Saturday, 16 February 2019 14:08

ኩራት፣ ኩራት አይልሽም ወይ፣ የ‘አክቲቪስቱ’ አይደለሽም ወይ…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(9 votes)

  እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ ‘የምናምን ዓመት፣’ ‘የምናምን ዓመት’ የሚባል ነገር አለ አይደል… ዘንድሮ ለእኛ ደግሞ ‘የቃለ መጠይቅ ዓመት’ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ልጄ… ዘንድሮ እንደ ምንም ብሎ በሆነ ቲቪ ጣቢያ ቃለ መጠይቅ ካልተደረጉ ‘ይህ እድል’ ሊያመልጥ ይችላላ! (አንዳንዶቹን ስናይ በጋዜጠኞቹ ተፈልገው፣ ተጠይቀው ስቱዲዮ የገቡ ሳይሆን በእሽቅድድም የገቡ ይመስላሉ፡፡ እናማ…  ለበርካታ ዓመታት ‘በውጪ አገር ሆኖ ሲታገል የኖረ አክቲቪስት’ ልናቀርብ ነው፡፡
ጠያቂ፡— ተመልካቾቻችን፤ በዛሬው ዝግጅታችን የምናቀርበው ኑሯቸውን በውጪ ሀገር ያደረጉና ላለፉት ሀያ ሰባት ዓመታት  ሲታገሉ የኖሩት አክቲቪስት አቶ… ናቸው፡፡ እንኳን ደህና መጡ፡፡
‘አክቲቪስት’፡— አንኳን ደህና ቆያችሁኝ፡፡ (ሙሉ ልብሷ ግን ሸላይ ነችሳ!)
ጠያቂ፡— ከሀገር ከወጡ ምን ያህል ጊዜ ሆነዎት?
‘አክቲቪስት’፡— እ…አይ ቲንክ  ወደ ሀያ፣ ሀያ አንድ ዓመት ያህል ይሆናል፡፡
(አንድ ጊዜ ቆዩኝማ፣ ከሀያ አንድ ዓመት በፊት ወጥተው ሀያ ሰባት ዓመት ሙሉ ‘በውጭ ሀገር’ አክቲቪስት የሆኑት… የዓመት አቆጣጠር ተጭበርብሮ ነው ወይስ ምንድነው!)
ጠያቂ፡— እስቲ ስለ አወጣጥዎ ይንገሩን፡፡
‘አክቲቪስት’፡— በአጭሩ ለመናገር አይደለም መኖር፣ በነጻነት ኦክሲጂን መተንፈስ አንኳን አቅቶኝ ነበር፡፡ (“በለው!” አለ ቱርኩ አልያናክ!)  በአግር በለው፣ በመኪና በለው፣ መዝናኛ ስፍራ በለው… ብቻ ምን ልበልህ ሀያ አራት ሰዓት ሙሉ ሲከታተሉኝ ነው የሚውሉት፡፡ በቃ ከአነሱ ጋር መሯሯጡ ሰለቸኝና ወጣሁ፡፡
ጠያቂ፡— ለምንድነው ሲከታተሉዎት የነበረው… የተቃዋሚ ፓርቲ ከሚባሉት ውስጥ አባል ነበሩ እንዴ?
‘አክቲቪስት’፡— አባል እንኳን አልነበርኩም፡፡
ጠያቂ፡— ታዲያ ለምንድነው ይህን ያህል ክትትል የበዛብዎት?
‘አክቲቪስት’፡— ምን መሰለህ፣ እኔ አንድ ነገር አይቼ ካልተመቸኝ መደበቅ አልችልም፡፡ ስለ አገሪቱ ፖለቲካ ችግሮች በየስብሰባው ላይ በቀጥታ ነበር የምናገረው፡፡ ወዳጆቼ ‘ተው ይቅርብህ’ እያሉ ቢመክሩኝም እኔ የህዝቡን በደልና ስቃይ እያየሁ ዝም ማለት አልቻልኩም፡፡ (ቆይ ‘ታይም አውት!’…ከሂሳብ ክፍል ሁለት ሰዎች ስልጣን ላይ ያለውን አካል አይወዱም ተብለው ከሥራ የወጡት፣ አንተ ሹክ ብለህ ነው ሲባል አልነበረም እንዴ!)
ጠያቂ፡— በምን መልኩ ወጡ? ማለት ይሄን ያህል ክትትል ሲደረግብዎ ከነበረ ከሀገር ሲወጡ እንዴት ዝም ተባሉ?
‘አክቲቪስት’፡— ሰተት ብዬ በኤርፖርት በአፍንጫቸው ስር እኮ ነው የወጣሁት፡፡ (ሰውየው እኮ፣ አይደለም በዓይነ ቁራኛ ሊጠበቅ ፣ መደበኛው ሥራ ላይ አለመኖሩን መሥሪያ ቤቱ እንኳን ያወቀው እኮ በዘጠነኛው ቀን ነው!)
ጠያቂ፡— ተመልሰው ወደ ሀገር ሲገቡ የነበረውን አቀባባል እንዴት አገኙት?
(እንግዳችን ራሳቸውን  ደፋ አድርገው ስለተከዙ ጥቂት ሴኮንዶች ታገሱን…)
‘አክቲቪስት’፡— ኢንክሬዲብል!... ኢንክሬዲብል!...
(ራሱን ይወዘውዛል) ኢንክሬዲብል!... (እኔ የምለው ሀያ ዓመት ፈረንጅ አገር ኖሮ ያለ ‘ኢንክሬዲብል’...ሌላ ‘የፈረንጀ አፍ’ አያውቅም እንዴ! አታናግሩና…ቢረሳ፣ ቢረሳ አንድ ሰሞን በሳምንት ሦስት ቀን ሲሰለፍባት የነበረችው ‘ሱፕ ኪችን’ የሚሏት ነገርስ!  ቂ…ቂ…ቂ…)
ጠያቂ፡— ውጭ ሀገር በነበሩበት ጊዜ ከፍተኛ ትግል ሲያካሂዱ እንነደበር የዛሬ ወር ገደማ በከፈቱት ፌስቡክ ገጽዎ አይቼ ነበር…
‘አክቲቪስት’፡— እውነት ነው፡፡
ጠያቂ፡— ለመሆኑ ሰዉ በአክቲቪስትነት ያውቀኛል ይላሉ?
‘አክቲቪስት’፡— ኦፍ ኮርስ! (ሁለተኛዋ ‘የፈረንጅ አፍ’) ያው እኮ አቀባባሉ ላይ የታየ ነው! (ቂ…ቂ…ቂ… ምስኪን፣ ብዙዎቻችን ለምን እንወጣ እንደነበር አያውቅም!)
ጠያቂ፡— ይህን ጥያቄ የጠየቅሁዎት ተመልካቾቻችን ጠይቅልን ስላሉ ነው፡፡ እንደሰማሁት በአውሮፕላን ጣቢያ የነበሩ ብዙ ሰዎች “ይሄ ደግሞ ማን የሚሉት ነው?” ሲባባሉ ነበር ተብለዋል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ የሰሙት ነገር አለ?
‘አክቲቪስት’፡— እንደዛ የሚያስቡ ሊኖሩ ይችላሉ…ምን መሰለህ፣ እኔ ሳደርግ በነበረው ትግል ብዙ ጠላቶች አፍርቻለሁ፡፡ እና…
ጠያቂ፡— ይቅርታ… እኔ ለመጠየቅ የፈለግሁት አውሮፕላን ጣቢያ ተገኝተው ስለነበሩት ሰዎች ነው። እንደውም ስምዎ ከሌላ ሰው ጋር ተምታቶባቸው ነበር ይባላል…
‘አክቲቪስት’፡— አየህ ትግል ማለት እንደዚህ ነው፣ እመነኝ ይሄ ስም ማጥፋት ይቀጥላል፡፡
ጠያቂ፡— እርስዎን ለማነጋገር ሳስብ ፌስቡክ ላይ ሲጽፏቸው ለነበሩት የተሰጡት ኮሜንቶችን ስመለከት ነበር፡፡
‘አክቲቪስት’፡— አንደ እውነቱ እኔ የፌስቡክ ኮሜንቶች አላይም…
ጠያቂ፡— ከስቱዲዮ ውጪ ስናወራ የፌስቡክ ገጽዎ፣ ከህዝብ ጋር የምገናኝበት ነው ብለውኝ ነበር እኮ! ታዲያ ኮሜንቶች ካላነበቡ የህዝቡን ስሜት በምን ሊያውቁ ይችላሉ!
‘አክቲቪስት’፡— ጉዳዩን ካነሳኸው አይቀር ልንገርህ… አደራጅተውብኛል…እየሰማኸኝ ነው! አደራጅተውብኛል!
ጠያቂ፡— አልገባኝም…
‘አክቲቪስት’፡— አንድ ነገር ገጼ ላይ ስለጥፍ እየተከታታሉ ስሜን የሚያጠፉና የሚሳደቡ ሰዎችን አደራጅተውብኛል፡፡
ጠያቂ፡— እርስዎ ላይ?
‘አክቲቪስት’፡— ኦፍ ኮርስ! እንደሰማሁት ለእኔ ብቻ የተመደቡ አስራ አራት፣ አስራ አምስት እሚሆኑ አሉ፡፡
ጠያቂ፡— ይቅርታ… አሁን እኮ ነገሮች እየተለወጡ ነው፣ እርስዎ ላይ እንዲህ በማድረግ ምን ይጠቀማሉ?
‘አክቲቪስት’፡— ቂም ነዋ!  ያንን ሁሉ ዓመት ሳጋልጣቸው ስለኖርኩ ቂም ነው፡፡
ጠያቂ፡— ግን ደግሞ እኛ በሚዛናዊነት የምናውቃቸው ሰዎችም ስለ እርስዎ ጠንከር ያሉ ትችቶች ነው የጻፉት፡፡
‘አክቲቪስት’፡— ስማኝ፣ አሁን አኮ ፌስቡክ በአጠቃላይ የሥራ ፈት መሰብሰቢያ ሆኗል፡፡
ጠያቂ፡— ቢሆንም አንድ ሁለቱን ለምሳሌ አነሳለሁ…አንድ በወገንተኝነት የማንጠረጥረው ሰው በጻፈው ኮሜንት… “ይሄን ፊክሽንህን ዲሲ ውስጥ ጥበቃ በምትሰራበት ሞል ላሉ አለቆችህ ንገራቸው። አንተ ደግሞ በየሀበሻው ሬሰቱራንት እየዞርክ በሰው ገንዘብ ከመጠጣት ሌላ አንድ ቀንስ ተቃውሞ ሰልፍ እንኳን ወጥተህ ታውቃለህ!” ይላል፡፡ በዚህ ላይ የሚሉት አለ?
‘አክቲቪስት’፡— ካልኩህ ሰዎች መሀል አንዱ ነው…እየተከፈለው የሚጽፍ ነው…
ጠያቂ፡— ሊሆን ይችላል…ግን እኮ ደግሞ ፌስቡክ ላይ በጣም ብዙ ከማንም በላይ ጭፍን ጥላቻ ሳይኖራቸው፣ ለማንም  ጭፍን ድጋፍ ሳያደርጉ፣ ለሀገራቸው በንጹህ ልብ የሚጮሁ እኮ ብዙ ናቸው፣ አሁን የጠቀስኩልዎት ሰው፣ ከእነሱ እንደ አንዱ የምናየው ነው፡፡
‘አክቲቪስት’፡— እባክህ ሁሉም ያው ናቸው፡፡
ጠያቂ፡— በነገራችን ላይ እርስዎን ለማናገር ስወስን፣አሜሪካ ካሉ ፖለቲካ ውስጥ ከሚሳተፉ ወዳጆቼም አስተያየት ለማግኘት ሞክሬ ነበር፡፡ ግራ የገባኝ፣ አንድ አስሩን ያህል ጠይቄ ማናቸውም ሊያውቁዎት አልቻሉም፡፡
‘አክቲቪስት’፡— እኔ እኮ እንደሌሎቹ እዩኝ፣ እዩኝ አልልም፡፡ ሰልፍ እንኳን ስወጣ በሻርፕና በሆነ ነገር ተሸፋፍኜ ነው፡፡
ጠያቂ፡— አሜሪካም ሆነው ይከታተሉኛል ብለው ይፈሩ ነበር ማለት ነው?
‘አክቲቪስት’፡— እዚህ ቤተሰቦቼን የሆነ ነገር ቢያደርጓቸውስ! ደግሞ እኔ ሰልፍ የምወጣው ስሜቴን ለማንጸባረቅ እንጂ በቴሌቪዥን ለመታየት አይደለም፡፡
ጠያቂ፡— ወደ አሜሪካ ተመልሰው ይሄዳሉ?
‘አክቲቪስት’፡— ኔቨር! ኔቨር!... ትግሉ አዚህ ደረጃ ደርሶ እንዴት ነው፣ በዚሀ ሽግግር ጊዜ ህዝቡን ትቼ የምሄደው!
ጠያቂ፡— የማይሄዱት በትግሉ ለመቀጠል ነው?
‘አክቲቪስት’፡— አዎ፣ የማልሄደው በትግሉ ለመቀጠል ነው፡፡
(ቆይ ከይቅርታ ጋር… አይ.አር.ኤስ እየፈለገህ ነው የተባለው ነገርስ! ቤትህና መኪናህ ሞርጌጅ ክፍያ መክፈል ባለመቻልህ መነጠቅህስ! በሀበሻ ሬስቱራንት ሰዉ አንተ መጋበዝ ሰልችቶት ጀርባውን ማዞሩስ!
ጠያቂ፡— እኔ ጥያቄዬን ጨርሻለሁ…የሚጨምሩት ካለ…
‘አክቲቪስት’፡— ትግላችን እዚህ በመድረሱ ትልቅ ደስታ ይሰማኛል፡፡ እስከመጨረሻው ከህዝቡ ጎን ለመቆም ቃል እገባለሁ፡፡ (ቆይ፣ ቆይማ! ማን ቃል ግባ አለህ! ይልቅ እኔ ጠያቂው ነኝ የህዝቡን ውድ ጊዜ ደግሜ በእንዳንተ አይነት ‘ፌክ አክቲቪስት’ ላለማጥፋት ቃል መግባት ያለብኝ!)
በነገራችን ላይ… ዘንድሮ የ‘አክቲቪስቱ’ን ብዛት ስናይ ለሀገራችን የሆነች ስንኝ ልንቋጥር ምንም አይቀረን፡፡
ኩራት፣ ኩራት አይልሽም ወይ
የ‘አክቲቪስቱ’ አይደለሽም ወይ፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 9048 times Last modified on Saturday, 16 February 2019 14:11