Saturday, 09 February 2019 13:13

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)

 የአንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ መሰል ተቋሟትና የመንግሥት ሠራተኞች፣ በሃሰተኛ ሠርተፊኬት እያጭበረበሩ በአገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ መሆናቸው እግዜር ጆሮ ደረሰ። ይኸው ጉዳይ ባለፈው ሰሞን በጋዜጣ ታትሞ ሲያይ፣ አሳሳቢነቱን ተረዳ፡፡ የእያንዳንዱን ሰው ሰነደ መመርመር ጊዜ ስለሚፈጅ፣ የመለመሏቸውና የሚያገለግሏቸውን ድርጅቶች “CV” እየታየ፤ በግል ፐርፎርማንስ ይወሰን የነበረው የጽድቅና ኩነኔ ጉዳይ፣ በጋራና በየድርጅታቸው እንዲሆን አመቻቹ፡፡ ከገሃነምና ከገነት የተውጣጡ አባላት ያሉበት አጣሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ ስራ ጀመረ፡፡
ድርጅቶቹ የሚያቀርቧቸው ሲቪዎች ግን አሳማኝ አልሆኑም፡፡ ስለዚህ ድርጅቶቹ “እንደ ድርጅት” የተማሯቸው ወይም የወሰዷቸው ኮርሶችና የሰለጠኑባቸው ሙያዎች በሚስጢር፣ ከየሬጂስትራሩ የተማሪ ኮፒ እንዲሰበሰብ ተደረገ፡፡
ሌሎች መደበኛ   የሆኑ ነገሮችን አስቀርተን ለዛሬ የአንደኛውን Grade እንመልከት፡፡
ዘረፋ………………………….…….............…….A
ስም ማጥፋት…………………….......………...A
እስርና ግድያ……………………………...........A
የዘር ፖለቲካ …………………………….........A
ማደናቆር………………………….……….........A
ስለላና ወከባ………………………….…….......A
ዲፕሎማቶችን ማታለል ……………………A
ሰብዓዊነት………………………………………...A
ኢትዮጵያዊነት……………………………………A
መንግሥተ ሰማያት ጠባብ በመሆኗ በሁለም ትምህርቶች “A” ያላገኘ ከደጃፏ አይደርስም፡፡ ይኸን ውጤት ዲያብሎስ ሲመለከት ቀና፡፡ “ለኔ የሚያስፈልጉኝ እንደዚህ ዓይነት ድርጅት ነው” በማለት ቋመጠ፡፡ አሰራሩ ስለማይፈቅድለት ሲያምረው ቀረ፡፡ ግን ደግሞ እግዜርም አልተመቸውም፡፡ ከሁለቱ በስተቀር ሌሎቹን ኮርሶች አያውቃቸውም፡፡ መነጽሩን ሰክቶ ለረዥም ጊዜ እያስተዋለ ሳለ፣ የሁለቱ ኮርሶች ውጤት ተፍቆ የተስተካከለ እንደሆነ ተገነዘበ። “D” የነበሩት በ “A” ተተክተዋል፡፡ የትኞቹ ይመስሉሃል?
***
አገር መውደድ፣ ነፃነት፣ ማንነት፣ ሰላም፣ ዕምነት፣ ፍልስፍና የመሳሰሉት ርዕሶች፣ ብዙ መፃሕፍት የተፃፉባቸው፣ ሊቃውንት የተከራከሩባቸው፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከኛነታችን፣ ከኑሯችን፣ ብሎም ከሌሎች የዓለም ህዝቦች ጋር የሚያስተዳድሩን ጉዳዮች ናቸው፡፡ የመኖርና ያለመኖር፣ የህልውና ነገር በመሆናቸው፣ በጋራም ሆነ በግል፤ በያንዳንዷ ደቂቃ ውስጥ ራሳችንን የምንፈልግበት፣ ትልልቅ የሚመስሉ ነገር ግን አጠገባችን ያሉ ዕውነታዎች ናቸው፡፡ ኑሯችንንና ልባችንን ለጥበብ ካላቀናን፣ ተሰርተው በሚጫኑ ሃሳቦች ስለምንዋዥቅ በሰባኪዎች፣ በጠንቋዮች በአምባገነኖችና በመሰሎቻቸው ስለምንታለል፣ ተፈጥሯችንን መኖር እንቸገራለን፡፡ ቅርባችን ያለውን ዕውነት ሩቅ እንፈልገዋለን፡፡
ወዳጄ፡- እጅህ በካቴና ቢታሰር፣ እግርህ በእግረ ሙቅ ቢደመደም፣ ካቴናው ይበጠሳል፣ እግር ብረቱም ይፈለቀቃል፡፡ በር ቢዘጋብህ ይበረገዳል፣ ቢቆለፍብህ ይከፈታል፡፡ በራስህ ሃሳብ ከታሰርክ ግን ማን ይፈተሃል? የፍቅር እስረኛ፣ የልማድ እስረኛ ልትሆን ትችላለህ። የማይጠቅሙህ ከሆኑ በሃሳብ ጉልበት ልታስወግዳቸው፣ ልትፋታቸው ትችላለህ። መላቀቅ እየፈለግህ ማሰብ ካልቻልክ ደግሞ ሊያከስሩህ፣ ሊያሳምሙህና ሊገድሉህ ይችላሉ። መንፈስህ ወይም ተፈጥሮህ የማይፈልገውን ነገር “እሸከመዋለሁ” ካልክ ተሸንፈሃል፡፡
ዐዋቂዎች፡- “ተፈጥሮ እንድትታዘዝህ ከፈለግህ፣ ልትታዘዛትና ልታከብራት ይገባል። ሲጋራዬን በፀሐይ ብርሃን ካለኮስኩ ብለህ ዕልክ አትጋባ፡፡ ልትረዳት ከቻልክ ግን እሱንም ታደርግልሃለች፡፡” ይላሉ፡፡
ወዳጄ፡- የተፈጥሮን ነገር ካነሳን አይቀር፣ ለኔ ኢትዮጵያዊነት ተፈጥሮዬ ነው፡፡ ማንም የሰጠኝ ወይም ሊሰጠኝ የሚችለው ነገር ሳይሆን የተሰራሁበት ሃሳቤ ናት፡፡ ከቶስ እራሴን ለራሴ ማን ይሰጠኛል? እራሴን ከራሴ ማንስ ይነጥቀኛል? በሌሎች አገራት ብኖር ወይም ሌሎች እዚህ ቢኖሩም አገሬ “ውስጤ ናት!!” ነፃነቴና መኩሪያዬ!!
ሰልማን ሩሽቲ …“በየጎዳናው ላይ ከሰዎች ጋር መጋፋት፣ ቆም ብሎ ከሱቅ የሆነ ነገር መግዛት፣ አረፍ ብሎ ማኪያቶ መጠጣት ወዘተ ትንሽ የሚመስል ትልቅ ነፃነት ነው” ብሎ ነበር፡፡
ወዳጄ፡- በራስህ ሃሳብ መታሰር፣ እራስን በራስ ነፃነት ማሳጣት፣ ከእስር ሁሉ የከፋ እስር ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ሪፖርተር ጋዜጣ ያስነበበንም ይሄን ሃቅ ነው፡፡ የውሸት ኮሌጅ አቋቁሞ፣ የዶክትሬትና የማስተርስ ዲግሪ ለማይገባቸው እየሸጡ፣ የመንግስት ገንዘብ መዝረፍ “አሳፋሪ ነው ተብሎ የሚታለፍ ብቻ አይደለም፡፡ አገራችን አሁን ለመውጣት ከምትፍጨረጨርበት አረንቋ የገባችው----በእንደዚህ ዓይነት በሌሎች የተሰሩ ሰዎች ስለምትመራ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ መኪና መንዳት ለማይችል ሰው፤ መኪናና መንጃ ፍቃድ ሰጥተህ “ንዳ ትችላለህ!” ማለት “ሂድና ግደል” ወይም “ሙት” ከማለት በምን ይለያል? … ከሰጭዎቹ ተቀባዮቹ ደግሞ ይብሳሉ፡፡ እዚህ ጋ ነው አለማሰብ! … በተሰራ ሃሳብ መንከላወስ፣ በተጫነ ሶፍትዌር መንቀሳቀስ … እዚህ ጋ ነው ነፃነት ማጣት! …. ጥፍር ግጥም አድርጎ ራስን በራስ ማሰር!!
ወዳጄ፡- ራሱን ያታለለ፣ ሌላውን ከማታለል፣ ራሱን ያዋረደ፣ ሌላውን ከማዋረድ፣ ራሱን የሰረቀ፣ ሌላውን ከመስረቅ፣ ራሱን የካደ ሌላውን ከመካድ፣ ራሱን ያልገነባ፣ ሌላውን ከማፍረስ ወደ ኋላ አይመለስም፡፡ የራሳቸውን ዋጋ ለማያውቁ ሰዎች ሌሎች ዋጋ ይተምኑላቸዋል፡፡ ዋጋቸውን የማያውቁ ግን የሌሎን አይቀንሱም። የብስለት ምልክት ነውና” ሰሞኑን ኢንተርኑት ላይ የተነበበ ፅሁፍ … እንዲህ ይላል፡- “ብስለት ማለት የአእምሮ ሰላምህን ከሚፈታተኑ ሰዎችና ሁኔታዎች፣ ክብርህን ከሚያወርዱ ማንነትህን ከሚያሳንሱ ነገሮች መሸሽ መቻል ነው፡፡ (Maturity is learning to what away from people and situations that threaned your peace of mind, self respect values and morals)
ወዳጄ፡- የጥያቄውን መልስ እንዳትረሳ። በበኩሌ “አላውቀውም” … አንድ ቀልድ ላጫውትህ፡፡ … ሰውየው እየደጋገመ ‹ሁለትና ሶስት ሲደመር ስንት ነው?› የሚል ዓይነት ጥያቄ እየጠየቀ ሲያስቸግረው … አጅሬ ‹ስድስት ነዋ› ብሎ መለሰለት፡፡ ሰውየውም “እንዴ? … አምስት ነው እንጂ ስድስትማ አይደለም” ሲለው፤  “ምታውቀውን ለምን ትጠይቀኛለህ?” አለው አሉ፡፡
ሠላም!!

Read 647 times