Saturday, 09 February 2019 13:15

(ቅኝት) “የመረጃ ነፃነት በኢትዮጵያ”

Written by  በደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)


    በአንድ ስሙ ድቅድቅ ጨለማ ተብሎ የመረጃ ነጻነትን ጎሮሮ አንቆ ሲጥ ካደረገው የደርግ ሥርዓት በኋላ የመጣው አባባይ መንግስት፤ ለመጀመሪያዎቹ የሥልጣን ዘመናት የመረጃ ነፃነት ፍንጭ አሳይቶ እንደነበር ሁላችንም እናስታውሳለን፡፡ ይሁንና ለቀቅ ያደረገውን ማሰሪያ ገመድ እያጠበቀ መጥቶ ወደ ለውጡ ዋዜማ አካባቢ ሙሉ ለሙሉ እስትንፋሱን ነጥቆት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ሰዎች የመናገርና የመጻፍ መብታቸውን አጥተው ነበር፡፡
አሁን እዚያ አሮጌ ሀሳብ ላይ መዳከር አይደለም እቅዴ፤ የዛሬ ጽሑፌ ዓላማ ሰሞኑን ለገፀ ንባብ የበቃውን የአቶ አማኑኤል አብርሃም “የመረጃ ነፃነት በኢትዮጵያ” መጽሐፍን በወፍ በረር መቃኘት ነው፡፡ መጽሐፉን ሳየው ቀደም ባሉት ዓመታት ቢታተም የተሻለ ነበር የሚል ምኞት ቢኖረኝም፣ ያኔ ታተመም አልታተመም መንግስት ላይ ለውጥ የሚያመጣ አልመስል ስላለኝ አሁን መታተሙ ለመጪው ጊዜ ህይወታችን፣ ለቀጣዩ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ህብረተሰብ ግንባታ ይጠቅማል በሚል “እሰየው!” ብያለሁ፡፡
መፅሐፉን ከውጭ ሳየው ከተሰማኝ ስሜት ይልቅ ውስጡ ገብቼ ያየኋቸው፣ ያነበብኳቸው ሀሳቦች አስደምመውኛል፡፡ እውነት ለመናገር፣ ስለ መረጃ ነፃነት ዕውቀት ማግነት የፈለገ ሰው ሁሉ ቢያየው ከዓለም አቀፍ ጅማሬና ፅንስ ጀምሮ ዕድገቱንና መጎልበቱን ከታሪክ ጋር እያጣጣመ ስላቀረበው አስተማሪነቱ የትየለሌ ነው፡፡ የዓለም አቀፉን ተሞክሮ ለውጥና ተግዳሮት ከተገነዘብን በኋላ ወደ ሀገራችን የመረጃ ነፃነት ህግና ደንብ ይነግረናል፡፡
በመጽሐፉ ምረቃ ላይ ተገኝቼ ከመድረክ አስተዋዋቂው እንደሰማሁት፣ ደራሲው አቶ አማኑኤል አብርሃም ከጋዜጠኝነት ትምህርቱ ባሻገር፣ የህግ ትምህርትም እንደተማረ ማወቅ ችያለሁ፡፡ መጽሐፉ ውስጥ ላሉት ህግና ጋዜጠኝነትን ያጋመዱ ጉዳዮች በተሻለ ሁኔታ መሰናሰል ምክንያቱ ይህ እንደሆነም መገመት አላቃተኝም፡፡ መጽሐፉ የሚጀምረው የመረጃን ምንነትና ትርጉም በማስረዳት ነው። በዚህ መነሻም በእንግሊዝኛው Information እና Data በሚል አስቀምጦት፣ ልዩነቱንና  ዝምድናውን በማሳየት ወደፊት ይጓዛል። ጠቅለል አድርጎ ሲገልፅም፤ “መረጃ ኃይል፣ ጊዜና ሀብት ነው” ይለዋል፡፡ ለሰላም፣ ለንግድና ለመጓጓዣ፣ ለፖለቲካዊ ግንኙነት በጥቅሉ ለሰው ልጆች የዕለት ተዕለት ኑሮ፣ መረጃ ወሳኝ መሆኑን ያስነብበናል፡፡
መረጃ እንደየቱም የአማርኛ ቃል በየዐውዱ የተለያየ ትርጉም እንደሚሰጥ ያመለከተው  ደራሲው፤ የአፍሪካ ሰብዓዊ መብት ቻርተር መረጃ የሚይዛቸውን ነገሮች እንዲህ አስቀምጧቸዋል፡፡
መረጃ በአካላዊ ባህሪው (ማለትም ቅጂ፣ ምልልስ፣ ፋክት፣ የግል አስተያየት፣ ምክር፣ የውስጥ ማስታወሻ፣ ዳታ፣ ስታቲስቲክስ፣ መጽሐፍ፣ ሥዕል፣ ዕቅድ፣ ካርታ፣ ዲያግራም፣ ፎቶግራፍ፣ የድምፅ ወይም የምስል ቅጅ፣ ወይም ማንኛውም ሊጨበጥ የሚችልና የማይጨበጥ ቁስ እንዲሁም ቅርጽ እና መረጃው ተዘጋጅቶ በተቀመጠበት ሚያም) ሳይወሰን ማስተግበሪያ ህግ በተደነገገው መሰረት፤ መረጃ ለማግኘት ጥያቄ በቀረበለት አካል ባለቤትነት ወይም ቁጥጥር ስር የሚገኝ ማንኛውም የጽሁፍ ማስረጃነት ያላቸው ልዩ ልዩ ማስረጃዎች ዋና ወይም ኮፒ ያካትታል፡፡
ይህም ማለት እኛ በዘልማድ እንደምናስበው መረጃ ማለት ለሬዲዮና የፕሬስ ውጤቶች የሚሰጥ መግለጫና ማብራሪያ ብቻ ሳይሆን ሳይንሱ ዘርፈ ብዙና ሁሉን አቀፍ እንደሆነ ያሳየናል፡፡ ታዲያ መረጃ ስንል፣ መረጃ የማግኘት መብት የስልጣኔና የዕድገት ምልክቶች አካልና መዘውርም እንደሆነ እግረመንገዱን በጥብቅ ያስታውቀናል፡፡
መብቶች ስንልም፤ መጽሐፉ ሆፊልድ የተባሉን ሰው ዋቢ አድርጎ 1) የሚከበር መብት፣ 2) ነፃነት የማግኘት ችሎታ 3) የማይደፈር መብት ብሎ በሶስት ይከፍልልናል፡፡ መብት፤ አዎንታዊና አሉታዊም ነው ይለናል፡፡
እንደ መጽሐፉ፤የመረጃ ነፃነት መብት በዓለም አቀፍ ደረጃ ህጋዊ ዕውቅና ካገኘ ምዕተ ዓመት አልደፈነም፡፡ ጨቅላና እምቦቀቅላ ነው። ይሁንና እንደየ ሀገራቱ ስልጣኔና ዕድገት ከፊሉ ሲድህ፤ ሌላው/ጡጦ እየጠባ፣ ያለለት ደግሞ በእግሩ ቆሞ እየሄደ እንደሆነ በማንፀሪያዎች ተደግፎ ይነበባል፡፡
የመረጃ ነፃነት ሲባል፤ ይህ ነፃነት ፋይዳው ምን እንደሆነ፣ በሀገራችን ህዝቦች ህይወት ላይ ምን ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ብዙም ላልተረዳን ሰዎች፤ መጽሐፉ በቅደም ተከተል ጥቅሞቹን እንዲህ እያለ ይነግረናል፡፡
የመረጃ ነፃነት፤ የዜጎችን የመወሰን አቅም ያጎለብታል
የመረጃ ነፃነት፤ ነፃ፣ ገለልተኛና የሃሳብ ብዝሐነት ለጠበቀ መገናኛ ብዙኃን ዕድገት ወሳኝ ነው
የመረጃ ነፃነት፤ ዴሞክራሲን ያጠነክራል (ዴሞክራሲም አሳታፊ፣ የውክልና ዴሞክራሲ፣ በውይይት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲ) በሚል ሶስት ፈርጅ እንደ የባህርይውና አውዱ ይቀመጣል
የመረጃ ነፃነት መልካም አስተዳደርን ያሰፍናል
እንግዲህ ይህ ማለት፣ ያለ መረጃ ነፃነት፣ የሰው ልጅ ህይወት፣ ከንቱና የከንቱ ከንቱ ነው ማለት ነው፡፡ ያለ እነዚህ ነገሮች የሰው ልጅ በዚህ ምድር ላይ ምን ዓይነት ኑሮ ሊኖር ይችላል? የተጠቀሱት ጉዳዮች ካልተሟሉለት ከሌሎች እንስሳት የሚለየው መስመርስ ምንድነው? …
ታዲያ ለዚህ የመረጃ ነፃነት መሟላት መንግስት ዋነኛው ሞተር ይሁን እንጂ ሲቪክ ማህበራትና የግሉ ዘርፍም ሚናቸው ቀላል አይደለም፡፡ እነዚህ ሶስቱ እጃቸውን ካላስገቡበት፣ የተሟላና የተስተካከለ የመረጃ ነፃነት ስርዓት ማግኘት አይታሰብም። በመንግስት በኩል ህግ አውጪው፣ ህግ ተርጓሚውና አስፈጻሚው፣ ተገቢ ተሳትፎ ያደርጉ ዘንድ ግድ ይላል፡፡ ሌላውና ትወናው ግድ የሚለው ህብረተሰብ ራሱ ነው፡፡ የህዝቡ ተሳታፊነት ለመረጃ ነፃነት ስኬት ትልቅ ድርሻ አለው፤ ይላል መጽሐፉ፡፡
ከላይ ከጠቀስኳቸው የመረጃ ነፃነትን በሚወስኑ ተዋናዮች፣ መንግስት ዋና መሆኑን መጽሐፉ እንዲህ አስቀምጦታል፡- “የመረጃ ነፃነት መኖር አለመኖርን የሚወስነው መንግስት ነው፡፡ አምባገነን መንግስታት ህብረተሰቡ ሊያገኛቸው የሚገባቸውን መረጃዎች ይወስናሉ፡፡ (ይህ ማለት መረጃ በነፃነት ማግኘት አይችልም፡፡) ይህንን ነፃነት ማጣት፣ ከእኛ ይበልጥ ያወቀው እምብዛም ነው፡፡
በመጽሐፉ ውስጥ በጉልህ ከተነሱት ጉዳዮች አንዱ፣ የነፃ መገናኛ ብዙኃን ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ደግሞ ባሳለፍናቸው ዓመታት በእጅጉ ሀገራችንን የተፈታተኑና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ህልማችን እውን እንዳይሆን ከተገዳደሩን እንቅፋቶች ዋነኛው እንደነበር የምናስታውሰው ነው፡፡
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበረው ስመ-ጥር ፕሬዚዳንት ቶማስ ጀፈርሰን፣ ቤንጃሚን ዋሪንግ ለተባለው ሰው በጻፈው ደብዳቤ እንደሚለው፤ “In every country where man is there to think and to speak, differences of opinion will arise from difference of perception, and the imperfection of reason” ቢልም፣ ይህ ህልም ግን እውን የሆነላቸው ሀገራት ዕድለኞች ብቻ ናቸው፡፡ የኛ ቢጤዎችም ዕድል ፈንታቸው መታሰር፣ መገደል መሳደድ ነበር፡፡ ይህንን ጨለማም ያለፍነው ይመስላል፡፡
መጽሐፉ ኔልሰን ማንዴላን ጠቅሶ እንዲህ አስቀምጧል፡፡
“ተቺ፣ ገለልተኛና በምርመራ የጋዜጠኝነት ስራዎች ላይ የሚተኩሩ መገናኛ ብዙኃን፤ ለማንኛውም ዴሞክራሲ የጀርባ አጥንት ናቸው፤ ፕሬስ ከመንግስት ጣልቃ ገብነት ነፃ መሆን አለበት፡፡” እያለ ይቀጥላል፡፡
እኛ ሀገር ጋዜጠኛ ያየውን፣ የሰማውንና የሚያውቀውን መጻፍ እንዳይችል ተደርጎ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። በ1690 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) አሜሪካ ውስጥ የጋዜጣ ስራ ሲጀመር፤ ሀሳቡና ፍላጎቱ መንግስትን እንዲያስደስት ታስቦ ስለነበር፣ ውሎ ሲያድር ብቅ ያሉት ሰዎች፣ መንግስትን በመተቸታቸው ወደ ዘብጥያ እንዲወርዱ ተደርጎ ነበር፡፡ ቤንጃሚን ፍራንክሊን የተባለው የአሜሪካ መስራች አባት በብዕር ስም የፃፋቸው መጣጥፎች፤ ለሌሎቹ መታሰር ምክንያት ሆነው ነበር፡፡ ግና ህልም ያለው መንግስት ሲመጣ፤ ትልቁ ቶማስ ጀፈርሰን፤ ነፃ ፕሬሶች ቢያማርሩትም “ቤቴን እስኪያቃጥሉት ድረስ እታገሳለሁ” በሚል የሰለጠነ ማንነት አሜሪካንን ትልቅ አድርጓታል፡፡ ጆን ኤፍ ኬነዲን የመሰሉ ለጥበቡና ፕሬሱ ቅርብ የሆኑ ሰዎች እርምጃውን አቃንተውታል፡፡ ለእኛም ይህ ዕድል በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ይመጣል ብለን እናምናለን! ለሁሉም ሀገር ዕድገትና ውድቀት፣ ህልም ያለው መሪ ወሳኝ እንደሆነም ሳይንሱና ታሪክ ይነግሩናል፡፡
የመረጃ ነፃነትን ጉዳይ ስናነሳ፣ የመረጃ ነፃነት ህጉ፣ የማዕዘን ድንጋይ እንደሆነ እናምናለን። “የመረጃ ነፃነት በኢትዮጵያ” የሚለው የአማኑኤል አብርሃም መጽሃፍም፣ በዚሁ ሀሳብ ላይ ትኩረት ሰጥቶ አስነብቧል፡፡
“የመረጃ ነፃነት ህግ ታሪክ ረዥም ዓመታት ወደ ኋላ ይመስለናል፡፡ በስካንዲቪያኗ አገር ስዊድን እ.ኤ.አ በ1766 ዜጎች በንጉሱ እጅ የሚገኝ መረጃን ጠይቀው ማግኘት እንዲችሉ የሚፈቅድ ህግ በፓርላማ የፀደቀበት ጊዜ ታሪካዊ ተደርጎ ይወስዳል” ይላል መጽሐፉ፡፡ በመለጠቅም አሜሪካ በ1967 ዓ.ም፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳና ኒውዝላንድ በተመሳሳይ ጊዜ፣ 1982 እንደወጡ መጽሐፉ ያሰምርበታል፡፡
በመረጃ ነፃነት ጉዳይ መደምደሚያውን ሀገራችን ላይ ያደረገው መጽሐፉ፤ በእኛ ዐውድ፣ ከባህላዊ የመረጃ ልውውጥ ባህሎች መነሻ በማድረግ፣ ህዝባችን ጥሩምባ፣ መለከትና ነጋሪት የመሳሰሉትን ይጠቀም እንደነበር በማውሳት ይጀምራል፡፡ ከዚያም በኋላ በ1910 ዓ.ም ለህትመት የበቃውን “አዕምሮ” ጋዜጣና ሌሎችም የመረጃ ምንጮችን እየተጠቀመ አሁን እስካለንበት የቴክኖሎጂ ዘመን ያደረገውን ጉዞ ይጠቅሳል፡፡ በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የወጣውን የ1931 ዓ.ም፣ በ1955 ዓ.ም የተሻሻለውን ህገ መንግስት ያስታውሳል፡፡
በተሻሻለው ህግም አንቀጽ 42 ላይ የሰፈረውን እንዲህ አስቀምጦታል፡ በመላው የንጉሰ ነገስት ግዛት ውስጥ በህግ መሰረት የንግግርና የጋዜጣ ነፃነት የተፈቀደ ነው፡፡
ለሀገር ፀጥታ፣ ለአስፈላጊ የሆነ ድንገተኛ ነገር በታወጀበት ጊዜ ካልሆነ በቀር በጽህፈት መላላክ ግንኙነት ላይ የመቆጣጠር ሥራ አይደረግም፡፡
ከዚህ በኋላ ሁለት መንግስታት ሀገሪቱን አስተዳድረዋል፡፡ አንደኛው መንግስት አንድ ፓርቲ፣ አንድ ተቀናቃኝ የሌለለው መንግስት በሚል ኮሙኒስታዊ መዝሙር አደንቁሮን አልፏል፡፡ ከዚያ በኋላ ያለው የኢህአዴግ መንግስትም ከዚያ ብዙም ባልተመቸ ሁኔታ ሀገሪቱን በመረጃ እጦት ድርቅ አቃጥሏታል። መጽሐፉ የኢህአዴግን መንግስት፣ የመረጃ ነፃነት ህጎች ዝርዝር አስቀምጧል፤ ምናልባትም ደራሲው የተወካዮች ምክር ቤት አባል በመሆኑ፣ የተሻለ ዕውቀትና ግንዛቤ ስላለው ፍትፍቱን አስፍሮታል፡፡ እኔ ግን የሚቀጥለውን የለውጡን መንግስት ጉዞ እንጂ ያለፈውን ጨለማ ማውራት አላስፈለገኝም፡፡   
ከማጠቃለሌ በፊት ግን “የመረጃ ነፃነት በኢትዮጵያ” የሚለውን መጽሐፍ፤ በጉዳዩ ላይ ዕውቀት እንዲኖረው ለሚፈልግና፣ ጥቅም ላይ ማዋል ለሚገባው የግልም ሆነ የመንግስት ድርጅት ሳልጋብዝ አላልፍም፡፡ ደራሲው ደግሞ በቀጣይ ህትመት ሊያሻሽላቸው የሚገባቸውን ግድፈቶች በበለጠ ሰርቶ እንዲያቀርብ አደራ እላለሁ፡፡
“የተከበሩ አቶ አማኑኤል አብርሃም”ን አንቱ ያላልኩት፣ ሰውየው ጋዜጠኛ በመሆናቸው ነው፡፡ በእዚህ ሰፈር “አንተ” የሚለው መጠሪያ የተሻለ ይወደዳል፡፡ የጥበብ ሰውና ጋዜጠኛ አንቱታ ቀንበሩ እንጂ ጌጡ አይመስለኝም፡፡      

Read 1330 times