Saturday, 09 February 2019 12:12

የአልኮል መጠጦችን በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ማስተዋወቅ ከ3 ወራት በኋላ ይቆማል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(4 votes)

 - ህጉ የቢራ ፋብሪካዎችንና የሚዲያ ተቋማትን በእጅጉ የሚጐዳ ነው ተብሏል
    - ውሣኔው ለአገሩና ለዜጐቹ የሚቆረቆር መንግስት መምጣቱን አመላካች ነው - አስተያየት ሰጪዎች
           
    በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች ወጣቶችና የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና የንግድና ኢንዱስትሪ ቋሚ ኮሚቴዎች፤ ከፍተኛ ክርክርና ውይይት አድርገውበት፣ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡትን የውሣኔ ሃሳብ መነሻ በማድረግ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የአልኮል መጠጦችን በሬዲዮና በቴሌቪዥን ማስተዋወቅ ሙሉ በሙሉ የሚከለክለውን ህግ አፀደቀ፡፡ ህጉ ከሶስት ወራት በኋላ ተፈፃሚ እንደሚሆንም ተገልጿል፡፡
ከትናንት በስቲያ በምክር ቤቱ ያፀደቀውና ከ3 ወራት በኋላ ተግባራዊ መሆን ይጀምራል የተባለው ህግ፤ ማንኛውም የአልኮል መጠጦችን በሬዲዮና በቴሌቪዥን ማስተዋወቅና የአልኮል መጠጦችን ከሎተሪ እጣ ወይንም ከሽልማት ጋር ማያያዝ እንዲሁም የአልኮል መጠጦች ማስታወቂያ በቢል ቦርድ ማስተዋወቅን ጭምር የሚከለክል ነው፡፡
በኢትዮጵያ የምግብና የመድሃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን፣ ከሳምንታት በፊት በምክር ቤቱ የሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና የንግድና ኢንዱስትሪ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ተወያይተውበት፣ የውሳኔ ሃሳባቸውን ለምክር ቤቱ እንዲያቀርቡ በሚል ተመርቶ ነበር፡፡ በዚሁ መሰረትም፤ ሁለቱ ቋሚ ኮሚቴዎች በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለ ውይይትና ክርክር ካደረጉ በኋላ፣ የአልኮል መጠጦች ማስታወቂያዎች በሬዲዮና በቴሌቪዥን ከምሽቱ 5 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት እንዲተላለፍ የሚለው የአንደኛው ቋሚ ኮሚቴ ሃሳብ ሆኖ ሲቀርብ፣ የአልኮል መጠጦች በሬዲዮና ቴሌቪዥን ፈጽሞ መተዋወቅ የለባቸውም የሚለው ደግሞ የሌላኛው ቋሚ ኮሚቴ ሃሳብ ሆኖ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱ ሁለቱንም የውሣኔ ሃሳቦች ተቀብሎ ውይይትና ምክክር ካደረገና በጉዳዩ ላይ የምክር ቤቱን አባላት ሃሳብ ካዳመጠ በኋላ፣ የአልኮል መጠጦች ማስታወቂያ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ፈጽሞ መተላለፍ የለበትም የሚለውን ሃሳብ ተቀብሎ አጽድቋል፡፡
በአልኮል አምራች ፋብሪካዎችና በሚዲያ ተቋማት መካከል የተፈረሙ የረጅም ጊዜ የማስታወቂያ ውሎችና ስምምነቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ፣ የሶስት ወራት የእፎይታ ጊዜ በመስጠት፣ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ ተቋማቱ ከፋብሪካዎቹ ጋር ያላቸውን ውል አጠናቀው እንዲጨርሱና ከ3 ወራት በኋላ ግን የአልኮል መጠጦች ማስታወቂያዎችን በብሮድካስት ሚዲያዎች ማስተላለፍ የማይችሉ መሆኑ ተደንግጓል፡፡
አዋጁ አላማው አድርጐ የተነሳው የህብረተሰቡን ጤና፣ የህፃናትን አስተዳደግና ደህንነት መጠበቅን ነው፡፡ ከዚህም አኳያ ቅድሚያ ሊሰጠው ለሚገባው ጉዳይ ቅድሚያ ተሰጥቷል ያሉት በኢትዮጵያ የምግብና የመድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የጤና ህግ አማካሪው አቶ ደረጀ ሽመልስ፤ አዋጁ ጥቅማቸውን ሊነካ ይችላል ተብሎ ለሚታሰቡ ወገኖች መንግስት ሌሎች አማራጮችን ማየት እንደሚቻልና በዚህ ዙሪያም እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በቢራ ፋብሪካዎች ላይ ህልውናቸውን የመሰረቱ አንዳንድ የሚዲያ ተቋማት በዚህ አዋጅ ጥቅማቸው መነካቱ የማይቀር ቢሆንም፣ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ግን የሚዲያ ተቋማቱ ገቢ መቀነስ ሳይሆን የህብረተሰቡ ጤናና ደህንነት መጠበቅ ነው ብለዋል፡፡
አያይዘውም በሚዲያ ተቋማቱ ላይ የሚደርሰውን የገቢ ማነስ ጫና ለመቀነስ ታስቦ እየተሰራ እንደሆነና የመንግስት ተቋማት፣ የግል ሚዲያዎችን በማስታወቂያዎችና በስፖንሰርሺፕ ድጋፍ የሚያደርጉበትን ሁኔታ ለማስፋት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
አዲሱ አዋጅ በፋብሪካችሁ ላይ ምን ጉዳት ያስከትላል ስንል ጥያቄ ያቀረብንላቸውና ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ የሥራ ኃላፊ እንደተናገሩት፤ “መንግስት ይህንን ህግ ሲያወጣ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ቀላል አይደለም፤ የቢራው ኢንቨስትመንት ዘርፍ የማይደግፈውና አሻራውን ያላሳረፈበት የአገር ኢኮኖሚ የለም፡፡ ህጉ ሲወጣ ይህ ሁሉ ነገር አብሮ ገደል ይገባል፡፡ እናም በደንብ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ህጉ በአገር ኢንቨስትመንትና በዜጐች የሥራ ዕድል ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ያሳድራል” የሚል እምነት አለኝ ብለዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡን አቶ ቴዎድሮስ አንተነህ የተባሉ የማስታወቂያ ባለሙያ በበኩላቸው፤ አዋጁ የቢራ ፋብሪካዎቹ በአገር ኢኮኖሚ ላይ እያበረከቱት ያለውን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገራችን በስፋት እየተንቀሳቀሱ ያሉት አምስት የቢራ ፋብሪካዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ፋብሪካዎች ከአስር ሺ የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን የስራ ዕድል የፈጠሩ ናቸው፡፡ ፋብሪካዎቹ ስራቸውን እየሰሩ ለመቀጠልና በአገር ኢኮኖሚ ላይ እያበረከቱት ያለውን አስተዋፅኦ እንዲቀጥሉ ለማድረግ የግድ ማስታወቂያዎችን ማስነገርና ምርቶቻቸውን መሸጥ ይኖርባቸዋል፡፡ አሁን ይህ እንዳይደረግ ከታገደ ግን በምን መልኩ ተንቀሳቅሰው ምርታቸውን እንደሚሸጡና ስራቸውን መቀጠል እንደሚችሉ አላውቅም፡፡ መንግስት ውሳኔውን በሚገባ አጢኖ ያሻሽለዋል የሚል እምነት አለኝ ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ መምህር የሆኑት አቶ ሰለሞን ገረመው በሰጡት አስተያየት፤ ከዚህ ቀደም በዚህ ጉዳይ ላይ ለዓመታት ጩኸታችንን ብናሰማም ሰሚ ማግኘት አልቻልንም ነበር፡፡ ሆነ ተብሎ ትውልዱን ለማጥፋትና ለምን የሞል ጠያቂ ትውልድ እንዳይፈጠር አደንዝዞ ለማስቀረት ሆን ተብሎ የተደረገ ጉዳይ ነው፤ ዛሬ ልጆቻችን 18 ዓመታቸውን በጉጉት የሚጠብቁት ትምህርታቸውን በየዩኒቨርሲቲዎች ለመቀጠልና የተሻለ ሰው ለመሆን ሳይሆን ቢራ ለመጠጣት ሆኗል፡፡ ይህንን የፈጠሩብን ደግሞ በየቴሌቪዥኑና በየሬዲዮው የሚተላለፉት ማስታወቂያዎች ናቸው፡፡ እኔ ይህ ህግ እንደውም ከጊዜው በጣም የዘገየና በአስቸኳይ ተግባራዊ ሊሆን የሚገባው ህግ ነው የሚል እምነት አለኝ፤ ይህ ውሳኔ አገሪቱ ለዜጎቿ የሚቆረቆርና ትውልድን የሚታደግ መሪ ማግኘቷን የሚያመለክት አዋጅ ነው ብለዋል፡፡
የሚዲያ ተቋማቱ በቀጣዮቹ 3 ወራት ከፋብሪካዎቹ ጋር ያላቸውን ስምምነትና ውል እንዲያጠናቅቁ ትዕዛዝ የተሰጠ ሲሆን በአዋጁ አፈፃፀም ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርቡ ውይይት እንደሚደረግም ታውቋል፡፡ 

Read 1126 times