Print this page
Saturday, 02 February 2019 15:29

የኢትዮጵያ ኪክቦክሲንግ ከሙያ ማህበር ወደ ፌደሬሽን

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

  ማስተር ኢንስትራክተር አዛዥ አየለ ይባላል። የዋርየር ኪክቦክሲንግ ክለብ ዋና አሰልጣኝና የአዲስ አበባ የኪክቦክሲንግ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ነው፡፡
በኮተቤ ሜትሮፖሌትያን ዩኒቨርስቲ በስፖርት ሳይንስ የ4ኛ ዓመት የዲግሪ ተማሪ ሲሆን በኪክቦክሲንግ በሰባተኛው ኢንተርናሽናል የማርሻል አርት ጌምስ ከተማሪው ጋር ኢትዮጵያን ወክሎ በመሳተፍ የወርቅና የብር ሜዳልያዎች አስመዝግቧል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኪክቦክሲንግን በመላው ኢትዮጵያ ለማስፋፋት ከሙያ ባልደረቦቹ ጋር ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን፤ የአሁኑ ትውልድ ስፖርቱን ለማስተዋወቅ፤ ወደ ፌደሬሽን አስተዳደር እንዲመጣና የሙያ ማህበራት እንዲደራጁ ከፍተኛ መስዕዋትነት መክፈሉን የገለፀው ኢንስትራክተር አዛዥ ይህን ልዩ ቃለምልልስ ከስፖርት አድማስ ጋር አድርጓል፡፡


    የኪክቦክሲንግ ፌደሬሽን እስካሁን በአገር አቀፍ ደረጃ ለምን አልተመሰረተም?
አዎ የኢትዮጵያ ኪክቦክሲንግ ፌደሬሽን የለም፡፡ ካለፉት አምስት ወራት ወዲህ ፌደሬሽኑን በአዲስ አበባ ደረጃ ለማቋቋም እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ በአደራጅ ኮሚቴ ስንሰራ ኪክቦክሲንግ ከአዲስ አበባ ኢንተርግሬትድ ማርሻል አርት ፌደሬሽን ራሱን ችሎ እንዲወጣ አድርገናል፡፡ እንደቴኳንዶ፤ እንደውሹ፤ እንደካራቴ ሁሉ ኪክቦክሲንግም በፌደሬሽን እንዲተዳደር ነው፡፡ ይህም በአህጉር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚሰሩ የኪክቦክሲንግ ተቋማት ጋር ግንኙነት ይፈጥራል፡፡ ለስፖርቱ ዋናው መዘውር ውድድሮች በመሆናቸው በአፍሪካ እና በዓለም ደረጃ ኢትዮጵያን ወክሎ ለመሳተፍና ፕሮፌሽናል ስፖርተኞችን በየጊዜው በማፍራት ለመስራት በፌደሬሽን ደረጃ መውጣቱ አስፈላጊ ነው፡፡ በኢንተርግሬትድ ማርሻል አርት ፌደሬሽን ውስጥ ሰባት የተለያዩ የማርሻል አርት አይነቶች የሚተዳደሩ በመሆናቸው የኪክቦክሲንግን ጉዳይ አጉልቶ ማውጣት አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በፌደሬሽን ደረጃ ለመንቀሳቀስ ከቻልን የኪክቦክሲንግን ጉዳይ በራሱ ስራ አስኪያጅ ኮሚቴ፤ በኪክቦክሲንግ ባለሙያዎች፤ ለማስተዳደርና ለመምራት ይቻላል ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ከኢንተርግሬትድ ፌደሬሽን የምናገኘውን በጀት በመጠቀም ለባለሙያዎችና ለስፖርተኞች ውድድሮችን ፤ ስልጠናዎችን የምንሰጥባቸውን እድሎች እንፈጥራለን፡፡ ለፌደራል ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን በደብዳቤ አሳውቀን በአገር አቀፍ ደረጃ ስፖርቱን በማስተዋወቅ ጠንካራ ስራዎችን በማከናወን ብሄራዊ ፌደሬሽን ለመመስረት እንቀሳቀሳለን፡፡
በአዲስ አበባ የኪክቦክሲንግ ፌደሬሽኑን ለመመስረት በመንቀሳቀስ ላይ ያላችሁት እነማን ናችሁ?
በአደራጅ ኮሚቴው ውስጥ አባል የሆኑት ስድስት   ክለቦች ዋርየር ኪክቦክሲንግ፤ ዴቭዳን ኪክቦክሲንግ፤ አፍሪካ ኪክቦክሲንግ፤ ዳኒ ኪክቦክሲንግ፤ ፋስተን ኪክቦክሲንግና ሶል ብሮ ኪክቦክሲንግ ናቸው፡፡ ሁሉም ክለቦች በተለይ በታይ ኪክቦክሲንግ የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ ታይ ኪክቦክሲንግ ሁሉም የሚሰሩት የታይላንድን ስፖርት ያጣመረ ዘመናዊ የኪክቦክሲንግ ደረጃ በመሆኑ ነው፡፡ ኪክቦክሲንግ መነሻው ከጃፓን ቢሆንም የአሜሪካ፤ የቻይና፤… ወዘተረፈ የተለያዩ ግን ዝምድና ያላቸው የኪክቦክሲንግ አይነቶች ናቸው፡፡ ሁሉም የሪንግ ስፖርት ሆነው 95 በመቶ የሚመሳሰሉ ሲሆን ልዩነት ቢኖራቸው በደንቦቻቸው እና በጨዋታ ህጎቻቸው ብቻ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የኪክቦክሲንግ ስፖርት የሚገኝበትን ደረጃ እንዴት ትመለከተዋለህ?
ፌደሬሽን ለመመስረት እየተንቀሳቀሱ ያሉት 6 ክለቦች በወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ፈቃድ ያገኙ እና ህጋዊ እውቅና ያላቸው፤ የረጅም ጊዜ የስልጠና ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች የሚመሩ፤ ኪክቦክሲንግ በከፍተኛ ደረጃ በመማርም በማስተማርም የተከኑ፤ የስፖርት ሳይንስ የተማሩ እና ያጠኑ ናቸው፡፡ በአደራጀት ኮሚቴው ስንቀሳቀስ ከላይ ከጠቀስኳቸው ህጋዊ የኪክቦክሲንግ ክለቦች ውጭ በሳይንሳዊ መንገድ ማኑዋል በማዘጋጀት የአሰልጣኝነት ስልጠናዎችንም ሰጥተናል፡፡ ስልጠናውን የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ባዘጋጀው የ15 ቀናት ውድድርና ስልጠና የኪክቦክሲንግ  አሰልጣኝነት ስልጠናውን የሰጠሁት እኔ ስሆን፤ ከ20 በላይ ባለሙያዎችን ያፈራንበት ነበር፡፡ በስልጠናው የሰራነው ስፖርቱን በተሻለ አቅጣጫ ለማስፋፋት እንዲሁም  ወደ ህብረተሰቡ በማድረስ በጎ ተፅእኖዎችን ለመፍጠር በማሰብ ነው፡፡ ይህንንም በማድረግ መልካም ስብዕና ያለውን ወጣት ትውልድ የምንፈጥረበት ራእይን ከማራመዳችን ባሻገር የአገራችንን የጤና ፖሊሲ ማገዝ እየቻልን ነው፡፡ በየጊዜው በምነሰጣቸው ስልጠናዎች አሰልጣኞች እየበዙ መምጣታቸው ብዙ ክለቦችን በህጋዊነት ለማንቀሳቀስ የሚያስችል ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ  በኪክቦክሲንግ አብሮ መስራት የሚችል ጤናማ አስተሳሰብ ያለው ወጣት ትውልድ የምንፈጥርበት ነው፡፡
በኢትዮጵያ የኪክቦክሲንግ ስፖርት ሲዘወተር በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም ከምስራቅ አፍሪካ አንፃር ስንገመግመው ብዙም እድገት እንዳላሳየና ብዙም እንዳልሰራንበት ነው የምገነዘበው፡፡ ለምሳሌ በኬንያ፤ በደቡብ ሱዳን፤ በኡጋንዳና በታንዛኒያ ብትመለከት በፕሮፌሽናል አስተዳደር የሚንቀሳቀሱ ከ20 በላይ ክለቦች እያንዳንዳቸው ያስመዘግቡ ናቸው፡፡ የክለቦቹ ብዛት በእነዚህ አገራት በየጊዜው ውድድሮች የሚካሄዱባቸውን ምቹ ሁኔታዎች ለመፍጠር ተችሏል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ክለቦች ባለመኖራቸው ውድድሮችን በምንፈልገው ብዛት እና ደረጃ ለማካሄድ አላስቻለንም፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የክለቦቹ ብዛት እየጨመረ በመምጣቱ ተስፋ አሳደርን እንጅ በፊት በነበሩት ሁለትና ሶስት ክለቦች ውድድር ማዘጋጀት የማይታሰብ ነበር። በፕሮፌሽናል የፌደሬሽን አስተዳደር መመራት ከቻልን፤ የክለቦች ብዛት እየጨመረ ከሄደ ኋላ ከቀረንብት የምስራቅ አፍሪካ ኪክቦክሲንግ ያለውን ልዩነት በማጥበብ በአጭር ጊዜ ውስጥ በክፍል አህጉራዊ ውድድሮች የምንሳተፍበትን እድል እንፈጥራለን፡፡ በእኛ ጌዜ የኪክቦክሲንግ ተወዳዳሪዎች ሆነን በምስራቅ አፍሪካ የተለያዩ አገራት በመዘዋወር ተሳታፊዎች ነበርን፡፡ በኬንያ፤ በኡጋንዳ፤ በደቡብ ሱዳንና በታንዛኒያ የተወዳደርንባቸው ተመክሮዎች ነበሩ፡፡ ዛሬ በእነዚህ የምስራቅ አፍሪካ አገራት የኪክቦክሲንግ ፌደሬሽኖች ተመስርተዋል፡፡ ኢትዮጵያም ከዚህ ሁኔታ የዘገየች በመሆኗ በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ ተፎካካሪ የሚሆኑ ተወዳዳሪዎችን ለማፍራትና ስፖርቱን ለማሳደግ የግድ በፌደሬሽን አስተዳደር መስራት ያስፈልጋታል ማለት ነው፡፡
አሁን በአደራጅ ኮሚቴ የአዲስአበባን ኪክቦክሲንግ ፌደሬሽን ለማቋቋም እየሰራችሁ ነው፡፡ ምን አይነት ለውጦችን ለመፍጠር በማቀድ ነው?
በፌደሬሽኑ ስራ አስኪያጅ ኮሚቴ የምናከናውናቸው የተለያዩ እቅዶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እኛ የኪክቦክሲንግ አሰልጣኞች ግን እንደባለሙያ ለመስራት የምንፈልጋቸው ተግባራት አሉ፡፡
ከተለያዩ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ከፍተኛ ደረጃ እና ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች እንዲሁም ብቁና ፕሮፌሽናል ተወዳዳሪዎችን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት የኪክቦክሲንግና የታይ ኪክቦክሲንግ ስልጠናዎችን ለመስጠት እና ውድድሮችን ለማዘጋጀት እቅድ አለን። በተለይ በቅርቡ ከምስራቅ አፍሪካ በተለይ ከኬንያ፤ ደቡብ ሱዳን፤ ኡጋንዳና ታንዛኒያ ተወዳዳሪዎችን በመጋበዝ ክፍለአህጉራዊ የኪክቦክሲንግ ውድድር በመጋቢት ወር መጨረሻ ላይ ለማዘጋጀት እየሰራን ነው፡፡ ይህን ውድድር የምናዘጋጀው በኪክቦክሲንግ ስፖርት የሚንቀሳቀሱ የኢትዮጵያን ወጣቶች ለማነሳሳት፤የውድድር መንፈሱን እንዲያገኙና የጎረቤት  አገራት ልምዶችን እንዲቀስሙ አስበን ከመሆኑም ባሻገር መንግስት እና ህብረተሰቡ ለስፖርቱ ያላቸውን ትኩረትና ግንዛቤ ለማሳደግ አቅደን ነው፡፡
በሌላ በኩል በፌደሬሽን ደረጃ መንቀሳቀስ ስንጀምር ከአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የኪክቦክሲንግ ተቋማት ጋር የሚኖሩንን ግነኙነቶች የሚያጠናክር ይሆናል፡፡ በተደራጀንባቸው የሙያ ማህበራት ኢንተርናሽናል ከሆኑ መሰል ተቋማት የምናገኘውን ድጋፍም ሊጨምር የሚችል ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ስልጠናዎችና ውድድሮችንም እናገኛለን፡፡ኢትዮጵያ ውስጥ ያለን የኪክቦክሲንግ አሰልጣኞች የሙያ ማህበር አደራጅተን ወደ ፌደሬሽን አስተዳደር ለማደግ እንቅስቃሴ መግባታችን ከወዲሁ የተረዱ አንዳንድ አገራት ለተለያዩ ስልጠናዎችና ውድድሮች እየጋበዙን ናቸው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ መጥተውም የተለያዩ ድጋፎችን ለመስጠት የሚፈልጉም አሉ፡፡ ለምሳሌ በማህበራችን የቦርድ አባል የሆነ ስዊዘርላንድ ውስጥ የሚኖር ባለሙያ የኪክቦክሲንግ እና የታይ ኪክቦክሲንግ ስልጠና ለመስጠት ቃል ገብቶልናል፡፡ በተመሳሳይ  ደቡብ ሱዳን  ውስጥ የሚገኘውና በምስራቅ አፍሪካ ኪክቦክሲንግ ፈርቀዳጅ የሆነው ሱሮ ኤኬሎ በሚቻለው አቅም አብሮን ለመስራት እንደሚፈልግ አሳውቆናል፡፡ ለሙያ ማህበራችንም ለኪክቦክሲንግ ፌደሬሽኑም ልዩ ልዩ ስልጠናዎችን እንደሚሰጥ ቃል የገባው ኦኬሎ በደቡብ ሱዳን ታዋቂ የሆነው የታይ ኪክቦክሲንግ ክለብ ትሪፕል ኪክቦክሲንግ መስራች ነው፡፡
የኪክቦክሲንግ ስልጠና የሚሰጡት ቅድም የዘረዘርካቸውና ህጋዊ ፈቃድና እውቅና ባላቸው 6 ክለቦች ብቻ ናቸው ወይ?
በተለያዩ የከተማው ክፍሎችና በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች የኪክቦክሲንግ ስልጠናዎች የሚሰጥባቸው ያለህጋዊ ፈቃድ የሚሰሩ ማሰልጠኛዎች ከ30 በላይ መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ይሁንና በቀጣይ እነዚህ የኪክቦክሲንግ ማሰልጣኛዎች አስፈላጊውን ህጋዊ ፍቃድ በማውጣት እና እውቅና በማግኘት መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡ አስፈላጊውን መስፈርት በማሟላት ህጋዊ ፈቃድ አውጥተው አብረውን እንዲሰሩ እንፈልጋለን፡፡ በፌደሬሽን በኩል በድጋሚ በምናዘጋጃቸው የአሰልጣኝነት ስልጠናዎች በመሳተፍ አስፈላጊውን የሙያ እና የብቃት ማረጋገጫ ሊይዙ ይገባል፡፡ በአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን የትምህርትና ስልጠና ክፍል ጋር በመተባበር የምናዘጋጀው ስልጠና በንድፈ ሃሳብ እና በተግባር ፈተናዎች በ15 ቀናት የሚያልቅ ነው፡፡ በዚህ መንገድ የሚሰለጥኑ ህጋዊ ፈቃድ እና እውቅና በማግኘት ክለቦች መስርተው እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ እንፈልጋለን፡፡
የሙያ ማህበራቸውን መስረተው ወደ ፌደሬሽን አስተዳደር እያቀኑ በሚገኙት ክለቦች  ውስጥ  የኪክቦክሲንግ አሰልጣኞች እና ተማሪዎች ብዛት፤ ወርሃዊ ክፍያ፤ በጀት፤ የስፖርት ትቆች እና ሌሎች መሳርያዎች ወጭና አቅም እንዴት ትገልፀዋለህ?
ህጋዊ ፈቃድ እና እውቅና ያላቸው የኪክቦክሲንግ ማሰልጣኛዎች እና ሌሎች ለአንድ አሰልጣኝ በአማካይ በወር ከ250 እስከ 300 ብር የሚያስከፍሉ ናቸው፡፡ የኪክቦክሲንግ ስልጠና ከ3 እስከ 4 ዓመታት ጊዜ የሚወስድ ሲሆን ስልጸናው ከ7 ዓመት ጀምሮ በሁሉም የእድሜ ደረጃዎች በሁለቱም ፆታዎች ሊሰጥ የሚችል ነው፡፡ በየክለቡ ቢያንስ አንድና ሁለት ዋና አሰልጣኝ እንዲሁም ሁለትና ከዚያም በላይ ረዳት አሰልጣኞች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ በ6ቱ ክለቦች ከ20 በላይ ዋና እና ረዳት አሰልጣኞች እና አሉ ማለት ነው፡፡ በእያንዳንዱ ክለብ በየፈረቃው የሚሰለጥኑ እሰከ 70 ተማሪዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በእርግጥ ስፖርቱ ላይ ከተጋረጡ ፈተናዎች ዋንኛው ከስፖርት ትጥቆችና ቁሳቁሶች ጋር በተገናኘ ያለው እጥረት ሳሆን በተለይ ከዋጋ መወደድ ጋር የተያያዘ ነው። የቦክስ ጓንቶች፤ የቅልጥም መከላከያዎች፤ የጭንቅላት፤ የጥርስ፤ የብልት መከላከያዎች፤ በአጠቃላይ ለስልጠናው ለአጠቃላይ ደህንነት የሚያስፈልጉ ማቴርያሎች አቅርቦት ላይ ከፍተኛ እጥረት አለ፡፡ አንድ የኪክቦክሲንግ ክለብ ለምሳሌ 10 ሳኮች ያስፈልጉታል ቢያንስ እስከ 30ሺ ብር፤ ቢያንስ ለ10 ተማሪዎች 10 የቦክስ ጓንት ለእያንዳንዱ ሁለት ሁለት ቢያዘጋጅ 15ሺ ብር፤ ለቦክስ እና ለኪክ ፓዶች ለእጅና ለእግር እስከ 50ሺ ብር፤ ለቅልጥም፤ ለጭንቅላት፤ ለጥርስ፤ ለብልት መከላከያዎች… በአጠቃላይ ለስፖርት ትጥቆችና ቁሳቁሶች 10 ሰልጣኞች ላሉት ክለብ እስከ 200ሺ ብር ወጭ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ለጥንካሬ መስርያ ብረቶች እና የጂም መሳርያዎች እንዲሁም ከማቴርያሎች ውጭ ለቤት ክራይ የሚያስፈልገውን ወጭ ስንደምረው ቢያንስ እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር ወጭ ይኖራል ማለት ነው፡፡ ስለዚህም በእኛ በኩል በሙያ ማህበራችን ከዚያም በምንመሰርተው ፌደሬሽን እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ በመንግስት በኩል ከቀረጥ ነፃ የስፖርት ትጥቆችና ቁሳቁሶችን ለማስገባት የመስራት ሃሳብ አለን፡፡ ለሰልጣኞቹ፤ ነገ አገርን ለሚወክሉ ተወዳዳሪዎች ደህንነት እና ጤንነት ሲባል አስፈላጊ ትኩረት ለመፍጠር እየተንቀሳቀስንም ነው፡፡በተጨማሪም ከባድ ካፒታል ለሚጠይቅ የኪክቦክሲንግ ክለብ ምስረታ መንግስት የብድር ድጋፍ በመስጠት ሊያበረታታ ያስፈልጋል፡፡

Read 6981 times