Print this page
Monday, 28 January 2019 00:00

የአድባር ዛፍ ቅኔ! (ጥበባዊ ወግ)

Written by  አብይ ተስፋዬ አሳልፍ/አተአ/
Rate this item
(3 votes)

  ከአያቴ ጋር በረንዳ ላይ ተቀምጠን ስለ አገርና ስለ ትውልድ እንከራከራለን፡፡ እኔም ከመጠየቅ ወደ ኋላ አልልም፣ አባባም ከማስረዳት አይደክምም፡፡ ‹‹…አባባ ደግሞ ታበዛዋለህ! ሰውና ዛፍ ምን ያገናኘዋል! ›› እለዋለሁ፤ ቀድሞ የሰጠኝን  ማብራሪያ ለጥቄ፣ የነገራችንን ቁም ነገር በመከተል፡፡ እያወራኝ ያለው ከደጃችን ስላለው ትልቅ ዛፍና ስለ ሰው ህይወት ነበር፡፡
‹‹…ይገናኛል እንጂ፡፡ በተፈጥሮ ሁሉም ነገር እርስ በራሱ የተጠላለፈ ነገር አለው፡፡ ምሳሌውንና ህይወታችንን ሁሉ የምንኮርጀው ከተፈጥሮ ነውኮ!›› ይለኛል ኮስተር ብሎ። በመዳፉ መካከል የያዛቸውን የሽምብራ ፍሬዎች እያሻሸ… ‹‹….አየህ ጌታመሳይ፤ አፈር ማለት አለም ነው፣ የሁሉ ነገር መቆሚያ መሰረት። አገር ማለት ደግሞ ይህ የምታየው ዛፍ ማለት ነው። ቅድመ አያቶችና ሌሎቹ የኋላ ቤተሰቦቻችን ደግሞ የዛፉ ስር ማለት ናቸው፡፡ ከላይ ለሚታየው ለዚህ ግንድ፣ ቅርንጫፍ፣ ቅጠል፣ አበባና ፍሬ መሰረቱ እነሱ ናቸው፡፡ የዛፉ ስር ሁሉን ወደ ላይ ካላመጣ፣ ከላይ ያማረ ነገር አይታይም፣ ከታች ስሩ ከተቆረጠ ህይወት አይገኝም። ግንዱ አያቶች ናቸው፣ሁሉን የተሸከሙቱ፣ ቅርንጫፉና ቅጠሉ ወላጆች ናቸው ከግንዱ የወጡና የልምላሜው መታያ ክፍሎች፣ የፀሃይን ሙቀት ለመላው አካል ማቀበያና የውጤቱ ሁሉ መዳረሻ፡፡ አበባውና ፍሬው ደግሞ ልጆች ናቸው፣ ሁሉን ከስሩና ከግንዱ፣ ከአፈሩና ከፀሃዩ እየተቀበሉ የሚያድጉ። ሲጎድልባቸው የሚኮስሱ ወይም የሚጠወልጉ፣ ሲመቻቸው የሚፋፉ፡፡ የውበት መገለጫና የቀጣይ ህይወት መስመር መቀጠያ መንገዶች፤ ዛፉ አብቦ ካላፈራ ቀጣይ የሚባል ትውልድ አይኖርምና!….››
ማብራሪያውን እየሰማሁ የሰፈራችን አድባር የሆነውን የጃካራንዳ ዛፍ በጥልቅ እይታ አጠናለሁ፡፡ ይህንን ዛፍ ሳስተውል ደግሞ ሁልጊዜ ከጭንቅላቴ የማይጠፋው ነገር፣ ጊዜን/ወቅትን/ ማሰብ ነው፡፡ ወቅቱ ሲሆንና ሲለመልም ይህ ዛፍ የብዙዎች ጥላና ማረፊያ ነው፡፡ ለብዙዎችም መከታ ነው፡፡ በወቅቶች መለዋወጥ ደግሞ ሁኔታው ሁሉ ሲቀየር ደግሞ እታዘባለሁ፡፡ በባለፈው ወቅት በሃምራዊ አበቦች ታጅቦ አካባቢውን በጣም አስውቦት ነበር፡፡ መዓዛው በመልካም ጠረን አካባቢውን ያውድ ነበር፡፡ አላፊ አግዳሚው፣ ሰፈረተኛውና መንገደኛው ሁሉ ለጥቂት ደቂቃዎች ቆሞ እያየው ይደነቅበት ነበር፡፡ ብዙ ሰዎች ምነው በኛ አካበቢ ቢኖር እያሉም ይመኙታል፡፡
በልምላሜው ወቅት ዛፉ በኩራት ሲንጠራራና በቀስታ በምትነፍሰው ነፋስ ውስጥ ወዲያ ወዲህ እያለ ሲንጎማለል ቁጭ ብዬ ታዝቤዋለሁ፡፡ አድናቂዎቹ ይበረክታሉ። ከአላፊ አግዳሚው ሰው በተጨማሪ ንቦች በመንጋ ይቀስሙታል፣ ነፍሳት በሰልፍ ይሰፍሩበታል፣ ድቃቂ ቁጫጮችና ጉንዳኖች ይርመሰመሱበታል፣ የሚያማምሩ ወፎች በላዩ ላይ ጎጇቸውን ቀልሰው እየተደሰቱ ይኖሩበታል፤ እኒሁ ወፎቹ በየማለዳው ሲዘፍኑና ሲጨፍሩ ለግቢያችንና ለአካባቢያችን ድምቀት ነበር። ዛፉም በሙሉ ደስታና በራስ መተማመን ለወራት ሲደሰት ይሰነብታል፡፡
ይህንን እያውጠነጠንኩ ከጭንቅላቴ የማይጠፋውን የቀዳማዊ ኃይለስላሴን መጨረሻ አስባለሁ፡፡ እውነትም ዛፍ ማለት የህይወትና የትውልድ ሞዴል፣ የትልቅ ሰው ምሳሌና የዘር ሐረግ ቅኔ ሰምና ወርቅ ነው፡፡ ጃንሆይ በሰላሙ ወቅት ህዝባቸው፣ በፍርሃትና በክብር ከመሬት ዘፍ እያለ ይሰግድላቸው ነበር፡፡ የድሃ አባት፣ የብዙዎች መመኪያና ጥላ ከለላም ይሏቸው ነበር፡፡ (ልክ እንደ ለምለሙ አድባር)። ህዝቡም በእርሳቸው ደስተኛ ይመስል ነበር። (ሳይወድቁና ያገሩ ሁሉ ምሳር በላያቸው ሳይወድቅ በፊት፡፡)
***
በመጨረሻቸው አካባቢ እንዲህ ሆኖ ነበር፡፡
ወታደሮቹ አንድ ማለዳ ቤተ መንግስቱን በታንክ አስከብበው ከች አሉ፡፡ ከቤተ መንግስት የተከሰቱት አስራ ሶስቱ የደርግ ልዑካን በሻምበል ደበላ ዲንሳ ተመርተው ነበር። ጃንሆይም እንደተፈለጉ ተነግሯቸው ከፎቅ ወርደው በዝግታ ከዙፋናቸው ተቀመጡ፡፡ የቴሌቪዥን ካሜራዎች ተደቅነዋል፡፡ በመቀጠል ሻምበል ደበላ ዲንሳ ወታደራዊ ሰላምታ ገጭ አድርገው ካቀረቡ በኋላ እንዲህ ሲሉ አነበቡላቸው፡ ‹‹…ለአገርና ለህዝብ ደህንነት ሲባል በዛሬው ዕለት ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ከስልጣን ወርደዋል፤ ለደህንነትዎ ሲባልም አስተባባሪው ኮሚቴ ወዳዘጋጀልዎ ቦታ እንዲሔዱ ተወስኗል!…›› (ሲጨርሱም  ሰላምታውን መሬቱን በተረከዝ ጫማ ገጭ አድርገው ደገሙ።)
ንጉሱ በድንዛዜ ሲያዳምጡ ከቆዩ በኋላ ምንም መልስ አልሰጡም፤ ዝም ዝም ሆነ፡፡ ሻምበሉም ከንጉሱ ጋር ወደነበሩት ራስ እምሩ ጠጋ ብለው፤ ‹‹ልዑልነትዎ አንድ ነገር ያድርጉ እንጂ፣ ሰዓት የለንም። …. ግርማዊነታቸውን ፍጠኑ ማለት አልችልም!›› አሏቸው፡፡ ራስ እምሩም በብዙ ነገር እየተብሰለሰሉ ጥቂት ከቆዩ በኋላ ወደ ግርማዊነታቸው ዝቅ ብለው፤ ‹‹… እንዳሉት ማድረግ ነው እንግዲህ፤ ሁሉም ነገር አልቆለታል! …›› አሏቸው፡፡
በድጋሚ ፀጥታ በቤተ መንግስቱ ለሰከንዶች የአመታት ያህል ረበበበት፡፡ በመጨረሻም ንጉሱ እንዲህ አሉ፤ … ‹‹ያነበባችሁትን ሰምተናል። የኢትዮጵያ ንጉሰነገስት ስንሆን ስም ብቻ አይደለም። ቢሆንም በየጊዜው የሚለዋወጠው ነገር ደግሞ ለአገር የሚጠቅም ነገር እስካለበት፣ የኢትዮጵያን ታሪክ ጠብቃችሁ ማልማት ከቻላችሁ የእኛ ታሪክ እዚህ ላይ ያበቃል፡፡ ካልቻላችሁ የናንተ ታሪክ እዚያ ላይ ያቆምና የእኛ ይቀጥላል፡፡ አገራችንንና ህዝባችንን በምንችለው አገልግለናል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ እድል የእኛን መወገድ የሚጠይቅ ከሆነ ግን ስራችንን አቁመን፣ ማንኛውንም ነገር ለመቀበል ዝግጁ ነን። አሁን ተራው የእኛ ነው ካላችሁ፣ ኢትዮጵያን ጠብቁ።››
ማንም መልስ አልመለሰላቸውም፡፡
***
ይኸው ነው፡፡ ጃካራንዳው ቅጠሎቹና አበቦቹ አምረው እያለ፣ ሁሉም ከበው ያሞግሱትና ይደነቁበት ነበር፡፡ ቅጠሎቹ ሲደርቁና  ሲረግፉ ብዙዎቹ አያስተውሉትም፡፡ ፊታቸውን ወደ ሌላውና ወደ ባለወቅቱ ያዞራሉ፡፡
***
እንዲያውም ቀጥሎ ያለው ታሪክ ነበር ልቤን የሚነካው፡፡ ከጸጥታዎች በኋላ ወታደሮቹ እንዲህ አሏቸው፤
‹‹ግርማዊ ሆይ፤ እባክዎ ይከተሉን እንሒድ!››
ጃንሆይም ቆጣ ብለው፤ ‹‹የት ነው የምትወስዱን? የት ነው የምንሔደው?››
‹‹ልዩ ማረፊያ ተዘጋጅቶልዎታል፤  ጃንሆይ!››
‹‹እኮ የት?››
‹‹አዲስ አበባ ነው ግርማዊ ሆይ፡፡ ለደህንነትዎ ሲባል በሚስጥር የተያዘ ቦታ ነው፡፡ ትክክለኛውን ስፍራም እንዳልነግርዎ አልተፈቀደልኝም፡፡››
‹‹አንድ አሽከር ሊከተለን ይችላል?!››
‹‹አዎን ግርማዊ ሆይ፡፡ ማንን ነው የሚፈልጉት?  ስሙ ማን ነው?››
‹‹ስሙን ምን አስጠየቀህ፡፡ አንድ አሽከር ነው የምንፈልገው ካልን አይበቃም?›› ቆጣ ብለው። ወዲያው ደግሞ ‹‹ወሰኔ!›› ብለው ተጣሩ፡፡ ወሰኔ ቀርቦ እጅ ሲነሳ፣ ጃንሆይ ሌላ ጥያቄ አስከተሉ፤ ‹‹መፅሃፍስ ይዘን መሄድ እንችላለን!?››
‹‹የፈለጉትን ያህል ጃንሆይ!…››
ጃንሆይ በዝግታ ከወንበራቸው ተነስተው፣ በወታደሮቹ መሃል ሲያልፉ አንዱ ወታደር መሳሪያውን በተጠንቀቅ ደግኖ ከፊቱ ለፊቱ አንጠልጥሎ አዩትና እንዲህ አሉት አሉ፤ … ‹‹ለምንድነው መሳሪያህን እንዲህ አንጠልጥለህ የያዝከው?!››
‹‹ለአያያዝ እንዲመቸኝ ነው ጃንሆይ!…››
‹‹እኛን ለመያዝ?!››
‹‹አይደለም ግርማዊ ሆይ! መሳሪያውን ማለቴ ነው!›› ሲላቸው ፈገግ ብለው፣ ከአዳራሹ ወደ በረንዳው ወጡና ሮልስ ሮይሳቸውን በአይናቸው ይፈልጉ ጀመር፡፡ በስፍራው የቆመችው አሮጌ ቮልስ ብቻ ነበረች፡፡ ቀጥታ ወርደው ከሾፌሩና ጋቢና ከተቀመጠው ወታደር ኋላ ከወሰኔ ጋር ተሳፈሩ። ከውጪ የተሰበሰቡ ህዝቦችም የመጨረሻውን ንጉሰ ነገስት፤ ‹‹ሌባ! ሌባ!..›› እያሉ ይከተሏቸው ነበር አሉ፡፡
ከአልባሾቻቸው አንዱ የሆኑት ደግሞ ስለ መጨረሻው አካባቢ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል። ‹‹…ትዝ እንደሚለኝ ነሐሴ 20 ቀን 1967 ተራዬ ደርሶ ለማደር ስሔድ ተከለከልኩ። ይህንኑ ለጃንሆይ ለመንገር ተፈቀደልኝና ልነግራቸው ገባሁ፡፡ ከምሽቱ ሶስት ሰዓት አካባቢ ነበር። ወደ መኝታቸው ቀርቤ የተባለውን ስነግራቸው፣ ከአልጋቸው ተነሱና እንዲህ አሉ፤ ‹‹ቤቱ ጠቧቸው ነው? እንግዲህ ውጣላቸው። ሰፋ አድርገን እንሰራላቸዋለን!›› ወዲያው በርከክ አሉና እንባቸውን ከአይናቸው እየጠረጉ፣ አገራቸውን እንዲህ ሲሉ ይጠይቁ ነበር፤  ‹‹እውነት ግን በድለንሻል ?! እውነት አልደከምንልሽም?!››
***
ይህ የደጃችን ጃካራንዳ ወቅት ሲቀየር ቅጠሎቹና አበቦቹ መርገፍ ይጀምራሉ። መጀመሪያ አበቦቹ በሙሉ እንደረገፉ የአካባቢያችን ሰውና አላፊ አግዳሚው መሬት ላይ የተነጠፉትን የአበባ ውዳቂዎች እየረጋገጠ ይሄዳል፡፡ ቀና ብሎ እንደ ድሮው እያስተዋለ ማድነቁ ይቀርና ሁሉንም ይረሳል፡፡ ትልቁ ዛፋችን ተስፋ መቁረጥ ሲጀምረው ይታወቀኛል። ቀስ እያሉ ቅጠሎቹ አንድ በአንድ እየወደቁ ወደ ማለቁ ሲቃረቡ፣ በላዩ ላይ ይኖሩ የነበሩት ወፎችም ጎጇቸውን እያፈረሱ ይጠፋሉ፡፡ የድሮ ግርማ ሞገሱ ስለሚጠፋ ሁሉም ይሸሹታል፤ በስተመጨረሻ ከዚያ ቦታ እንዳልነበረ ሁሉ እርግፍ አድርገው ይተውታል፡፡
ወቅቱ ሲገፋ እንደ መናፍስት አስፈሪ ሆኖ ይቆማል፡፡ በየቀኑ በብቸኝነት አካባቢውን ሲቃኝና አድናቂና ተደናቂዎቹን በጉጉት ሲጠብቅ አየዋለሁ። ሆኖም ሁሉም ይረሱታል። የተንጨፈረሩ ቅርንጫፎቹን ወደ ሰማይ ቀና አድርጎና ሽቅብ ዘርግቶ ወደ አምላኩ ሲጮህና ሲያማርር በአይነ ህሊናዬ ይታየኛል፡፡ ከብቸኝነቱ የተነሳ የተማረረ፣ መኖሩንም የጠላ ይመስለኛል። ወደ ሰማይም ቀና ብሎም ‹‹አምላኬ ሆይ ምን በደልኩ? እባክህ ገላግለኝ!›› እያለ የሚጮህ ይመስለኝና ጠጋ ብዬ የደረቁ አካላቶቹን በዝግታ እዳብሳለሁ፡፡ እርሱ ግን በብቸኝነት ሲሰቃይ ይከርማል፡፡ በመማረርም ወራቶቹን በጽናት ለማለፍ ይታገላል፡፡ በአንዲት የቀጣይ ወቅት መግቢያ ማለዳ ከእንቅልፉ ሲነቃ፣ አንዲት ወፍ ከቅርንጫፉ ላይ አርፋ ስትዘፋፍን ይመለከታል፡፡ በሙሉ ንቃት ተነስቶ አካሉን ሲመለከት ትንንሽ ቅጠሎች ከአካሉና ከቅርንጫፎቹ ላይ ማጎንቆል ጀምሮ ነበርና ተስፋ ያደርጋል፡፡ በደስታ ሲቃ ሲወዛወዝ ይታወቀኛል። በቀናት ውስጥ የሚያማምሩት ወፎች ወደ እርሱ መመለስ ይጀምራሉ፡፡ አንድ … ሁለት … ሶስት … እያሉ ይበዛሉ …  
በእንባ ዘለላ በተጋረዱ አይኖቼ መሃል በደስታ የሚርገፈገፈውን ዛፍ እያየሁ፤ ‹‹ቀጣይ የስቃይና የብቸኝነት ወራት ከፊቱ እንደሚመጡ ማን በነገረው!?›› ብዬ አሰላስላለሁ፡፡ ‹‹…አዎ! ወቅት ይቀየራል፡፡ መውደቅና መረሳት ወይም መታገልና መነሳት በርግጥም ይኖራል!››
***
አባባ እንዲህ ሲል ማሳረጊያውን  ቀጠለ… ‹‹አየህ ይህ ዛፍ አንድ ቀን ተገርስሶ ሊወድቅና በዘሮቹ ሊተካ የተፈጥሮ ህግ ነው፡፡ ማንም ያንን ሊያስቀር አይችልም፡፡ የተፈጥሮ የማይሆነው ግን ቆርጠን ከጣልነውና ያለ ምትክና ያለ ዘር ካስቀረነው ብቻ ነው፡፡ የሚያማምሩ አበቦቹንና ፍሬዎቹን ሳያይ ከገነደስነው ነው፡፡…›› … ቀስ ብሎ በሚንቀጠቀጡ መዳፎቹ ከዘራውን ተደግፎ ከተቀመጠበት ተነሳና ወደ ቤት መጓዝ ጀመረ፡፡ ‹‹…ቅዝቃዜው በርትቷል ጌታመሳይ! ወደ ቤት እንግባ! ዘመኑም እንደ ወቅቱ ይቀያየራል፡፡ አስቸጋሪ ዘመን!…›› ሲል በለሆሳስ አማረረ፡፡ አባባ አርጅቷል፤ ሆኖም አበቦቹንና ፍሬዎቹን አይቷልና አይቆጭም፣ ሞቴን በክብር እጠብቃለሁ የሚል አባት ነው፡፡ በቀስታ ተነስቼ ተከተልኩት፡፡ የሆነ ጥያቄ ግን በልቤ ነበረ። ‹‹…ዛፉ ሳያፈራ ከቀረስ ግን ምን ይሆናል? ዛፉ በመንሰራፋቱ የተነሳ ከስሩ የተከለሉና የተፈጥሮ ፀሃይ በማጣት የጠወለጉትስ? የተፈጥሮ ውሃቸውን እየቀማ የሚጠጣባቸውና የሚያስጠማቸውስ? ቀድመው በአካባቢው የነበሩትና በእርሱ መምጣት የጠፉትስ?….›› ምናምን የሚሉ ጥያቄዎችን ላዘንብበት በፍጥነት ተከተልኩት፡፡ እኔም ጥያቄዬ አያልቅ፣ እርሱም በአድባር ዛፍ ቅኔ (በጃካራንዳችን ምሳሌም ቢሆን!) ማብራራቱን ይቀጥላል፡፡
ዛፉ ወቅቶችን ለማለፍ ይታገላል እንጂ ወቅቶች ለዛፉ ብለው አያልፉለትም፡፡ ትውልድ ያልፋል፣ ጊዜ ግን ህያው ነው፡፡ ለሁሉም ጊዜ አለው አይደል የሚባለው? ጊዜ የሁሉም መፍቻ ነው፡፡ ማንም ቢሆን ከረገጠው ስልጣን፣ ከተነፈሰው ህይወትና ከተመካበት ጉልበት በታች መሆኑ የማይቀር ነዋ፡፡
… ባልጋ መኝታ በጠፍር፣ መልካም ይመስለኝ ነበር፤
አባቶቼ ግን ባያቸው፣ ሁሉም በመሬት ናቸው፡፡ …. (እንዲል ዘለሰኛ)

Read 1259 times