Saturday, 02 February 2019 14:57

ጃዋር ሆይ! - ኧረ እየተስተዋለ!!!

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(4 votes)

  ሞኑን በማህበራዊ ሚዲያው ትኩረት ተሰጥቷቸው የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆነው ከከረሙት ጉዳዮች አንዱ የትውልደ ኢትዮጵያዊው ባለሃብት የሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ከእስር መፈታት ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ሁለት ሃሳቦች ሲንጸባረቁ ነበር፡፡ በአንድ በኩል፤ ሼህ ሙሐመድ ከአንድ ዓመት እስር በኋላ በመፈታታቸው ደስታቸውን የሚገልጹ ወገኖች አስተያየት ሲሰጡ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ “ሼሁ እግራቸው የኢትዮጵያን ምድር ሲረግጥ ሊታሰሩ ይገባል” የሚል አስተያየት ነበር፡፡ “ሼሁ ይታሰሩ” የሚሉት ወገኖች የሚያቀርቡት ምክንያት ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን የተሰኘው የሼሁ ኩባንያ በማዕድን ማውጣት ሂደት የሚያስወግደው ቁሻሻ (ተረፈ-ምርት)፤ በሻኪሶ - ለገደንቢ አካባቢ ማህበረሰብ ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው የሚል ነው፡፡ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝም በዚሁ ጉዳይ ላይ ታዋቂው አክቲቪስት አቶ ጃዋር ሙሐመድ የጻፈው የፌስቡክ ማስታወሻ ነው፡፡
የሼህ ሙሐመድን ከእስር መፈታት አስመልክቶ ከቀረቡት አስተያየቶች ውስጥ ሼህ ሙሀመድን በአዎንታዊነት የሚያነሱ፣ በጎነታቸውን የሚጠቅሱት፣… በቁጥር የሚበልጡ ቢሆንም፤ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች አሉታዊ የነቀፌታና የጥርጣሬ አስተያየት ሲሰጡ ተስተውሏል፡፡ ከእነዚህ አስተያየት ሰጪዎች መካከል በተፈቱ በሰዓታት ውስጥ በትንታግ አንደበቱ የብዕር ዘገሩን የሰበቀባቸው አቶ ጃዋር ሙሐመድ እንደሆነ አስተውለናል፡፡
ጃዋር በሼህ ሙሐመድ አል-አሙዲንም ላይ ይሁን በሌላ ሰው ላይ አስተያየት መስጠቱ የሚገርም አይደለም፡፡ መብቱም ነው፡፡ እኔን የገረሙኝ ግን ሁለት ነገሮች ናቸው፡፡ አንደኛ፤ ሼህ ሙሐመድ መፈታታቸው በተነገረ በሰዓታት ውስጥ በጥድፊያና በተቻኮለ ሁኔታ እንዲታሰሩ የፌስቡክ የእስር ትዕዛዝ ማስተላለፉ ነው። ሁለተኛው የገረመኝ ነገር ደግሞ ተጨባጭ መረጃዎችን በአግባቡ ሳይዝ ሼህ ሙሐመድን መወንጀሉ ነው፡፡ እነዚህን ሁለት ግርምቶቼን ማብራራቱ አስፈላጊ ስለሆነ ወደዚያው ላምራ፡፡
ጥድፊያ ለምን?
በዓለም ላይ ያለ ሰው ሁሉ ሼህ ሙሐመድን ይወዳቸዋል፣ ያደንቃቸዋል፣ ያወድሳቸዋል፣… የሚል እምነት የለኝም፡፡ እናም የሼህ ሙሐመድ መፈታት የሚያስደስተን ሰዎች እንዳለን ሁሉ፣ ሼህ ሙሐመድን በጥላቻ ዓይን የሚያዩዋቸው ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ማሰብ ሊቅነትን የሚጠይቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ ነገር ግን፤ የሰው ልጅ የፈለገውን ያህል “ልበ-አለት” ቢሆን እንኳ፣ በግፍ የታሰረ ሰው፣ ፀሎቱ ሰምሮ ሲፈታ ባህር ተሻግሮ፣ በሀበሻ ምድር እንደገና ከርቸሌ እንዲወርድ የእስር ዋራንት ቆርጦ፣ የእስር ቤቱ በር ላይ መጠበቅ ተገቢ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ በተለይ ደግሞ ይህንን ድርጊት የፈጸመው የእስርን አስከፊነት በደንብ የሚገነዘበው፣ ለሰብአዊ መብት መከበር ተሟጋች የሆነው ጀዋር ሙሐመድ መሆኑ “ሰውየውን ምን ነካው?” የሚል ጥያቄ እንዳነሳ አደረገኝ፡፡
ቢያንስ ቢያንስ ሼህ ሙሐመድ ለጀዋር የሀገሩ ልጅ ናቸው፡፡ ሼህ ሙሐመድ ለጀዋር (ከሃይማኖት አኳያ) የአኸይራ ወንድሙ ናቸው። ጀዋር ለሚወዳት ኢትዮጵያ፤ ሼህ ሙሐመድ በርካታ በጎ በጎ ስራዎችን የሰሩ ሰው ናቸው። ይሁንና ሼህ ሙሐመድ ሰው ናቸውና ጥፋት ሰርተው ከሆነ እንኳ ከጥፋታቸው ልማታቸው የሚያመዝን መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት፣ የሼሁ ከእስር መፈታት ጀዋርን ጭምር ደስ ሊያሰኘው ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እንኳን ተፈቱ እንጂ ጥፋት ካለም አግባብ ባለው የህግ መስመር ለመጠየቅ ያን ያህል መጣደፍ አስፈላጊ ሆኖ አይታየኝም፡፡
የጥፋተኛው ብዛት አንድ ከተማ ሊያስመሰርት እንደሚችል በሚነገርበት ሀገር፤ ሼህ ሙሐመድ አል-አሙዲንን ሀገር ካስመረሩ ግፈኞች ጋር እኩል ይታሰሩ ማለት ቢያንስ ቢያንስ ከሞራል አኳያ ተገቢ ሆኖ አይታየኝም - ሼሁ ከወሰዱብን የሰጡን ይበልጣልና!
ተጨባጭ ማስረጃ ሳይዙ መወንጀልን በተመለከተ፤
ሁለተኛው ግርምት የፈጠረብኝ ነገር ጀዋር “አስተማማኝ ማስረጃ” ሳይዝ ወይም በሼህ ሙሐመድ ኩባንያ በኩል ያለው አሰራር ምን እንደሚመስል ሳይጠይቅ፣ ከአንድ ወገን ያገኘውን ሃሳብ ትክክለኛ አድርጎ ወስዶ፣ ሼህ ሙሐመድን ለመወንጀል መጣደፉ ነው፡፡
ሁላችንም እንደምንገነዘበው በዓለም ላይ በመንግስት ባለስልጣናት፣ በታዋቂ ግለሰቦችና በኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ላይ የማይወራ ነገር የለም፡፡ የውሸት ዜና (fake news) እንደ ጉድ በሚፈበረክበት በዚህ ዘመን የሰማነውን ተባራሪ ወሬ ሁሉ፣ የሚናፈሰውን አሉባልታ ሁሉ፣ በአግባቡ ሳያጣሩ እውነት ነው ብሎ መውሰድ ከውሸት ፈጣሪዎቹ የበለጠ ስህተት ላይ የሚጥል መሆኑ ይታየኛል፡፡ ለዚህም ነው “ወንድሜ ጀዋር ሆይ! ኧረ ባክህ እየተስተዋለ!” ለማለት የወደድሁት፡፡
ጀዋር፤ የሰውን ልጅ ሰብዓዊ መብትና ክብር አይነኬነት ጠንቅቆ ስለሚገነዘብ፣ ብዙ መስዋእትነት መክፈሉን እናውቃለን። እንደ ጀዋር ያለ ኃላፊነት የሚሰማው የዚህ ዘመን ልሂቅ፤ ጉዳዩን ረጋ ብሎ በሰከነ መንፈስ መመልከት ሲገባው ከግራም ከቀኝም ተጨባጭ ማስረጃዎችን ሳያሰባስብ፣ በተቻኮለ ሁኔታ የፌስቡክ ግርግር መፍጠሩ ተገቢ ሆኖ አይታየኝም፡፡ ወደፊት እውነቱ ነጥሮ ሲወጣ መጸጸት እንዳይፈጠር፣ ከወዲሁ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
ባለፉት 27 ዓመታት የሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ስም በጥሩም በመጥፎም ሲነሳ፣ ሲጣል መክረሙ ይታወቃል፡፡ የሚወዷቸው ሰዎች ሲያሞግሷቸው፣ የሚጠሏቸው ሲያብጠለጥሏቸው፣ ዝንጥል ጉፍታቸውን ሲያወጧቸው ነው የባጁት፡፡ በጎ በጎውን ትተን የተለጣጠፉባቸውን ውርጅብኞች በጥቂቱ ስንመለከት፤ ሼህ ሙሐመድ በመስጠታቸው ተወቅሰዋል፣ በትዳራቸው ታምተዋል፣ በሃይማኖታቸው ተተችተዋል፣ በድርጅቶቻቸው ተከሰዋል፣ ከመንግስት (ከኢህአዴግ) ጋር ባላቸው ቀረቤታ ጣት ተቀስሮባቸዋል፡፡
…ይሄ ሁሉ ሀሜትና ወቀሳ እንደ ሼህ ሙሀመድ ባሉ ጎምቱ ሰዎች ላይ የሚሰነዘር የተለመደ ጉዳይ ነው፡፡ የጀዋርን ትችት ለየት የሚያደርገው ከሀሜትና ከወቀሳ ባለፈ “ወንጀለኛ” አድርጎ ማቅረቡ ነው፡፡ “ወንጀለኛ” አድርጎ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን፣ ፍርድ ሰጥቶ እግራቸው የኢትዮጵያን ምድር ሲረግጥ ወደ ቃሊቲ እንዲወርዱ በፌስቡክ በተቋቋመ ችሎት ውሳኔ ማሳለፉ ነው፡፡
ሌላውን ነገር ልተወውና፣ ጀዋር፤ በሼህ ሙሐመድ ላይ የእስር ዋራንት ሊያስቆርጥባቸው ይችላል ብሎ በ“ወንጀልነት” ያነሳውን አንድ ጉዳይ ጠቅሼ የማውቀውን ላብራራ። በቅድሚያ ጀዋር በፌስቡክ ገጹ የጻፈውን አስተያየት ልጥቀስ፡-
እንዲህ ይላል፡- “Al Amoudi is said to have been released. In case you have forgotten what had done, remember he did not just rob our country with Woyane; he caused unimaginable damage to human life by releasing toxic waste at Midroc Gold... Ample evidence have been compiled for day he faces the court.”
ወደ አማርኛ ስንመልሰው “አል-አሙዲ ተለቀቀ እየተባለ ነው፡፡ ሰውየው የሰራውን ምናልባት ረስታችሁት ከሆነ ላስታውሳችሁ። ከወያኔ ጋር ሆኖ ሀገራችንን መዝረፉ ብቻ ሳይሆን ከሚድሮክ ወርቅ ማእድን መርዛማ ቁሻሻ በመልቀቅ በሰው ህይወት ላይ ወደርየለሽ ጉዳት አድርሷል… በፍርድ ቤት ተጠያቂ የሚያደርገው በቂ ማስረጃ ተሰብስቧል” የሚል ግርድፍ ትርጉም ይሰጠናል፡፡
ይህንን ክስና ውንጀላ እዚህ ላይ እናቁምና ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ ስለ ወርቅ አመራረት ሂደት የማውቃትን ላካፍል፡፡ (የማዕድን ሳይንስ ባለሙያ ስላልሆንኩ፣ ሃሳቤ ስህተት ከሆነ ለመታረም ዝግጁ መሆኔን አስቀድሜ ለማሳሰብ እወዳለሁ)
ወርቅ እንዴት ነው የሚመረተው?
ወርቅ በተለያዩ መንገዶች ሊመረት ይችላል፡፡ በብዙ ሀገሮች ወርቅ የሚመረትባቸው መንገዶች ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው ዘዴ “ሜርኩሪ” በተባለ ኬሚካል ወርቁ ከአፈሩ የሚለይበት በእንግሊዝኛ “Amalgamation Method” የሚባለው ዘዴ ነው፡፡ ይኸውም፤ ከአፈርና ከድንጋይ ጋር ተደባልቆ የሚገኘው የወርቅ ማዕድን (Ore) በደንብ ድቅቅ እስኪል ድረስ ይፈጫል፡፡ ከዚያም የተፈጨው አፈርና ድንጋይ “ሜርኩሪ” ከሚባል የኬሚካል ሶሉሽን ጋር ይደባለቃል። ውህዱን ሶሉሽን በእሳት በማቃጠል ወርቁ በፈሳሽ መልክ ተለይቶ እንዲወጣና እንዲጠፈጠፍ ይደረጋል። ሜርኩሪው ደግሞ በእንፋሎት መልክ እንዲተን ይደረጋል፡፡ የተነነው ሜርኩሪ ስለማይፈለግ ቀዝቅዞ በዝቃጭ መልክ፣ ተረፈ-ምርት ሆኖ እንዲወገድ ይደረጋል። (ሜርኩሪ የተባለው ኬሚካል ከሰው አካል ጋር ንክኪ ከተፈጠረ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ መሆኑ ስለተረጋገጠ፣ ይህ የወርቅ ማንጠሪያ ዘዴ በአሁኑ ጊዜ በዓለም በብዙ ሀገሮች እንዲቀር እየተደረገ ነው።)
ሁለተኛው የወርቅ ማውጫ ዘዴ፣ “ሲያናይድ” (Cyanide) የተባለ ኬሚካልን በወርቅ ማንጠሪያነት በመጠቀም የሚከናወን ነው፡፡ ይኸውም፤ ወርቁን የተሸከመው አፈርና ድንጋይ (Ore) ይከሰከስና እንዲደቅ ይደረጋል። የደቀቀው ወርቅ አዘል አፈርና ድንጋይ በውሃ እንዲላቁጥ ይደረጋል፡፡ ከዚያም የላቆጠው ውሁድ ከሶድየም ሲያናይድ ጋር እንዲደባለቅ ይደረጋል፡፡ ከዚያም ይህ ድብልቅ በተለያዩ ሂደቶች እንዲያልፍ ይደረግና በመጨረሻ ወርቁ ካርበን (carbon) በተባለ ንጥረ ነገር ላይ እንዲያርፍ (Absorb) ይደረጋል፡፡ በመጨረሻም፤ ሲያናይድን የያዘው ተረፈ-ምርት ወደ ሁለት አቅጣጫዎች እንዲሄድ በማድረግ፣ “ሲያናይድ” የተባለው ኬሚካል በሂደት መጠነ ይዘቱ እንዲቀንስ ይደረጋል፡፡ ይህም የሲያናይድ የኬሚካል መጠነ ይዘት በሰው ላይ ጉዳት በማያደርስ መጠን በሂደቱ እየቀነሰ እየቀነሰ እንዲሄድ ይደረግና በመጨረሻም በተረፈ-ምርት መልክ (waste) ይወገዳል፡፡
ሲያናይድን ተጠቅሞ ወርቅ የማምረት ዘዴ በጥንቃቄ ስራ ላይ ከዋለ የሚያስከትለው የጉዳት መጠን በጣም አነስተኛ ስለሆነ በተባበሩት መንግስታት ጭምር ተቀባይነት ያለውና በብዙ ሀገሮች የሚሰራበት ዘዴ ነው፡፡ (በነገራችን ላይ በብዙ ሀገሮች በሜርኩሪ መጠቀም የቆመው እ.ኤ.አ ከ1960ዎቹ ጀምሮ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ የፈረመችበት የተባበሩት መንግስታት ድንጋጌም እ.ኤ.አ በ2013 ወጥቷል)
የወርቅ ማዕድን የሚመረትበት ሂደት ከፍ ሲል የተገለጸው ከሆነ የሼህ አል-አሙዲን ኩባንያ የሆነው ሚድሮክ የወርቅ ማዕድን የሚጠቀመው የትኛውን የማምረቻ ዘዴ ነው? የሚለውን ጥያቄ እዚህ ላይ ማንሳት ተገቢ ነው።
እንደሚታወቀው ሼህ ሙሐመድ ይህንን ኩባንያ የገዙት በ1989 ዓ.ም ገደማ ነው፡፡ ሼሁ ከመግዛታቸው በፊት በነበሩት ዓመታት (እስከ 1989 ዓ.ም ድረስ) በዚህ ኩባንያ ወርቅ ይመረት የነበረው አደገኛነቱ የሚነገርለትን ሜርኩሪ የተባለ ኬሚካልን በመጠቀም ነበር፡፡ ሼሁ ከገዙት በኋላ ግን ሜርኩሪን መጠቀም ሙሉ ለሙሉ እንዲቆምና በዓለም በብዙ ሀገሮች አገልግሎት ላይ ያለውና የጉዳት መጠኑ የተሻለ ነው የሚባለው ሲያናይድን ተጠቅሞ ወርቅ የማምረት ዘዴ ሥራ ላይ እንዲውል ተደርጓል፡፡
የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎችና እንደ ጤና ቢሮ ያሉ መስሪያ ቤቶችም በየጊዜው ወደ ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኩባንያ በመምጣት ምርመራ እንደሚያደርጉና የሚድሮክ ፈቃድም የሚታደሰው በዚሁ የምርመራ ውጤት ላይ ተመርኩዞ መሆኑን ለማወቅ ችያለሁ፡፡
ታዲያ በለገ ደንቢ አካባቢ የሚኖሩ ወገኖቻችን አካል ጉዳተኛ እንዲሆኑ ያደረጋቸውና ልጅ መውለድን (Birth Defectን) ጨምሮ እየደረሰባቸው ያለው የአካልና የጤና ጉዳት ከምን የመነጨ ነው? ይህንን ጉዳት የሚያመጣው “ሲያናይድ” የተባለ ኬሚካል ነው ወይስ “ሜርኩሪ”? የሙያተኞች አስተያየት የሚያመለክተው ከሲያናይድ ይልቅ ሜርኩሪ የተባለው አደገኛ ኬሚካል ለችግሩ መንስዔ ሊሆን እንደሚችል ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ጉዳዩ በሙያተኞች መጣራት ይገባዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ሌላው መነሳት የሚገባው ጥያቄ፣ የሼህ ሙሐመድ አል-አሙዲ የወርቅ ማዕድን ኩባንያ ሲያናይድን የሚጠቀም ከሆነና ሲያናይድ ደግሞ የከፋ ጉዳት አያደርስም ከተባለ ታዲያ በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ሜርኩሪን የሚጠቀም ኩባንያ ወይም ግለሰብ አለ? የሚል ነው፡፡
በግሌ ይህንን ጉዳይ ለማጣራት ሞክሬአለሁ። ባገኘሁት መረጃ መሰረት፤ በአካባቢው በሺዎች የሚቆጠሩ ባህላዊ ወርቅ አምራች ግለሰቦችና ድርጅቶች ጭምር መኖራቸውንና እነዚህም ግለሰቦች ጥንቃቄ በጎደለው ሁኔታ ሜርኩሪውን በስፋት እንደሚጠቀሙና በስራ ሂደት ይህንኑ አደገኛ ኬሚካል በእጃቸው እንደሚነኩ ለማወቅ ችያለሁ፡፡ አንዳንድ ሰዎችም ተመሳሳይ ሃሳብ በሶሻል ሚዲያ ጽፈው አንብቤአለሁ፡፡
በሶሻል ሚዲያ ሃሳባቸውን ካቀረቡት ውስጥ Amigo Amigo የተባለ ሰው በፌስቡክ ገጹ ላይ፤ “…በሻኪሶና አካባቢው በትክክልም የሜርኩሪ ገበያ ካለ ኬሚካሉን ለሽያጭ የሚያቀርበው አካል ማነው? በአካባቢው ሰዎችና እንስሳት ላይ ጉዳት እያደረሰ ያለው ኬሚካል ከሚድሮክ ወርቅ ማምረቻ እየተወገደ ያለው ሲያናይድ ነው ወይስ የአካባቢው ህብረተሰብ በባህላዊ መንገድ እየተጠቀመበት ያለው ሜርኩሪ? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ጠለቅ ያለ ጥናት የሚፈልግ ይመስለኛል!” የሚል አስተያየት አቅርቧል፡፡ እኔም ከዚህ የተለየ አስተያየት የለኝም!!! ጥናቱ የተሟላ እንዲሆን “ሜርኩሪ” የተባለውን ኬሚካል ከውጪ ሀገር ማን እንደሚያስመጣው መረጃዎቹን ከጉምሩክ ባለስልጣን ማግኘት ይቻላል፡፡
ውድ አንባብያን! እኔ ያገኘሁት መረጃ ከላይ የቀረበውን ይመስላል፡፡ እውነታው ይህንን የሚመስል ሆኖ ሳለ ኦቦ ጀዋር ሙሐመድ፤ ሚድሮክ ወርቅ ማእድን ኩባንያ ጉዳት እያደረሰ ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ “ማስረጃ አለኝ” ማለቱ አስተዛዛቢ ብቻ ሳይሆን አሳሳቢም ነው፡፡ “አሳሳቢም ነው” ያልኩበት ምክንያት በመንግስት በኩል እየተደረገ ያለው ጥናት ተጠናቆ ውጤቱ ከሼህ ሙሐመድ አል-አሙዲ ኩባንያ የሚወጣው ፍሳሽ የችግሩ መንስዔ መሆኑን ባላረጋገጠበት ሁኔታ፣ በስማ በለው የተገኘን ሰነድ አልባ ውንጀላ በሶሻል ሚዲያ መርጨት፣ በሼህ ሙሐመድና በኩባንያቸው ላይ ሊፈጥር የሚችለውን ውዥንብር በማሰብ ነው፡፡
እንደኔ እንደኔ፤ የሚድሮክ ችግር “ሥራ ይመስክር” በሚል መንፈስ እውነታውን ለህዝብ ይፋ አለማድረጉ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ የድርጅቱ ስም እንዲጠፋ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በሰራተኛውና በባለ ሃብቱ ላይ ጉዳት እንዲደርስ እያደረገ መሆኑ እየተስተዋለ ነውና፣ እንደ አሰራር ይህም ቢታይ መልካም ነው እላለሁ፡፡
በመጨረሻም አንዲት ነጥብ ልጨምርና ሃሳቤን ልቋጭ፡፡ በየትም ሀገር (ባደጉት ሀገሮች ጭምር) እንደታየው፤ ሙሉ ለሙሉ (100%) ጉዳት የሌለው ኢንቨስትመንትም ሆነ ልማት የለም፡፡ ሊኖርም አይችልም፡፡ ስለሆነም፤ ዛሬ ያሉትንም ሆነ ነገ የሚመጡትን የልማት ተቋማት በዚህ የአስተሳሰብ ማዕቀፍ ውስጥ ብናያቸውና በተቻለ መጠን በኃላፊነት መንፈስ ስራቸውን እንዲሰሩ ክትትልና ቁጥጥር ቢደረግ መልካም ነው፡፡
ጸሐፊውን በEmail: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.   ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 2822 times