Print this page
Saturday, 16 February 2019 14:34

መደመር

Written by  አሸናፊ ግጥሞች
Rate this item
(2 votes)

ከአዘጋጁ፡- አዲስ አድማስ ጋዜጣ ባለፈው ነሐሴ ወር ባወጣው “የመደመር የግጥም ውድድር” በርካቶች የተሳተፉ ሲሆን የዩኒቨርሲቲ የግጥም ባለሙያዎችና የሥነጽሁፍ ሃያሲያን ግጥሞቹን ገምግመው ከ1ኛ-3ኛ የወጡትን ይፋአድርገዋል፡፡ አሸናፊዎቹም ባለፈው ሰኞ በብሔራዊ ቴአትር በተካሄደው “የመደመር” እና የፍቅር የኪነጥበብ ምሽት ላይ ግጥሞቻቸውን ለታዳሚያን እያነበቡ ሽልማቶቻቸውን ተቀብለዋል፡፡ 1ኛ የወጣው ላፕቶፕ፣ 2ኛ የወጣው ዘመናዊ ስማርት ፎን፣ 3ኛ የወጣው መለስተኛ ስማርት ፎን ተሸልመዋል፡፡ ሦስቱን አሸናፊ ግጥሞች ለአንባቢያን የምናቀርብ ሲሆን ከዚህ በታች የቀረበው ሦስተኛ የወጣው ግጥም ነው፡፡ ቀሪዎቹን ደግሞ በመጪዎቹ ሳምንታት፡፡

መደመር

ዝንጉ ዘመን ይዞን
የተረሳ መሰል የትንቢት ቋጠሮ
የማናረፍድበት ባበሻ ወጋችን
ባቻምናው አኗኗር በጥንት በድሮ
በሃሳብ በፀሎት፣ በትግል በተስፋ፣ በእንባ ተቋጥሮ
በሚመጣ ቀን ውስጥ በነገ ዓለም ተስፋ
መቼት ሳይነገር፣ በወል ያፀናነው፣ ከልብ የተሰፋ
ነበረን ቀጠሮ እንገናኝ ያልነው፣ አልፎልን ለከርሞ
ቀኑ ደረሰልን አገኘነው ደግሞ
ትናንትና ስንል
ትዝታው መጥፎ ነው ያመጣን ጎዳና
ሁሉም ወድቆበታል፤
ማንም የለም ንፁህ፣ አንድ እንኳን የፀና
ካራ አሳስቦናል፣ ደም አላልሶናል፣ በከፋ ጥላቻ
ሙሉ እንጀራ ሽተን፣ ለመሶብ ተጋድለን፣ አጥተናል እንጎቻ፡፡
ዛሬ ማለት ለኛ
አዲስ ፀአዳ ቀን፣ እለተ ደስታ
ጀብዳዊ ጀግንነት፣ በጀብዳዊ ይቅርታ
አንተ ትብስ አንቺ፣ በገድሎ ድል ፈንታ
ነግሰው የሚታዩበት
ህልም አለም ሚመስል
ማይባል ህልም እልም፡፡
ገዳይ ሟችን አቅፎ
እጅና እግሩን ሲስም
ዛሬ ማለት ለኛ
የቀጠሮ ቀን ነው፤
ሳንል ያገኘነው አሲዮ ቤሌማ፤
ድምፅ የሰማንበት
የፍቅር ዜማ፡፡
ነገ ማለት ለኛ
ሁሉም ወንዝ ዉሃ ነው፣
ይጠጣል ከሁሉ
ከሩቅም ከቅርብም
የተጠሙ በጎች እኩል ይጠጣሉ፤
መደመር ‘ምንለው የቃል ግብሩ መፍቻ
በጊዜ ሰንሰለት፣ ትላንት፣ ዛሬ ነገን፣ ካዛመደ ብቻ፡፡
(በተስፋ ልደት ብዙወርቅ)

Read 1840 times