Saturday, 09 February 2019 12:17

ፖለቲከኞች እና ምሁራን በተጀመረው “ብሔራዊ ውይይት” ተስፋ ሰንቀዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)


     በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት በሃገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የፖለቲካ ልሂቃን፣ የሲቪክ ተቋማትና ፖለቲከኞች መካከል የተጀመረው “ብሔራዊ ውይይት” (National Dialogue) የሃገሪቱን የፖለቲካ ስርአትና የዲሞክራሲ ይዞታ ያሻሽላል የሚል ተስፋ መሰነቃቸውን ፖለቲከኞች እና ምሁራን ገለፁ፡፡
የተጀመረው ብሔራዊ ውይይት ለረጅም አመታት እንዲፈጠር ሲጠየቅ የነበረ መሆኑን የገለፁት በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ፖለቲከኞች እና ምሁራን እንዲህ ያለው ውይይት በሃገሪቱ ከጉልበት ይልቅ ሃሳብ የገዥነቱን ቦታ እንዲያገኝ እንዲሁም የሃሳብ ገበያ በሁሉም ማህበረሰብ ውስጥ እንዲንሸራሸር በማድረግ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
ይህ “የብሔራዊ ውይይት” መድረክ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት መጀመሩና ቁርጠኝነታቸውን ለማሳየት የውይይቱ አካል መሆናቸው በሃገሪቱ በተጀመረው የሃሳብ ገበያን የማስፋትና ዲሞክራሲን የማጎልበት ሂደት በእጅጉ ተስፋ እንዲሰንቁ እንዳደረጋቸውም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡
በዚህ የውይይት መድረክ ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የተወከሉ፣ ከሲቪክ ተቋማት የተውጣጡ እንዲሁም በተለያየ መድረክ ሃሳባቸውን ሲገልፁ የቆዩ የፖለቲካ ልሂቃንን ጨምሮ 8 መቶ ያህል ተሳታፊዎች ተገኝተው እንደነበር የሚገልፁት የመድረኩ አመቻችና አስተናባሪ የሆኑት አቶ የሸዋስ አሰፋ ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ የሃገሪቱ መሪ እና ሌሎች ፖለቲከኞች ስለሃገራቸው የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ያላቸው ምልከታ ጎልቶ የወጣበት መድረክ እንደነበር ይገልፃሉ፡፡
በዋናነት በሃገሪቱ የውይይት ባህልን ለማዳበር እና የሃሳብ የበላይነት በሃገሪቱ እንዲያብብ የተጀመረው ብሔራዊ ውይይት በእጅጉ ጠቃሚ መሆኑን የሚጠቅሱት አቶ የሸዋስ የሰለጠነና ዘመናዊ የፖለቲካ ስርአት ለመገንባትም ይህ ዓይነቱ ውይይት መጎልበት አለበት ይላሉ፡፡
በእለቱ ጠ/ሚኒስትሩ እንደ አንድ የፖለቲካ ሰው ብቻ ሆነው ለውይይት መቀመጣቸው በዚህ ሃገር ፖለቲካ ውስጥ ትርጉሙ ብዙ ነው የሚሉት የዩኒቨርሲቲ መምህርና የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ስዩም ተሾመ በበኩላቸው በአቻነት ተቀምጦ የሃሳብ የበላይነትን የማንገስ ባህል እንዲሰፍን ጠ/ሚኒስትሩ ያላቸውን ቁርጠኝነት አመላካች ነው ይላሉ፡፡
ትናንት ፀረ ሰላም፣ አሸባሪ፣ ተላላኪ ሲባሉ የነበሩ ኃይሎች በሙሉ በአንድ መድረክ ተሰባስበው ሃሳብ መለዋወጣቸውና ያላቸውን ሃሳብ በእኩል መግለፃቸውም በበላይነትና በበታችነት የጉልበት አስተሳሰብ ተወጥሮ ለቆየው የሃገሪቱ ፖለቲካ አዲስ ባህል ነው ይላሉ አቶ ስዩም፡፡
በሃሳብ የበላይነት ላይ የተገነባ የፖለቲካ ስርአት ለመፍጠር እንዲህ ያለው መድረክ በእጅጉ ጠቃሚ ነው የሚሉት አቶ ስዩም ከጉልበት የበላይነት ወደ ሃሳብ የበላይነት ፖለቲካ ለመሸጋገርም አዎንታዊ ጅምር አድርጌ እመለከተዋለሁ ብለዋል፡፡ መድረኩ ሊለመድና ሊሰፋ የሚገባ እንደሆነም አስገንዝበዋል አቶ ስዩም፡፡
ይህን የአቶ ስዩምን ሃሳብ የሚጋሩት የመኢአድ ፕሬዚዳንት ዶ/ር በዛብህ ደምሴ በበኩላቸው ብሔራዊ ውይይት ለዘመናት ስንጠይቀው የነበረ ነው ብለዋል፡፡ መድረኩ በቀጣይ ሰፍቶ ሁሉን አካታች በመሆን የሃገሪቱን ፖለቲካ ከጉልበትና ኃይል ወደ ሃሳብ የበላይነት እንዲወርድ ማድረግ ያስፈልጋል ይላሉ ዶ/ር በዛብህ፡፡
በተጀመረው ብሔራዊ ውይይት በእጅጉ ተስፋ መሰነቃቸውን የገለፁት ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው መድረኩ ፓርቲዎች ያለንን ፖሊሲ የምንገመግምበት ሳይሆን ስለሃገሪቱ የፖለቲካ ስርአት መሻሻልና የዲሞክራሲ ግንባታ ያለውን ሃቅ የማስቀመጥ ጉዳይ በመሆኑ ሃገራዊ መግባባትንም ለመፍጠር አጋዥ ነው ይላሉ፡፡
ይህ ውይይት ቀጣይነት እንዲኖረው የመገናኛ ብዙኃን ክትትል አስፈላጊ ነው የሚሉት ፕ/ር በየነ ጠ/ሚኒስትሩም ለውይይቱ ቀጣይነት ቁርጠኛ መሆናቸውን ተረድቻለሁ ይላሉ፡፡
“እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ የብሶት ፖለቲካ ነው ሲናኝ የነበረው” ያሉት ፕ/ር በየነ የመበዳደል፣ የመጠቃቃት እንጂ ሃሳብን የመሞገት ፖለቲካ አልነበረም፤ አሁን የውይይት ፖለቲካ ተጀምሯል ባይ ናቸው፡፡
ከብሶት ፖለቲካ ወደ መርህ፣ አላማ እና ርዕዮት አለምን መሰረት ያደረገ ፖለቲካ እንድንሸጋገር የተጀመረው የብሔራዊ ውይይት ጠቀሜታው የላቀ ነው ይላሉ ፕ/ር በየነ፡፡
በዚህ የሃገሪቱን የፖለቲካ ባህል ይለውጣል፣ ያሻሽላል ተብሎ ተስፋ በተሰነቀበት መድረክ ላይ ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ “የዲሞክራሲ ባህል በኢትዮጵያ”፣ የቀድሞ የህውሓት መስራች ዶ/ር አረጋዊ በርሄ “በዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ የብሄርተኝነትና ሃይማኖኝነት ሚና”፣ ፕ/ር መረራ ጉዲና “የኢትዮጵያ ፌደራል ስርአትና የሚጋጩ ህልሞች” እንዲሁም ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ “ለዘመናዊ የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ የፓርቲዎችና መገናኛ ብዙኃን ሚና” የሚል የውይይት መነሻ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ለ20 ደቂቃዎች ያህል ባቀረቡት የውይይት መነሻ ፅሁፋቸው በዋናነት በዓለም፣ በአፍሪካ እና በኢትዮጵያ ዲሞክራሲን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ዳሰዋል፡፡
በዚህ ምልከታቸው እስካሁን ተሳክቶለት ፍፁም ዲሞክራሲን በዓለም የገነባ ሃገር እንደሌለም ዶ/ር ዐቢይ ጥናቶችንና አስረጅዎችን በመጥቀስ አስረድተዋል፡፡
“ሃገሮች ዲሞክራሲን ይሻሉ እንጂ አንዳቸውም እንዳሰቡት ተግባራዊ ማድረግ አልቻሉም” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ “ኢትዮጵያ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ የምትዋልል ሃገር ነች” ብለዋል፡፡
ፖለቲከኞቿም ላለፉት 50 ዓመታት ዲሞክራሲን እኔ በተሻለአሰፍናለሁ እያሉ እርስ በእርስ ሲቋሰሉ መኖራቸውን ጠ/ሚኒስትሩ አውስተዋል፡፡
አሁንም ኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ወደ ኋላ የቀረባት በመሆኑ ባህሉን በህብረተሰቡ ላይ መገንባት ቀዳሚው ተግባር መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው ከ30 ዓመት በፊት አባል የነበሩበት ህውሓት ወደ ጫካ የገባው የብሔሮችን እኩልነት የምታስተናግድ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመመስረት የሚያስችል ስትራቴጂ ነድፎ እንደነበር አስታውሰው በኋላ ግን ስትራቴጂው ሙሉ ለሙሉ ተቀልብሶ ፀረ ዲሞክራሲያዊ የሆነ ስርአት መገንባቱን ማሳያዎችን በመጥቀስ አስረድተዋል፡፡
ባለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት ብዙኃንን ካገለሉ ጥቂቶችን ከፍ ካደረጉ ስርአቶች ሃገሪቱ መላቀቅ ባለመቻሏም አሁንም የህዝቡ መከራ ተራዝሟል ባይ ናቸው ዶ/ር አረጋዊ፡፡
በሃገሪቱ ለህዝብ ተስማሚ የሆነ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለመገንባት ወሳኙ ጉዳይ ግለሰቦች ሳይሆኑ ህግ የበላይ የሚሆንበትን ተቋማዊ ስርአት ማዋቀር ወሳኝ መሆኑንም ዶ/ር አረጋዊ ጠቁመዋል፡፡
“ዲሞክራሲያዊ ስርአት ማለት በመጀመሪያ የህዝብን ሉአላዊ የስልጣን ባለቤትነት ማስከበር ነው” ያሉት ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው “ህዝብ የሉአላዊ ስልጣን ባለቤት የሚሆነው ደግሞ ምንም አይነት ጫና፣ ማስፈራራት ሳይደረግበት የሚፈልገውን መምረጥ ሲችል ነው” በማለት የቀጣዩ ምርጫ በዚህ መርህ ለሃገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
አንድ የተመረጠ መንግስት አደራ የሰጠውን ህዝብ መብት በስልጣን ዘመኑ መሃል ማክበርና ማስከበር ሲሳነው እንደገና በህግ ማፍረስ የሚቻልበት ስርአት ማበጀትም ለዲሞክራሲ ግንባታ ጠቀሜታ የጎላ ነው ብለዋል፡፡
አሁን ያለው የፌደራል አወቃቀርን ለማፈራረስ መሞከር አደገኛ መሆኑን ያወሱት ፕ/ር መረራ ጉዲና በበኩላቸው ያለውን የፌደራል ስርአት አወቃቀር ስልት የበለጠ ዲሞክራሲዊ ማድረጉ የሃገሪቱን ቀጣይ ህልውና የበለጠ ለማጠናከር ይረዳል የሚል ምልከታቸውን በመድረኩ አጋርተዋል፡፡
ይህን መሰሉ ምሁራንና ፖለቲከኞች ስለ ዲሞክራሲና ስለ አገሪቱ የፖለቲካ ስርአት የሚመክሩበት “ብሔራዊ ውይይት መድረክ ቀጣይነት እንዳለው የገለፁት ከአዘጋጆቹና አስተናባሪዎቹ አንዱ የሆኑት አቶ የሺዋስ አሁን ከአንጋፋዎቹ ይጀመር ብለን ነው በቀጣይ ወጣቶችም ምልከታቸውን እንዲያጋሩ ይደረጋል ብለዋል፡፡      

Read 5902 times