Print this page
Saturday, 16 February 2019 14:23

የካዚኖዋ እመቤት

Written by  መሐመድ ኢድሪስ
Rate this item
(13 votes)


          ዳንኤል ግራንት፤ ላስቬጋስ ውስጥ በግራንት ካዚኖ የቁማር አጫዋች ነው፡፡ ለረጅም ጊዜ ምናልባት በጣም ካልተጋነነ የሃያ አመት ቁማር የማጫወት ልምድ ያለው ሲሆን ይህ ልምዱም በጣም ተከማችቶ የራሱን የቁማር ማጫወቻ ቤት ለመክፈት አድርሶታል፡፡
ለረጅም ጊዜ ባጠራቀመው ገንዘብ አንድ አፓርታማ ከገዛ በኋላ የድሮ ተጫዋች ጓደኞቹን አሰባስቦ፣ አንዳንዴም በብላሽ እየጋበዘ፣ ቤቱን ማለማመድ ጀመረ፡፡ ብዙ ጊዜ ቢፈጅበትም በመጨረሻ ተሳክቶለታል፡፡ አልፎ አልፎ የሚመጡት አዳዲስ ደንበኞች ሳይቆጠሩ እስከ መቶ ሺህ ዶላር መመደብ የሚችሉ ደርዘን ያህል ሃብታም ተጫዋቾች ግን የግሉ ናቸው፡፡
በዚህ ሁኔታ ለአንድ አመት ያህል ከቆየ በኋላ በጣም ዝነኛ ያልሆነው ግራንት ካዚኖ፤ ከአስር ሚሊዮን ዶላር በላይ ካፒታል በላይ ያለው ድርጅት ለመሆን በቃ፡፡ ዳንኤል ግራንት፤ ለረጅም ጊዜ ባካበተው የመጫወትና የማጫወት ልምዱ ሁሌ አትራፊ ለመሆን ችሏል፡፡
ማንም ውርጋጥ ተጫዋች የቤቱን ደረጃ ዝቅ እንዳያደርገው የሰለጠኑ አስተማማኝ ታጣቂዎችን ቀጠረ፡፡ የደንበኞችን ምቾት ለመጠበቅ ወለሉ በውድ ምንጣፍ እንዲያጌጥ ከማድረጉም በላይ ለደንበኞቹ ምቾት ከቆዳ የተሰሩ ሶፋዎችን አስመጣ፡፡ በእርግጥ ያለው የማጫወቻ ጠረጴዛ አንድ ቢሆንም ይህንን ያደረገበት ምክንያት አለው፡፡ ጋጋታ ስለማይፈልግ በኮሪደሩ ጠርዝ ላይ ጨዋታውን ያሸነፉ እየተደሰቱ የሚጠጡበት፣ የተሸነፉ ደግሞ እየቆዘሙ የሚተክዙበት አነስተኛ ባር አለ፡፡
ሁኔታው ለዳንኤል እንዲህ አስተማማኝ ሆኖ ለስድስት ወራት ከቆየ በኋላ ከእለታት አንድ ቀን ያልተለመደ አዲስ ክስተት ተፈጠረ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡
አርብ ማታ ከምሽቱ አራት ሰአት ሲሆን አንዲት በጣም ውብ ጥቁር ፀጉር ያላት፣ ረጅም አረንጓዴ የእራት ልብስ የለበሰች ሴት ተከሰተች። እሷን መፈተሽ መቸም የማይታሰብ ነው፡፡ ሁሉም በፈገግታ እጅ እየነሳ መንገድ ለቀቀላት፡፡ ሽቶዋ ቤቱን አወደው፡፡
ዳንኤል በፈገግታና በአክብሮት ምን እንደምትጠጣ ጠየቃት፡፡
“ነጭ ወይን-----ፈረንሳይ” አለች ሙዚቃ በሚመስል ድምጽ፡፡
ቀረበላት፡፡ በጠረጴዛው ዙሪያ ከእሷ ጋር አራት ሰዎች ተቀመጡ፡፡
“--- ይሻላል ወይስ -- ወይስ ኮንከር?”
“እኔ ኮንከር እመርጣለሁ” አለች የምሽቱ እመቤት፡፡
 ሁሉም ሞቅ ባለ ፈገግታ መስማማታቸውን ገለፁ፡፡
ዳንኤል አዲስ ካርታ ፈታና በጥንቃቄ መበወዝ ጀመረ፡፡  
“በስንት እናድርገው?” ጠየቀ ዳንኤል፡፡
“እኔ ሁለት መቶ ሺህ ዶላር ይዣለሁ”
ሁሉም ተስማሙ፡፡
“ካሽ?”
“እኔ ቼክ ነው የያዝኩት”… አለ፤ነጭ ሱፍ የለበሰ፣ ረጅም መልከ መልካም፣ ቄንጠኛ ሪዝ ያለው ተጫዋች፡፡ ዳንኤል ቼኩን ተቀበለ፡፡
በመሃል “ይቅርታ” አለና  ወደ ውስጠኛ ቢሮው ገብቶ፣የረጅም ጊዜ የባንክ ባለሙያ ለሆነው ጓደኛውና የጥቅም ተካፋዩ ደወለ፡- “ማስተር ዊልያም ስሚዝ፣ የባንክ ቁጥር 9044፣ ቢይ ኢንተርናሽናል ባንክ… አካውንት እይልኝ”
ከሶስት ደቂቃ በኋላ ባንከሩ መልሶ ደወለለት፤ “ስድስት መቶ ሺህ ዶላር አለው” አለው፡፡
ዳንኤል ሁለት መቶ ሺህ ዶላር የተፃፈበትን ቼክ ይዞ ወደ ጠረጴዛው መጣና ፈገግ ብሎ፤
 “መቀጠል እንችላለን” አለ፡፡
በአራት ደቂቃ ውስጥ ጨዋታው ተጠናቀቀ። እመቤቲቱ ስምንት መቶ ሺህ ዶላር በላች፡፡ የወይዘሮዋ መኪና መብራቱን አብርቶ ሲፈተለክ፣ ባንኮኒው ላይ ዊስኪ እየጠጣ የሚቆዝመውን  ነጭ ሱፍ የለበሰ፣ አዲሱን የተከበረ ደንበኛ፣ የስራው ፀባይ ነውና ማጽናናት ነበረበት፡፡
“እስከፈለግከው ድረስ መጠጣት ትችላለህ” አለው፡፡ ጀርባውን እየጠበጠበ፡፡
“ምን ይደረግ?”
“መምጣትዋ አይቀርም እናገኛታለን፡፡”
ያለው አልቀረም፡፡ በነጋታው ቅዳሜ መጣች። ያው የተለመደው ጨዋታ ቀጠለ፡፡ ዳንኤል በጥንቃቄ በወዘ፡፡
“በስንት እናርገው?”
“እኔ ችግር የለብኝም፡፡”
“በአራት ለምን አናረገውም?” ሃሳብ አቀረበ፤ ዳንኤል
በግዴለሽነት ትከሻዋን ሰበቀች፡፡
ዶላሩ ተመደበ፡፡ ጨዋታው ቀጠለ፡፡ ስድስት ደቂቃ አልፈጀም፡፡ ጨዋታው በሴትየዋ አሸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡ ዶላሩ ሳምሶናይቱ ላይ ሲደረደርላት፣ ወይንዋን ይዛ ስትዝናና ዳንኤል ጠጋ ብሎ “እንዳንቺ አይነት ተጫዋች አይቼ አላውቅም… ብንተዋወቅ” አለ በጨዋታ ያልቻላትን ሴት በፍቅር አጥምዶ ብሩን ለማስመለስ እያደባ፡፡
“ሚስዝ ስሚዝ” አለችው፤ ፈገግ ብላ፡፡
“ኦው አግብተሻል?!”
“አዎ አልመስልም?” አለችው፤ አይኑን በአይንዋ እየሰረሰረች፡፡
“ትመስያለሽ” አለ፣ እሱም አይኑን ከአይንዋ ሳይነቅል፡፡
“መልካም ምሽት” አለችው፡፡
“ኦ ነገ ብትመጪ ሌሎች የተሻለ አቅም ያላቸው ደንበኞች አሉኝ፤ ትመጫለሽ?”
“ነገ የለሁም”
ወጣች፡፡ ዳንኤል ደንበኞቹን አጽናንቶ፣ ነገ አዲስ ቀን እንደሆነ ዞር ሲል ሁሉም አሉ፤ ከአንዱ በስተቀር፡፡  ቄንጠኛ ሪዝ ያለው መልከ መልካሙ መጤ ተጫዋች አልነበረም፡፡
“የት ሄደ እዚህ የነበረው እንግዳ?” ጠየቀ፡፡
ማንም የሚያውቅ አልተገኘም፡፡ ክፍሎቹን እየከፋፈተ ዞር ዞር ብሎ ፈለገ፡፡ ሰውየው የለም። ነገር ውስጡ ገባና፣ ወደ ቢሮው አምርቶ፣ ጠረጴዛውን ከፍቶ ቼኩን አወጣና ተመለከተ። “ዊልያም ስሚዝ” ይላል፤ ፊርማው፡፡ ለአፍታ በዓይነ ህሊናው ወደ ኋላ ተጓዘ፡፡ ሰውየው ሁለቱንም ምሽት የተቀመጠው ከእመቤቲቱ ሴትየዋ ጋር በግራ በኩል ነበር፡፡ ምርጥ ምርጥ ቁጥር እየሰጣት፣ ጨዋታውን ለሁለት የተጫወቱ ባልና ሚስት መሆናቸውን የተረዳው ዘግይቶ ነው፡፡
ነግራዋለች፡፡ ነገ የለችም፡፡

Read 2978 times