Saturday, 02 February 2019 15:20

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(6 votes)

  “ልብህ ቢያቆም ልብ ሊቀየርልህ ይችል ይሆናል፤ ማሰብ ስታቆም ግን ሞተሃል”
            
    አንድ ምሽት አንድ ጐረምሳ ዳቦ ሰርቆ ሲሮጥ ባለቤቶቹ ተከታትለው ያዙት፡፡ ክፉኛ እየደበደቡ ንጉሡ ችሎት አቀረቡት፡፡…
“ለምን ሰረቅህ?”
ዝም፡፡
“የታለ ዳቦው?”
“ውጦታል” አሉ ሰዎቹ፡፡
“ሌላ ዳቦ አምጡና እንዴት እንደዋጠው ያሳየን” አለ ንጉሡ፡፡
…ዳቦውን አምጥተው ለሌባው ሰጡትና…፤
“እንደ ቅድሙ ብላው?” አሉት፡፡
እየታገለ በልቶ ጨረሰ፡፡ ንጉሡም የዳቦውን ዋጋ ሰጥቷቸው፤…
“እናንተ ሂዱ፤ እሱ ይቆይ” ብሎ ከሳሾቹን አሰናበታቸው፡፡
እንደሄዱም፤ “አሀንስ ጠገብክ?...ዳቦ ያስጨመርኩት ርቦሃል ብዬ ነበር፤ አንተ ግን እየተናነቀህ ነው የበላኸው፡፡ ሳትራብ ነው የሰረቀኸው?” ሲል ንጉሡ አቀርቅሮ መሬት መሬቱን የሚያየውን ሌባ ጠየቀው፡፡
ዝም፡፡
..እንደገና ቢጠይቀውም መልስ አልሰጠውም፡፡
 ንጉሡ ተቆጣ፡፡
“ቀና ብለህ መልስልኝ” አለ እየተበሳጨ፡፡
“እኔ አልራበኝም፤ ለሌሎች ሰዎች ነው፡፡” መለሰ ሌባው፡፡
ንጉሡም ድምፁን እንደሰማ የሚያውቀው ስለመሰለው፣ ብድግ ብሎ ወደ ሌባው ቀረበና፣ በከዋክብቱ ብርሃን በዱላ ያባበጠውን ፊት ትኩር ብሎ ሲመለከት፣ ያየውን ማመን ከብዶት ራሱን ሳተ፡፡…
***
ለመኖር መታገል፣ መጓጓትና መመኘት ያለ፣ የነበረና የሚኖር የሰው ልጆች ባህሪ ነው፡፡ ገንዘብ እየሰበሰቡ “ነገን” ለመኖር መዘጋጀት፣ “ነገ እደሰታለሁ” ብሎ ማሰብ ግን ሞኝነት ይሆናል። ይልቁንም የደስታ በር የሚከፈተው፤ እነዚህን ባህሪያት ገርተህና ተጭነህ ልክ ስታበጅላቸው ነው፡፡ ወዳጄ፡- ቅጥ ያጣ ፍላጐትና ምኞት ምክንያታዊነትህን ይፈታተናል፣ ደመ ነፍስህን ይገዳደራል፣ ህሊናህን ይጋርዳል፡፡ ውሎ አድሮም “ደነዝ”፣ “ልበ ድንጋይ” ወዘተ ያሰኝሃል፡፡
ወዳጄ፡- ጥፋታችንን በስልጣናችን ጉያ ብንሸሽገው፣ በድህነታችንና በኑሯችን ቀጫጫነት ብናመካኝ ወይም “ዓላማ” በምንለው ነገር ብናሳብብ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ፣ የሌሎችን አፍንጫ እስከነካን ድረስ ተጠያቂ ነን፡፡ ከተነቃብን በህግ፣ ካልተነቃብን በህሊና። ማህበራዊ ዋጋችንም የዚያኑ ያህል ይቀንሳል፡፡ ፍርሃትና ፀፀትም ያሳድርብናል፡፡
ደስታ የምንለው ስሜት ሩቅ የተቀመጠ፣ ለነገ ያደረ ተስፋ ወይም ምኞት አይደለም፡፡ ደስታ የሚገባው ዕውቀታችን፣ ሚዛናዊነታችን፣ በጐነታችን፣ ጤንነታችን፣ አሸናፊነታችን የሚገለጽባት ይቺ አሁን ያለንባት ቅጽበት ናት፡፡
ወዳጄ፡- መኖርና መፈለግ አንድ ላይ የተወለዱ መንታ ዕውነት ናቸው፡፡ መኖር  መፈለግና ሰውን መነጠል አይቻልም፡፡ ዕውቀት የሚያነቃን፣ እንዴት መኖር፣ ምን እንደምንፈልግና መቼ እንደሚያስፈልገን እንድንረዳና በዚህ የዕለት፣ ተዕለት ውሏችን ውስጥ ከበረታን መልካምነትን አለዚያም ተቃራኒውን የምንሸምት መሆኑን ነው፡፡ በዚሀ ዕለት ተዕለት ስንል፣ ዕድሜም እየተቆጠረ መሆኑንን አትርሳ፡፡ አንድ ነገር ግን ልብ በል፡- ሰው ሆነን መብላት መጠጣት ከመልመዳችን፣ ሥጋ ከመልበሳችን በፊትም ነበርን፡፡ “መጀመሪያ ቃል ነበር፣ ቃልም ስጋ ሆነ” እንዲሉ፡፡ እዚህ ጋ ሃሳብ ከሆድ እንደሚቀድም ተመስክሯል፡፡ ሃሳብ ህይወት መሆኑ ተነግሯል፡፡ ልብህ ቢያቆም ልብ ሊቀየርልህ ይችል ይሆናል፡፡ ማሰብ ስታቆም ግን ሞተሃል፡፡
አእምሯቸው የተሰናከለባቸው ወይም አእምሯቸው እንደ ሰውነት አካላቸው የማያድግ (Retarded ይሏቸዋል) ሰዎች አሉ፡፡ ሌሎች አካላቶቻቸው፣ ዓይናቸው፣ ሳንባቸው፣ ልባቸው፣ ኩላሊታቸው ወዘተ ከማንኛውም ሰው አይለይም፡፡ ማሰብ ግን አይችሉም። ቢርባቸው ይመገባሉ፡፡ የሚበሉት ካጡና ምግብ ካዩ፣ የማንም ይሁን የማን፣ ሳያስፈቅዱ ይወስዳሉ ወይም ይቀማሉ፡፡ ያንን ማድረግ ለነሱ ትክክልና ተፈጥሯዊ ነው፡፡ እነሱ እየተራቡ ሌላው ተርፎት እያዩ ቢከለከሉ አይገባቸውም። ይቆጣሉ፣ አቅም ካላቸውም ይናከሳሉ። እንደ ህፃን ወይም እንደ እንስሳ፡፡ “ጤነኛ” የሚባል ሰው፤ በተለያዩ ሰው ሰራሽም ሆነ ተፈጥሯዊ ምክንያቶች ቢርበው ይለምናል ወይ ይሰርቃል እንጂ ትርፍ ነው ልውሰድ፣ አንተ ጠግበሃል እኔ ልብላ ብሎ አያስገድድህም፡፡ የሚተዳደረው በማህበራዊ ህግና ስርዓት ነው። እነሱ አይከሰሱም፣ ግን ይከሰሳል፣ ይጠየቃል። የልዩነቱ ምክንያት የማሰብና አለማሰብ ጉዳይ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ‹ሰው› የመሆንና ያለመሆን፡፡
ወዳጄ፡- የዳቦን ነገር ካነሳን በዚህ ዘመን “ስትፀልዩ የዕለት ዳቦአችንን ዛሬ ስጠን” በሉ፣ ነገ የናንተ አይደለችም”፤ “ሁለት ያለው አንዱን ለሌለው ያካፍል” የሚባለው ነገር እንደማይሰራ የተረጋገጠ ይመስላል፡፡ እንኳን እኛ ተማሪዎቹ፡- ቀሳውስቶቹ፣ ፓስተሮቹ፣ ሼሆቹና መሰሎቻቸውም አያደርጉትም፡፡ ጥቂቶች ግን አሉ፡፡ ከተረፋቸው ሳይሆን ከሚያስፈልጋቸው የሚያካፍሉ፡፡ መስጠት የመንፈስ እርካታ፣ ነፃነትና ደስታ መሆኑ የገባቸው፡፡ … “ሰው በእህል ብቻ አይኖርም” ሲባል፤ ካላሰበ፣ በጥበብና በዕውቀት ታንፆ ህይወቱን መምራት ካልቻለ፣ ‹አጋሰስ› ይሆናል እንደማለት ይመስለኛል፡፡
መኪናህን ነዳጅ ሞልተህ ካልጠቀምክበት፣ ለበቅሎህ ጭድ እየከመርክ አስረህ ብትቀልባት ትርጉም የለውም፡፡ ሰውም እህልና ውሃ የሚያስፈልገው እንዲያስብ፣ እንዲመራመር፣ እንዲፈጥርና እንዲሰራ፣ በአእምሮው፣ በአካሉ፣ ለጉልበትና ኃይል እንዲሆነው ካልሆነ፣ ከእንስሳዊ ወይም ከቆመው ማሽን በምን ይሻላል? …“ለመኖር ብላ እንጂ ለመብላት አትኑር” የሚባለው ነገር እዚህ ጋ ትክክል ይመስለኛል። አዋቂዎች እንዲህ አይነቱን ባካናነት ፊሊስቲን (philistine:- a man who has no mental needs) ይሉታል፡፡
ወዳጄ፡- ቀልዱም ቀልድ፣ ቁም ነገሩም ቁም ነገር ይሁንና፤ በዚህ ሳምንት በዜና ማሰራጫዎች የሰማሁዋቸው፣ ከዳቦ ጋር የተያያዙ ሁለት አሳዛኝና አስደሳች ዜናዎች አሉ፡፡ አሳዛኙ፡- ስምንት ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝባችን ከፍተኛ ረሃብ አጋጥሞታል፡፡ የሚተነፍሰው በየዕለቱ በሚደርሰው ዳቦ ነው፡፡ ለምን? እንዴት ብሎ ለመጠየቅ ጊዜ የለም፡፡ በአስቸኳይ የምትችለውን ለማድረግ ብቻ ቁረጥ፡፡ እግረ መንገድም የለውጡን ኃይሎች ማገዝ ይሆናል። አስደሳቹ ነገር ደግሞ ትልቅ የዳቦ ፋብሪካ በውጭ ሃገር ባለሀብቶች ሊቋቋም መነገሩ ነው፡፡ በነገራችን ላይ “ዶሮ ብታልም ጥሬዋን” አትበሉኝና፣ የኛዎቹን ዳቦ ቤቶች (እንደ ሸዋ ዳቦ ዓይነቶቹን ሃቀኞች አይመለከትም) ምነው ‹ሃይ!› የሚላቸው ጠፋ? … ከጥራት ጥረት፣ ከክብደት ክብደት፣ ከዋጋ ዋጋ እንዲህ ‹ዜሮ ሰም› ሆነው ይረፉት? … የዳቦ ጉዳይ የፈረንሳዮቹንና የኛን ጨምሮ ስንት ታላላቅ ሪቮሉሽን ያስነሳ፣ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ መሆኑን ለማን አቤት እንበል? … ማሪያ አንቶኖቴ ተነስታ እስክታስረዳቸው ነው እሚጠብቁት?
***
ወደ ተረታችን ስንመለስ፡- ንጉሱ ራሱን ሲያውቅ ሌባውን አስጠርቶ፣ ሁኔታን በዝርዝር ተረዳና አለቀሰ፡፡ ታሪኩም በእምነታቸው ሰበብ ማህበረሰቡ ስላገለላቸው ረሃብተኛ እናትና ልጅ ነበር፡፡ በሁኔታው ያዘነው የዛሬው ሌባችንም፤ ምግብ ደብቆ እየወሰደ ይሰጣቸው ነበር፡፡ የዛን ቀን ይህን ማድረግ ስላልተመቸው ተደብቆ ዳቦ ሰረቀ፡፡ በአጋጣሚ ተነቃበት፤ ማምለጥ አልተቻለምና ተያዘ፡፡ ሌባው ራሷን የቀየረች የንጉሱ ልጅ ነበረች፡፡
ወዳጄ፡- “Better bread with water than pie with trouble” ያለንን ታስታውሳለህ?
ሠላም!!

Read 2742 times