Print this page
Saturday, 09 February 2019 13:00

የኤሌክትሮኒክ ስፖርት eSport አብዮት በዓለም ዙርያ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 • ከ380 ሚሊዮን በላይ መደበኛ ተከታታዮችና ሌሎች ተመልካቾች
   • በዓመት እስከ 906 ሚሊዮን ዶላር ገቢ
   • ከ588 በላይ ሻምፒዮናዎችና ውድድሮች


     ኤሌክትሮኒክ ስፖርት eSport የኢንተርኔት አገልግሎትና ዲጂታል የሚዲያ አውታሮችን በተደራጀ ሁኔታ በመጠቀም ፕሮፌሽናል የቪድዮ ጌም ጨዋታዎችና ውድድሮች የሚካሄዱበት መድረክ ነው፡፡ ለኢስፖርት ኳስ፤ የመወዳደርያ ትራክ ፤ ስታድዬምና ሌሎች መደበኛ የስፖርት ቁሳቁሶችና ሁኔታዎች…አያስፈልጉም፡፡ ኢስፖርት በኢንተርኔት የተለያዩ የጌም ጨዋታዎችን በተናጠልና በቡድን መጫወት ሲሆን በተያያዥ ዲጂታል አውታሮች በቀጥታ ስርጭት ሽፋን የሚያገኝ ነው፡፡ በጌም ተወዳዳሪዎች በየጊዜው ተወዳጅነቱ እየጨመረ ሲሆን ውድድሮችን በመደበኛነት የሚከታተሉ  ደጋፊዎችና አድናቂዎችም በከፍተኛ ደረጃ እያገኘ መጥቷል፡፡
ኢስፖርት  በከፍተኛ የእድገት ደረጃ ላይ እንደሚገኝና የዓለምን የስፖርት ኢንዱስትሪ በአብዮታዊ እንቅስቃሴው እያናወጠ መሆኑን በተለያዩ ማስረጃዎች ማመልከት ይቻላል፡፡ በታላላቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች እና ብራንዶች ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እየተደረገበት ሲሆን በተለይ ስፖንሰሮች  ቀጣይነት ባላቸው የውል ስምምነቶች እየሰሩ መሆናቸው ይጠቀሳል፡፡ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች አዳዲስ የሊግ መዋቅሮች እየተመሰረቱና እየተደራጁ ሲሆን  በዲጂታል የሚዲያ አውታሮች የሚያገኘው  ትኩረት መደበኛ ተከታታዮቹን እያበዛቸው ነው፡፡ ጌሞችን የሚፈጥሩ ትልልቅ ኩባንያዎች በመላው ዓለም   የገበያ አድማሳቸውን የሚያሰፉበት እድል ስለፈጠረላቸው ኢንቨስትመንታቸውን አሳድገዋል፡፡ የኢስፖርት ተወዳዳሪዎች ደሞዝና ገቢ በከፍተኛ ደረጃ መናሩንም ቀጥሏል፡፡ ከኢንተርኔት፤ ከሞባይል ቴክኖሎጂ፤ ከቪድዮ ጌሞች፤ ከብሮድካስትና ግዙፍ ንግድ ኩባንያዎች በፈጠረው ትስስርም አትራፊነቱ እየጎላ መጥቷል፡፡
ኒውዙ የተባለ ተቋም በሰራው ጥናት በአሁኑ ወቅት ኤሌክትሮኒክ ስፖርት በዓለም ዙርያ   ከ380 ሚሊዮን በላይ መደበኛ ተከታታዮችና ሌሎች ተመልካቾችን ያፈራ ሲሆን በዓመት እስከ 906 ሚሊዮን ዶላር ገቢ የሚያስገኝ ሆኗል፡፡ ከስፖንሰርሺፕ ከፍተኛው ገቢ  359 ሚሊዮን ዶላር የሚገኝ ሲሆን  ከማስታወቂያዎች 174 ሚሊዮን ዶላር፤  ከትኬት ሽያጭ 116 ሚሊዮን ዶላር  እና ከተለያዩ የጌም ጨዋታዎች እና ቁሳቁሶች ንግድ   96 ሚሊዮን ዶላር እየገባ ነው፡፡
 ከዓመታዊ ገቢው ከ345 ሚሊዮን ዶላር በላይ ከሰሜን አሜሪካ እንዲሁም ከ164 ሚሊዮን ዶላር በላይ ከቻይና እንደሚገኝ ጠቅሷል፡፡  በኢስፖርት የሚገኘው ዓለም አቀፍ ገቢ በየዓመቱ በ38% ዕድገት እያሳየ እንድሚቀጥል ያመለከተው ጥናቱ፤ በሚቀጥሉት 2 እና 3 ዓመታት ዓመታዊ ገቢው ከ1.46 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያልፍ ገምቷል፡፡ በዓመት ውስጥ ከ588 በላይ ግዙፍ የኤሌክትሮኒክ ስፖርት ውድድሮች በመላው ዓለም እየተካሄዱ ሲሆን ዋንኞቹ የመወዳደርያ ማዕከሎች የዩቲውብ የጌም ቻናል እና ትዊች ከ380 ሚሊዮን በላይ መደበኛ ተከታታዮችና ተመልካቾች አግኝተዋል፡፡
እንደ ማንኛውም ስፖርት በኢስፖርት ፕሮፌሽናል ተወዳዳሪዎች፤ ኮሜንታተሮች እና ዝነኛ ባለታሪኮችም እየተፈጠሩ ናቸው፡፡ ኢስፖርት በተለያዩ ዞናዊ እና ዓለም አቀፍ ሻምፒዮናዎች ላይ በሚያቀርበው የሽልማት ገንዘብም የላቀ ነው፡፡ በአሜሪካ የቅርጫት ኳስ ሻምፒዮና እስከ 13 ሚሊዮን ዶላር ፤ በጎልፍ ዓለም አቀፍ ሻምፒዮና እስከ 11 ሚሊዮን ፤በፊፋ ኮንፌደሬሽን ካፕ እስከ 20 ሚሊዮን ዶላር የሽልማት ገንዘብ የሚቀርብ ሲሆን በዓለም የኢስፖርት ኢንዱስትሪ ግን በአንድ ሻምፒዮና ከ24.7 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሽልማት ገንዘብ እየቀረበ ነው፡፡ በመላው ዓለም በሚካሄዱ ግዙፍ የኤሌክትሮኒክ ስፖርት ሻምፒዮንሺፖች በድምሩ ከ120 ሚሊዮን ዶላር የሽልማት ገንዘብ በየዓመቱ እየቀረበ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ስኬታማ የኤሌክትሮኒክ ስፖርት ተወዳዳሪዎችና ጌም ተጨዋቾች በሽልማት ገንዘብ፤ በተሳትፎ ክፍያዎች እና በስፖንሰርሺፕ እስከ 25 ሚሊዮን ዶላር የሚያገኙበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡  በከፍተኛ ገቢው በአንደኛ ደረጃ የሚጠቀሰው ተወዳዳሪ ጀርመናዊው ኩሮ ታካሞሺ ሲሆን እስከ 3.5 ሚሊዮን ዶላር በአንድ የውድድር ዘመን በማግኘቱ ነው፡፡ በከፍተኛ ደረጃው ከኢስፖርት ዋና ሻምፒዮንሺፖች አንዱ የሆነው ሊግ ኦፍ ሌጀንድስ የተባለው ጌም ጨዋታ በጣም ፍጥነት የሚጠይቅ የፍልሚያ ስትራቴጂ ያስፈልገዋል፡፡  ከመላው ዓለም የምርጦች ምርጥ የሆኑትን በማሰባሰብ በሚያካሂደው ውድድር ለሻምፒዮኑ እስከ 1 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ያቀርባል፡፡  ሊግ ኦፍ ሌጀንድስ በ2016 እኤአ ላይ ባካሄደው የዓለም ሻምፒዮና እስከ 43 ሚሊዮን ተመልካች ሊያገኝ መብቃቱ እንደክብረወሰን የተመዘገበ ነው፡፡
በኢስፖርት ኢንዱስትሪው ቡድኖችና ተወዳዳሪዎችን በመግዛት እና በመሸጥ እየተሰራ ሲሆን ሃብታሞቹ ኩባንያዎች በብዙ ሻምፒዮናዎች የሚሳተፉ እና በብዛት የሚያሸንፉት ናቸው፡፡ ክላውድ 9  ፕሮፌሽናሉ እና ባለከፍተኛ ዋጋው ኩባንያ  ሲሆን በ310 ሚሊዮን ዶላር ሲተመን ቲም ሶሎ ሚድ በ225 ሚሊዮን ዶላር ሁለተኛ ደረጃ ይገኛል፡፡አንዳንድ የጌሞች ፈጣሪ፤ አምራች እና አከፋፋይ ኩባንያዎች  ከ60 እስከ 80 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ በሚተመን ካፒታል እየተንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ በሰሜን አሜሪካው ስኬታማ ኢስፖርት ሊግ ኦፍ ሌጀንድስ የሚወዳደሩ ክለቦች እና ቡድኖች በአማካይብ እስከ 50 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ናቸው፡፡
ኒውዙ (NewZoo) በ2018 ሪፖርቱ በዓለም ዙሪያ የኢስፖርት እንቅስቃሴ የተጠናከረባቸውን 10 ቀጠናዎች በጥልቀት የዳሰሰ ሲሆን፤የኢስፖርት መደበኛ ተከታታዮች ብዛት በዓለም ዙሪያ 165 ሚሊየን የደረሰ ሲሆን፤ በየዓመቱ በ15.2% እድገት እያሳየ በመቀጠል በሚቀጥሉት 3 እና 4 አመታት ከ380 ሚሊዮን በላይ እንደሚሆን ተገምቷል፡፡  ከአንድ የኢስፖርት  መደበኛ ተከታታይ  በየዓመቱ 5.49 ዶላር በአማካይ እየተገኘም ነው ብሏል፡፡
ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ብራንዶች በኢስፖርት ላይ ከ694 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት ያደረጉ ሲሆን፤ ከአጠቃላይ እንቅስቃሴው 77% የገበያ ድርሻ ይዘዋል።  እንደኒው ዙ ትንበያ የዓለማችን ታላላቅ ብራንዶች እና ኩባንያዎች ኢንቨስትመንት በ2021 እ.ኤ.አ ከ1.4 ቢሊዮን ዶላር የሚያልፍ ሲሆን የገበያ ድርሻቸውን ወደ 84% ያሳድገዋል፡፡ በየዓመቱ ከ50 ቢሊዮን ደላር በላይ ገቢ የሚያንቀሳቅሰው የሞባይል ኢንዱስትሪም ከጌሞች ጋር የፈጠረው መተሳሰር የኢስፖርትን እድገት አቀላጥፎታል፡፡ ከዚህ ጐን ለጐንም የሚዲያ ተቋማት እና የቴሌኮም ኩባንያዎች በኢንዱስትሪው ላይ የሚኖራቸውን ድርሻ እያሰፉ እንዲሄዱ አድርጓቸዋል፡፡ በተለያየ ዓለም ክፍል የኢስፖርትን አጠቃላይ እንቅስቃሴ የሚያስተላልፉና ውድድሮችን የሚመሩ ዓለምአቀፍ ማህበራት እየተፈጠሩ መሆናቸውም የሚጠቀስ ይሆናል፡፡
በ2021 እ.ኤ.አ ላይ የኢስፖርት ገቢ  በዓለም ዙሪያ እስከ 1.65 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ የኒውዙ ሪፖርት ገምቷል፡፡ የኢስፖርት ኢንዱስትሪ አጠቃላይ ገቢ የሚዲያ መብት፣ የማስታወቂያ፣ የስፖንሰርሺፕ የትኬት ሽያጭ እና ሌሎች ተያያዥ ንግዶች እንዲሁም የጌም አሳታሚዎችና ፈጣሪዎች ክፍያን የሚያካትት ነው፡፡ በሚቀጥሉት 3 ዓመታት በኢስፖርት ከስፖንሰርሺፕ 359.4 ቢሊዮን ዶላር ፤ ከትኬት ሽያጭ እና ሌሎች 95.5 ሚሊዮን ዶላር ፤ ከጌም አሳታሚዎች 116.3 ሚሊዮን ዶላር ፤ ከሚዲያ መብት 160.7 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ከማስታወቂያ 173.8 ሚሊዮን ዶላር በዓመት ገቢ የሚሆንበት ደረጃ ይደረሳል፡፡
ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ እና ዓለም አቀፉ የስፖርት ፌደሬሽኖች ማህበር ኢስፖርት በዓለም ዙርያ የፈጠረውን አብዮታዊ ተዕእኖ በማስተዋል ልዩ ትኩረት መስጠት ጀምረዋል፡፡ ባለፈው ዓመትም ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ እና ዓለም አቀፉ የስፖርት ፌደሬሽን በጋራ በመሆን በኢስፖርት ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ፎረም በፈረንሳይ ያደረጉ ሲሆን የአሜሪካ መንግስት በኢስፖርት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰውን ሊግ ኦፍ ሌጀንድስ በመደገፍ በሻምፒዮንሺፑ ለሚሰተፉ ፕሮፌሽናል ተወዳዳሪዎች ሙሉ እውቅና መስጠቱን የተለያዩ አገራት እያጤኑት መነሆናቸው ከዚሁ ጋር ተያይዞ ይጠቀሳል፡፡ የኢስፖርት ፕሮፌሽናል ተጨዋቾችን ለማፍራት በበርካታ የዓለማችን ዩኒቨርስቲዎች ፍላጎቱ ላላቸው የነፃ ትምህርት እድሎች እየተዘጋጁ ሲሆን በቻይና ሙሉ ኮሌጅ የተቋቋመበት ደረጃ ላይም ተደርሷል፡፡ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር ፊፋ በኢስፖርት በእግር ኳስ ጌም የዓለም ዋንጫ የሚያዘጋጅ ሲሆን FIFA18 Xbox and PlayStation በሚል ስያሜ ከመላው ዓለም 32 ፕሮፌሽናል ተወዳዳሪዎችን በማሳተፍ ያካሂደዋል፡፡

በኢስፖርት ታዋቂ እና ከፍተኛ የሽልማት ገንዘብ የሰበሰቡ ጌሞች በገቢ፤ በተወዳዳሪያቸው ብዛት እና ባደረጓቸው ውድድሮች ከ1 እስከ 5ኛ የሚሰጣቸው ደረጃ ከዚህ በታች እንደቀረበው ነው፡፡
ዶታ 2 Dota 2
የሽልማት ገንዘብ $173,271,037.22 የተወዳዳሪዎች ብዛት 2868 ውድድሮች  1060 ውድድሮች
ካውንተር ስትራይክ ግሎባል ኦፌንሲቭ Counter-Strike: Global Offensive
የሽልማት ገንዘብ $69,217,405.65 የተወዳዳሪዎች ብዛት 11067 ውድድሮች 3830
ሊግ ኦፍ ሌጀንድስ League of Legends
የሽልማት ገንዘብ $63,966,752.80 የተወዳዳሪዎች ብዛት 6068 ውድድሮች 2205
ስታር ክራፍት 11 StarCraft II
የሽልማት ገንዘብ $29,125,350.34 የተወዳዳሪዎች ብዛት 1888 ውድድሮች5282
ፎርትናይትFortnite
የሽልማት ገንዘብ $20,080,503.95 የተወዳዳሪዎች ብዛት 1386 ውድድሮች 162
የዓለም ህዝብ ብዛት -7.6 ቢሊዮን
የኦንላይን ተጠቃሚዎች ብዛት - 3.97 ቢሊዮን
ስለ ኢስፖርት የሚያውቁ - 1.6 ቢሊዮን
የኢስፖት ቀንደኛ ተከታታዮች - 165 ሚሊዮን
የኢስፖርት ገቢ በዓለም ዙሪያ 906 ሚሊዮን ዶላር

በትዊች ላይ በኢስፖርት ከፍተኛ ተመልካች ያገኙ 10 ጌሞች
ሊግ ኦፍ ሌጀንድስ - 274.7 ሚሊዮን  
ካውንትሪ ስትራይክ ግሎባል ኦፌንሲቭ- 232.9
ዶታ 2 -217.9
ሃርዝ ስቶን -76.9
ኦቨር ዎች - 25.2
ስታር ክራፍት - 21.2
ሄሮስ ኦፍ ዘስትሮም - 19.6
ሮኬት ሊግ - 17.3
ስትሪት ፋይተር 5- 11.5
ስማይት - 10.7
ሁለት የውድድር አይነቶችን የሚያዘጋጀው ፊፋ ከላይ በቀረበው የደንበኛ ሰንጠረዥ እስከ 50ኛ ;;; እርከን ሁለቱን ያስመዘገበ FifA 17 2018 ያስመዘገበው 48.7 ሚሊየን ሰዓታት ነው፡፡

Read 6423 times