Monday, 04 February 2019 00:00

ከድጥ ወደ ማጥ….

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(5 votes)

 ነዳጅ በጀሪካን መሸጥና መግዛት አይደለም ችግሩ፡፡ በነዳጅ እጥረት መኪኖች በየቦታው ሲቆሙና ነዳጅ ማደያ መድረስ ሲያቅታቸው፣ ሌላ ምን መላ አለ?
ይልቅ ዋናው ችግር፣ ኢንቨስትመንትና ቢዝነስ ተዳክሞ፣ በብር ህትመት ሳቢያ የዶላር ምንዛሬ ተዛብቶ ኤክስፖርት ከማደግ ይልቅ የኋሊት መንሸራተቱ ነው፡፡ የውጭ እዳ አለቅጥ በዝቶ የእዳ ክፍያው እጥፍ ድርብ እየከበደ መምጣቱም ዶላሩን በአመት ከ1.5 ቢ.ዶላር በላይ እስከመፍጀት ደርሷል፡፡
ኤክስፖርት ያለመሰናክል ቢያድግና ከኤክስፖርት የሚገኘው ዶላር ቢጨምር ኖሮ፣ ነዳጅ ከበቂ መጠባበቂያ ጭምር ማስመጣት ይቻል ነበር፡፡ አልሆነም፡፡ የነዳጅ ግዢ ከእጅ ወደ አፍ ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡ በሌላ አነጋገር፣ አገሪቱ ባለፉት አመታት ከገባችበት የኢኮኖሚ ቀውስ ጋር የተቆራኘ ችግር ነው፡፡
የኢኮኖሚ ቀውሱ ያነሰ ይመስል፣ የነዳጅ ነገር ከእጅ ወደ አፍ እየሆነ መምጣቱ አልበቃን ብሎ፣ ከመከራ አልመከር ብለን፣ ሌላ የባሰ ችግር እንጨምርበታለን፡፡
መንገድ የመዝጋት ስርዓት አልበኝነትና ሕገወጥነትን ተለማመድን፡፡ የኑሮን መንገድ መዝጋት ማለት እንደሆነም እያየነው ነው፡፡ በአንድ በኩል፣ የግል ኢንቨስትመንትን የሚያሰናክል፣ በዋጋ ንረት ኑሮን በሚያናጋ የገንዘብ ሕትመት ሳቢያ የዶላር ምንዛሬን እያዛባ፣ ኤክስፖርትን የሚያዳክም፣ አክሳሪ የመንግስት ቢዝነስን እያስፋፋና የውጭ ብድር እየቆለለ፣ በእዳ ክፍያ አገርን የሚያራቁት የተሳከረ የኢኮኖሚ ቅኝት ነው ዋናው ችግር፡፡ የተሳከረውን ቅኝት ለማስተካከል፣ የተቃወሰውን ኢኮኖሚ በአስቸኳይ ተረጋግቶ መልሶ እንዲነቃቃና በተቃና እድገት እንዲጓዝ መትጋት በይደር መዘግየት የሌለበት ስራ ነው፡፡
ከቀውስ ቶሎ መውጣት ተስኖን ኢኮኖሚው መፍረክረክ ከጀመረ፣ መልሶ ማንሰራራት እድል ማግኘት ይቸግራል - በዛሬው የአለም ሁኔታ ዛሬ ዛሬ መልሶ የማንሰራራት የራቃቸው አገራት እንጂ የተቃናላቸው አገራት ማየት እየቀረ ነውና የህልውና ጉዳይ ነው - ሰዎች፡፡ ነዳጅ የማስመጣት አቅም እየመነመነ፣ እጅ እያጠረው የመጣ የተሳከረና የተቃወሰ ኢኮኖሚን ለማስተካከልና ለማቃናት ደፋ ቀና ከማለት ይልቅ፣ “ነዳጅ በጀሪካን ተሸጠ” የሚል አስቂኝ ውዝግብና ውግዘት፣ ውንጀላና የቅጣት ዛቻ አገር አዲስ ስካር ሲጨመርባት ማየት ያሳዝናል፡፡
ነዳጅ ሲጠፋ፣ የመኪና ሞተር ተንተፋትፎ ሲቆም፣ በጀሪካን ጋዝ ለማምጣት መሞከር፣ መካሪ የማያሻው፣ የተራቀቀ ዕውቀትና የሰላ ስልሃት የማይጠይቅ፣ “ምን ይሻላል? ምን ይሻለኛል?” ብለው ከሁለት ሦስት ሴኮንድ በላይ ቢያሰላስሉት የሚያሰለች ቀላል ጉዳይ አይደለም?
“መኪና ተሸክሞ መሄድ ቢቻል ኖሮ” እያሉ ከሃሳብ ሃሳብ ያልሆነ፣ ከሞኝነትም ሞኝነት እንጂ ምኞት ያልሆነ የቁም ቅዠት ነው - ሌላኛው አቅጣጫ፡፡ እውነተኛ ችግር በበዛበት አገር፣ የነዳጅ እጥረትና እጦትን ከመሰለ ከባድ ችግር ጋር እየተጋጩ እውነተኛውን ችግር ትቶ፣ “ነዳጅ በጀሪካን ተሸጠ” የሚል እሮሮና ጫጫታ ውስጥ መዘፈቅና በውዝግብና በዛቻ መሳከር ይገባል?
የቧንቧ ውሃ ሲጠፋ በጀሪካን ውሃ እየተቀዳ ነው” ብለን አገርን መቀመጥ ምንድነው ይልቅ ዋናው ችግር፣ በራሱ ጊዜ የማይቃና፣ በዘፈቀደ የማይድን ስለሆነ፣ መላ በማበጀት ላይ ብናተኩር ይሻላል፡፡ ለነገሩ የተሳከረውን የኢኮኖሚ ቅኝት የማስተካከል፣ የተቃወሰውን የማቃናት ጥረት ቀላል ስራ አይደለም፡፡
ላለመንኮታኮትና ከቀውስ ለማምለጥ መፍጠን፣ መትጋትና መገስገስ ያስፈልጋል፡፡ ነገረ ስራችን ግን ከመንፏቀቅና ከመንሸራተት፣ ከመደናበርና ከመላተም ማለፍ ከብዶታል፡፡
ይህም አንሶት ነው መንገድ የመዝጋት በሽታ የበረከተው፡፡ ከድጥ ወደ ማጥ የበረከተበት አገር ሆነና፡፡  

Read 6588 times