Saturday, 02 February 2019 14:48

የፓርላማ የጠ/ሚኒስትሩ ማብራሪያ (ሪፖርታዥ)

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(7 votes)


  - እራስን ነፃነት ነፍጐ በአንድ ቦታ ተወስኖ መቆየት ያው እስር ቤት ነው
  - በህገወጦች ላይ የምንወስደው እርምጃ የትዕግሥታችንን ያህል መራራ ነው
  - በአገራችን ያለው የጦር መሳሪያ ብዛት ከህዝብ ቁጥር ይበልጣል
  - የዛሬ 30 ዓመት የነበረ አስተሳሰብ የከሰረ አስተሳሰብ ነው፤ አያስፈልገንም
           

     በኢትዮጵያ ውስጥ ወንጀል ፈፅሞና ወንጀል መፈፀሙ ታውቆ ያልታሰረ አንድም ሰው አለመኖሩንና ልዩነቱ የቦታ ጉዳይ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለፁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ትናንት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከአባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው በህግ የሚፈለጉ ግለሰቦችን እየያዙ ለፍርድ የማቅረቡ ጉዳይ ቀጣይነት ያለው ነው ብለዋል፡፡ የሰብአዊ መብት ጥስትና የተደራጀ ዘረፋ በመፈፅም የተጠረጠሩ ግለሰቦችን መንግስት ከተደበቁበት መያዝ ያልቻለበት ምክንያት ምንድነው በሚል ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ወንጀል ፈፅሞ ያልታሰረ አንድም ሰው አለመኖሩንና ልዩነቱ መንግስት እየቀለበውና እየጠበቀው መታሰሩ ላይ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
“ራስን ነፃነት ነፍጐ በአንድ ቦታ ተወስኖ መቀመጥ መታሰር ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “እነዚህ በመንግስት ጥበቃ ውስጥ ያልሆኑና ያልታሰሩ ወገኖች መንግስት ወዳዘጋጀውና ጥሩ አያያዝ ወዳለው እስር ቤት በጊዜ ቢገቡ የተሻለ ነው” ብለዋል፡፡
በመንግስት ጥበቃ በእስር ላይ የሚገኙት ተጠርጣሪዎች፤ ሰብአዊ መብታቸው ተጠብቆ በአግባቡ እየበሉ እየጠጡ፣ ቤተሰብ እየጐበኛቸው፣ ስፖርት እየሰሩ እንደሆነና ይህም በግል እስር ቤቶች እንኳን የማይገኝ ትልቅ ዕድል እንደሆነ ተናግረዋል።
ተጠርጣሪዎቹን በመያዝ ሂደት ውስጥ እርምጃው ብሔር ተኮር እንደሆነና አንድን ብሔር ብቻ ለማጥቃት ታቅዶ የሚሰራ ነው የሚባለውን ፍሬ ቢስ ወሬ ነው ያሉት ዶ/ር ዐቢይ፤ ሌብነት ብሔር የለውም፤ ሌቦች ሲሰርቁም ሲያዙም ብልጥ ናቸው፤ ሲያዙ በብሔር ጥላ ስር መከለልና ያንተ ብሔር አባል ስለሆንኩ ነው በማለት ህዝብን ለማሳሳት ይሞክራሉ፤ ከሰብአዊ መብት ጥሰትና ከሙስና ጋር በተያያዘ እየተያዙ ያሉት የሁሉም ብሔር አባላት ናቸው ብለዋል፡፡
ከህገወጥ የጦር መሣሪያና የገንዘብ ዝውውር ጋር በተያያዙ ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ህገወጥ የጦር መሳሪያና የገንዘብ ዝውውር ባለፉት ዓመታት በአገራችን ህጋዊ እስከሚመስል ድረስ ሲሰራበት የቆየ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ አርሶ አደሩ በሬውን እየሸጠና ከባንክ ብድር እየወሰደ መሳሪያ ይገዛል፡፡ ሆኖም መታጠቁ ብቻ ሳይሆን ትጥቁ የሚያስከትለውን ችግርም አስቀድሞ ሊያስብበት ይገባል። መሳሪያ በገፍ ሲገባና ሁሉም ታጣቂ ሲሆን እርስ በርስ እንደሚያባላንና እንደሚያጫርሰን ሊያውቅ ይገባል ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የጦር መሳሪያ ብዛት ከህዝቡ ቁጥር በላይ እንደሆነም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
የመከላከያ ሰራዊቱን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሲናገሩም፤ ሰሞኑን በተደረገው የአንድ መቶ ቀናት የስራ ግምገማ፣ መከላከያ ሰራዊቱ ምርጥ ስራዎችን ከሰሩ ተቋማት መካከል ዋንኛው እንደሆነ ጠቅሰው፤ መከላከያ ሰራዊታችን ህይወቱን ሰውቶ ህይወት ለመስጠት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
የለውጥ ጉዞአችን ማዳን እንጂ ማከም አይደለም ያሉት ዶ/ር ዐቢይ፤ ለማዳን ጊዜ እንደሚያስፈልግና መታከም ሳይሆን መደን እንደሚፈልገው ታማሚ መድሃኒታችንን ሁሉ በአግባቡ ጨርሰን ልንወስድ ይገባል ብለዋል፡፡
“የዛሬ 30 ዓመት የነበረ አስተሳሰብ የከሰረ ነው፤ አንፈልገውም፤ አሁን ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት እውነትና ሰላም ብቻ ነው” ብለዋል፡፡
የመንግስት ትዕግስተኝነት መብዛታና ህግን ለማስከበር ያሳየውን ዳተኝነት አስመልክቶ ለቀረበው ጥያቄም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ መንግስት ለህገወጦችና ለስርዓት አልበኞች የመጨረሻ ደረጃ ትዕግስት ማሳየቱ እሙን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያን አንድነትና ሉአላዊነት በሚገዳደሩ ጉዳዮች ላይ ምንም አይነት ድርድር የለንም። አሁን የትዕግስታችን ልክ ተሟጧል፤ የምንወስደው እርምጃም እንደ ትዕግስታችን ሁሉ መራራ ነው ብለዋል፡፡ ከዚሁ ጋር አያይዘውም ለተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ወደ ሰላማዊና ትክክለኛ የትግል መስመር ብትገቡ የተሻለ ነው ሲሉ አሳስበዋል፡፡
አንድ እግራቸውን አዲስ አበባ አንድ እግራቸውን ደግሞ በውጪ አገር አስቀምጠው በሁለቱም እግራቸው መጫወት የሚፈልጉ ኃይሎች ሊጠነቀቁ ይገባል፡፡ ዘመናችንን ሁሉ ስንዋጋ ስለኖርን የሚሄዱበትን መንገድ እናውቀዋለን ስለዚህም ከዚህ ድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ባላቸው ጊዜ ተጠቅመው ከደጋፊዎቻቸው ጋር ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መወያየትና መመካከር ይኖርባቸዋል፡፡
ማንም ፓርቲ በራሱ ፓርቲ ያልተለማመደውን ዲሞክራሲ ኢትዮጵያ ላይ ሊለማመድ አይችልም፡፡ ራሳቸውን ለቀጣዩ ምርጫ ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡ ጊዜም አይኖራቸውም ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡
በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በዋጋ ግሽበት መሻሻልና በህዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ላቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ 10 ሚሊዮን ገደማ ስራ አጥ ዜጋ መኖሩን አመልክተው፣ በየዓመቱ 2 ሚሊዮን አዳዲስ ስራ ፈላጊ የሚፈጠር ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ ስራ የሚያገኘው አንድ ሚሊዮኑ ብቻ ነው ብለዋል፡፡
መንግስት ለስራ ዕድል ፈጠራው የተለያዩ ነገሮችን በማመቻቸት ዜጐች ወደ ስራ እንዲሰማሩ ለማድረግ አበክሮ እንደሚሰራና ለወጣቱ የስራ ዕድል ፈጠራ ተበጅቶ ከነበረው የ10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ በጀት ውስጥ ከተሰጠው ገንዘብ ሊሰበሰብ የቻለው አንድ በመቶው ብቻ እንደሆነ ተነግረዋል፡፡ የዋጋ ግሽበቱን በተመለከተም ላለፉት 15 ዓመታት በአገሪቱ ሰፍኖ የቆየውን የ14 በመቶ የዋጋ ግሽበት ወደ 10.3 በመቶ ማድረስ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡ የሕዳሴ ግድብ በመጓተቱ ምክንያት ከ60 በመቶ በላይ ጭማሪ ወጪ ማሳየቱን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚቀጥሉት 4 ዓመታት ሕዳሴ ግድብን ሙሉ በሙሉ አጠናቆ ወደ ስራ ለማስገባት ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው ብለዋል። ሕዳሴ ግድብን ማጠናቀቅ የሞትና ሽረት ጉዳይ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የ300 ቢሊዮን ብር ባለዕዳ መሆኑን ያስታወሱት ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ ድርጅቱ ካለው ሃብት የሱ ድርሻ 1 በመቶ ብቻ ነው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በማጠቃለያቸው የመገናኛ ብዙሃን ሚናን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ጤነኛ የሚባል ሚዲያ እንደሌለና አብዛኛዎቹ የሕብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት የሚፃረሩ ነገሮችን እየሰሩ እንደሆነ ገልፀዋል። የክልል ሚዲያዎችም ተነስ፣ ታጠቅ የሚሉ እንደሆነም ተናግረዋል።
“መንግስት እየቀለባቸው ህዝብን የሚያባሉ ሚዲያዎችም ሃይ ሊባሉ ይገባል፡፡ የግል ሚዲያዎችን መደገፍ አብሮ መቆምና ማገዙ ሚዲያዎቹ ራሳቸውን ከተፅዕኖ ነፃ በማድረግ የአገር ልማትና የህዝብን ሰላም ለማገዝ እንዲሰሩ ለማድረግ ይቻላል” ብለዋል ጠ/ሚኒስትሩ፡፡   

Read 6598 times