Monday, 28 January 2019 00:00

ያሬዳዊው ሥልጣኔ

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(2 votes)

 ክፍል- ፯ ሥልጣኔው ላይ የተሰነዘሩ ትችቶች
               
     እስከ ዛሬ ድረስ ያሬዳዊው ሥልጣኔ የቆመባቸውን አምዶችና በባህላችን ውስጥ ያስቀመጣቸውን አሻራዎች ስንመለከት ቆይተናል፡፡ ከዚህ በኋላ ደግሞ ሥልጣኔው በሂደት ያጋጠሙትን የዘመናዊነት ተግዳሮቶችንና በኢትዮጵያ ምሁራን ዘንድ የተሰነዘረበትን ትችቶች በተከታታይ እንመለከታለን፡፡
በመጀመሪያ፣ ጥንታዊው የአክሱም ሥልጣኔና ያሬዳዊው ሥልጣኔ በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘመናት ላይ የተከሰቱ ሁለት የተለያዩ ሥልጣኔዎች መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ያሬዳዊው ሥልጣኔ፣ ጥንታዊውን የአክሱም ሥልጣኔ ከ6ኛው ክ/ዘ ጀምሮ በመተካት የመጣ ሥልጣኔ ነው፡፡ ምንም እንኳ ጥንታዊው የአክሱም ሥልጣኔ ዲበ አካላዊ፣ ሥነ ምግባራዊና ኪነ ጥበባዊ መሰረቶቹ እንዴት ያሉ እንደነበሩ የተሟላ መረጃ ባይኖረንም፣ በዚህ ረገድ ስለ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ግን በቂ መረጃ አለን፤ አንድም፣ አሁን ዘመን ድረስ እየኖርንበት ስለሆነ፣ ሌላም በየዘመኑ የነበሩትን ነገሮች በተለያዩ መዛግብት ሰፍረው ስለምናገኛቸው፡፡
ከዚህ ቀደም እንዳልኩት፣ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ዲበ አካላዊ፣ ሥነ ምግባራዊና ኪነ ጥበባዊ መሰረቶች በምንላቸው ሦስት አምዶች ላይ የተመሰረተ ነው፤ በቅደም ተከተልም ተአምራዊነት (ሚስጥራዊነት)፣ ብህትውናና ሰሞነ ሕማማት ናቸው፡፡ እንግዲህ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን እስከ ዛሬ ድረስ በባህል፣ በሃይማኖት፣ በኪነ ጥበብ፣ በስነ ምግባር፣ በስነ ልቦና፣ በታሪክ፣ በፖለቲካና በሀገር ግንባታ የፈጠርናቸው አስተሳሰቦችና እሴቶች ሁሉ ከእነዚህ ሦስት አምዶች የሚቀዱ ናቸው፡፡
በመሆኑም፣ ያሬዳዊውን ሥልጣኔ ከሌሎች የተመሳሳይ ዘመን ሥልጣኔዎች ጋር ስናነፃፅር ወደ ኋላ ቀርተናል? ወይስ ወደ ፊት ተስፈንጥረናል? የምንለው የእነዚህን ሦስት አምዶች ምንነትና ውጤት በመፈተሽ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የምሁራን ታሪክ ውስጥ ይሄንን ፍተሻ ለመጀመሪያ ጊዜ ያደረገው ፈላስፋው ዘርዓያዕቆብ ነው - በ17ኛው ክ/ዘ፡፡
በሌላ አነጋገር፣ ምንም እንኳ ተአምራዊነት፣ ብህትውናና ሰሞነ ህማማት ላይ የተመሰረተው ያሬዳዊው ሥልጣኔ ከ6ኛው ክ/ዘ ጀምሮ ላለፉት 1500 ዓመታት ለኢትዮጵያውያን የሀገራዊና ማህበረሰባዊ ግንባታ መሰረት ሆኖ ቢያገለግልም፣ ቆይቶ ግን ይሄ መሰረት ከትችት አላመለጠም፡፡ ትችቶቹም የመጡት በዋነኛነት ከኢትዮጵያውያን ፈላስፎች፣ የታሪክ ባለሙያዎችና የዘመናዊነት አቀንቃኝ ምሁራን ነው፡፡ በዛሬው ፅሁፌ የትችቶቹን አጠቃላይ ባህሪ እንመለከትና፣ በቀጣይ ፅሁፎቼ ግን እያንዳንዱን ትችት ለየብቻው ሰፋ አድርገን እንመለከታለን፡፡
ከፈላስፎች የመጣ ትችት
ያሬዳዊው ሥልጣኔ እስከ 17ኛው ክ/ዘ ድረስ ካፈራቸው ሊቃውንት ውስጥ ከየትኛውም ወገን ምንም ዓይነት የሰላ ትችት አላጋጠመውም ነበር፡፡ በ17ኛው ክ/ዘ ግን የመጀመሪያው ትችት ከኢትዮጵያውያን ፈላስፎች መጣ፡፡ በታሪክ እንዳየነው፤ ሥልጣኔዎች በውስጣቸው የተሸከሙትን ጉድፍ በመጀመሪያ የሚያዩላቸው ፈላስፋዎች ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር ያሬዳዊው ሥልጣኔም ካጋጠሙት ተግዳሮቶች ውስጥ የመጀመሪያው ትችት ከኢትዮጵያውያን ፈላስፎች መምጣቱ የሚጠበቅ ነው፡፡
ሆኖም ግን፣ ከአክሱም ተነስቶ በጎንደር እንፍራንዝ የቀጠለው ይህ ትችት፤ ሁለት ግለሰቦችን (ዘርዓያዕቆብንና ወልደ ህይወትን) ብቻ ያቀፈ ነው፡፡ አሳዛኙም ነገር፣ ይህ ፍልስፍናዊ ትችት ከሁለት ግለሰቦች በላይ መሄድ አለመቻሉ ነው፡፡ ምናልባት ግን ትችቱ ጎንደር ላይ መሰረቱን በድብቅ በማስፋት አሁን ያለውን የአውራምባ ማህበረሰብ ሳይፈጥር አይቀርም የሚል ግምት አለኝ፡፡
በዘርዓያዕቆብና በወልደ ህይወት በ17ኛው ክ/ዘ አጋማሽ ላይ የተጀመረው ይህ ትችት ግን ሌሎች ተቀባይ ምሁራንን ሳያገኝ ለ300 ዓመታት ተዳፍኖ ከቆየ በኋላ፣ ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ሌላ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ በ20ኛው ክ/ዘ አጋማሽ ላይ ተነሳ - ዶ/ር እጓለ ገብረ ዮሐንስ። እጓለ ‹‹የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ›› በሚለው መፅሐፉ ውስጥ ስለ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ባህሪና የአስተሳሰብ መሰረት የተብራራ ሐሳብ በማቅረብ በመንፈስ የዘርዓያዕቆብ ቅጥያ መሆኑን አሳይቶናል፤ ምንም እንኳ እጓለ ስለ ዘርዓያዕቆብ ያለው ነገር ባይኖርም፡፡  
ሆኖም ግን፣ የእጓለን ሐሳብ ተቀብሎ ያስቀጠለ ሌላ ኢትዮጵያዊ ምሁር ሳናገኝ፣ 46 ዓመታት ከቆየን በኋላ በ2002 ዓ.ም ሌላ አንድ እንግዳ ሰው ‹‹አክሱማዊነትና ላሊበላዊነት›› የሚል እንግዳ ሐሳብ ይዞ ከዚያው ከፍልስፍና ትምህርት ክፍል ወጣ - ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ። በጣም የሚገርመው ነገርም እነዚህ ሦስት የፍልስፍና መምህራን (ዘርዓያዕቆብ፣ እጓለና ዳኛቸው) በየራሳቸው ዘመን ላይ ሆነው ምንኩስና፣ ያሬዳዊው ሥልጣኔና ላሊበላዊነት በማለት ያነሷቸው ሦስት ሐሳቦች ተመሳሳይ ሲሆኑ፣ በይዘታቸውም ያሬዳዊው ሥልጣኔ የተሸከማቸውን ጉድፎች በተለያየ ቅላፄ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ የትችታቸው ይዘት ሰፋ ስለሚል ለብቻው በክፍል-8 እና 9 እመለስበታለሁ፡፡
ከታሪክ ፀሐፊዎችና ከዘመናውያን የመጣ ትችት
ከፈላስፎች በመቀጠል ያሬዳዊው ሥልጣኔ ላይ የመጣው ትችት፣ ከታሪክ ፀሐፊዎችና ከዘመናውያን ሲሆን፣ ዘመኑም 19ኛውና 20ኛው ክ/ዘ ነው፡፡ በዚህ ትችት ውስጥ የሚመደቡት አለቃ ተክለየሱስ ዋቅጅራ፣ አለቃ አፅመ ጊዮርጊስና ነጋድራስ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ ናቸው፡፡
ከፈላስፎች የመጣው ትችት ያሬዳዊው ሥልጣኔ የቆመበት የባህል መሰረት ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣ ከታሪክ ፀሐፊዎችና ከዘመናውያን የመጣው ትችት ግን ሥልጣኔው የሚጠቀምበት የታሪክ አተራረክ ላይ ጥያቄ የሚያነሳ ነው፡፡ ትችቶቹም የታሪክ አተራረኩ ከተአምራዊነትና ከሚስጢራዊነት እንዲርቅ፣ እንዲሁም ገለልተኛና ሚዛናዊ እንዲሆን የሚጠይቁ ናቸው፡፡
የትችቶቹ አጠቃላይ ባህሪ
ያሬዳዊው ሥልጣኔ ላይ ከኢትዮጵያውያን ፈላስፎች፣ የታሪክ ፀሐፊዎችና ዘመናውያን አማካኝነት የተሰነዘሩት ትችቶች አድማሳቸው ከዲበ አካላዊ (ፍልስፍናዊ) ትችት እስከ ባህልና የታሪክ አተራረክ ድረስ የሰፋ ነው፡፡ ምንም እንኳ በያሬዳዊው ሥልጣኔ ላይ የተሰነዘሩት እነዚህ ትችቶች፣ የቆዩና ዘርፈ ብዙ ቢሆኑም፣ ትችቶቹ ግን በየዘመናቱ የተበታተኑና ያልተቀናጁ፣ ቀጣይነት የሌላቸው (የተቆራረጡ)፣ እርስበርስ የማይተዋወቁና አንደኛው በሌላኛው ላይ ያልተገነባ፣ እንዲሁም ጥልቀት የሌላቸው ናቸው። እስቲ ከኢትዮጵያውያን ፈላስፎች የመጡትን ትችቶች እንደ አብነት እናንሳ፡፡
ከላይ እንደጠቀስኩት፣ በተለያዩ ዘመናት በዘርዓያዕቆብ፣ በእጓለና በዳኛቸው አማካኝነት የተነሱት ምንኩስና፣ ያሬዳዊው ሥልጣኔና ላሊበላዊነት የሚሉት ሐሳቦች በይዘታቸው ተመሳሳይ ቢሆኑም፣ ምሁራኑ ሐሳቦቻቸውን እርስበርስ ለማዛመድ አልቻሉም፡፡ ለምሳሌ፣ እጓለ ስለ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ሲፅፍ፤ ከዘርዓያዕቆብ ሐተታ በመንደርደር አይደለም፡፡ ዳኛቸውም ስለ ‹‹አክሱማዊነትና ላሊበላዊነት›› ሲተነትን እጓለና ዘርዓያዕቆብ ካነሱት ሐሳቦች ጋር በማዛመድ አይደለም፡፡ የዚህ ችግር ምንጭ ደግሞ ምሁራኑ ስለ ተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳይ እየፃፉ እንደሆነ አለማስተዋላቸው ነው፡፡ በዚህም የተነሳ፣ ምሁራኑ ስለ ተመሳሳይ ጉዳይ እየፃፉ፣ ሲጠቀሙበት የነበሩት ቃላት (ፅንሰ ሐሳቦች) ግን የተለያዩ ነበሩ - ‹‹ምንኩስና››፣ ‹‹ያሬዳዊው ሥልጣኔ›› እና ‹‹ላሊበላዊነት›› የሚል፡፡ ምሁራኑ ለተመሳሳይ ሐሳብ አንድ የጋራ ፅንሰ ሐሳብ አለመጠቀማቸው ሐሳቡ እየተገነባ እንዳይሄድና እንዳይዳብር አድርጎታል፡፡
በዚህም የተነሳ፣ ትችቶቹ በየዘመናቱ የተበታተኑ፣ ቀጣይነት የሌላቸው (የተቆራረጡ)፣ አንደኛው በሌላኛው ላይ ያልተገነባና ጥልቀት የሌላቸው እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ ይሄም በተራው፣ በሀገራችን ምሁራዊ ከባቢ (intellectual climate) ላይ ሦስት ተያያዥ ችግሮችን አምጥቶብናል፡፡ የመጀመሪያው፣ ትችቱ በደንብ የተዋቀረ ፍልስፍናዊ መሰረት እንዳይኖረው አድርጎታል፡፡
ሁለተኛ፣ ሐሳቡ በከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ተቋማት ውስጥ ራሱን የቻለ የክርክር ተዋስኦ (Academic Discourse) ሆኖ መውጣት እንዳይችል አድርጎታል። ሦስተኛ፣ ሐሳቡ (ትችቱ) ፍልስፍናዊ መሰረት በማጣቱ የተነሳ በሌሎች የጥናት መስኮች ውስጥ የተነሱ ምሁራንም (ለምሳሌ፣ የታሪክ ባለሙያዎች፣ የኪነ ጥበብ ሐያሲያን፣ ፖለቲከኞችና ዘመናውያን) ትችቶቻቸውን ከፍልስፍናዊው መሰረት መቅዳት እንዳይችሉ አድርጓቸዋል፡፡
ለምሳሌ፣ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ በ20ኛው ክ/ዘ መጀመሪያ ላይ ምንኩስናንና የታሪክ አተራረክን በተመለከተ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ላይ የሰነዘረው ትችት፤ ዘርዓያዕቆብና ወልደ ህይወት በ17ኛው ክ/ዘ በሐተታቸው ከፃፉት ሐሳብ ጋር በጣም ተመሳሳይ ነው፡፡ ሆኖም ግን፣ የእነ ዘርዓያዕቆብን ሐሳብ ወደ እነ ገብረ ህይወት ያሻገረ ሌላ ኢትዮጵያዊ ምሁር መካከል ላይ ባለመገኘቱ፣ ገብረ ህይወት ትችቱን ዘርዓያዕቆብ ባነጠፈው ፍልስፍናዊ መሰረት ላይ ማድረግ አልቻለም፡፡ በዚህም የተነሳ የገብረ ህይወት ትችት ጥልቀትና ስፋት ሊያገኝ አልቻለም፡፡
በእንደዚህ ዓይነት የቀጣይነት ችግር የተነሳ፣ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ላይ የተሰነዘሩ ትችቶች በየዘመኑና በየምሁራኑ የተበታተኑና ወደ ዘመናዊ ማህበረሰብነት ለመሸጋገር የሚረዳ ማህበራዊ ንቅናቄን መፍጠር የተሳናቸው ሆነው ቀርተዋል፡፡

Read 1297 times