Saturday, 09 February 2019 12:34

‘በአየር ላይ የሚፈለፈል እንቁላል’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)


          “--ግለሰቦች እስከ ጥግ እንዋሻለን፣ ባለስልጣናት እንክት አድርገው ይዋሻሉ፣ ባለሀብቶች ለነገ ሳያስተርፉ ጥግ ድረስ ይዋሻሉ፣ ተቋማት የመዝገብ ቁጥር በተሰጠው መልኩ ይዋሻሉ… በኃይማኖት ስም የሚመጡትም ዲያብሎስን በቅናት በሚያንጨረጭር መልኩ በጥቅስ አሳምረው ይዋሻሉ፡፡--”
     
    እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሁለት ሰዎች በየአገሮቻቸው ስላሉ ትያትር ቤቶች ግዙፍነት ጉራ እየተነዛዙ ነው፡፡
“እኛ አገር ያለው ትያትር ቤት ግዙፍ ከመሆኑ የተነሳ እግር ኳስ ግጥሚያ እንኳን ሊካሄድበት ይችላል፣” ይላል አንዱ፡፡
ሁለተኛው ሰው ምን ቢል ጥሩ ነው… “እኛ አገር ያለው ትያትር ቤት ግዙፍ ከመሆኑ የተነሳ መጨረሻ ወንበር ላይ የተቀመጠ ሰው እንቁላል ቢወረወር፣ እንቁላሉ መድረክ ከመድረሱ በፊት አየር ላይ ይፈለፈላል፡፡” (ከዋሹ አይቀር እንዲህ ጥግ ድረስ መሄድ ነው፡፡ እኔ የምለው… ከዚህ ሰውዬ ጋር ቡና የተጣጡ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች አሉ እንዴ! ለጠቅላላ እውቀት ያህል ነው፡፡)
እኔ የምለው----ህብረተሳችን ውስጥ አንገት ሲያስደፉ ከነበሩ ባህርያት ዋናው ውሸት መናገር ነበር፡፡
“እሱ እኮ እንዴት አይነት ውሸታም መሰላችሁ…”
“አንቺ እንዴት ከእሷ ጋር ትገጥሚያለሽ! አገር ያወቃት ውሸታም አይደለችም እንዴ!”
በእንደዚህ አይነት ስሞች ከመጠራት የሚዘገንን ነገር አልነበረም፡፡ የሚዋሽ ሰው በመንደሩና በሥራ ቦታው ሁሉ መጠቋቆሚያ የነበረበት ዘመን እኮ በጣም ሩቅ አይደለም፡፡
አይደለም አገር፣ መንደረተኛው የሚያውቀው ዋሾ መሆን የመጨረሻ ፍርድ ቤት ያልወሰነው ቅጣት ነው፡፡ አሁን ውሸት መናገር ከአርትነት ወደ ሳይንስነት ሊሸገጋር! በቃ እየተዋወቅን ምን እናደርገዋለን…
ለምሳሌ… የሆነ ሰው የስንዴ ዱቄት ፋብሪካ ያቋቁማል፡፡
“ለመሆኑ የስንዴ ዱቄት ፋብሪካ ለማቋቋም ምን አነሳሳዎት?”
“በእውነቱ ህብረተሰቡ ጠዋት ማታ ዳቦ ለመግዛት እንደዛ ተሰልፎ ሳየው ልቤ ይሰበር ነበር፡፡ ታዲያ ምን ማድረግ አለብኝ ብዬ አሰብኩና ይህን ፋብሪካ ለማቋቋም ወሰንኩ።” (ቢጫ መብራት! ዓይን የሚያጭበረብር ቢጫ መብራት!)
“የስንዴ ዱቄት ፋብሪካ አትራፊ ነው ይላሉ?”
“በጭራሽ!…የልፋታችንን እሩብ እንኳን አናገኝም!”
ስሙኛማ...“በህግ አምላክ!” የሚባልበት ዘመን አለፈና ነው እንጂ ወደ ጣቢያው ስልክ ደውሎ “በህግ አምላክ ይሄን ሰው አንድ በሉን!” የሚያሰኝ ነው፡፡ ግን ምን ይደረግ፣ ውሸት ምናልባት… በአፍሪካም፣ በዓለምም አንደኛ በሚያደርገን ፍጥነት ወደ ሳይንስነት እያሳደግነው ነው፡፡ “ጫማ ፋብሪካ ከፍቼ እኮ ኤክስፖርት እያደረግሁ፣ በመንፈቅ ውስጥ ቀጭን ጌታ ሆኜ  ነበር፡፡” (ቀይ መብራት!) እኔ የምለው…እኛ ቤታችን ራታችንን እየጎራረስን ‘ውይይቱን’ ለምንከታተለው አስቡልን አንጂ! አሀ… ስንሳቀቅ ትን ቢለን የማን ያለህ ሊባል ነው! (ይቅርታ ጌታው… ዱቄት ፋብሪካ የከፈቱት ለጫማ ፋብሪካ የሚሆን ፍራንክ ስለሌዎት ነው።)
እዘኑልና! “ህዘብ ስለተቸገረ አረቄ ፋብሪካ አቋቋምን” አይነት ነገር ስትሉ እንደው ለእኛ ለተራዎቹ ዜጎች አስቡልና!
ስሙኝማ…እግረ መንገዴን ፖለቲካ ማውራት እንዲህ እንትና ምግብ ቤት ጮክ ብሎ… “እስቲ አንድ ቋንጣ ፍርፍር፣” እንደ ማለት ‘ቀላል ነገር’ የሆነ ይመስላል፡፡ እኔ የምለው… ስንሸሸው የነበረው ‘የፖለቲካ ወሬ’ ከኋላ ደርሶብን ይያዘን፣ ወይ እኛ አሳደን እንያዘው፣ ገና የሚለይ ነው፡፡
“የዚች አገር ነገር ግራ አይገባችሁም!”
“አቦ፣ አንተ ሰው አትነጅሰን…”
“ስለ አገር ማውራት መነጀስ ነው እንዴ!”
“አቦ ወላ ሀገር፣ ወላ ክፍለ ሀገር የራሳቸው ጉዳይ፣ ድራፍታችንን እንጠጣበት…” ይባልና ዘወር፣ ዘወር ብሎ በሁለት እግሩ የሚሄድ ጂ.ፒ.ኤስ. ምናምን መኖሩን እናጣራ ነበር… አሁን ነገሩ ሁሉ እንዲህ ሊለወጥ፡፡
ድራፍቱ ገና ሳይቀዳ፣ ከወራት በፊት “አቦ፣ አትነጅሰን!” ይል የነበረው ሰው…
“ስማ ፌስቡክ ላይ አየህ?…” ሲል ይጀምራል።
“ምኑን?”
“እመነኝ፤ እዚህ አገር ፖለቲካ የሆነ ያልገባን እየተካሄደ ያለ ጌም አለ…”
“አልገባኝም…”
“እንትና የሚባለው ፖለቲከኛ ትናንት ‘በአብዮቴና በዓይኔ የመጣ ወዮለት’ ምናምን ሲል የነበረው፣ አሁን መልሶ ትናንትን ይኮንናል!” (የዘንድሮ ጂምናስቲካችንን የዓለም አቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ እስካሁን አይቶ እውቅና አለመስጠቱ ለምን እንደሆነ ይጣራልንማ! በዚችም ‘ቀንተውብን ይሆን እንዴ!)
እናላችሁ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… አሪፍ ፖለቲከኛ መሆን በአሪፉ የመዋሸት ጥበብ ነው ምናምን የሚሉት ነገር አለ፡፡  ይቺን ስሙኛማ… አንዱ ፖለቲከኛ ለምረጡኝ ዘመቻ የሆነ መድረክ ላይ ንግግር ሲያደርግ ቆይቶ ረዳቶቹን “ወረቀትና  ብእር አምጡልኝ፣” ይላል። ረዳቶቹም ንግግሩን ከጨረሰ በኋላ ወረቀት ምን እንደሚያደርግለት ይጠይቁታል። ምን ቢል ጥሩ ነው…
“እሠራለሁ ብዬ ቃል የምገባቸውና ከተመረጥኩ በኋላ የማልሠራቸውን ነገሮች ለመዘርዘር፣” አለ አሉ፡፡
አሁን በየመድረኩም፣ በየቴሌቪዥን ቃለ መጠይቁም…ፖለቲከኞችና የፖለቲከኝነት ታርጋ የተለጠፈላቸውን እየሰማን ነው፣ እየሰማንም “ጉድ” እያልን ነው፣ “ጉድ” እያልንም… እንደ ወጣቶቹ “ኸረ ሼም ይያዛችሁ፣” እያልን ነው፡፡
ቀላል ‘ይረግጡታል’ እንዴ!
ግለሰቦች እስከ ጥግ እንዋሻለን፣ ባለስልጣናት እንክት አድርገው ይዋሻሉ፣ ባለሀብቶች ለነገ ሳያስተርፉ ጥግ ድረስ ይዋሻሉ፣ ተቋማት የመዝገብ ቁጥር በተሰጠው መልኩ ይዋሻሉ… በኃይማኖት ስም የሚመጡትም ዲያብሎስን በቅናት በሚያንጨረጭር መልኩ በጥቅስ አሳምረው ይዋሻሉ፡፡ እናላችሁ… “ሰው ካልዋሸ እንዴት መኖር ይችላል!” አይነት ነው፡፡
ይቺን ቀልድ ቢጤ ስሙኝማ… ልጆቹ የሆነች ደስ የምትል ትንሽዬ ውሻ መንገድ ላይ ያገኙና ቤት ይወስዷታል፡፡ ቤተሰቡን ይሰበስቡና በአንድ ነገር ይስማማሉ፡፡
“ከመሀላችን ትልቁን ውሸት የሚናገረው ሰው ውሻዋን የራሱ ያደርጋታል፡፡”
ይሄን ጊዜ አባትየው ቆጣ ይላል፡፡
“ልጆች፣ እንዴት እንዲህ አይነት ነገር ታስባላችሁ! እኔ በበኩሌ በህይወቴ ውሸት የሚባል ነገር ወጥቶኝ አያውቅም፡፡”
አንደኛው ልጅ፤ውሻዋን ለአባቱ እየሰጠው ምን ቢለው ጥሩ ነው… “አባዬ አንተ በዝረራ አሸንፈሀል፡፡”
ስሙኛማ…ዘንድሮ መስሎ ተመሳስሎ ማደር… አለ አይደል… ‘ለሁሉም የማይቀር እዳ’ አይነት እየሆነ ነው፡፡ በእርግጥም ‘መመሳሰሉ’…ጥሬ ስጋ ያስበላል፣ ውስኪ ያስጠጣል፣ ምናልባትም ቤትና መኪና ሁሉ ‘በስጦታ’ ሊያስገኝ ይችላል፡፡ መስሎ ተመሳስሎ ለመኖር ደግሞ በውሸት ጥበብ ሦስተኛ ዲቪዚዮን ሳይሆን… አለ አይደል… ፕሬሚየር ሊግ መግባት ያስፈልጋል፡፡ (በዚች፣ በዚች  እንኳን ብዙዎቻችን አንታማም!
እናላችሁ፣ ‘የህይወት መርህ’ አይነት ነገር እስካደረግነው ድረስ ለ‘ውሸት’ ለማመሳከሪያነት  የሚያገለግል ትንታኔ መስጠት አለብን፡፡ “ካልተዋሸ የሚኖርበት ዘመን ስላልሆነ፣ እውነት ተናግሮ የመሸበት ማደር የሚባል ነገር አይሠራም፡፡ ወይ ዋሽተህ ጠግበህ ታድራለህ፣ ወይ እውነቱን ተናግረህ ባዶ ሆድህ ሲንገጫገጫ ያድርልሀል፣” አይነት ማመሳከሪያ እንስጠውና ይለይልናማ፡፡”     
እናማ…ውሸት የባህሪይ ችግር ሳይሆን የብልጥነት መለኪያ የሆነበት ዘመን ላይ ነን፡፡
ሰውየው ሥራ ለመቀጠር ለቃለ መጠይቅ ቀርቧል፡፡
“እርግጠኛ ነህ፣ እኛ ዘንድ መሥራት ትፈልጋለህ?”
“በጣም ነው የምፈለገው፡፡”
“እሺ፣ ውሸት ተናግረህ ታውቃለህ?”
“አላውቅም ጌታዬ፣ ግን እየሠራሁ ልማረው አችላለሁ፣” አለ አሉ፡፡
እናላችሁ…የዘንድሮ ውሸት በአየር ላይ እንደሚፈለፈለው እንቁላል አይነት እየሆነ ነው… መዋሸት የባህሪይ ችግር ሳይሆን የብልጥነት መለኪያ እየሆነም ነውና!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 8194 times