Saturday, 02 February 2019 15:05

እባካችሁ ኢትዮጵያዊነትን አታሳንሱት!

Written by  ከኤርሚያስ ላቀው
Rate this item
(2 votes)

  ባለፉት 27 ዓመታት የአማራ ህዝብ  በእጅጉ ተበድሏል፤ ተሰዷል፣ ተገርፏል፣ ተገድሏል-----ማንነቱን እንዲክድ ተደርጎ ተሸማቋል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ከአቅሙ በላይ የታቀደና የተደራጀ የሚመስል ብሔር ተኮር ጥቃት ተሰንዝሮበታል። ግን  እጅ አልሰጠም፡፡ ጠላቶቹ እንደሚመኙት አልሆነላቸውም፡፡ ምንም ያህል መስዋዕትነቱ ቢበዛም ጸንቶ ነው የዘለቀው፡፡  
የአማራ አባቶች፣ እናቶችና  ወጣቶች የሞቱት፣ አሰቃቂ ግፎችንም የተቀበሉት ለአገራቸው ባላቸው ቀናኢነት ነው፡፡ ለኢትዮጵያዊነት ጥልቅ ፍቅር፡፡ አማራው ልክ እንደ ሌሎቹ ሀገር ወዳድ የኦሮሞ፣ ወላይታ፣ ሲዳማ፣ ሶማሌ፣ ትግሬ፣ አፋርና ጉራጌ --- ህዝብ ለኢትዮጵያዊነቱ መስዋዕትነት ሲከፍል ኖሯል፡፡ ህይወቱን ሰጥቷል፡፡  ራሱን ሰውቶ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን አኑሯል፡፡ ያለዚያማ  ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ድምጥማጥዋ በጠፋ ነበር፡፡  
 ዛሬ ያ የሞተለት፣ የተሰደደለት፣ የታሰረለት፣ የተሰቃየለትና ፈጽሞ ለድርድር የማያቀርበው ኢትዮጵያዊነቱ አሸንፏል፡፡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነቱ ከፍ ከፍ ማለት ጀምሯል። ኢትዮጵያዊነት የሚቀነቀን ዜማ ሆኗል፡፡ የሚሰበክ ቃል፡፡ ከጥፋት የሚያድን፣ ከበሽታ የሚፈውስ መድሃኒት ሆኗል - ኢትዮጵያዊነት፡፡ ዛሬ “ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር” ማለት፣ ሌላ ስም አያሰጥም፡፡ አያስፈርጅምም፡፡ ያ ዘመን ተመልሶ ላይመጣ አልፏል፡፡ ኢትዮጵያዊነቱን አሽቀንጥሮ ጥሎ በብሄሩ--- በጎሳው--- በመንደሩ--- በቀበሌው----እንዲጠብ ወይም እንዲታጠር----የተደረገው ጥረትና ልፋት ሳይሰምር  ቀርቷል፡፡ ኢትዮጵያዊነት አሸንፏል፡፡
ዛሬማ «ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው!» ፣ «ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ»....የሚሉ ድንቅ መሪዎች አግኝቷል፡፡ አደባባይ በወጣ ቁጥር «ኢትዮጵያና ልጆቿን ፈጣሪ ይባርክ!» የሚል --- ኢትዮጵያን ጠርቶ የማይጠግብ፣ ኢትዮጵያዊነትን አወድሶ የማይረካ --- በአገር ፍቅር ስሜት የነደደ ---- ጠ/ሚኒስትር ተችሮታል፡፡  
ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በአገሪቱ ላይ በብሄርና በዘር የተደራጁ  ፓርቲዎች እንደ አሸን ሲፈሉ፤ ብሄራችንን ከጭቆና ነጻ እናወጣለን የሚሉ የዘር ፖለቲከኞች እንደ ጉድ ሲበዙና ሲባዙ፤ ለአማራው ህዝብ መብት የሚታገሉ፣ ግፍና በደሉን ከጫንቃው ላይ የሚያቃልሉለት፣ ከእስርና ከእንግልት የሚታደጉት  ፓርቲዎችም፣ ፖለቲከኞችም፣ አክቲቪስቶችም፣ ጦማሪያንም አልነበሩትም፡፡ አማራው፤ ለ20 እና 30  ዓመታት ከኖረበት የተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በተደጋጋሚ ሲፈናቀልና ሲባረር፣ ቤቱና ማሳው ተቃጥሎ ሲሳደድ፣ የሰው እጅ ጠባቂ ሲሆን ---- ማንም የጮኸለት አልነበረም፡፡ ፖለቲከኞች ሁሉ  ብሄርን  መሰረት አድርገው የተደራጁ በመሆናቸው፣ ከብሄራቸው ውጭ በሆኑ ዜጎች  ላይ የሚደርሱ በደሎችና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የሚቆረቁራቸው አይመስሉም። በዚህም የተነሳ ከብሄር ይልቅ ኢትዮጵያዊነትን ሲያቀነቅን የኖረው አብዛኛው የአማራ ህዝብ፤ የሚታደገው አጥቶ ለብዙ መከራና ስቃይ ተዳርጓል፡፡ የማታ ማታ ጽዋው ሲሞላም፣ እንደ ወንድሙ የኦሮሞ ህዝብ ሁሉ፣ ለሁለት ዓመት ገደማ መሬት አንቀጥቅጥ አመጽና ተቃውሞ አድርጎ፣ ብዙ መስዋዕትነትም ከፍሎ ነጻነቱን በራሱ ተቀዳጅቷል፡፡ በስሙ የተደራጀ አንድም የፖለቲካ ፓርቲ በሌለበት!! ከኢህአዴግ ወጥተው ኢህአዴግን ፈጽሞ የማይመስሉትን እነ ዶ/ር ዐቢይ፣ ኦቦ ለማና አቶ ደጉ አንዳርጋቸውን --  ያመጣው የህዝቡ በተለይም የወጣቱ ትግል ነው፡፡ በጥቂት ወራትም በ20 ዓመታት ውስጥ  ያልታዩ የለውጥ ትሩፋቶች  ማየት ተችሏል፡፡
ለዓመታት አማራው ሲበደልና ሲገፋ፣ ሲታሰርና ሲገደል----ድምጻቸው ጨርሶ ተሰምቶ የማያውቅ፣ ራሳቸውን «የአማራ አክቲቪስት» ብለው የሾሙና የሸለሙ፣ የድል አጥቢያ አርበኞች፤ (ያመለጣቸውን የዘረኝነት ኮርስ ሊያሟሉ) በፌስቡክ አውድማ ዘመቻውን አጧጡፈውታል፡፡ አማራውን ከኖረለትና  ከሞተለት ትልቅ ህልም (ኢትዮጵያዊነት)፣ ወደ ጠባብ ቅዠት (አክራሪ ብሔርተኝነት) ለማውረድ፡፡ አክቲቪስቶቹ፤ የአማራ ብሔርተኝነትን ሊሰብኩ ወይም ሊያጠምቁ የተነሱት፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት ቢሆን ኖሮ  አልፈርድባቸውም  ነበር፡፡ ብሄር-ተኮር  በደልና ጭቆናን ለመታገል፣ ጠበብ ባለ መልኩ በዘውግ መደራጀት ብቸኛ አማራጭ ሊሆን ይችላል፡፡ (በግሌ  ጨርሶ ባልቀበለውም!) አማራው፤ የተለያዩ ጥቃቶች፣ግድያዎች፣እስሮች፣መፈናቀሎችና ሌሎች ብዙ ስቃዮች  ሲደርስበት በነበረ ጊዜ፤ የዛሬዎቹ የአማራ አክቲቪስቶች የት ነበሩ? እንኳን በብሄር ተደራጅተው ለህዝቡ ሊታገሉ ቀርቶ፣ ስለ ጭቆናውና በደሉ አፍ አውጥተው ሊቃወሙ እንኳን ድፍረቱ አልነበራቸውም፡፡
እኔ በበኩሌ፤ የብሔር ፖለቲካ፣ ለምናልማት የበለፀገች፣ የህዝቦችዋ እኩልነትና ነፃነት የሰፈነባት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውን መሆን  ይጠቅማል ብዬ አላስብም፡፡ ሲጀመር ኢትዮጵያዊ አንድነትና የዘር ፖለቲካ አይስማሙም፡፡ ውሃና ዘይት ናቸው፡፡ አንዱ ሌላውን የሚያጠፋ እንጂ የሚያለማ አይደለም።  የዘር ፖለቲካ የሚያስከትለውን መዘዝ ለማወቅ  ሳይንቲስት መሆንን አይጠይቅም፡፡ በተለይ በአሁኑ ሰዓት በዕለት ተዕለት ኑሮአችን በተጨባጥ እያየነው ነው፤ እየኖርነው ነው። በብሄርና በዘር መደራጀት፣ ትልቁን አገራዊ ምስል አስረስቶ፣ወደ ክልልና መንደር ያሳንሳል። ለኔ ብቻ ወደሚል ጠባብ ሃሳብና ምኞት የሚያስገባ፣ ሌላውን የሚገፋና የሚያፈርስ እንጂ የሚያሰባስብ አይደለም፡፡
ሌላው ፈፅሞ የማይገባኝ ነገር ደግሞ ሁሉም በብሔሩና በክልሉ ብቻ ከተደራጀ እንዴት አድርጎ ነው መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ከዳር እስከ ዳር አስተባብሮና አንድ አድርጎ፣ ሀገር ማስተዳደርና ማሳደግ የሚቻለው፡፡ እውነት ለመናገር፤ በዘር ወይም በብሄር መደራጀትን የሚመርጡ  ሰዎች፤ እውነት ለህዝባቸው እያሰቡና እየተቆረቆሩ ነው። ለምን በዚህ መልኩ ብቻ ማሰብና መደራጀት እንደፈለጉ  ብረዳው ደስ ባለኝ ነበር፡፡
በእርግጥ የብሔር ፖለቲካን የሚያቀነቅኑና በዘር መደራጀትን የሚመርጡ ፖለቲከኞች ወይም አክቲቪስቶች ወደዚህ  ቅኝት የሚገቡበት ሰበብ ወይም መነሻ ይኖራቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ ከተራ ጀብደኝነትና ከጊዜያዊ ፖለቲካዊ ትርፍ የሚመነጭ ነው፡፡ አብዛኞቹ የብሔር ፖለቲካ አቀንቃኞች ግን መነሻቸው ከበደል፣ መገፋትና መጨቆን የመጣ እልህና ብሶት ይመስለኛል። ግን ደግሞ መርሳት የሌለብን ሃቅ ቢኖር፣ በደልና ጭቆና ኢትዮጵያችን ውስጥ ከተንሰራፋ ብዙ ዘመናትን አስቆጥሯል፡፡ እስቲ  ኢትዮጵያ ውስጥ ተበደልኩ፣ ተጨቆንኩ፣ ተገፋሁ፣ ተገደልኩ ----የማይል ብሔረሰብ  ፈልጋችሁ ንገሩኝ። በፍፁም አታገኙም፡፡  ሆኖም መታወቅ ያለበት፤ ያ በደልና ጭቆና፣ በጥቂት የገዢ መደብ ክፍሎች የተፈፀመ እንጂ መርዘኛ ፖለቲከኞች እንደሚሰብኩት፤ አንዱ ህዝብ በሌላው ላይ የፈጸመው  አይደለም፡፡ ህዝብ በህዝብ ላይ በደልና ጭቆና ሊፈጽም አይችልም፡፡ አቅሙም  ባህርይውም  ተፈጥሮውም አይደለም፡፡ በዘር የተለከፉ ፖለቲከኞች ግን ለጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ፣ የህዝብን ስሜትን ለማናር ሲሉ፣ አዳዲስ ታሪክ እየፈበረኩ ጭምር ህዝቡን ይሰብካሉ፡፡ ይህ ደግሞ በህዝብ መካከል ጥላቻና ጥርጣሬን ይፈጥራል፡፡ የዘር ፖለቲከኞች ዓላማም ይኸው ነው፡፡
የአማራ አክቲቪስቶች፤ አሁን ባለው ሁኔታ የዜግነት ፖለቲካን መሬት ላይ ማውረድ ወይም መተግበር አይቻልም ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ የኢትዮጵያ ህዝብ እርስ በእርሱ የተዛመደ፤ የተዳቀለና የተሳሰረ  ነው፡፡ ለምሳሌ የከሚሴ ኦሮሞ፣ ወለጋ  ካለው ኦሮሞ ይልቅ በባህልና በአኗኗር ዘይቤው፣ ከወሎ አማራ ጋር  ይቀራረባል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ፤ የሀረር ኦሮሞ፣ ከጅማ አሮሞ  ይልቅ ለሶማሌ ህዝብ እጅግ የቀረበ ነው፡፡ ጅማ ያለው አማራ፣ ባህርዳር ካለው አማራ ይልቅ ጅማ ላለው ኦሮሞ፣ በባህልና አኗኗር ዘይቤው፣ በእጅጉ  የቀረበ ነው፡፡
ስለሆነም እነዚህን ህዝቦች አንድ ቋንቋ በመናገራቸውና ከአንድ ብሄረሰብ ተፈጥረዋል በሚል አስተሳሰብ ብቻ ሰብስቦ በአንድ ኮሮጆ ውስጥ መጨመር አይቻልም፡፡ ያልተጠበቀ ሌላ ችግርና ቀውስ ሊፈጥር ይችላል፡፡ በአጭር ቋንቋ፤ ለነዚህ ህዝቦች ከዜግነት ፖለቲካ ውጪ ሌላ ምንም አማራጭ አለ ብሎ መገመት አይቻልም።  እኔ እስከማውቀውና እስከሚገባኝ ድረስ፣ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ያለው መስተጋብርና በየሚዲያው  የሚነገረው በጣም የተራራቀ ነው፡፡ ሆኖም  የዜግነት ፖለቲካን መሬት ላይ ማውረድ እንደሚባለው ከባድ አይመስለኝም፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የአማራ አክቲቪስቶች፤ እንደ ህዝብ ተጨቁነናል ለማለት ከሚያቀርቡት መከራከሪያ ውስጥ አንዱ፤ ላለፉት በርካታ አመታት ህውሓትን የሚደግፉ ሰዎች፣ በሌሎች ስቃይ አልተደሰቱም ወይ? የሚል ደካማ ሀሳብ ይገኝበታል፡፡ በእርግጥ ሊኖሩ ይችላሉ፤ ነገር ግን እንደዚህ አይነት ሰዎች ሁሉንም ህብረተሰብ ወይም ህዝብ አይወክሉም፡፡ የአለም ታሪክ የሚያሳየን ይህንኑ ሀቅ ነው፡፡ ናዚን የሚደግፉ ጀርመናውያን እንዲሁም በአሜሪካም በአውሮፓም የሚኖሩ አክራሪዎች  ነበሩ፡፡ ታዲያ በነዚህ  ሰዎች ወይም ጥቂት አክራሪዎች የተነሳ ጠቅላላ የጀርመንም  ሆነ የአሜሪካና የአውሮፓ ህዝብ፤ የናዚ ደጋፊዎች ናቸው ማለት ይቻላል? በፍጹም አያስኬድም፡፡
እነዚህ ብሄርተኛ አክቲቪስቶች በተጨማሪም፤ እነ ታማኝ በየነ፤ ዶ/ር ብርሀኑ ነጋና አንዳርጋቸው ፅጌ፤ ሰዎች በብሄራቸው መደራጀት የለባቸውም ማለታቸውን እንደ ፀያፍ አስተሳሰብ ያቀርባሉ፡፡ ይልቁኑ እራሳቸውን አንድ ነገር ልጠይቃቸው፡፡ ለምንድነው እነ ታማኝ፤ በብሄር መደራጀትን የሚቃወሙት? የኢትዮጵያ ብሄሮችን ጠልተው ነው?  እነዚህ ሰዎች አኮ ልክ እንደ ሌላው ሁሉ የወጡበት  ብሔር፤ ባህል፤ ቋንቋና ማንነት አላቸው፡፡ ዝም ብለው ከሰማይ የወረዱ ሰዎች አይደሉም። እናንተ ለአማራው የሚሰማችሁን ቁጭትና ስሜት ሳይሰማቸው ቀርቶ ይመስላችኋል? በፍፁም አይደለም፡፡ እነዚህ ሰዎች በብሄር ከመደራጀት ይልቅ በዜግነት ላይ ተመስርተን ብንደራጅና ፖለቲካችንን በዜግነት ላይ ብቻ ብንቃኘው እኩልነት፤ ነፃነት፤ መከባበርና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማስፈን ተመራጩ ርዕዮት ነው በማለት ነው፡፡ ይሄ አስተሳሰብ ደግሞ የተቀደሰ ብቻ ሳይሆን ዘመናዊና የሰለጠነ ፖለቲካ አስተሳሰብም  ጭምር ነው፡፡
እኒህ የፌስቡክ አክቲቪስቶች አውቀውም ይሁን ሳያውቁ የዘነጉት ነገር ያለ ይመስለኛል። ይኸውም ሁሉም ነገር የሚቻለው ሀገር እስካለ ድረስ መሆኑን፡፡ ሌላው ቀርቶ መርዘኛ የዘር ፖለቲካ ለማቀንቀንም ጭምር ሀገር ያስፈልጋል። ሌላውን በአክራሪ ብሄርተኝነት ጠበል ለማጥመቅም ሀገር መኖር አለባት፡፡ ሰሞኑን እንደምንሰማው “ሰላምና መረጋጋት ተፈጠረም አልተፈጠረም፣ ምርጫው በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ መካሄዱ የግድ ነው” ብሎ ለመፎከርም  ሀገር ያስፈልጋል፡፡ ወገኖቼ፤ ደጉም ክፉውም የሚያምረው በሀገር ነው፡፡ እናም የምታራምዱት ፖለቲካ፣ የምትቀሰቅሱት ፕሮፓጋንዳ፣ የምትሰብኩት ርዕዮት---ሃገር እንዳያሳጣን ተጠንቀቁ፡፡ እንጠንቀቅ፡፡ ከሆነ በኋላ ከማዘንና ከመጸጸት፣ ከወዲሁ በጥበብና በዕውቀት መንቀሳቀስ ብልህነት ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሶርያዊያን ህጻናት ታቅፈው በአዲስ አበባ ጎዳና ላይ መለመን የጀመሩት፣ እንደ ራስ ተፈሪያን፣ ጦቢያን፣ የተስፋይቱ ምድር ናት በሚል አይደለም። ይልቁንም ውድ አገራቸው ሶሪያ፤ በጦርነት በመፈራረሷ ነው፡፡ የሶሪያ እናቶችና ህጻናት ተሰደው  ጦቢያ የመጡት፣ ሀገር ስለሌላቸው ነው፡፡ ሀገር ክብርና ጌጥ ብቻ አይደለችም። ገበናን የምትደብቅ እናትም ጭምር ናት። በአጭሩ አገር የሌለው ምንም ነው፡፡ አገር የሌለው ባዶ ነው፡፡
ምናልባት በመዲናዋ መንገዶች  በልመና ከሚተዳደሩት ሶሪያዊያን አንዱን ብትጠይቀው፣ ሶርያ ላይ በጦርነት  ስለተገደሉትና ቀባሪ አጥተው ስለተጣሉት እናቱ፣ አባቱ፣ እህቱና ወንድሞቹ በሀዘን ስሜት ሊነግርህ ይችላል፡፡ ከዛም በላይ ግን የእግር እሳት ሆኖበት፣ የሞቱ ዘመዶቹን ሁሉ በሚያስረሳ የሀዘን ስሜት የሚነግርህ ሌላ ነገር አለ፡፡ ይኸውም የተወለደባትና  ከልጅነት እስከ ዕውቀት፣ ሁሉን ነገር ያየባት፣ ሀገሩ መፍረስዋን ነው በቁጭትና በመሪር ሀዘን ሊነግርህ ይችላል። ሀገሩ ሶሪያ ብትኖር፣ ሌላው ቢቀር፣ የሞቱ ቤተሰቦቹን በክብር አልቅሶ መቅበር ይችል ነበር። ሆኖም  አገር የለውም፡፡
እኛ ኢትዮጵያዊያን ከሌሎች መማር አቅቶን፣ በስሜት እየተናጥን፣ በእሳት እየተጫወትን ይመስለኛል፡፡ በነገራችን ላይ ከየትኛውም ብሔር መፈጠር ምንም የሚያኮራ ነገር የለውም፤ ምንም የሚያሳፍርም ነገር የለውም፣ ምክንያቱም የተፈጠርንበት ብሔር በተፈጥሮ አጋጣሚ እንጂ መርጠንና ፈቅደን ያገኘነው  አይደለም፡፡ መኩራት ያለብን በላባችን፣ በትጋታችንና በስራችን ባገኘነው ነገር ብቻ ነው። እንዴት በአጋጣሚ በተገኘ ነገር  ይኮራል? ይልቁኑ ከኢትዮጵያ መፈጠር እጅግ  ብዙ የሚያኮራ ነገር አለው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ የተገኘችው በአባቶቻችን ደምና አጥንት ነው። በመጨረሻም አንድ አክቲቪስት ወዳጄ የነገረኝን ሀሳብ ላንሳና የኔን ሀሳብ ገልጬ ፅሁፌን ልቋጭ። “ስለ ወደፊት እጣ ፋንታችን ሁላችንም ነው ማሰብ  ያለብን እንጂ እኔና አንተ ብቻ አይደለንም ማሰብ ያለብን” ነበር ያለኝ፡፡ እውነት ነው፤ ሁላችንም ኢትዮጵያዊያን በሰከነና በተረጋጋ መንፈስ፣ በእውነትና በእውቀት ላይ ብቻ ተሞርኩዘን ማሰብና መነጋገር ይገባናል። ነገር ግን ሌላው አላሰበም ብዬ፣ እኔም እንደ እሱ ወርጄ ማሰቤን ማቆም እንዴት እችላለሁ፡፡ 100 ሚሊዮን ህዝብ ስለ ሀገሩ ማሰቡን ቢያቆም እንኳን እኔ ማሰቤን በፍፁም ላቆም አልችልም። ምክንያቱም ሌላው ሲያስብ እኔም አብሬ ሳስብ፣ ሌላው ማሰብ ሲያቆም፣ እኔም ላቆም  አይደለም የተፈጠርኩት። እኔ ብቻዬን በማሰቤ ምንም አልፈጥር ይሆናል፡፡ ነገር ግን ስለ ሀገሬ ኢትዮጵያ፣ ብቻዬን ብቀር እንኳን ማሰቤን ላቆም አልችልም!!!   

Read 6159 times