Monday, 11 February 2019 00:00

“የእኛ ሰው የት አለ?” ባዮች

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(3 votes)

በኢትዮጵያ ከሰማኒያ በላይ ብሔረሰቦች እንደሚገኙ ለረጅም ጊዜ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ያሉ ግን ለይተን ያላወቅናቸው ብሔረሰቦች ይኖራሉ ብለው የጠረጠሩትና ወደ ጥናቱ የገቡት ዶ/ር ባይለኝ፤ ይህን ቁጥር ወደ ሁለት መቶ ከፍ አድርገውታል፡፡ ለይተን ያላወቅናቸውን ለይተን በማወቃችን፣ “ሕዝቦች” እያልን ስንጨፈልቃቸው የቆዩትን፣ ከዚህ ሳጥን አውጥተን ብሔር ብለን ለማክበር በመብቃታችን፣ ለእኔ ትልቅ የምሥራች ነው። ኢትዮጵያን የሁለት መቶ ብሔረሰብ አገር አድርገን እንድናውቃትም አስችለውናል፤ አጥኚውን ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
አሁን አንድ መቶ ሚሊየን የሚገመተው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የእነዚህ ብሔረሰቦች ድምር ያስገኘው ነው ማለት ነው፡፡ የእነዚህን ብሔረሰቦችና የሕዝባቸውን የወደፊት ሕይወት የተቃና ለማድረግ የተሰለፉ የብሔረሰብና በአገር አቀፍ ደረጃ የተደራጁ ከአንድ መቶ በላይ ክልላዊና አገር አቀፍ ፓርቲዎች፣ ሰሞኑን በኢሲኤ  አዳራሽ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ እንደ አንድ ሰው፣ እንደ አንድ የፖለቲካ ድርጅት መሪ የተሳተፉበት ስብሰባ ተካሂዷል፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ እራሳቸውን ዶክተር ዐቢይን ጨምሮ ዶ/ር አረጋዊ በርሔ፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋና ዶ/ር መረራ ጉዲና የመወያያ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡
የአቅራቢዎችን የዘር ግንድ ያሰሉ፣ ከእነሱ የዘር ግንድ ወገን የሆነ በአወያይነትም በጥናት አቅራቢነትም አለመሳተፉ ቅሬታ የፈጠረባቸው “የእኛ ሰው የት አለ” የሚል ጥያቄ ሲያነሱ አጋጥመውኛል፡፡ በእውነት “የእኛ ሰው የት አለ” ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡
እኛም ከእነ እከሌ እኩል (አሁን ያነሰ ሰው አላቸው እያልኩ አይደለም) ጐልቶ የማይታይ ሰው አናውጣ፣ ኢትዮጵያን ሰው በሰው እናድርጋት የሚል ፉክክር ከሆነ እሰየው የሚባል ሃሳብ ነው፡፡ ሰው ስል ያወቀ የበቃ ማለቴ እንጂ በተፈጥሮ የሰው ትንሽ እንደሌለ አሳምሬ አውቃለሁ፡፡
እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ያነሰም የበለጠም መብት የለውም፡፡ ግዴታም አይጣልበትም ብለን እንደምናምነው ሁሉ፣ በኢትዮጵያ እያንዳንዱ ብሔረሰብ ከሌላው ብሔረሰብ ያነሰም የበዛም መብትና ግዴታ እንደሌለውና እንደሌለበት ልናምን ይገባል፡፡
ይህ የመብትና የግዴታ እኩልነትና ተመሳሳይነት፣በብሔረሰቡ ሕዝብ ብዛት ላይ የሚመሠረት ሳይሆን ብሔረሰብ ሆኖ በመገኘት ላይ የሚቆም ነው፡፡ ለምሳሌ የአርጐባና የአማራ ብሔረሰቦችን ብንወስድ፣ በሕዝብ ብዛት የሰማይና የመሬት ያህል የሚራራቁ ቢሆንም በብሔረሰብነት ግን እኩል መሆናቸውን እንገነዘባለን፡፡ ጊዜ እድልና ሁኔታው ቢመቻች ከእያንዳንዱ ብሔረሰብ፣ እንደ ዶ/ር ዐቢይ፣ ዶ/ር አረጋዊ፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋና ዶ/ር መረራ ጉዲና አይነት ሰዎች ለማግኘት የሚቸግር አይደለም ብዬ አምናለሁ፡፡ ወደዚህ ጉዳይ የሳበኝ በኢሲኤ አዳራሽ በተካሄደው ስብሰባ ላይ “እንዴት አንድ አማራ ጥናት አቅራቢ ሳይገኝ ቀረ? አማራው እየተገፋ ነው” ብለው የሚብሰለሰሉ ሰዎች ስላጋጠሙኝ  ነው፡፡
ከየብሔረሰቡ አንዳንድ ሊቅ እየተፈለገ ወጥቶ፣ ሃሳቡን እንዲገልፅ እንዲህ ዓይነት መድረክ ቢዘጋጅለት፣ የሚቀጥለው ጭቅጭቅ፣ “የእኛው ሰው የመጀመሪያ ተናጋሪ የሚሆነው ምን ቢጎለው ነው?” የሚል እንደሚሆን መገመት አያስቸግርም፡፡ በግለሰብ ደረጃ ሲሆን “እኔ”፣ በብሔር ደረጃ ሲሆን “የእኛ መቅደም አለበት” ማብቂያው የት ነው? ብሎ መጠየቅ ይገባል። እንዲህ የሚሉት ሰዎች ደግሞ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት የምናስብ እኛ ነን የሚሉ መሆናቸው  የበለጠ ግራ የሚያጋባ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡
በፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ አወያይነት የተካሄደውን ያንን ስብሰባ፣ እንደ እኔ ብዙዎች በቴሌቪዥን ተከታትለውታል፡፡ በጉባኤው ብዙ የተነገረውና ያናገረው የዛሬዋና የነገዋ ኢትዮጵያ እጣ እንጂ የአንድ ብሔረሰብ ጉዳይም አልነበረም፡፡ “ብሔረሰቤ ተረሳ” ለማለትም የሚያስኬድ ነገር የለውም፡፡
ዘርን ሳይሆን ዘረኝነትን የሚጠሉ ሰዎች፤ “የእኛ ሰው የት አለ?” ለሚል ጥያቄ ወደ አደባባይ መውጣት እንደሌለባቸው አምናለሁ፡፡ ሰውን በሰውነቱ ለማየት፣ በሙያና በብቃቱ ወደ መለካት መራመድ  ይኖርባቸዋል፡፡ የዛሬዋም የነገዋም ኢትዮጵያ የምትፈልገው ይህንን ነው፡፡      

Read 1421 times