Saturday, 16 February 2019 13:50

የኢሳት ጋዜጠኞች አገር ቤት ገብተዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በአሜሪካ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንን በማቋቋም ሲሰሩ የቆዩ ጋዜጠኞችና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ትናንት ወደ ሃገራቸው ተመልሰዋል፡፡
ጋዜጠኞቹ ትናንት ማለዳ 1 ሰዓት ላይ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሙያ አጋሮቻቸው፣ አክቲቪስቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎችና ፖለቲከኞች አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን አንጋፋው ጋዜጤኛና የጋዜጠኝነት መምህር ዶ/ር ማዕረጉ በዛብህ የእንኳን ደህና መጣችሁ ጉንጉን አበባ አበርክተውላቸዋል፡፡
ወደ ሃገራቸው ከተመለሱት የኢሳት ጋዜጠኖችና ባልደረቦች መካከል በስብሰባ መሃል የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ላይ ተቃውሞ ያቀረበው አበበ ገላው፣ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና፣ ገሊላ መኮንን፣ መሳይ መኮንን፣ መታሰቢያ ቀፀላ፣ ወንድማገኝ ጋሹ፣ እንግዱ ወልዴ፣ ደረጄ ሃ/ወልድ፣ አፈወርቅ አግደውና ሰርክ አዲስ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ኢሳት በሃገር ውስጥ መሰረቱን ለማስፋትና ራሱን በጠንካራ መሰረት ላይ ለማቆም የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እያደረገ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን የዚህ ንቅናቄ አካል የሆነው “የኢሳት ቀን በዛሬው ዕለት ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል፡፡
በዚህ ዝግጅት ላይ 20ሺህ ያህል ታዳሚያን ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
“ኢሳት ለሃገሬ” በሚል መሪ ቃል በሚከበረው “የኢሳት ቀን” ላይ አንጋፋና ወጣት ሙዚቀኞች ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ ተብሏል። በዚህ መድረክ ላይ ዛሬ ማለዳ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የአውሮፓ ፓርላማ አቧላና በምርጫ 97 የአውሮፓ ታዛቢ ቡደን መሪ አና ጎሜዝ ተገኝተው ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Read 8958 times Last modified on Saturday, 16 February 2019 13:54