Saturday, 09 February 2019 12:18

ለፖለቲካ ፓርቲዎች የቀረበው የቃል ኪዳን ሰነድ አወዛጋቢ ሆኗል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

 ‹‹ከዚህ በፊት በማናውቀው ሰነድ ላይ እንድንወያይ ተደርገናል” - የፖለቲካ ድርጅቶች

     በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚኖረውን ግንኙነት እና በተናጠል የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች የሚገዛ የአሠራር የቃል ኪዳን ሰነድ በምርጫ ቦርድ በኩል ለፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት የቀረበ ቢሆንም ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም በማናውቀው ሰነድ ላይ ነው እንድንወያይ የተደረገው ብለዋል፤ ውይይቱም ያለ ስምምነት በይደር ለሌላ ጊዜ ተላልፏል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ የአገርን ብሔራዊ ደህንነት፣ የዜጐችን ነፃነትና መሠረታዊ መብት ባከበረ መልኩ እንዲንቀሳቀሱ ለማስቻል ሰነዱ መዘጋጀቱ በምርጫ ቦርድ በኩል ተገልጿል፡፡
ይሁን እንጂ የፖለቲካ ድርጅቶች በእለቱ ለውይይት የተጠሩት ለተጀመረው ሃገራዊ ድርድር እና ውይይት እንደነበር ነገር ግን ከዚህ ቀደም በማያውቁት “የቃል ኪዳን” ሰነድ ላይ እንዲወያዩ መደረጋቸውን በውይይቱ የተሳተፉ ፖለቲከኞች ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
በዚህም በውይይቱ ወቅት በርካታ አለመግባባቶች መፈጠራቸውንና ውይይቱ በስርአቱ ባለመመራቱ በይደር የካቲት 15 ቀን መተላለፉን ከተሣታፊዎቹ አንዱ የሆኑት የመኢአድ ም/ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ አመልክተዋል፡፡
ሰነዱ ከየት መጣ? የፓርቲዎች ስነስርአት አዋጅ በ2002 የወጣውን የሚሽር ነው? አገልግሎቱ ምንድን ነው? ቀድሞስ እንዲህ ያለ ሰነድ እየተዘጋጀ ስለመሆኑ ለምን መረጃ አልተሰጠንም? ለምን በድንገት እንድንወያይ ተደረገ? የሚሉ በርካታ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡
ወደ ውይይቱ ከተገባ በኋላም ሰነዱ ላይ የተመለከቱ ጉዳዮች በእጅጉ ሲያወዛግቡ የነበረ ሲሆን፤ በኋላም ጊዜ ባለመብቃቱ ጉዳዩ በይደር እንዲቆይ ተወስኖ ስብሰባው አብቅቷል፡፡
ሰነዱ የቃልኪዳን ሰነድ ተብሎ እንደሚጠራ የሰነዱ አላማም በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ አመራሮቻቸውና አባሎቻቸው በሚያደርጉት እንቅስቃሴ በማገዝ በሃገሪቱ የተጀመረውን የዲሞክራሲ ስርአት ማጠናከር፣ በፓርቲዎች መሃል ሊነሳ የሚችልን አለመግባባት በጋራ ውይይት መፍታት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
ጠንካራ የመድብለ ፓርቲ ስርአት ለመመስረት የሚደረገውን ጥረትም የቃል ኪዳን ሰነዱ ያግዛል ተብሏል፡፡
ፓርቲዎች በሀገራዊ ስሜትና ፍቅር የመንቀሳቀስ፣ የስልጣን ገደብን የማክበር ግዴታንም በፓርቲዎች ላይ ይጥላል ሰነዱ፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በማናቸውም መልኩ ከሚገለፁ የሃይል አሠራሮች፣ ከሁከትና ከአመፃ ድርጊቶች እንዲጠበቁ የሚደነግገው ሰነዱ ሃይል የመጠቀም ስልጣን የመንግስት ብቻ መሆኑን በመጠቆም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ለዚህ መርህ ተገዥ መሆን እንዳለባቸው ያትታል፡፡
ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የመንቀሳቀስ፣ አመለካከታቸውን፣ የፖለቲካ አላማቸውን፣ ሃሳባቸውንና መርሆዋቸውን የማስተዋወቅ፣ አባላትን የመመልመል፣ ጽ/ቤቶች የመክፈት ሙሉ ነፃነት ይኖራቸዋል ለዚህም መንግስት አስፈላጊውን ጥበቃ ያደርጋል የሚለውም ከድንጋጌዎቹ ተጠቃሽ ነው፡፡
ፓርቲዎች የፖለቲካ አላማቸውን ሲያራምዱ ህብረተሰቡን ለጠብ ሊያነሳሱ የሚችሉ በዘር፣ በብሔር፣ በጐሣ፣ በሃይማኖት ላይ የተመሠረቱ ድርጊቶችን መፈፀም የመቆጠብ ግዴታ እንዳለባቸው በቃል ኪዳን ሰነዱ ተመልክቷል፡፡
በፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ በደጋፊዎቻቸው ባለቤትነት የሚተዳደሩ ማህበራዊ ሚዲያ ገፆች፣ ድረ ገፆች እና የህትመት ውጤቶች፣ የማህበራዊ ሚዲያ ድረገፆች በተመሳሳይ እሴቶች እንዲቃኙ እንዲሁም ማህበረሰባዊ ጥላቻን፣ መቃቃርን፣ አመፃን፣ መለያየትን እና ህገወጥ ድርጊቶችን የማደፋፈር ውጤት ያላቸው መልዕክቶች ከማስተናገድ የመቆጠብ ሃላፊነት እንዳለባቸውም ተመልክቷል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች በራሣቸው የሚያስተዳድሯቸውን ድረ ገፆች በዝርዝር ለህዝብ ይፋ እንዲያደርጉም ያስገድዳል ሰነዱ፡፡
የፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት እንደሚመሠረትም ሰነዱ ያትታል፡፡ ም/ቤቱም እያንዳንዱ ፓርቲ በአንድ ወንበር (አንድ ድምፅ) እንዲወከል ይደነግጋል፡፡ በየ6ወሩም የጋራ ም/ቤቱ ሰብሳቢ እና ፀሐፊ እየተለዋወጠ ይመርጣል፡፡ የጋራ ም/ቤቱ ጽ/ቤት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሚሰጠው ቦታ ይሆናል ይላል ሰነዱ፡፡
ም/ቤቱ በዋናነት በፓርቲዎች መካከል የሚፈጠርና አለመግባባት የመፍታት አላማ ይኖረዋል፡፡ ችግሮች የሚፈቱበትን ስልትም አያይዞ ሰነዱ አመልክቷል፡፡ ስህተት የፈፀሙም የሚቀጡበት አግባብ በሰነዱ ተዘርዝሯል፡፡   

Read 7315 times