Saturday, 16 February 2019 14:13

“ለፈጣሪም፣ ለመንግስትም፣ ለራሱም የማይመች ሕዝብ”

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(5 votes)


          የጽሁፌን ርእስ ያገኘኋት ከፌስቡክ ነው፡፡ አበበ አለበል የተባለ ወዳጄ የፌስቡክ ግድግዳው ላይ “ለሰው፣ ለመንግስት፣ ለፈጣሪ የማትመች ህዝብ ሆይ! እንዴት አመሸህ?” የሚል አጭር መልእክት አስፍሮ አነበብኩና አቀማመጡን ገልብጬ ለዚህ ጽሁፌ ርዕስ ላደርገው ወደድሁ፡፡
ብዙ ሰዎች “ሕዝብ እንደ ሕዝብ አይሳሳትም ወይም ሕዝብ እንደ ሕዝብ እንዲህ አያደርግም…” ሲሉ እሰማለሁ፡፡ በበኩሌ በዚህ አባባል አልስማማም፡፡ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ይሳሳታል! ሕዝብ እንደ ሕዝብ ጥሩም መጥፎም ነገር ሊያደርግ ይችላል! ለምሳሌ፤ በ2ኛው የዓለም ጦርነት የጀርመን ህዝብ እንደ ሕዝብ በወሰደው “የእብደት” እርምጃ 6 ሚሊዮን አይሁዶች ተጨፍጭፈዋል፡፡ ዓለም ያወቀው፣ ፀሐይ የሞቀው ግፍ ተፈጽሟል፡፡ (ለዚህ አባባል ማረጋገጫ ይሆን ዘንድ እ.ኤ.አ. በ1933 እና በ1938 ሒትለርን የመረጠውን የጀርመን ሕዝብ ብዛት ልብ ይሏል)
በርግጥ እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ጀርመኖች ያበድንበት ሁኔታ አልነበረም፣ የለም፡፡ ይሄ ማለት ግን እንደ ሕዝብ የፈጸምነው ስህተት አልነበረም ማለት አይደለም፡፡ በበኩሌ ኢትዮጵያውያን እንደ ሕዝብ መጥፎ ተግባር ፈጽመዋል የሚል ድምዳሜ ላይ የሚያደርስ ማስረጃ አላገኘሁም፡፡ ይሁን እንጂ ከጥንት ጀምሮ ያለ ታሪካችንን ሳስተውል አንድ ነገር ተገንዝቤአለሁ፡፡ ይኸውም፡- የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ ህዝብ (እንደ የእምነቱ) ለፈጣሪው ህግጋት የመገዛት የተሟላ ባህሪ አለው ብዬ ለማመን እቸገራለሁ፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ለፈጣሪው ብቻ ሳይሆን ለሚያስተዳድረው ንጉስ ወይም መንግስታዊ የአስተዳደር ስርዓት የተመቸ እንዳልነበርና ዛሬም የተመቸ እንዳልሆነ አምናለሁ፡፡ የሚገርመው ነገር የኢትዮጵያ ህዝብ ለፈጣሪውና ለመንግስት ብቻ ሳይሆን፤ እርስ በርስ ያለው ግንኙነትም በሸፍጥ፣ በሸር፣ በተንኮል፣ በሃሜት፣ በሴራ፣… የተሞላ በመሆኑ ለራሱ ጭምር የተመቸ እንዳልሆነ በራሴ ህይወት ጭምር ያስዋልኩት ጉዳይ ነው፡፡ (እንዲህ ያለ ባህሪ ሊኖረን የቻለው ለምንድነው? የሚለውን ጥያቄ አንስተው ተመራማሪዎች ባህሪያዊ ጥናት ቢያደርጉ መልካም ነው)
በእኔ ተራ እይታ ኢትዮጵያውያን ለአምልኮም፣ ለአስተዳደርም፣ አብሮ ለመኖርም ምቹ ያልሆነ ባህሪ ሊኖረን የቻለው በሁለት ምክንያቶች ነው ብየ አስባለሁ፡፡ አንደኛው ምክንያት፤ ኢትዮጵያውያን እንደ ማህበረሰብ “እኔ የምለው ብቻ ትክክል ነው፣ እኔ ያልኩት ብቻ መፈጸም አለበት” የሚል ራስ-ተኮር (Self Centered) የሆነ ለዘመናት አብሮን የኖረ አስተሳሰብ ያለን በመሆኑ ይመስለኛል፡፡ እንዲህ ያለ ባህሪ ለፈጣሪና ለመንግስት ህግጋት ባለመገዛት የሚቆም አይደለም፡፡ እንዲህ ያለ አስተሳሰባችን የወለደው ግትርነት፣ አልሸነፍም ባይነት፣ ለመቻቻልና ለሰጥቶ መቀበል እድል አለመስጠት፣… የህዝቡን የእርስ በርስ ግንኙነት የፍቅርና የመተሳሰብ ሳይሆን የማሸነፍ፣ የመናናቅና የመጠፋፋት እንዲሆን አድርጎታል፡፡ የሚያሳዝነው ነገር እንዲህ ያለውን ማፈሪያ አስተሳሰባችንን ሸፋፍነን ለዘመናት መኖራችን ነው! (ይህንን እውነት በድፍረት በመጻፌ ሊወርድብኝ የሚችለውን የትችት ናዳ አውቀዋለሁ፣ ከዓመታት በኋላ ትውልድ እውቅና የሚሰጠው ሃሳብ እንደሚሆን ግን እርግጠኛ ነኝ)
ሁለተኛው ምክንያት፤ ኢትዮጵያውያን እንደ ማህበረሰብ የጋራ የሆኑ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮቻችንን እና ችግሮቻችንን አንጥሮ የማውጣትና ካለን ሀገራዊ ሀብት አኳያ በቅደም ተከተል (Priority) አስቀምጠን ምላሽ እንዲያገኙ የማድረግ ፍላጎት የሌለን መሆኑ ይመስለኛል፡፡ ይህም ማለት “ሁሉም ጥያቄዎቻችን ሂደቱን ጠብቆ ሳይሆን አሁኑኑ ምላሽ ማግኘት አለባቸው፣ ችግሮቻችን ዛሬውኑ መፈታት አለባቸው፣ ካልሆነ ጥንቅር ይበል” የሚል ችኩልነት የወለደው፣ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ዓይነት ራስ-ተኮር አመለካከት ነው፡፡
እንዲህ ያለው ለዘመናት የመጣንበት ራስ-ተኮር አመለካከት ከፈጣሪ ከመጣላት፣ ከመንግስት ከመጋጨት፣ እርስ በርሳችን ከመናቆር ውጪ ያስገኘልን አንዳች ፋይዳ አልነበረም፣ የለም፡፡ ለዘመናት አብሮን የኖረው ራስ-ተኮር አስተሳሰባችን እኛንም አላሳደገንም፣ ሀገራችንንም አላበለጸገም፣ ለትውልድ የሚተርፍ ነገር እንድናፈራ አልረዳንም። የተጓዝንበት ራስ-ተኮር አስተሳሰብ፣ ትውልድን ማዕከል ያደረገ የረጅም ዘመን ስትራቴጂ እንዲኖረን አላደረገም፡፡ ራዕይ አልባ በመሆናችን መጪውን ጊዜ በመተንበይ ዘመን ተሻጋሪ ስራ መስራት አልቻልንም። ድምር ውጤቱም ኋላቀርነት እንዲሆን አድርጓል፡፡
ዛሬ የምንገኝበት ወቅት ለኢትዮጵያውያን ህልውና እጅግ ወሳኝ ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅት እንዳለፉት ዘመናት ራስ-ተኮር አስተሳሰባችንን እና “እኔ ብቻ ትክክል ነኝ” የሚል ትምክህታችንን አጥብቀን ይዘን ለፈጣሪም፣ ለመንግስትም ለራሳችንም የማንመች ሆነን የምንቀጥልበት ወቅት አይደለም፡፡ ይህ ወቅት እንደ ህዝብ አረፍ ብለን የመጣንበትን ጎዳና በጽሞናና በሰከነ መንፈስ በመገመገም በቀጣይ ዘመናት መጪዎቹ ትውልዶች በሰላም፣ በፍቅር፣ በመተሳሰብና በጋራ ተጠቃሚነት የሚኖሩበትን አቅጣጫ የምናመላክትበት መሆን አለበት፡፡ ይህ ወቅት እንደ ማህበረሰብ የሃምሳ እና የመቶ ዓመት ግብ አስቀምጠን፣ ስትራቴጂ አውጥተን፣ በቅደም ተከተል የመስራት ንድፍ የምናዘጋጅበት ወቅት ነው፡፡ ይህ ወቅት ለኢትዮጵያውያን የድርድር፣ የምክክርና የውይይት ወቅት ነው፡፡ ይህ ወቅት ለኢትዮጵያውያን የጋራ ፍላጎቶቻቸውን አንጥረው በማውጣት የጋራ ህልማቸውንና የጋራ ግባቸውን የሚያስቀምጡበት ወቅት ነው፡፡ ይህ ወቅት ለኢትዮጵያውያን ከአሉባልታ፣ ከሃሜት፣ ከሴራና ከፍረጃ ወጥተው፣ የመተማመንና የመተሳሰብ መደላድል የሚያስቀምጡበት ወቅት ነው፡፡
ከላይ በዝርዝር ያስቀመጥኩትን “ህዝብ-ተኮር ሂስ” (ማህበራዊ ሂስ) የዚህ ጽሁፍ መንደርደሪያ አድርጌ ያቀረብኩት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ይህንን “ሂሳዊ” መንደርደሪያ ያቀረብኩት ከማህበራዊ ሞሜዲያ እስከ ጎጥ በተዘረጋ የነውጥ ኃይል እየተናጠ ያለው የጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዓብይ መንግስት ይዞት የመጣውን የለውጥ መንፈስ እጁን መትተን እንዳናስበትነውና ወደተለመደው የጉልበት አገዛዝ እንዳንመለስ ስጋት ስላደረብኝ፤ ቢያንስ ቢያንስ በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት በህዝቡ፣ በመንግስትና በፓርቲዎች ምን ምን ተግባራት ይከናውኑ? የሚለውን ጥያቄ በማንሳት የተወሰኑ ሃሳቦችን ለማካፈል ነው፡፡ ከዚያ በፊት አንድ ነገር ላስቀድም - የምሁራንን አስተያየት፡፡
የምሁራን ስጋትና አስተያየት
በዚህ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ይህቺን ማስታወሻ ለመጻፍ ስነሳ እንደተለመደው በዲላ ዩንቨርስቲ ከሚያስተምሩ ወዳጆቼ ጋር የሃሳብ ልውውጥ አድርጌ ነበር፡፡ ምሁራኑ የአሁኑን የኢትዮጵያ ሁኔታ ከቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ጋር በማነጻጸር “የገጠሙንን ፈተናዎች በሰከነ ሁኔታ ለመፍታት ጥረት ካላደረግን ኢትዮጵያ ከቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ በፈጠነ ሁኔታ የመበተን አደጋ ተጋርጦባታል፡፡ እንደ አልባንያ ድንበሯን የዘጋቺውና ‘ሶሻሊስት ሪፐብሊክ’ ለመባል ያቆበቆበቺው ትግራይ፤ የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት አካል ናት ለማለት የማይቻልበት ደረጃ ላይ መድረሷ እየተስተዋለ ነው፡፡ አደጋው ወደ ከፋ ደረጃ ከመሸጋገሩ በፊት ሁሉም ዜጋ እየሆነ ያለውን ነገር በጥንቃቄ ሊመለከተው ይገባል፡፡ ህዝብ ለዘመናት በከፈለው መስዋእትነት የተገነባችን ሀገር ባለመደማመጥና በእብሪት የጦር ቀጠና ልናደርጋትና ትንንሽ ሪፐብሊኮች እንዲፈጠሩ ምክንያት ልንሆን እንችላለን…” በማለት ስጋታቸውን ይገልጻሉ ምሁራኑ፡፡
በምሁራኑ እይታ ለዚህ ሁኔታ አንዱ መፍትሄ አሁን የሽግግር የሚመስለውን የመንግስት አስተዳደር መለወጥ ነው፡፡ ይህንን ለውጥ ለማምጣት ደግሞ ምርጫ ማካሄድ አስፈላጊ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ምርጫ ለማካሄድ የምንችልበት ነባራዊ ሁኔታ ላይ ነው ወይ ያለነው? በሀገሪቱ ያሉ ፓርቲዎች በምርጫ ለመሳተፍ ዝግጁ ናቸው ወይ? ህብረተሰቡ በምርጫ ተሳትፎ ለማድረግ የሞራልና የስነ-ልቦና ዝግጅት አለው ወይ? በሀገሪቱ ያለው ተጨባጭ የሰላም ሁኔታስ ነጻ ምርጫ ለማካሄድ ያስችላል ወይ? የሚሉትን ጥያቄዎች በማንሳት መተንተንና ስምምነት ላይ መድረስ አስፈላጊ ነው ይላሉ ምሁራኑ፡፡
ለእነዚህ ጥያቄዎች ተገቢው ምላሽ ከተገኘ በኋላ ደግሞ ምርጫውን በመጪው ዓመት ማካሄድ ይሻላል ወይስ ለተወሰነ ጊዜ ማራዘም ይሻላል? ምርጫው በመጪው ዓመት ካልተደረገ የኢህአዴግ ፓርላማ የጊዜ ገደቡ ያበቃል፡፡ እና ከዚያ በኋላ ምን ይደረጋል? ሀገሪቱን ማን ይምራት? የሽግግር መንግስት ይቋቋም ከተባለ የሽግግሩ መንግስት አባላት እነማን ይሁኑ?... በሚለው ላይ ተወያይቶ ከወዲሁ መወሰን ተገቢ ነው፡፡ ምርጫው ይራዘም ወይም አይራዘም የሚለውን ለመወሰን የፖለቲካ ትርፍና ኪሳራው (Political balance sheet) ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱና ለህዝቧ ያለው ፋይዳ ግምት ውስጥ መግባት ይኖርበታል ባዮች ናቸው ምሁራኑ፡፡
በዓለም ላይ በተለያዩ ሀገሮች አሁን እኛን እንደገጠመን ዓይነት መስቀለኛ መንገድ ማጋጠሙና የሽግግር ሂደት መፈጠሩ የተለመደ ነው፡፡ የሽግግርን ሂደት በአግባቡ ከተጠቀምንበት የተሳካ ስራ በመስራት ወደሚፈለገው ግብ ሊያደርሰን ይችላል። የሽግግርን ሂደት በሰከነ መንፈስ ካልተጠቀምንበት ግን ወደ ባሰ ሁኔታ ሊከተን ይችላል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ ሦስት የሽግግር ወቅቶች አጋጥመዋታል፡፡ በ1966፣ በ1983 እና አሁን፡፡ ሁለቱ ቀዳሚ የሽግግር ወቅቶች ብዙ ዋጋ የተከፈለባቸው ቢሆኑም በጉልበተኞች ተጠልፈው ዴሞክራሲያዊ ውጤት ሊያመጡልን አለመቻላቸው ይታወቃል፡፡ አሁን የተገኘው ሦስተኛው እድል እጃችን ላይ ነው ያለው፡፡ እናም፤ ካለፉት ስህተቶቻችን ተምረን ይህኛውን የመሸጋገሪያ ወቅት ሁሉንም ዜጋ ተጠቃሚ የሚያደርግ ውጤት እንዲኖረው በሰከነ መንፈስ መስራት ይጠበቅብናል፡፡
በሕዝቡ በኩል ምን ይደረግ?
ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ህዝብ እንደ ህዝብ (እንደየእምነቱ) ለፈጣሪው ህግጋት ተገዢ መሆን አለበት፡፡ ፈጣሪውን የሚፈራ ማህበረሰብ፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር (ፈሪሃ አላህ) ያደረበት ማህበረሰብ እንቅስቃሴው ሁሉ በሰከነ መንፈስ የሚከናወን ነው፡፡ ፈጣሪውን የሚፈራ ህዝብ መንግስትን “ሱሪ ባንገት አውልቅ” ከማለት ይልቅ ራሱን አደራጅቶ የመንግስትን በጎ ተግባራት ያግዛል። በተረጋጋ መንፈስ የመንግስትን ስህተት ያጋልጣል፣ ያወግዛል፡፡ ፈጣሪውን የሚፈራ ህዝብ ወቅትን ጠብቆ በሚካሄድ ምርጫ መንግስትን ለመቀየር እንደሚቻል ተገንዝቦ የሰለጠነ አካሄድ ይሄዳል እንጂ ለትንሹም ለትልቁም ነገር አደባባይ እየወጣ አይጮህም፣ የመንግስትን ተቋማት አያፈርስም፡፡ ፈጣሪውን የሚፈራ ህዝብ ይተዛዘናል እንጂ እርስ በርሱ አይጨካከንም፡፡ ፈጣሪውን የሚፈራ ህዝብ መስጊድ አያቃጥልም፡፡ ፈጣሪውን የሚፈራ ህዝብ ቤተ-ክርስቲያን አያጋይም፣ ቤተ-ጸሎት አያነድም። ፈጣሪውን የሚፈራ ህዝብ ዘርን መሰረት ያደረገ ጥላቻ አያራምድም፡፡ ፈጣሪውን የሚፈራ ህዝብ ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ ጥላቻ አያራምድም፡፡
በመሆኑም እኛ ኢትዮጵያውያን ሃይማኖት አለን የምንል ከሆነ፣ ፈጣሪን እንፈራለን የምንል ከሆነ የሀገራችንን ህግና ስርዓት አክብረን መብትና ጥቅማችንን የማስጠበቅ መንገድን መከተል ይገባናል። ፈጣሪን እንፈራለን የምንል ከሆነ ለመንግስት ህግና ስርዓት ተገዢ መሆን ይጠበቅብናል፡፡ ፈጣሪን እንፈራለን የምንል ከሆነ እርስ በርሳችን መገዳደላችንን መቆም አለብን፡፡ ይህንን ማድረግ የሰለጠነ ሰው ተግባር መሆኑን ልብ ልንለው ይገባል፡፡
ከመንግስት ምን ይጠበቃል?
ወደድነውም ጠላነውም የህዝብን ስልጣን ይዞ ዛሬም ሀገሪቱን የሚያስተዳድራት ፓርቲ አለ፡፡ ይህም ፓርቲ ኢህአዴግ ነው፡፡ አንዳንዶች ይህንን እውነታ ይዘነጋሉ፡፡ አንዳንዶች ዶ/ር ዓብይን የኢህአዴግ መሪ አድርገው አያዩዋቸውም፡፡ ኢህአዴግ ፖሊሲዎቹን ሳይለውጥ፣ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ “ዳዊቱን” እንዳነገበ የቀየረው መሪውን ነው፡፡ መሪው የመንግስትን አሰራር በህግና በዴሞክራሲያዊ አግባብ በማስተካከል፤ የሀገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር ለማስፋት ላለፉት አስር ወራት “አብዮታዊ” እርምጃዎችን እየወሰዱ መሆኑ ይስተዋላል፡፡ ይህ በጎ ጅምር ነው፡፡ ይህ በጎ ጅምር ግን በርካታ መሰናክሎች ተጋርጠውበታል፡፡ መሰናክሎቹ በጥበብና በትእግስት ካልታለፉ ለዘመናት ስንመኘው የነበረው ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን እውን የማድረግ ህልማችን “ህልም” ሆኖ ሊቀር ይችላል፡፡ ስለሆነም በመንግስት በኩል በሚከተሉት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ወቅታዊ እርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡
ቀደም ባሉት ዓመታት ኢህአዴግ በውስጡ አንጻራዊ ሰላም ነበረው፡፡ ከሌሎች ተቃዋሚዎች ጋር ግን ምንም ዓይነት ሰላም አልነበረውም። ኢህአዴግ ማንንም ስለማያምን እርጥቡንም ደረቁንም በጠላትነት ፈርጆ ነበር የሚንቀሳቀሰው - ባለፉት 27 ዓመታት፡፡ አሁን ግን ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኗል፡፡ ኢህአዴግ በውስጡ ሰላም የለውም፡፡ ከተቃዋሚዎች ጋር ግን (ጠመንጃ አንስተው ከነበሩት ጋር ጭምር) ሰላም ፈጥሯል፡፡ በመሆኑም፤ በአሁኑ ወቅት ኢህአዴግ ከፖለቲካ አኳያ ከሁሉ አስቀድሞ ማድረግ የሚገባው በውስጡ እየተንተከተክ ያለውን፣ የሀገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ችግር በዴሞክራሲዊ አግባብ መፍታት ነው፡፡ እንደ ገዢ ፓርቲ ኢህአዴግ ሰላም ሳይኖረው የሀገሪቱ ፖለቲካ ጤናማ ሊሆን አይችልምና! ይህንን ለማድረግ ደግሞ ኢህአዴግ የረጅም ጊዜ ልምድና የችግር አፈታት ስርዓት አለው፡፡
ከፖለቲካ አኳያ ሌላው መፈታት ያለበት መሰረታዊ ጉዳይ ምርጫው መቼ ይካሄድ የሚለው ነው፡፡ በዚህ ረገድ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ኢህአዴግ አስፈላጊውን ውይይት በማድረግ የምርጫ መርሐ-ግብር ላይ መስማማትና ለህዝብ ይፋ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መፍትሄ ማግኘት ያለበት ፖለቲካዊ ጉዳይ የሀገሪቱንና የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ ነው፡፡ እዚህም እዚያም መልካቸውን እየቀያየሩ የሚቀሰቀሱ ግጭቶች መቆም አለባቸው፡፡ ሃይማኖትና ብሔር ተኮር ቁርቋሶዎች እንዲገቱ፣ የቤተ-እምነቶች ቃጠሎ እንዲቆም፣ ዩንቨርስቲዎች ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራቸውን እንዲያከናውኑ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡
አንዳንድ ክልሎች ኢህአዴግን እያስፈራሩ መሆኑ ጭምጭምታ እየተሰማ ስለሆነ፣ የልዩነት መንስዔ ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱ ህልውና አደጋ የሆኑ እንደ አንቀጽ 39 እና 47 ያሉ የህገ መንግስቱ አንቀፆች ከምርጫ በኋላ ህዝብ ይሁንታ የሰጠው አዲስ መንግስት እስከሚመሰረት ድረስ ስራ ላይ እንዳይውሉ ማገድ (Suspend ማድረግ)… የመሳሰሉ ፖለቲካዊ እርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ መሆኑ ይታየኛል፡፡
ሌላው መንግስት እርምጃ ሊወስድበት የሚገባው ጉዳይ በኢኮኖሚው ዘርፍ ነው። በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት የመንግስት ኢንቨስትመንት ተቀዛቅዟል። የግል ሴክተሩም ተዳክሟል፡፡ በዚህም ምክንያት ስራ አጥነት የጎላ ችግር ሆኗል፡፡ በርግጥ ይህ ችግር በአንድ ጊዜ የሚወገድ እንዳልሆነ ይታመናል፡፡ ይህ ችግር በአንድ ጊዜ ሊወገድ ባይችልም እንዲረግብ ካልተደረገ፤ አደባባይ ወጥቶ ሲጮህ የነበረ ቄሮ (ወጣት) የሚበላው ሲያጣ ለመንግስት ፈተና መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ በመሆኑም ለገጠሩ ስራአጥ ወጣት በየሚኖርበት ወረዳና ዞን ኪስ መሬቶችን እየፈለጉ የሰፈራ ፕሮግራም በማዘጋጀት ወጣቱን የመሬት ባለቤት ማድረግና ማቋቋም አስፈላጊ ነው፡፡
ለከተማ ወጣቶች የአደባባይ (የጎዳና ዳር) መሸጫዎችን ማመቻቸት፣ አዳዲስ የስራ መስኮችን መክፈት፣ ተጀምሮ የነበረውን ተዘዋዋሪ ፈንድ መፍቀድ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች (NGOs) በስፋት እንዲቋቋሙና ለወጣቶች የስራ እድል እንዲፈጥሩ ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ በመጨረሻም የሀገሪቱን የገንዘብ ኖት በመቀየር የተረጋጋ የኢኮኖሚ ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረግ ከኢኮኖሚ አኳያ መወሰድ የሚገባቸው እርምጃዎች ናቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡
ከማህበራዊ ጉዳይ አኳያ በተቋቋመው የሰላምና የእርቅ ኮሚሽን አማካይነት በመላ ሀገሪቱ የሰላምና የእርቅ ኮንፈረንሶችን በማካሄድ በህብረተሰቡ ውስጥ ያሉ ቂምና ቁርሾዎችን ለማከም ጥረት ማድረግ ቀዳሚው ተግባር መሆን አለበት፡፡ ሌላው የህዝብ ኮሚቴዎችን ማቋቋም ነው፡፡ ኢህአዴግ ስልጣን እንደያዘ “የሰላምና መረጋጋት ኮሚቴ” የሚባሉ አካላት በየቀበሌው ተቋቁመው ነበር፡፡ አሁንም የመንግስት መዋቅሮችን የሚያግዙ “የሰላምና መረጋጋት” ኮሚቴዎች (ስያሜው ሊታይ ይችላል) እንዲቋቋሙ ቢደረግና ሌብነትን መከላከል፣ የአካባቢን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ፣ መንግስት የሚፈልጋቸውን ወንጀለኞች ለፖሊስ ማስረከብ፣ ደንና የዱር አራዊትን መጠበቅ፣ ቤተ-እምነቶችን መጠበቅ፣ የአካባቢ ኢንቨስትመንቶችና የመንግስት ተቋማት ጥቃት እንዳደርስባቸው መከላከል፣… የመሳሰሉትን ስራዎች እንዲሰሩ ማድረግ፣ ሰላማችንን ለማረጋገጥ ይረዳናል የሚል እምነት አለኝ፡፡
በዚህ ወቅት በቴሌቪዥን ከምንሰማቸው አሰልቺ ነገሮች አንዱ የሙስና ተጠርጣሪዎች የ14 ቀን የምርመራ ማራዘሚያ ነው፡፡ በፖሊስ ተጠርጥረው በተያዙ ሰዎች ላይ ፍ/ቤት በተደጋጋሚ የ14 ቀን የእስር ፈቃድ እየሰጠ በታሳሪዎችና በህዝቡ ዘንድ ጥርጣሬን ከሚፈጥር (አንዳንዶቻችንን ከሚያሰለቸን) ተጠርጣሪዎቹ በቁም እስር (House Arrest) በቤታቸው እንዲቀመጡ ተደርጎ የምርመራ ስራው እንዲካሄድ ማድረግ የተሻለ አማራጭ ሆኖ ይታየኛል። እንዲህ ያለው አሰራር በብዙ የአውሮፓ ሀገሮች ጭምር ይሰራበታል፡፡
ጸሐፊውን በEmail: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 3000 times