Saturday, 02 February 2019 15:13

ከአንገት በላይ ታቦት፤ ከአንገት በታች ጣኦት

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(4 votes)

በአፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት ላይ አመታት ያስቆጠሩ የተማሪዎች አመፃዎች ተደርገዋል። ቦግ እልም ይል የነበረው አመጽ፣ ግው ብሎ የነደደው በየካቲት 1966 ዓ.ም ላይ ነው፡፡
በነዳጅ ዋጋ ላይ በተደረገው ጭማሪ ታክሲዎች ስራ አቆሙ፡፡ በጅማ ጉባኤ በቀጠሮ ያደረው የመምህራን ተቃውሞ ተከተለ፡፡ ትምህርት ቤቶች ሥራ አቆሙ፡፡ ሠራተኞች በየቦታው ቀጠሉ፣ የባንክ ሠራተኞች ሳይቀር ሥራ አቆሙ፡፡ የንጉሡ መንግስት ግራ እየገባው ሄደ፡፡
ከነገሌ ቦረና የጀመረው የወታደሩ አመጽ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሐረርና አስመራን አዳረሰ። “የኑሮዬ ሁኔታ ይሻሻልልኝ፣ ደመወዝ ይጨመርልኝ” የሚለው የጦሩ ጥያቄ ፈጣን መልስ ተሰጠው፡፡ “ጦሩ ደመወዙን አስጨምሮ ካምፑ ገባ” የሚል ትችት በመምጣቱ፣ ሠራዊቱ ይበልጥ ወደ አመፁ እየተሳበ ገባ፡፡ ሰኔ 1966 የጦር ኃይሉን፣ የፖሊስ ሠራዊትንና የብሔራዊ ጦርን ያስተባበረ አንድ ቡድን ተቋቋመ፡፡ ይህ ቡድን እራሱን ደርግ ብሎ ሰየመ፡፡ ተማሪ መምህራንና ሠራተኛ የቀሰቀሰውና ያቀጣጠለው የሕዝብ አመጽ፣ በወታደሩ እጅ ወደቀ፡፡ ወታደራዊ መንግሥት ተቋቋመ፡፡ ደርግና ንጉሡ ወንበር ተለዋወጡ፡፡ ሕዝብ አቤት ባይ ሆኖ ቀረ።
የንጉሡ መንግስት፣ ኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ሥርዓት እንድትከተል፣ የመንግሥት ሥልጣን በሕዝቡ ድምጽ እንዲያዝ የሚያደርግ ሥርዓት ባለመዘርጋቱ የተነሳ፣ ለእርሱም ለራሱ አወዳደቁ አላማራም፡፡ ንጉሡና ከፍተኛ ባለሥልጣናቱ፣ ያልተጠበቀ የማይፈለግ ሞት ተወሰነባቸው፡፡
የደርግን መንግሥት ተዋግቶ አሸንፎ፣ አዲስ አበባ የገባው ህወኃት/ኢሕአዴግ ኃይል፤ ሰላም እንዳልነበረው የታወቀ ነው፡፡ ከመጀመሪያው አንስቶ ብዙዎች በሃሳብ ሲፋለሙት የቆዩ  ሲሆን ወደ ኋላም መሣሪያ እያነሱ ጥራኝ ደሩ የሚሉ በዝተውበታል፡፡ እሱም አንዱ በድርድር ገባ፣ ሌላው እጁን ሰጠ ሲል ቆይቷል፡፡ በ2008 ዓ.ም ማብቂያ ላይ የገጠመው ግን ያልታሰበና ያልተጠበቀ ነበር፡፡
በአዲስ አበባ አዲሱ የማስተር ፕላን ምክንያት በኦሮሚያ የተቀሰቀሰው በኋላም ወደ አማራና ደቡብ የተዛመተው የሕዝብ አመጽ፣ የሺዎችን ህይወት የነጠቀ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፋብሪካዎችን ያወደመ፣ ቁጥራቸው የበዛ መኪናዎችን የእሳት እራት ያደረገ፣ መንግሥትንም ከአንዴም ሁለቴ የአስቸኳይ ጊዜ  አዋጅ እንዲጣል ያስገደደ ነበር፡፡
በመቶዎች የሚቆጠሩትን ገድሎ ወደ ሰባ ሺህ የሚቆጠር አስሮ፣ የተሀድሶ ስልጠና የሰጠው መንግሥት፤ በጉልበቱ ብርታት የሚፈልገውን ሰላም አላገኘም፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማራዘምም መዳን አላመጣም፤ሕዝብ በአመፃው ገፋ፣ ሁለተኛው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ፡፡ በኦሮሚያ ቄሮ፣ በአማራ ፋኖ እየተባሉ እራሳቸውን የሚጠሩ፣ ሌላውም የሚጠራቸው መሪ የሌላቸው ኃይሎች ተፈጠሩ። የአመፁ አድማስና የአማፂው አይነትም በዛ፡፡ ዘርማ ተጨመረ፡፡ ሁለተኛውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መንግሥት አወጀ፡፡
በሕወሓት/ኢህአዴግ መንግሥት ሥር በመኖርና በሕወሓት/ኢሕአዴግ መንግሥት እጅ በመሞት መካከል ልዩነት ያልታያቸው ክፍሎች ሁለተኛውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥሰው ተቃውሞ ወጡ፡፡ መንግሥት ደነገጠ። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ፣ የሥልጣን መልቀቂያ ጥያቄ፣ ለኢሕአዴግ ምክር ቤት አቀረቡ፡፡ ኢሕአዴግ ለአስራ አምስት ቀን በር ዘግቶ ስብሰባ ተቀመጠ፡፡ ለድርጅቱ አዲስ ሊቀመንበር፣ ለመንግሥቱ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጐ፣ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድን ሾመ፡፡ ማንም አይክድም፤ በመንፈስና በግብር የሕወሓት/ኢሕአዴግ ሰው ያልሆኑት ዶክተር፣ የመሪነቱን ሥልጣን ጨበጡ፡፡
ኢትዮጵያ ከአንዱ መንግሥት ወደ ሌላው ሥልጣን የምታስተላልፍበት ሥርዓት አሁንም ያልዘረጋች በመሆኑ፣ ቄሮ፣ ፋኖ ዘርማ እና ሌላውም ተቀናቃኝ ኃይል፣ ደም ተፍቶ ያመጣው ለውጥ፤ በሕዝብ ትግል ተገፍቶ መውረድ በነበረበት በኢሕአዴግ እጅ እንዲቆይ ሆነ፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያው ደግሞ ሕዝብ ለፍርድ እንዲቀርቡ የሚፈልጋቸው ሰዎች በስልጣን ላይ መገኘታቸው ነው፡፡
ወደድንም ጠላንም፣ አመንም አላመንም ዛሬ የኢትዮጵያ የመንግሥት ሥልጣን ያለው በወንጀለኛው በኢሕአዴግ እጅ ነው፡፡ ታግለውና ደም ተፍተው ድሉን ያመጡት ቄሮ ፋኖና ሌላውም፣ እራሳቸው የተደራጁና የተሰባሰቡ ባለመሆናቸው፣ አሸናፊነታቸው የተያዘው፣ ዞሮ ወይም ቆይቶ በሚቃወሙት ክፍል ነው፡፡ ከዚህ የምንረዳው የ1966 እና የ2010 የሕዝብ አመጽና ድል፣ በውጤት አንድና ተመሳሳይ መሆኑ ነው፡፡  ሕዝባዊ መንግስት የመምጣቱ ነገርም፣ ገና ዘንቦ ተባርቆ ሆነ ማለትነው፡፡
ሰው ጨው አይደለም፣ አይቀመስም ይባላል። በሌላ በኩል ሰው፤በንግግሩና በተግባሩ ይለካል። ከዚህ አንጻር የዶ/ር ዐቢይ አሕመድን ቅንነት፣ ለአገርና ለታሪክ ተቆርቋሪነት፣ እሩቅ አላሚነት፣ ዜጎችን አክባሪነት ወዘተ-- የሚክድ ወይም ላለመቀበል የሚዳዳ መንፈስ የለኝም፤መቶ በመቶ እቀበላለሁ፡፡ ሆኖም መፍረስ መበስበስ የነበረበት የኢሕአዴግ ድርጅታዊ መዋቅር፣ አሁንም እንዳለ መቀጠሉ ያሳስበኛል፡፡ የመለወጥ ፍንጭ እየታየ አይደለም፡፡ በቅርብ በተካሄዱት የኢሕአዴግ ሴቶችና ወጣቶች ሊግ ስብሰባዎች ላይ የተንጸባረቀው፣  ያው የኢሕአዴግ ለለውጥ አሻፈረኝ  ባይነት ነው፡፡
አጋር እየተባሉ የሚጠሩት የአፋር፣ የጋምቤላ፣ የቤንሻንጉል፣ የሶማሌና የሐረር ክልል ገዥ ፓርቲዎች ሊቀ መናብርትና ምክትል ሊቀ መናብርት፤ በኢሕአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ተደርገዋል፡፡ የለውጥ ምልክት እንጂ መለወጥ አለመሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። አራቱ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች፣ እንደ አጋር ድርጅቶቹ ሁሉ የዘር ድርጅቶች ናቸው። ልዩነታቸው የሕዝብ ብዛት ብቻ ነው፡፡ ይህ ልዩነት የመብት ልዩነት ማምጣት እንዳልነበረበት የሚያምኑት ዶ/ር ዐቢይ፤ ገፍተው ሄደው ሁሉም ድርጅቶች እኩል የሚቆሙበት መሬት ሊፈጥሩ ግን አልደፈሩም፡፡ እስከ መቼ?
ኢሕአዴግ የዘር ስብስብነቱን አፍርሶ፣ አጋር ድርጅቶችን አስተባብሮ፣ ወደ ኅብረ ብሔራዊነት ይለወጣል ቢባልም አንዳች የሚታይ ጅምር የለም፡፡ ከመለወጥ ይልቅ ይባስ ወደ መከፋፈል እየሄደ ነው የሚመስለው፡፡ በተለይ በሕወሓት ዙሪያ፡፡ እስከ ታች ድረስ ባለው መዋቅር የኢሕአዴግ አለመለወጥ፣ ወይም እንዲለወጥ አለመሥራት፣ የዶ/ር ዐቢይን መንግሥት ከአንገት በላይ ታቦት፣ ከአንገት በታች ጣኦት ሆኖ እንዲታይ የሚያደርገው መሆኑ አይካድም፡፡ ቀደም ሲል እንደተጠቆመውም፤ ለለውጥ አደጋ ወደሚሆንበት ሁኔታ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል መጠርጠር የሚከብድ አይደለም፡፡
እኔም ሆንኩ ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ማየት የምንሻው፣ የተለወጠውን ኢሕአዴግ ነው፡፡ ፈርሶ እንደገና የተሠራ ኢህአዴግ!!

Read 447 times