Saturday, 09 February 2019 12:36

የጋዜጠኛነትና የአክቲቪስትነት መደበላለቅ፤ የ“ዲጂታል ወያኔ” መምጣት

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(4 votes)

 በዚህ ጽሁፍ ትኩረት የማደርገው በጋዜጠኛነት፣ በአክቲቪስትነትና በማህበራዊ ሚዲያ ዙሪያ ይሆናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ ዓርብ ጥር 24 ቀን 2011 ዓ.ም ፓርላማ ቀርበው፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ላቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ውስጥ በነዚሁ ጉዳዮች ዙሪያ ያነሷቸው ነጥቦች ስለነበሩ፣ የእርሳቸውንም ሃሳብ በጽሁፌ ውስጥ አስገብቼ ለማየት እሞክራለሁ፡፡ አስተያየቴን የምጀምረው ግን ስለ ፓርላማ ስብሰባና ስለ ምክር ቤት አባላት አቀማመጥ (በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማው ውስጥ የሚቀመጡበትን ስፍራ መቀያየር በተመለከተ) አንዳንድ ነጥቦችን በማቅረብ ነው፡፡  
ስለ ፓርላማ አቀማመጥ
እንደሚታወቀው በአቶ መለስ ዜናዊ የስልጣን ዘመን፣ በፓርላማው ውስጥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መቀመጫ (ከአፈ ጉባዔው አቅጣጫ ሆኖ ሲታይ) ከአዳራሹ የመሐል አካፋይ መተላለፊያ በስተግራ፣ ሁለተኛው ረድፍ ላይ የመጀመሪያዋ መቀመጫ ላይ ነበር፡፡ አቶ መለስ እስከ ህይወታቸው ፍጻሜ እዚያች ቦታ ላይ ተቀምጠው ሪፖርት ያቀርቡ ነበር፣ ለጥያቄዎች መልስ ይሰጡ ነበር፡፡ አቶ መለስ በየትኛውም የስብሰባ ሂደት ከአፈ ጉባዔው ጎን ተቀምጠው አያውቁም፡፡
አቶ ኃ/ማርያም ወደ ስልጣን ሲመጡ (በተለይም ከ2007 ምርጫ በኋላ) አቶ መለስ ይቀመጡበት የነበረው የጠቅላይ ሚኒስትሩ መቀመጫ ተቀየረና ከመሐል አካፋይ መተላለፊያ በስተቀኝ፣ ሁለተኛው ረድፍ የመጀመሪያው መቀመጫ ላይ (አቶ መለስ ይቀመጡበት ከነበረው በተቃራኒ ትይዩ) እንዲሆን ተደረገ፡፡ የመቀመጫ ለውጡ ለምን እንደተደረገ ባይገባኝም፣ በግራና በቀኝ ከመሆኑ በስተቀር በሁለቱ መቀመጫዎች መካከል ልዩነት የለም፡፡ አቶ ኃ/ማርያምም እንዲሀ ስልጣናቸውን እስከለቀቁበት እለት ድረስ የተመደበላቸው መቀመጫ ላይ ሆነው ሪፖርት ያቀርቡ ነበር፣ ለጥያቄዎች መልስ ይሰጡ ነበር፡፡ አቶ ኃ/ማርያም በየትኛውም የስብሰባ ሂደት ከአፈ ጉባዔው ጎን ተቀምጠው አያውቁም፡፡
እዚህ ላይ መነሳት የሚገባው ጥያቄ፣ “የፓርላማ አባላት የመቀመጫ ድልድል የሚደረገው በማን ነው?” የሚል መሆን እንዳለበት አስባለሁ፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሰራርና የአባላት የስነ ምግባር ደንብ ቁጥር 6/2008፣ አንቀጽ 20 “የአባላት የስብሰባና የአቀማመጥ ፕሮቶኮል” በሚለው ርእስ ስር በንዑስ አንቀጽ 5 ላይ፤ “የምክር ቤቱ ስብሰባ በሚካሄድበት አዳራሽ ውስጥ የአባላት … አቀማመጥ የሚመለከታቸውን በማማከር በአፈ ጉባዔው ይወሰናል” ይላል፡፡ ንዑስ አንቀጽ 6 ደግሞ “ማንኛውም አባል … በስብሰባው ሂደት ከመቀመጫው ውጪ መቀመጥ የለበትም” ይላል፡፡
በአቶ መለስም ይሁን በአቶ ኃ/ማሪያም ዘመን ከአፈ ጉባዔው ጎን የሚቀመጡት የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር ዓመታዊ የህግ አወጣጥ መርሐ-ግብር የሚገልጹበትን የመክፈቻ ንግግር ለማድረግ በሚመጡበት ወቅት ከሁለቱ ምክር ቤቶች አፈ ጉባዔዎች መሀል ይቀመጣሉ። ሌሎች ሚንስትሮች ሪፖርት ለማቅረብ ወደ ፓርላማ በሚመጡበት ጊዜም እንዲሁ ሪፖርት አቅራቢው ሚንስትር ከአፈ ጉባዔው በስተቀኝ በኩል፣ ሪፖርት አቅራቢውን መስሪያ ቤት የሚከታተለው ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ከአፈ ጉባዔው በስተግራ በኩል ይቀመጣሉ፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ በየትኛውም የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ወደ ፓርላማ ሲመጡ የሚቀመጡት መደበኛ መቀመጫቸው ላይ ነው፡፡ እዚያ ሆነው ሪፖርት ያቀርባሉ፣ እዚያ ሆነው ጥያቄ ይመልሳሉ፡፡
ዶ/ር ዓብይ ስልጣን እንደያዙ መቀመጫቸው ቀደም ሲል አቶ ኃ/ማርያም ይጠቀሙበት በነበረው መቀመጫ ላይ ነበር፡፡ ቆየት ብሎ አቶ መለስ ይቀመጡበት ወደነበረው ተቀየረ። አቶ ዓብይን ለየት የሚያደርጋቸው ሪፖርት ሲያቀርቡም፣ የፓርላማ አባላት ላቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ለመስጠትም፣ ከአፈ ጉባዔው ጎን በቀኝ በኩል መቀመጣቸው ነው። ይሄ ፕሮቶኮል በኢትዮጵያ ፓርላማ የተለመደ አሰራር አልነበረም፡፡
ይህ አቀማመጥ ትክክል ነው አይደለም የሚለው ሃሳብ አካራካሪ ሊሆን ይችላል። የተለያዩ ሀገሮች ፓርላማዎች እንዳላቸው የአዳራሽ ዓይነት የምክር ቤቱ አባላትም ይሁን የጠቅላይ ሚኒስትሩ መቀመጫ የተለያየ ስፍራ ላይ ይሰየማል፡፡ ለምሳሌ፤ የእንግሊዝ ፓርላማ አፈ ጉባዔ መሀል ላይ ሆነው ተቃዋሚዎችና የገዢው ፓርቲ አባላት ግራና ቀኝ፣ ፊት ለፊት ተፋጠው ይቀመጣሉ፡፡ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትርና ተቃዋሚያቸው ቆመው የሚናገሩባቸው ሳጥኖችም አሏቸው፡፡
በአንዳንድ ሀገሮች የፓርላማ መቀመጫው ዲዛይን ግምሽ ጨረቃ ቅርጽ አለው፡፡ በአንዳንድ ሀገሮች ደግሞ የአፈ ጉባዔው መቀመጫ መሀል ላይ ሆኖ ሌሎች የምክር ቤት አባላት በግምሽ ክብ ቅርጽ ይቀመጣሉ፡፡ የተቃዋሚና የገዢ ፓርቲ አባላት እንደ ቁጥራቸው ብዛት ለየብቻ እንዲቀመጡ ማድረግ በብዙ ሀገሮች የለመደ አሰራር ነው፡፡
ከዚህ ቀጥሎ ባስቀመጥኩት መስፈንጠሪያ (ሊንክ) ተሸግራችሁ በምታገኙት ዌብሳይት ላይ (https://hyperallergic.com/387883/the-outdated-architecture-of-parliaments-around-the-world/) የተለያዩ ሀገሮች ያላቸውን የምክር ቤት መቀመጫ ዲዛይን መመልከት ይቻላል፡፡ ከሌሎች ሀገሮች ዲዛይን ጋር ሲተያይ የእኛ ሀገር የፓርላማ መቀመጫ ዲዛይን ኋላቀር የሚባል ነው፡፡
እንደኔ እንደኔ አሁን ካለው የፓርላማ አባላት ስብጥር አኳያ ዶ/ር ዓብይ በመደበኛ መቀመጫቸው ላይ ሆነው ጥያቄዎችን ቢመልሱ ወይም ሪፖርት ቢያቀርቡ የተሻለ ነው፡፡ ይህ ይለወጥ ከተባለ ደግሞ አፈ ጉባዔው አጠገብ ከሚቀመጡ የተሾሙ እለት ንግግር ባደረጉበት ፖዲየም (የመነጋገሪያ ሳጥን) አጠገብ ቆመው ጥያቄ ቢመልሱ ወይም ሪፖርት ቢያቀርቡ የተሻለ ነው፡፡ የህዝብ እንደራሴዎች የሉዓላዊ ህዝብ ወኪል እንደመሆናቸው እነሱ ፊት ቆሞ ሪፖርት ማቅረብም ይሁን እነሱ ለሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች መልስ መስጠት፣ ሕዝብ ፊት እንደ መቆም የሚቆጠር፣ ለህዝብ ያለንን ክብር  የሚያሳይ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡
የዓርብ እለቱ ስብሰባ ህጋዊ ነው?
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 6/2008 አንቀጽ 24/3 መሰረት የምክር ቤቱ መደበኛ የስብሰባ ቀናት ማክሰኞና ሐሙስ ናቸው፡፡ እኔ በነበርኩበት ዘመን በነበረው ደንብ (ደንብ ቁጥር 2/1998) ላይ የነበረው ጠቅላይ ሚንስትሩ በወር አንድ ቀን (ሀሙስ ዕለት) ከምክር ቤት አባላት ለሚቀርቡ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጡበት ድንጋጌ በአዲሱ ደንብ ላይ የለም፡፡ እናም ዓርብ ዕለት የተጠራው ስብሰባ “አስቸኳይ ስብሰባ” ነው እንዳይባል፤ አስቸኳይ ስብሰባ የሚጠራው ምክር ቤቱ በእረፍት ላይ ሲሆን ነው፡፡ “ልዩ ስብሰባ” ነው እንዳይባል፤ ልዩ ስብሰባ የሚጠራው ምክር ቤቱ የስራ መደራረብ ሲገጥመው ወይም አፋጣኝ መፍትሄ የሚሻ ጉዳይ ሲያጋጥም ነው፡፡ ታዲያ በየትኛው የደንቡ ድንጋጌ ነው የዓርብ እለቱ ስብሰባ የተካሄደው?  
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ጋዜጠኛነት በተናገሩት ላይ…
የተከበረው ምክር ቤት፤ዓርብ ዕለት ያካሄደውን ስብሰባ በተመለከተ፣ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ያልጠሩ ሁኔታዎች መታየታቸው እንደተጠበቁ ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባነሷቸው አንዳንድ ጉዳዮች ላይ አስተያየት ላቅርብ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር  ዶ/ር ዓብይ ጋዜጠኛነትን በተመለከተ አንድን የኢሳት ቴሌቪዥን የስራ ባልደረባ ስም በመጥቀስ የሰጡትን አስተያየት ሰምቻለሁ፡፡ በመሰረቱ ያ በስም የጠቀሱት “ጋዜጠኛ” ፤የጋዜጠኛነትን መርህም ሆነ ስነ ምግባር ጠንቅቆ እንደሚያውቅ አምናለሁ። በሙያው ውስጥ ለረዥም ጊዜ መቆየቱንም አውቃለሁ፡፡ ታታሪነቱንና ለሀገሩ ያለውን ፍቅርም ሆነ ለዚህም ሲል የከፈለውን መስዋእትነት እመሰክራለሁ፡፡ ይሁን እንጂ፤ ቴሌቪዥንን ወይም ሌላ የብዙሃን መገናኛ አውታርን ተጠቅሞ (በፖለቲካ አክቲቪስትነት) የፖለቲካ ዓላማን በማራመድና መሰረታዊ የጋዜጠኛነት ሥራን በመስራት መካከል ሰፊ ልዩነት ያለ መሆኑ በአጽንዖት ሊታይ ይገባል፡፡
በኔ እምነት ኢሳት ከአመሰራረቱ ጀምሮ ልዩ ባህሪ ያለው ጣቢያ ነው፡፡ የተቋሙ ባለቤቶችን ማንነትም ጭምር ማየቱ ተገቢ ነው፡፡ ጣቢያው የሚያሰራጫቸው ፕሮግራሞች “የጋዜጠኛነትን ሙያና ስነ ምግባር ጠብቆ በመስራት የተሰናዱ ናቸው” የሚለውን በሙሉ ልብ ለመቀበል ግን እቸገራለሁ፡፡ ይሄ ማለት ግን ኢሳት የሚሰራው ስራ ትክክል አይደለም ማለት አይደለም። እያልኩ ያለሁት ኢሳት የሚደግፈውን አስተሳሰብ ለማራመድ (promote ለማድረግ) ጥንቃቄ የተሞላው ስራ እያከናወነ መሆኑን አስተውያለሁ ለማለት ነው፡፡ ከአቀራረብ ቅርጽ አኳያ በድምፂ ወያኔ እና በኢሳት መካከል ያለው ልዩነት አይታየኝም፡፡ ኢሳት ለቆመለት ዓላማ ሽንጡን ገትሮ እየሰራ ነው፡፡ የቆመለትን ዓላማ ከሞላ ጎደል አሳክቷል፡፡ የኢህአዴግን አስከፊ ተግባራት በማጋለጥ ኢህአዴግ ውልቅልቁ እንዲወጣ የአርበኝነት ስራ ሰርቷል፡፡ ግን ይሄ ጋዜጠኛነት ነው አርኝነት? ይሄም ቢታይ መልካም ነው፡፡
ለትንታኔ የሚመረጡት አጀንዳዎችና የሚተነተኑበት መንገድ ጣቢያው የቆመለትን ዓላማ ከግቡ ለማድረስ ካለው ፋይዳ አንጻር የሚታይ እንጂ የተመልካችን ፍላጎት ማዕከል አድርጎ የተቃኘና የጋዜጠኛነትን መርህና ስነ ምግባር ጠብቆ የተሰራ ነው ብዬ ለማመን እቸገራለሁ፡፡ ለቃለ ምልልስ የሚመረጡት ሰዎች ኢሳት የቆመለትን ዓላማ ከማሳካት አኳያ እንጂ ሃሳብን ከመግለጽ አኳያ የተመረጡ መሆናቸው አልታየኝም፡፡ ዜናውም ሆነ ሌሎች ፕሮግራሞቹ በዚሁ መልክ የተቃኙ ናቸው፡፡
ከዚህ አኳያ ኢሳት ውስጥ የጋዜጠኛነት ሙያ ያላቸው፣ የጋዜጠኛነትን መርህና ስነ ምግባር በአግባቡ የሚያውቁ ሰዎች መኖራቸው የማያጠራጥር ቢሆንም “ጋዜጠኛነት” ሚዛኑን ጠብቆ፣ ሙሉ ለሙሉ ሥራ ላይ ውሏል ብዬ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ያህል ለማመን ግን እቸገራለሁ፡፡
የጋዜጠኛነትና የአክቲቪስትነት መደበላለቅ፤
በመሰረቱ እዚህ አገር ብዙ ያልጠሩና የተደበላለቁ ነገሮች አሉ፡፡ በተለይም የጋዜጠኛነት ሙያ ውስጥ እጁን ያልነከረ የለም። በዚህም ምክንያት ትክክለኛው የጋዜጠኛነት ሙያ ትልቅ አደጋ እንደተጋረጠበት ይታየኛል። ምክንያቱም በጋዜጠኛነትና በዲጄ፣ በጋዜጠኛነትና በካድሬነት፣ በጋዜጠኛነትና በአክቲቪስትነት፣ በጋዜጠኛነትና በመድረክ አስተዋዋቂነት፣ በጋዜጠኛነትና በስብሰባ መሪነት፣ በጋዜጠኛነትና በማህበራዊ ሜዲያ ባለሟልነት፣ በጋዜጠኛነትና በጦማሪነት፣ በጋዜጠኛነትና በፌስቡክ ተሳታፊነት… መካከል ያለው ልዩነትና ድንበር በግልጽ አልተሰመረም፡፡
አንዲት ነጠላ ዜማ የለቀቀው ሁሉ ከእነ ጥላሁን ገሠሠ እኩል “አርቲስት” የሚል መጠሪያ ሲሰጥ እንዳየነው ሁሉ፤ በፌስቡክ ሁለት ሦስት መስመር አስተያየት ጽፎ የለጠፈ ሁሉ “አክቲቪስት” አንዳንድ ጊዜም “ጸሐፊ” አለፍ ሲልም “ጋዜጠኛ”፣ ተንታኝ፣ ጦማሪ፣… የሚል ካባ እስከ መደረብ የደረሰበት ሁኔታ እየተስተዋለ ነው፡፡ በማህበራዊ ሚዲያው ከሩብ ገጽ ያልበለጡ አስተያየቶችን በመጻፍ የታወቁ ሰዎች “ጋዜጠኛ” ተብለው በዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን እስከ መቆጠር እየደረሱ ነው፡፡
ሌላውን ትተን በጋዜጠኛነትና በአክቲቪስትነት መካከል ያለውን ልዩነት ከአድማጭ/ ተመልካች/ አንባቢ (Audience) አንጻር እንየው፡፡ በብዙዎች ዘንድ አራተኛ አእማደ መንግስት እንደሆነ የሚነገርለት ጋዜጠኛነት ደረጃው ከህግ አውጪ፣ ከህግ አስፈጻሚና ከህግ ተርጓሚ ጋር ተመጣጣኝ በመሆኑ ደረጃው ብቻ ሳይሆን ኃላፊነቱም ከፍ ያለ ነው፡፡ እናም ጋዜጠኞች አለቃቸውን (አድማጭ/ተመልካች/አንባቢ) ስለሚፈሩ የሙያውን መርህና ስነ ምግባር ጠብቀው በመስራት ራሳቸውንም ሙያቸውንም ያስከብራሉ፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ አክቲቪስትነትን እንይ፡፡ አንደኛ አክቲቪስት አለቃ የለውም፡፡ ቢኖረውም አይፈራውም፡፡ አክቲቪስትነት እንደ ሙያ መርህም ሆነ የስነ ምግባር ድንጋጌ የለውም። በሁለተኛ ደረጃ አክቲቪስትነት ዘርፉ ብዙ ነው፡፡ የአካባቢ ጥበቃ አክቲቪስት፣ የፖለቲካ አክቲቪስት፣ የሰብአዊ መብት አክቲቪስት፣… እያሉ ራሳቸውን ከቆሙለት ዓላማ ጋር አቆራኝተው የሚገልጹ አክቲቪስቶች አሉ፡፡ በፌስቡክና በሌላ የማህበራዊ ሜዲያ አውታር ባገኙት ጉዳይ ላይ የሚጽፉ ሰዎች “አክቲቪስት” ተብለው ከመጠራት ውጪ ዓላማና ግባቸው ግልጽ ሆኖ አይታወቅም፡፡
የማህበራዊ ሜዲያና ዲጂታል ወያኔ፤
በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ማህበራዊ ሜዲያን በተመለከተ ለብቻው ለማየት መርጫለሁ። ማህበራዊ ሜዲያ እንደ ጋዜጠኛ ወይም እንደ አክቲቪስት ሰብአዊ ፍጡር አይደለም፡፡ ማህበራዊ ሜዲያ የመስተጋብር (የግንኙነት) መድረክ (Venue) ነው፡፡
ማህበራዊ ሜዲያው ለሀገር ደህንነትም ይሁን ለህዝብ ሰላም የስጋት ምንጭ መሆኑ እየተስተዋለ ነው፡፡ በዚህም ምክንት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ (ጠቅላይ ሚንስትሩ ጭምር) ማህበራዊ ሜዲያውን በተመለከተ የሚመራበት ህግ እንደሚያስፈልግ አስተያየት ሲሰጡ ይሰማል፡፡ ህግ መውጣቱን በተመለከተ በአዎንታዊም በአሉታዊም ጎኑ የተመለከቱት ሰዎች አጋጥመውኛል፡፡
ማህበራዊ ሜዲያን በተመለከተ ከአንድ የዩንቨርስቲ ፕሮፌሰር ጋር ስናወራር “ማህበራዊ ሜዲያው ልክ እንደ ቢላዋ ነው፡፡ ጥቅምም ጉዳትም አለው፡፡ ቢላዋን ህይወት ልናጠፋበትም ምግብ ልናዘጋጅበትም እንችላለን፡፡ አጠቃቀማችን ይወስነዋል፡፡ እናም ቢላዋን ጉዳት ያደርሳል ብለን ከቤታችን እንደማናጠፋው ሁሉ የድምፅ አልባዎች ድምፅ የሆነውን፣ ልሳነ ግፉአን የሆነውን ማህበራዊ ሜዲያን በአሳሪ ህግ መከርቸም ጉዳት አለው፡፡ … በአንዳንድ ሀገሮች ወደ ዩኒቨርሲቲ ለሚገቡ ተማሪዎች ‘Introduction to University - 101’ የተባለ ትምህርት በማስተማር የ“ፍሬሽ ማን” (የአንደኛ ዓመት) ተማሪዎች ዩኒቨርስቲውን አውቀው ራሳቸውን እንዲያስተካክሉ ይደረጋል፡፡ በእኛም ሀገር በተለይም ወጣቶች ወደ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ሲሸጋገሩ ‘Introduction to Social Media’ የሚል ትምህርት በካሪኩለማችን አካተን ወጣቶች ስለ ማህበራዊ ሜዲያ ምንነት፣ ጥቅም፣ ጉዳትና አጠቃቀም ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ የተሻለ ነው…” በማለት ሰፋ ያለ አስተያየት ሰጥተውኛል ምሁሩ፡፡
በአጠቃላይ በዚህ ዘመን ዓለምን እየለወጡም እየበጠበጡም ካሉ ነገሮች አንዱ ማህበራዊ ሜዲያ ነው፡፡ ሰሞኑን የኛው ሀገር የማህበራዊ ሜዲያ ‘አርበኞች’ “ዲጂታል ወያኔ” የሚል ቡድን ማደራጀታቸውን እያየን፣ እየሰማን ነው። ይህንን የ“ዲጂታል ወያኔ” ጉዳይ በተመለከተ አንድ የዩንቨርስቲ የታሪክ ምሁር በፌስቡክ ገጻቸው ላይ “Digital ወያነ is a transition from Kalashnikov to the Internet... I think a political force that monopolizes the Ethiopian cyber space will prevail in the ongoing game of thrones.” በማለት ጽፈው አንብቤአለሁ፡፡ በግርድፉ ስንተረጉመው “ዲጂታል ወያኔ ከክላሽንኮቭ ወደ ኢንተርኔት የሚደረግ ሽግግር ነው… ከንግዲህ የኢትዮጵያን ድረ ገፆች የተቆጣጠረ የፖለቲካ ኃይል ነው ለስልጣን የሚደረገውን ሩጫ ማሸነፍ የሚችለው” እንደማለት ነው፡፡
እንደ ምሁሩ አስተያየት ይህ የዲጂታል አብዮት ዘመን ነው፡፡ ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት የዲጂታል አብዮቱን እንዴት እንጠቀምበት በሚለው ላይ መምከር ይገባናል እንጂ ከዚህ አብዮት ማምለጥ የሚቻልበት ሁኔታ የለም። የውሸት ዜናን (fake news) የሚያስፈራራ ህግ በማውጣት፣ ኢንተርኔትን በመዝጋት ማገድ ሳይሆን የውሸት ዜና የማይፈበርክ ማህበረሰብን በመፍጠር መመከት የተሻለው አማራጭ መንገድ ነው፡፡  
    ጸሐፊውን በEmail: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 4525 times