥበባዊ ሥራዎችን የሚሠሩ ሠዓሊያን ናቸው፡፡ የዚህን ንቅናቄ ዋና አቀንቃኝ ሠዓሊያን ልዩ የሚያደርጋቸው በሥነ-ጥበብ ሥራዎቻቸው ውስጥ ቅፅበታዊ ጥበባዊ ስሜታቸው (automatic impression) ቁልፍ ሚና ያለው መሆኑ ነው፡፡ እንደ አብስትራክት ኤክስፕረሺኒስቶች እሳቤ፤ እውነተኛ የጥበብ ፈጠራ በደመ-ነብስ የሚሠራ ሲሆን የሥዕል ሥራው ወደፊት ምን መልክ ሊኖረው እንደሚችል ሠዓሊው ቀድሞ የተለመው አይደለም፡፡
የአብስትራክት ኤክስፕረሺኒዝም ሥነ-ጥበብ ንቅናቄ ዐቢይ  አቀንቃኝ አሜሪካዊው ሠዓሊ ጀክሰን ፖሎክ ነው፡፡ ፖሎክ በልማዳዊው የሥዕል አሠራር ስልት ባለመወሰን ፍፁም አዲስ የሆነ መንገድ የሚከተል ሲሆን ይህም ቀለም የተነከረን ብሩሽ ሥዕል ከመሥሪያው ሸራ ጋር ሳይነካካ እላዩ ላይ በማንጠባጠብ (dripping) ደመነብሳዊ ጥበባዊ ፈጠራውን የሚገልፅበት ዘዴ ነው፡፡ ይህ ዘዴ ቀጥተኛ በሆነ መንገድ ሥዕልን የመሥራት ዘዴ (action painting) ይሰኛል፡፡ ፖሎክ ይህን የአሣሣል ስልት እንዲያዳብር የኪዩቢዝምና ሱሪያሊዝም ንቅናቄዎች ሰፊ ተፅእኖ ያሳደሩበት ሲሆን የአሠራር ስልቱንም የሚከተለው ግላዊ ጥበባዊ ስሜቱን ለመግለፅ ነው፡፡
በዚህ ዘዴም ብዙ ተደናቂ የሥዕል ሥራዎቹን ሠርቷል፡፡ ከፖሎክ የአብስትራክት (nonobjective) የሥዕል ሥራዎች መካከል ዋን፣ ነምበር ስርቲ ዋን፣ 1950 (One: Nuber 31, 1950)፣ ብላክ ኤንድ ዋይት  (Black and White )፣ ኮንቨርጀንስ (Convergence)፣ ሪፍሌክሽን ኦፍ ዘ ቢግ ዲፐር (Reflection of the Big Dipper)፣ ብሉ ፖልስ (Blue Poles) እና ላቬንደር ሚስት (Lavender Mist)  በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡                                

Read 1664 times