Saturday, 16 February 2019 13:54

የለውጥ ሽታው ለቁጫ ህዝብ አልደረሰም ተባለ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

“የማንነት ጥያቄ ያነሱ ተማሪዎችና ሰራተኞች እየታሰሩ ነው” - የአካባቢው ተወላጆች
                          
          በአገሪቱ ላይ የመጣው የለውጥ ሽታ በአካባቢያቸው እንዳልደረሰ በደቡብ ክልል በጋሞ ዞን የሚገኙት የቁጫ ወረዳ ነዋሪዎች አስታወቁ። የቁጫ ብሔረሰብ ላለፉት በርካታ ዓመታት የማንነት ጥያቄው እንዲመለስለት በሰለጠነና በሰከነ መንገድ ከወረዳ እስከ ክልል ብሎም እስከ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አቤቱታ ሲያሰማ መቆየቱን ያስታወሱት የብሄረሰቡ ተወካዮች፣ አሁን በመጣው ለውጥ ጥያቄያቸው እንደሚመለስ በማመን በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ተማሪዎችን ጨምሮ በርካታ የመንግስት ሰራተኞች ለእስርና ለእንግልት እየተዳረጉ እንደሆነ አቶ ሀብታሙ ሃ/ጊዮርጊስና አቶ ተስፋዬ ፈለሃ የተባሉ የአካባቢው ተወላጆች ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
በቅርቡ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከተማሪዎችና ከተለያዩ ግለሰቦች የተውጣጡ ወደ 600 የሚጠጉ አባላት ወደ ሃዋሳ በመጓዝ፣ ለክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት አቤቱታ ማቅረባቸውን የተናገሩት አቶ ሀብታሙ፤ የክልሉ ብሄረሰቦች ምክር ቤት ኃላፊዎች ጉዳዩን በአግባቡ ካደመጡ በኋላ የቁጫን ብሔረሰብ ጨምሮ ለአራት ብሔረሰቦች እውቅና የመስጠቱ ጉዳይ በቅርብ እንደሚፈፀም ቃል መግባታቸውን አስታውሰዋል፡፡ በዚህ ጥያቄ መመለስ የስልጣን ወንበራቸው እንዳይነቃነቅ ፍራቻ ያደረባቸው የጋሞ ዞን አስተዳዳሪና የቁጫ ወረዳ ባለስልጣናት በቁጫ ብሄረሰብ ላይ የእስርና መብት እረገጣ ዘመቻ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ወደ ሃዋሳ አቤቱታ ለማቅረብ ከሄዱ ሰዎች ጋር አብረው ተጉዘዋል፤ የቁጫ ማህበረሰብ ባህላዊ ልብስ (ሻማጪያ) ለብሰዋል በሚል ከ12 በላይ ዕድሜያቸው 18 ዓመት ያልሞላና ለእስር ያልደረሱ ልጆችን ሰብስበው፣ በቁጫ ወረዳ ሰላም በር ከተማ ላይ ማሰራቸውን የገለፁት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ የመንግስት ሰራተኞች ሳይቀሩ ለእስርና ለስደት መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
አቶ ተስፋዬ ፈለሃ በበኩላቸው፤ በአገሪቱ ላይ በመጣው ለውጥ ሰዎች ከእስራት እየተፈቱ ባለበት በዚህ ወቅት ከለውጡ በተቃራኒ የቆሙ የጋሞ ዞንና የቁጫ ወረዳ አስተዳዳሪዎች በቁጫ ማህበረሰብ ላይ የመብት ረገጣውን ተያይዘውታል ብለዋል። እንደ ተወላጆቹ ገለፃ እነዚህ የለውጡ ተቃራኒ ባለስልጣናት፣ ብሄረሰብን ከብሄረሰብ ለማጋጨትና የማንነት ጥያቄውን ሌላ መልክ ለማስያዝ እየጣሩ ነው ካሉ በኋላ፤ በቅርቡ የቁጫ ማህበረሰብ የጋሞን ማህበረሰብ የሚያንቋሽሽ ስድብ እንደተሳደበ በማስመሰልና በወረቀት ፅፈው በመበተን፣ ሁለቱን ብሔረሰቦች ለማጫረስ ጋሞዎቹን ቀስቅሰው ከፍተኛ የጦርነት ድባብ ፈጥረው፣ ነገሩ በአገር ሽማግሌዎች በሳል ስልትና ትዕግስት በሰላም እንደተቋጨ በፎቶ አስደግፈው አቅርበዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የማንነት ጥያቄ አቀንቅነዋል በሚል ከስራ የተባረሩ ከ10 በላይ ሰዎች በወረዳው ሽግሽግ ሲደረግ ወደ ስራቸው ተመልሰው የነበረ ቢሆንም እነሱ ወደስራ ከተመለሱ በኋላ ነው የማንነት ጥያቄው ያገረሸው በሚል፣ እነዚህ ሰራተኞች ደሞዛቸው ታግዶ በችግር ላይ መሆናቸውን ተወላጆቹ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ኃላፊ አቶ ለማ ጉዙማ፤ የቁጫ፣ የዶርዜ፣ የወለኔና የደንጣ የማንነት ጥያቄ ተገቢና ምላሽ ሊሰጠው የሚገባ ሆኖ ሳለ በመዘግየቱ ይቅርታ መጠየቃቸውንና በቅርቡ ምላሽ እንደሚሰጥበት ቃል መግባታቸውን የተናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ይሄ ያበሳጫቸው የዞንና የወረዳው ባለስልጣናት በብሔረሰቡ ላይ እያደረሱ ያሉት ኢ-ሰብአዊ ድርጊት በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡
የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ አርኮ ደምሴ በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲጡን ስልክ ደውለን፣ ስለ ጉዳዩ ካስረዳናቸው በኋላ “መልሳችሁ ደውሉ” የሚል ምላሽ ቢሰጡም፣ ስልካቸው ባለመነሳቱ ሃሳባቸውን ማካተት አልተቻለም፡፡

Read 7402 times