Saturday, 02 February 2019 14:50

ካልተሳፈሩበት ቶሎ ተሽቀዳድሞ ጊዜ ታክሲ አይደለም አይጠብቅም ቆሞ

Written by 
Rate this item
(12 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ ጅብ በረት እየገባ ጊደር እየበላ፣ ጥጃ ነክሶ እየወሰደ፣ ሰፈር እያመሰ፤ እጅግ አድርጎ ያስቸግራል፡፡
አባትና ልጅ ይህን ጅብ የሚገድሉበትን ጊዜ ለመወሰን ይወያያሉ፡፡
አባት፤
“ለምን አንድ ሌሊት አድፍጠን ሲመጣ አናቱን በጥይት ብለን አንገድለውም?”
ልጅ፤
“አባዬ እንደሱ አይሆንም፡፡ ድንገት ከሳትነው ጦሱ ለእኛም ይተርፋል፡፡ በዛ ላይ በየትኛው ሌሊት እንደሚመጣ አናውቅም”
አባት፤
“ታዲያ ሌላ ምን መላ አለ ብለህ ነው?”
ልጅ፤
“ለምን አናጠምደውም?”
አባት፤
“ጅብ እንዴት ይጠመዳል ልጄ?”
ልጅ፤
“ጅብ መቼም ሥጋ ይወዳል፡፡ ስለዚህ አንድ ሙዳ ሥጋ በገመድ አስረን ጠመንጃችን አፈ- ሙዝ ላይ አድርገን፣ የገመዱን ጫፍ ቃታው ላይ እናስረዋለን፡፡ ጅቡ ሥጋውን ሊበላ ሲጎትት፣ ቃታውን ይስበውና ይገላገላል!”
አባት፤
“በጣም ቆንጆ ዘዴ ዘየድክ”
 በተስማሙበት መሰረት፤ ስጋውን አፈ-ሙዙ ላይ ገጠሙና ገመዱን ቃታ ላይ አስረው፤ ጅቡ ይመጣበታል ብለው በሚጠረጥሩት አቅጣጫ አስቀመጡት፡፡
አባት፤
“በል እንግዲህ ልጄ ጅቡን ጠብቅና፣ የምስራቹን መጥተህ አሰማኝ፡፡ እኔ አረፍ ልበል።” ብሎ ሄደ፡፡
ልጅ ሲጠብቅ ቆየ፡፡ ጅቡ መጣና በመጨረሻ ሲሮጥ፣ አባቱ ወዳለበት ቤት መጣና፤
“አባዬ፤ አባዬ፤ ጉድ ሆነናል፡፡”
አባት፤
“እንዴት? ምን ተፈጠረ?”
ልጅ፤
“ጅቡ፤ ጠመንጃችንን በኋላ በኩል ነክሶ እየጎተተ ይዞት ሄደ!”
አባት፤
“ኧረ ልጄ! እንኳን ጠመንጃ ሰጥተኸው እንዲሁም አልቻልነው!” አለ፡፡
*   *   *
ያጠመድነው ሁሉ ይሳካል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው! ያቀድነው ሁሉ ምን ተግዳሮት ወይም ተገዳዳሪ እንቅፋት እንዳለበት አለማመዛዘንም አጉል ገርነት ነው፡፡ ባላንጣዎቼ ይተኙልኛል ብሎ ማንቀላፋትም አጉል ሞኝነት ነው፡፡
ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን “እንቅልፍ ነው የሚያስወስድህ” በሚለው ግጥሙ፤
“ትቻቸዋለሁ፤ ይተዉኝ
አልነካቸውም አይንኩኝ
ብለህ ተገልለህ ርቀህ
ዕውነት ይተውኛል ብለህ
እንዴት ተስፋ ታደርጋለህ?
የተወጋ በቅቶት ቢተኛ የወጋ መች እንቅልፍ አለው?
የጅምሩን ካልጨረሰው…”
ማለቱን ልብ እንበል፡፡
ለሥራም፣ ለእርምጃም፣ ለለውጥም እንንቃ፣ እንፍጠን፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ ለምንም ነገር አይረፍድም፡፡ የጥንቶቹ ሚሲዮናዊያን የታሪክ ፀሐፍት፤ “Ethiopia slept a hundred years, forgetful of the world by whom it was forgotten” ይሉናል። (ኢትዮጵያ የረሳትን ዓለም ረስታ ለመቶዎች ዓመታት ተኝታ ነበር፤ እንደማለት ነው፡፡) ማንቀላፋታችን ዕውነት ነው፡፡ አሥራ ሰባት ዓመት፣ ሃያ ሰባት ዓመት እየተባባልን ዛሬም ጊዜ እየፈጀን እንዳይሆን ያሰጋል፡፡ ተለወጠ የምንለውን ሥርዓት በማወደስም ሌላ ጠፊ- ጊዜ አለማባከን ደግ አስተሳሰብ ነው፡፡ ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው፡፡ ዋናው የዳበረ ዕውቀትና የበለፀገ ዕውነት ሊኖረን ተገቢ መሆኑ በጭራሽ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ባለሙያዎቻችን፣ ሹመኞቻችን፣ መሪዎቻችን፣ የጊዜ አጠቃቀማቸውን በጥሞና ማወቅና በጠንቃቃ መልኩ መገልገል ይገባቸዋል፡፡ “ጊዜ የሥልጣን እጅ ነው” ይላል ሎሬት፡፡
“ካልተሳፈሩበት ቶሎ ተሽቀዳድም ጊዜ ታክሲ አይደለም
አይጠብቅም ቆሞ” ----- የሚባለውም ለዚሁ ነው!

Read 9680 times