Monday, 28 January 2019 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)

  በተለያዩ ሚዲያዎችና አጋጣሚዎች የምንሰማቸው አንዳንድ ቀልዶች ህይወት አላቸው፡፡ መረራው ኑሮአችን ውስጥ እንደ ማር ጠብ እያሉ፣ የተኮማተረው ስሜታችንን እያፍታቱ በራሳችን ላይ እንድንስቅ ያደርጉናል፡፡
ልጆች እያለን “ማዕከላዊ” የሚባል ቦታ “ስንኖር”፤ አንድ ገዘፍ ያለ፣ ተጫዋችና ሳቂታ ጓደኛ ነበረን፡፡ የተፈቀደልን የነፋስ መቀበያ ደቂቃዎች ሲያልቁ፣ ለተረኞች ቦታ ለመልቀቅ ወደ ክፍላችን ስንመለስ፣ ይኸ ጓደኛችን ሁልጊዜ ወደ ኋላ ይቀራል፡፡ “ቶሎ በሉ” እያለ የሚነዳን የአስተዳደሩ ሠራተኛ የነበረ ሰው ታዲያ መጨረሻ ላይ ሲንቀራፈፍ የሚያገኘው እሱን ስለሆነ” “ግባ አንተ ቀርፋፋ” እያለ ያጣድፈዋል። አንዳንዴም ይገፈትረዋል፡፡ እሱ ግን ከመሳቅ በስተቀር በ”ክፉ ዓይን” እንኳ አያየውም፡፡
“ሁልጊዜ እያመናጨቀህ ለምን ትስቃለህ?” ስንለው..
“እሱ ባይኖር እነማን እንደሚገዙኝ ማን ያስታውሰኛል” ይለን ነበር፡፡ ቀልዶቹም እንደዛ ናቸው፡፡
ሰውየው ለጉዳይ (ምናልባት መታወቂያ ለማውጣት ይሆናል) ወደ አንድ የመንግስት ተቋም እንደሄደ “ፈፃሚ” የሚባለው ሰው ቅጽ እየሞላ…
“ብሔር?” ብሎ ሲጠይቀው
ባለጉዳዩ -
“የናቴን ነው ያባቴን?”
ፈፃሚ
“ያባትህን”
ባለጉዳዩ
“ያባቴን?” የናቱን ወይስ ያባቱን?” መጨረሻውን አስበው፡፡
አንድ ህፃን ደግሞ ከት/ቤት እንደተመለሰ አባቱን ያገኝና፤
“አባዬ! ቲቸር ያሳዩንን አስማት ላሳይህ?” …
አባት፤
“ከኔ የበለጠ አስማተኛ ከየት መጣ?”፡፡
አቡሽም እየተደነቀ፤
“አስማት ትችላለህ እንዴ?”  
አባት፤
“ታዲያ በስድስት መቶ ብር ደሞዝ አራት ልጅ እንዴት አሳድግ ነበር?”
አንድ እንጨምር፡፡
የአውሮፓ አሰሪዎች ሠራተኛ ሲቀጥሩ፤ “እስቲ ሰርተፊኬትህን አሳየን?” በማለት ሲጠይቁ፣ አሜሪካውያኑ ግን፤ “ስራውን ትችለዋለህ?” ብለው ይጠይቃሉ፡፡ እኛስ አገር? ምን እንደምትጠየቅ ታውቃለህ?...
***
ወዳጄ፡- እያንዳንዱ ሰው፤ “ሰው” የሚያሰኘው፤ የተሰራባቸው ነገሮች (essence)፣ የተቀባቸው ፀጋዎችና ራሱን ችሎ የሚያቆሙት የተፈጥሮ ስጦታዎች አሉት። ከሌሎች ጋር “ሲደመር” ማህበረሰብ፣ ህብረተሰብ፣ ብሔረሰብ፣ አገረሰብ ወዘተ ሊባል ይችላል። ማህበራዊ ተቋማቱ በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች፣ በህብረተሰብ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ በስልጣኔ ሂደትና የሽግግር ጉዞዎች ሳቢያ የሚፈጠሩ ናቸው፡፡
ሰው በጋራ ወይም በማህበር ተደራጅቶ ማሰብ ሲጀምር ራሱን መሆን ያቆማል፣ ማንነቱ ይደበቃል፡፡ ማህበራዊ አስተሳሰቡ፤ የስነልቦናና የማቴሪያል ጥቅም ካለው ይገፋበታል፡፡ ጥቅም ካላገኘበት ወይም ሲያገኝ የነበረው ጥቅም ከተቋረጠበት በጋራ አስተሳሰብ አይዘልቅም። የሚዘልቅበት ቢመስል እንኳ በተለየ መልክ ይሆናል፡፡ አማራጭ በማጣት፣ የሚፈራው ነገር በመኖሩ ወይም በሌሎች በማያምንባቸው፣ ነገር ግን በአድርባይነት በሚቀበላቸው ምክንያቶች ወዘተ፡፡ ይህ ካልሆነ ወይም አጋጣሚ ካገኘ፣ ያጣውን ለማስመለስ ወይም ለሚፈለገው አዲስና ሌላ ሲል በሌሎች ከመጠቀምና ሌሎችን መስዋዕት ከማድረግ ወደኋላ አይልም። ግድ ከሆነበት፣ ሁኔታዎች የሚቀየሩ ከመሰለው ወይም ተስፋ ከቆረጠ ደግሞ ያምፃል፡፡ ዓመፁ በራሱም፣ በሌሎችም ላይ ሊሆን ይችላል። የፍቅር እስከ መቃብሩ ፊታውራሪ መሸሻ፤ ልጃቸው የተባለችውን ሲሰሙ.. “ምነው ይኸን ሳልሰማ በሞትኩ” ነበር ያሉት፡፡ መቄዶኒያ ተዳክማ አቴናውያን ሃያል በሆኑበት ጊዜ፣ አርስቶትል አቴንስ በፍልስፍና ላይ ለሁለተኛ ጊዜ እንድትቀልድ አልፈቅድላትም በማለት በራሱ ላይ አምጿል፡፡ ዴዎጋንም እንዲሁ፡፡
ሰላማዊ በሆነ መንገድና በተሻለ ሃሳብ ሁኔታዎችን መቀየር ያልቻሉ አንዳንዶች ደግሞ በሌሎች ላይ መጨከን መፍትሔ ይመስላቸዋል፡፡ ጋንዲ፣ ኬኔዲ፣ ፖፕ ጆን ፖል፣ ሬጋንና ሌሎች ብዙ ታላላቅ ሰዎች፤ የእንደነዚህ ዓይነት ስሜታውያን ሰለባ ነበሩ፡፡ አንዳንዶቹ ቢተርፉም፡፡
ወዳጄ፡- እግዜርና መላዕክትን፣ ሰውና ሰውን የለየው ሃሳብ ነው፡፡ ሃሳብ አንዱን እርኩስ፣ አንዱን ቅዱስ ያሰኛል፡፡ እንደ መልካም ነገሮች ሁሉ የቅናትና የምቀኝነት፣ የመጋደልና የመጠፋፋት ሃሳብ በሰው ልጆች አእምሮ ውስጥ የታየው በ“ታሪክ” የመጀመሪያው ቤተሰብ ውስጥ ነው፡፡ በአቤልና ቃየል፡፡ ሁለቱ ወንድማማቾች፤ ከሰው የተፈጠሩ ሲሆኑ… ወላጆቻቸው አዳምና ሄዋን የሰው ልጆች አልነበሩም፡፡ አለመግባባትና ልዩነት ከነሱ ጋር አብረው የተወለዱ ሲሆን… የሃይማኖት፣ የድንበር፣ የኢኮኖሚና የመሳሰሉት ጦርነቶችም በሰዎች መሃከል ያለ የሃሳብ ልዩነት መገለጫና ሰበቦች ናቸው፡፡
ጽንፈኛ አስተሳሰቦች እየተገሩ የመጡት፣ የሰው ልጅ የኑሮ ፈተና ከሆኑበት ሁለት ምርጫዎች፡- ድንቁርናና ጦርነት ወይም ዕውቀትና ስልጣኔ አንዱን መምረጥ በመገደዱ፣ ተጋግዞና ተረዳድቶ መኖር ብቻ እንደሚያዋጣው በመገንዘቡ ነው፡፡
ወዳጄ፡- ሰዎች በአካልና በአእምሮ እንደሚለያዩ ሁሉ ሃሳባቸውም ይለያያል፡፡ ጠቃሚና ሰብዓዊነትን እስካገዙ ድረስ ሁሉም የስልጣኔ ማድመቂያ ናቸው፡፡ አንደ ነገር ልብ በል፡፡ ሰው ሁሉ ካወቀ እውቀት የለም፡፡ ሰው ሁሉ አማኝ ከሆነ እምነት የለም፡፡ የሚኖረው “ሰው” ብቻ ነው፡፡ ሁሉ ሰው በሽተኛ ከሆነ ሃኪም፣ ሁሉም ከዘፈነ አድማጭ፣ ሁሉም ከሞተ ሕይወት የለም፡፡ ሁሉም ሰው እውነትን ከተናገረ ወይም ከዋሸ፣ ሃቀኝነት ወይም ሃሳዊነት አይለይም፡፡
ወዳጄ፡- ሁሉም ሰው አንድ የፖለቲካ ፓርቲን ከመረጠ፣ ፓርቲው ወይም መራጩ የለም፡፡ የኛም “ጉድ” እንዲሁ ነው፡፡ ኢህአዴግ 100% ተመርጫለሁ ሲለን፤ ወይ እሱ ወይ እኛ አልነበረንም፡፡ “የለም” ስንል “አለሁ” ካለ፣ “የላችሁም” ሲለን “አለን” ካልን፣ ከሁለት አንዳችን ዋሽተናል፡፡ ህዝብ እንደ ህዝብ፣ ሰው እንደ ግለሰብ ሙሉ በሙሉ አይዋሽም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ ግን ይዋሻል፡፡
ኢህአዴግ ዋሽቷል፡፡ ውሸታም ፓርቲ በሚመራው መንግስትና ባዋቀራቸው ተቋማት ውስጥ “ሰው ሰው” የሚሸቱ፣ እውነተኛ ግለሰቦችና የአገር ተቆርቋሪዎች መኖራቸው አያጠራጥርም፡፡ እንደ ፓርቲና እንደ መንግሥት ግን አጭበርብሯል፡፡
ወዳጄ፡- “እንቁላል ከውስጥ ሲሰበር ህይወት ይወለዳል” ሲባል፣ ፓርቲው ውስጥ ያሉ ቀና ሰዎች የታሰሩበትን አጓጉል ሃሳቦች ንደው፣ ጨለማውን ሰብረው “ቦግ” እንዲሉ፣ እንደገና ታድሰው አታላይነትን፣ ዘረፋን፣ ጉቦኝነትን፣ ዘረኝነትና ህገወጥነትን በማጋለጥ ትግሉን ካላገዙ፤ ፓርቲው ወይም ቅርፊታቸው ወስጥ ይበሰብሳሉ እንደ ማለት ይመስለኛል፡፡ “ፓርቲ የሬሳ ሳጥን አይደለም” እንደሚባለው!!
ወዳጄ፡- ወደ ቀልዳችን ስንመጣ፣ ስራ ለመቀጠር አውሮፓውያንና አሜሪካውያኑ የሚጠይቁትን ሰምተናል፡፡ የኛ ነበር የቀረን፡፡ የእኛ አገርን ቀጣሪዎች ጥያቄ “ማነው የላከህ?” ነው አሉ፡፡
ሠላም!!

Read 1102 times