Saturday, 09 February 2019 12:11

ኬኬ ኩባንያ ለ“ነህምያ ኦቲዝም ማዕል” ከግማሽ ሚ. ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 በቤት ኪራይ እጦት ችግር ላይ ወድቀን ነበር - ማዕከሉ
                    
     ኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በቤት ኪራይ ችግር ላይ ለነበረው “ነህምያ የኦቲዝም ማዕከል” የ600 ሺህ ብርና የ50 ብርድልብሶች ድጋፍ አደረገ፡፡ የኩባንያው ኃላፊዎች ትላንት ረፋድ ላይ በተለምዶ ጎተራ ኮንዶሚኒየም ተብሎ በሚጠራው አቅራቢያ በሚገኘው የኦቲዝም ማዕከሉ በመገኘት ነው ድጋፉን ያደረጉት፡፡
የኬኬ ኩባንያ የቦርድ ዳይሬክተርና አስፈፃሚ አቶ ቴዎድሮስ ቦጋለና ባልደረቦቻቸው ድጋፉን ካደረጉ በኋላ ማዕከሉን የጎበኙ ሲሆን ማዕከሉ ከሚሰጠው አገልግሎት አንፃር ብዙ ድጋፍ እንዳላገኘ ገልፀው፣ ያደረግነው ድጋፍ ጥቂት ቢሆንም ሌሎችም ባለሀብቶችና መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንዲደግፋቸው ለማነሳሳት ነው ሲሉ አቶ ቴዎድሮስ ገልፀዋል፡፡
የማዕከሉ ዳይሬክተር ወ/ሮ ራሄል በበኩላቸው፤ በቤት ኪራይ ክፍያ ችግር በጭንቀት ላይ በነበርንበት ወቅት ስለደረሱልን እናመሰግናለን ብለዋል፡፡ ማዕከሉ የተመሰረተው የመስራቿ የወ/ሮ ራሄል ነህምያ የተባለ ሁለተኛ ልጃቸው የኦቲዝም ተጠቂ በመሆኑ እርሱን የሚያስተምሩበት ት/ቤት አጥተው መቸገራቸውን ተከትሎ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ማዕከሉ 60 ልጆችን እየረዳ መሆኑንና ለመመዝገብ የሚጠባበቁ ልጆች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
መንግስትና ባለሀብቶች ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው የጠየቁት መስራቿ፤ በቀጣይ በአዲስ አበባም ሆነ በክልል ቅርንጫፎችን በመክፈት በኦቲዝም ተጠቂ ምክንያት ከመገለል ጀምሮ መከራ የሚያዩ እናቶችን ለማገዝ ፍላጎት እንዳላቸው ወ/ሮ ራሄል ገልፀዋል፡፡
የኬኬ ኩባንያ ኃላፊዎችም ማዕከሉን መንግስትና ባለሀብቶች እንዲደግፉት ጥሪ አቅርበው፤ በቀጣይ ማዕከሉን ለመደገፍ ሃሳብ እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡ ኬኬ ኩባንያና የኩባንያው ባለቤት አቶ ከተማ ከበደ ከዚህ ቀደም ለተለያዩ ሃገራዊ ጉዳዮችና ለህሙማን ድጋፍ በማድረግ የሚታወቁ ሲሆን ከነዚህም መካከል ለእንቦጭ አረም 15 ሚ. ብርና 5 ሚ. የሚያወጣ ኤክስካቫተር፣ ከኦሮሚያ ለተፈናቀሉ ወገኖች የ15 ሚ. ብር፣ በዘውዲቱ ሆስፒታል ውስጥ ለሚገኘው ለኩላሊት ህሙማን እጥበት በጎ አድራጎት ማዕከል 5 ሚ.፣ ለአርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያም ህክምና 1 ሚ. ብር እና ሌሎችም በርካታ ድጋፎች ሲያደርጉ መቆየታቸው የሚታወስ ነው፡፡

Read 485 times