Saturday, 09 February 2019 13:11

ያሬዳዊው ሥልጣኔ

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(1 Vote)

ክፍል- ፱ የዘርዓያዕቆብ ትችት ዲበ አካላዊ መነሻ
               

     በክፍል-8 ፅሁፌ ዘርዓያዕቆብንና ወልደ ህይወትን እየጠቀስን፣ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ከኢትዮጵያውያን ፈላስፎች የተሰነዘረበትን ትችቶች ተመልክተናል፡፡ በዛሬው ፅሁፌ ደግሞ ዘርዓያዕቆብ በስነ ምግባርና በመንፈሳዊ ህይወት አስተሳሰብ እንዴት ከያሬዳዊው ሥልጣኔ አስተምህሮ ሊነጠል ቻለ? የትችቱስ ዲበ አካላዊ (metaphysical) መነሻ ምንድን ነው? የሚሉትን ሐሳቦች እንመለከታለን፡፡
ዘርዓያዕቆብ በያሬዳዊው ባህልና ማህበረሰብ ውስጥ ተወልዶ ያደገ፣ እንዲሁም በቤተ ክርስትያኑ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ‹‹ትርጓሜ ቤት›› እስከሚባለው ከፍተኛ ደረጃ ድረስ የተማረ ሊቅ ነው፡፡ ሆኖም ግን፣ በዚያ ዘመን ከኦርቶዶክሳዊው ትምህርት በተጨማሪ ካቶሊኮችም የራሳቸውን ትምህርት እንዲያስተምሩ ተፈቅዶላቸው ስለነበር፣ ያሬዳዊው ባህል የሚናጥበት ወቅት ነበር፡፡ ዘርዓያዕቆብ ተወልዶ ያደገው በዚህ የባህል መነቅነቅ ውስጥ ነው፡፡
ይሄም የባህል መናወጥ ዘርዓያዕቆብን የድሮውን ትምህርት ከማነብነብ እንዲወጣና በኦርቶዶክስና በካቶሊክ ሃይማኖቶች መካከል ንፅፅራዊ የሃይማኖት ጥናት (Comparative Religious Studies) ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል፡፡ ይሄ ንፅፅራዊ ጥናት ለዘርዓያዕቆብ አይን ከፋች ከመሆኑም ባሻገር፣ ሁለቱን ሃይማኖቶች በተመለከተም የራሱ የሆነ ምክንያታዊ ውሳኔ (Rational Decision) ላይ እንዲደርስ አድርጎታል፡፡ ዘርዓያዕቆብ፣ በባህልም ሆነ በሰዎች አስተያየት ‹‹ያልተበረዘ እውነት›› ላይ ለመድረስ የአመክንዮን ያህል ኃያል መሳሪያ እንደሌለ የተረዳውም በዚህ ሂደት ውስጥ ነበር፡፡
ዘርዓያዕቆብ፣ ከያሬዳዊው አስተሳሰብ በመነጠል የራሱ ምክንያታዊ ውሳኔ ላይ ከደረሰባቸው ነገሮች መካከል ሦስቱ እጅግ መሰረታዊ ናቸው፡፡ እነሱም፣ የሰው ልጅ ተፈጥሮን በተመለከተ፣ የመንፈሳዊና ዓለማዊ ህይወት መስተጋብርን በተመለከተ፣ እንዲሁም በአመክንዮና በእምነት መካከል ያለውን ቅደም ተከተል በተመለከተ ናቸው፡፡ ዘርዓያዕቆብ በእነዚህ ሦስት የዲበ አካላዊ ፅንሰ ሐሳቦች ላይ ከያሬዳዊው ሥልጣኔ የተለየ አቋም የያዘ ሲሆን፤ ዲበ አካላዊ ልዩነቱም ያሬዳዊው ሥልጣኔ ላይ መሰረት የሚያናጋ ትችት እንዲሰነዝር አድርጎታል፡፡ እስቲ ሦስቱንም ፅንሰ ሐሳቦች በየተራ እንመልከታቸው፡፡
የሰው ልጅ ተፈጥሮን በተመለከተ
ዘርዓያዕቆብ፣ ብህትውናና ተአምራዊነት ላይ ምህረት የለሽ ትችት እንዲሰነዝር ያደረገው የመጀመሪያው ነገር የሰው ልጅ ተፈጥሮን በተመለከተ ከያሬዳዊው ሥልጣኔ የተለየ ዲበ አካላዊ አቋም መያዙ ነው፡፡ ያሬዳዊው ሥልጣኔ የሰው ልጅ ተፈጥሮን በተመለከተ ‹‹ሰው እርስበርስ ከሚጠፋፉና መለኮታዊና ቁሳዊ ከሆኑ ሁለት ተቃራኒ ኃይሎች (ነፍስና ሥጋ) የተሰራ ነው›› ይላል፡፡ ይሄም ቅራኔ ብህትውና ላይ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይደርሳል። ይሄ ተቃርኖ ለዘርዓያዕቆብ የችግሮች ሁሉ መነሻ ነው፡፡ ሆኖም ግን፣ ዋናው ችግር ‹‹ነፍስና ስጋ ተቃራኒ ናቸው›› ማለቱ ሳይሆን፣ ይልቅስ ለነፍስና ለስጋ የሰጠናቸው ባህሪያት እንጂ። በዚህ የሁለትዮሽ ተቃርኖ ውስጥ ነፍስ የቅዱስነት፣ የመለኮታዊነትና የዘላለማዊነት ባህሪያትን ስትሸለም፣ ስጋ ደግሞ በተቃራኒው በስባሽና ፈራሽ፣ የክፉ ሐሳቦች መፍለቂያና የክፉ መናፍስት መሸሸጊያ ተደርጎ ይታሰባል፡፡
ይሄ በነፍስና በስጋ መካከል ያለው ዲበ አካላዊ ቅራኔ የራሱ የሆነ የስነ ምግባር ምልከታ አለው፡፡ ምልከታውም ‹‹ሥነ ምግባርም ሆነ መንፈሳዊ ህይወት የሚገኘው ከዚህ ቅራኔ ውስጥ ስጋ በተሸናፊነት፣ ነፍስ ደግሞ በአሸናፊነት ስትወጣ ነው›› የሚል ነው፡፡ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ከተመረኮዛቸው ሶስት ምሰሶዎች ውስጥ የአንደኛውን ምሰሶ (የብህትውናን) መሰረት የምናገኘው እዚህ ቅራኔ ላይ ነው፡፡ ብህትውና፣ ‹‹ሰዎች ስጋዊ ፍላጎታቸውን እያረኩ ለእግዚአብሔር መሆን አይችሉም›› ብሎ ያስባል፡፡ ‹‹ስጋዊ ተፈጥሯችንን ይበልጥ በተቃወምን መጠን፣ ይበልጥ መንፈሳዊ እንሆናለን፡፡ ስጋችንን ይበልጥ በውሃ ጥም፣ በርሃብና በፍትወት ባቃጠልነው ቁጥር፣ ይበልጥ ለእግዚአብሔር የተገባን እንሆናለን፤›› ይላል ብህትውና፡፡
‹‹ሥነ ምግባርና መንፈሳዊነት የሚገኘው ስሜትንና የስጋ ፍላጎትን በመጨቆን ነው›› የሚለው ይህ ብህትውናዊ አመለካከት፤ እንደ ፕሌቶ፣ ቶማስ ሆብስ እና ዚግመንድ ፍሮይድ ያሉ የምዕራቡ ዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪ ምሁራንም ሲደገፍ ኖሯል፡፡ እንዲያውም፣ ቶማስ ሆብስና ዚግመንድ ፍሮይድ ‹‹የሰው ልጅ ሥልጣኔን ያለ ስሜት ጭቆና ማምጣትም ሆነ ማስቀጠል አይታሰብም!!›› እስከ ማለት ደርሰዋል፡፡  ይሄንን አስተሳሰብ ክፉኛ በመተቸት የተነሱት ፈላስፎች ኒቸ እና ማርኩዘ ሲሆኑ፣ ዘርዓያዕቆብም እዚህ ቡድን ውስጥ ይመደባል፡፡ ይሄ ‹‹የሁለትዮሽ የቅራኔ ሐሳብ›› (dualism) መነሻ መሰረቱ፤ የአይሁድ እምነትና የፕሌቶ ፍልስፍና ነው። ክርስትናም ይሄንኑ አመለካከት ከአይሁድ እምነትና ከፕሌቶ ፍልስፍና በመቀበል ቅራኔውን ይበልጥ አፅንቶታል፡፡ ያሬዳዊው ሥልጣኔም ከመካከለኛው ምስራቅ ጋር በነበረው የባህልና የታሪክ ትስስር የተነሳ፣ ይሄንን አመለካከት ከአይሁድ እምነትና ከክርስትና ወርሷል፡፡
ዘርዓያዕቆብ ‹‹የሰው ልጅ ከነፍስና ከስጋ የተሰራ ህላዌ ነው›› የሚለውን ዲበ አካላዊ አመለካከት ይቀበልና፤ ሆኖም ግን፣ ‹‹ነፍስና ስጋ እርስበርስ የሚጠፋፉ ተቃራኒ ኃይሎች ናቸው›› የሚለውን የያሬዳዊው ሥልጣኔ ስነ ምግባራዊ አስተምህሮ ግን አይቀበልም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ‹‹ነፍስም ሆነ ሥጋ የተፈጠሩት በእግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ መልካም ስለሆነ፣ እሱ የፈጠራቸው ነገሮች ሁሉ መልካም ናቸው፡፡ ስለሆነም፣ ነፍስና ስጋ በእግዚአብሔር የተፈጠሩ ስለሆነ ሁለቱም መልካም ናቸው፡፡ ስለዚህ፣ ነፍስን ጨቋኝ፣ ስጋን ተጨቋኝ፤ አንደኛውን ቅዱስ፣ ሌላኛውን እርኩስ ልናደርጋቸው አይገባም›› የሚል ነው፡፡
የነፍስና ስጋ ተቃርኖ ለያሬዳዊው ሥልጣኔ ወሳኝ የሆነ ዲበ አካላዊ አመለካከት ቢሆንም፣ ዘርዓያዕቆብ ግን ይሄንን ቅራኔ የሚፈታበት አዲስ አስተሳሰብ ይዞ መጥቷል፡፡ በዚህም የተነሳ፣ ዘርዓያዕቆብ በታረቀው የነፍስና የስጋ ግንኙነት ላይ ለያሬዳዊው ሥልጣኔ እንግዳ የሆነና ስጋን በእጅጉ የሚንከባከብ የስነ ምግባር አስተምህሮ ይዞ መጥቷል፡፡ በዘርዓያዕቆብ አመለካከት፤ ትክክለኛው መንፈሳዊ ህይወትና የሰውን ልጅ የሚያበለፅገውን ሥነ ምግባር የምናገኘው በነፍስና ስጋ ቅራኔ ላይ ሳይሆን፣ ይልቅስ የቅራኔው መጥፋት ላይ ነው - በነፍስና ስጋ እርቅ ላይ፡፡

የመንፈሳዊና ዓለማዊ ህይወት መስተጋብርን በተመለከተ
ስለ ሰው ልጅ ተፈጥሮ ያለን ‹‹የነፍስና ስጋ›› ዲበ አካላዊ አመለካከት ይበልጥ ወሳኝ የሚሆነው፣ ስለ ማህበረሰብ ያለን አመለካከት የሚቀዳው ከዚሁ ዲበ አካላዊ ፅንሰ ሐሳብ በመሆኑ ነው፡፡ ‹‹ስለ ግዙፉ ዓለም ለማወቅ፣ በመጀመሪያ ግዙፉ ዓለም ስለተሰራበት ጥቃቅን ነገር ማወቅ አለብን›› የሚለው አስተሳሰብ በፍልስፍና፣ በሳይኮአናሊሲስና በሳይንሱ ዓለም በጣም የተለመደና ደግሞም ውጤታማ የሆነ አካሄድ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ ፊዚክስ ስለ ዩኒቨርሱ ለማወቅ የሚሞክረው በመጀመሪያ ዩኒቨርሱ ስለተሰራበት ጥቃቅን አተሞች በማጥናት ነው፡፡ ሳይኮአናሊሲስም ስለ ሰው ልጅ ባህሪ ለማወቅ ቅድሚያ ሰጥቶ የሚያጠናው Id, Ego እና Super Ego የሚባሉትን ፅንሰ ሐሳቦች ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ፣ ፕሌቶም ስለ አንድ ማህበረሰብ ፖለቲካዊ ችግሮች ለማወቅ የሚጥረው፣ በመጀመሪያ ‹‹ሰው›› ስለሚባለው ግለሰብና ‹‹ሰው-ነት›› ስለተሰራባቸው የነፍስና የስጋ ባህሪያትና ግንኙነት በማጥናት ነው፡፡ ዘርዓያዕቆብ ላይም ከዚህ የተለመደ ምሁራዊ አካሄድ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ነገር እናይበታለን፡፡
ዘርዓያዕቆብ፣ በመጀመሪያ የነፍስና ስጋን ቅራኔ ከፈታ በኋላ፣ ይሄንን እርቅ በቀጥታ በትልቁ የመንፈሳዊና ዓለማዊ ህይወት ላይ ተግባራዊ ያደርገዋል፤ እርቁን ከግለሰብ ወደ ማህበረሰብ ይወስደዋል፡፡ መንፈሳዊ ህይወት የነፍስ ባህሪ ነፀብራቅ ሲሆን፣ ዓለማዊ ህይወት ደግሞ የስጋ ባህሪ ነፀብራቅ ነው፡፡ ይሄም ማለት፣ ስለ ነፍስና ስለ ለበስነው ስጋ ያለን አመለካከት በቀጥታ በመንፈሳዊና ዓለማዊ ህይወታችን ላይ ይንፀባረቃል፡፡ በመሆኑም፣ የነፍስና የስጋ እርቅ፣ የመንፈሳዊና የዓለማዊ ህይወት እርቅን ይፈጥራል፡፡
ዘርዓያዕቆብ፣ በመንፈሳዊና በዓለማዊ ህይወቶች መካከል እርቅ ከመፍጠሩም ባሻገር፣ ቁሳዊ ህይወትን የመንፈሳዊ ህይወት መሰረት ያደርገዋል፡፡ ከዚህም አልፎ ‹‹ሐብትን (ገንዘብን) ያለመጠን ማከማቸት ተገቢ ነው›› እስከማለት ድረስ ሄዷል፡፡ ምክንያቱም፣ ዘርዓያዕቆብ የኢትዮጵያውያንን ድህነትና ኋላቀርነት ሥሩን የሚመዘው፣ ከዚህ የነፍስና ስጋ ቅራኔ ነው። ይሄ ሁሉ ለያሬዳዊው ሥልጣኔ እንግዳ የሆነ ትምህርት ነው፡፡

በአመክንዮና በእምነት መካከል ያለውን ቅደም ተከተል በተመለከተ
ምንም እንኳ፣ በተለያየ ደረጃም ቢሆን አመክንዮና እምነት ለመንፈሳዊ ህይወት የሚጠቅሙ ቢሆኑም፣ ከሁለቱ የትኛው ይቀድማል የሚለው ጥያቄ ግን ከድሮ ጀምሮ ፈላስፋዎችንና የሥነ መለኮት ልሂቃንን ሲያከራክር ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አማኞችም ሆኑ የሥነ መለኮት መምህራን የእምነት ቀዳሚነት ላይ ወይም ደግሞ ‹‹ለማወቅ በመጀመሪያ ማመን ያስፈልጋል›› የሚል ፅኑ አቋም አላቸው፡፡ ዘርዓያዕቆብም በሐሰተኛ ክስ ተከሶ እስኪሰደድ ድረስ የዚሁ አመለካከት አራማጅ ነበረ፡፡ ዘርዓያዕቆብ ‹‹ለማመን በመጀመሪያ ማወቅ ያስፈልጋል›› ወደሚል የአመክንዮ ቀዳሚነት አመለካከት የተቀየረው በዋሻ ውስጥ ሆኖ በሚፀልይበት ወቅት ነበር። ዘርዓያዕቆብ ሲፀልይ የነበረው ‹‹ለማወቅ በመጀመሪያ ማመን ያስፈልጋል›› በሚለው ያሬዳዊ አመለካከት በመሄድ ነበር፡፡ ሆኖም ግን፣ በፀሎቱ መካከል ‹‹ለመሆኑ ወደ ማን ነው የምፀልየው? የሚሰማኝስ ኃይል አለን?›› የሚል ጥያቄ መጣበት፡፡
ዘርዓያዕቆብ ለዚህ ጥያቄ መልስ ያገኘው በእምነት ሳይሆን በአመክንዮ በመመራት ነው። በአመክንዮ ረዳትነት ለጥያቄው መልስ ካገኘ (ፈጣሪ መኖሩን ካረጋገጠ) በኋላ ወዳቋረጠው ፀሎቱ ተመለሰ፡፡ በዚህም፣ ‹‹ለማመን በመጀመሪያ ማወቅ›› እንደሚያስፈልግ አዲስ ግንዛቤ ላይ ደረሰ፡፡ ይሄም አዲስ ግንዛቤ ለያሬዳዊው አስተሳሰብ እንግዳ ነው፡፡
በክፍል-10 ፅሁፌ፣ ዶ/ር እጓለ ገ/ዮሐንስ፣ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ እና ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም ያሬዳዊው ሥልጣኔ ላይ የሰነዘሩትን ‹‹የተለሳለሰ›› ተግሳፅና ምክር እንመለከታለን፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 477 times