Print this page
Tuesday, 19 February 2019 00:00

የግብጽ ፓርላማ የፕሬዚዳንቱን የስልጣን ዘመን ለማራዘም ወሰነ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የግብጽ ፓርላማ አባላት የፕሬዚዳንቱን የስልጣን ዘመን የሚያራዝመውንና የአገሪቱን መሪ አብዱል ፈታህ አልሲሲን ለተጨማሪ 12 አመታት በስልጣን ላይ ለማቆየት ሆን ተብሎ የታቀደ ነው የተባለውን የህገ-መንግስት ማሻሻያ ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ከትናንትና በስቲያ በከፍተኛ የድጋፍ ድምጽ ማሳለፋቸው ተዘግቧል፡፡
ከአገሪቱ 596 የፓርላማ አባላት መካከል 485ቱ ድጋፋቸውን የሰጡት የህገመንግስት ማሻሻያ፣ ሁለተኛ የስልጣን ዘመናቸውን ከሶስት አመታት በኋላ የሚያጠናቅቁት ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ለተጨማሪ ሁለት የስልጣን ዘመናት ወይም 12 አመታት በስልጣን ላይ እንዲቆዩ የሚያስችል መሆኑን ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል፡፡
በፕሬዚዳንት አልሲሲ ደጋፊዎች የተሞላው የግብጽ ፓርላማ በአብላጫ ድምጽ የደገፈው የውሳኔ ሃሳብ፣ እ.ኤ.አበ2014 በጸደቀው የአገሪቱ ህገመንግስት ላይ የተቀመጠውን የፕሬዚዳንቱ የስልጣን ዘመን ከአራት አመት ወደ ስድስት አመት የሚያራዝም ሲሆን፣ ለፕሬዚዳንት አልሲሲ የፍርድ ቤት ዳኞችንና ዋና አቃቤ ህግን መሾምን ጨምሮ የተለያዩ ተጨማሪ ቁልፍ ስልጣንና ሃላፊነቶችን የሚሰጥ ነው በሚል እየተተቸ መሆኑን ገልጧል፡፡
አልሲሲ ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን በአገሪቱ ፕሬዚዳንትነት የመቀጠል እቅድም ሆነ የህገመንግስት ማሻሻያ በማድረግ ስልጣን የማራዘም ዕቅድ የለኝም ሲሉ በ2017 ለቢቢሲ መናገራቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ባለፈው አመት መጋቢት ወር ላይ በ97 በመቶ ድምጽ ተመርጠው ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን መቀጠላቸውን ባረጋገጡ ማግስት ግን ደጋፊዎቻቸው የህገመንግስት ማሻሻያ ተደርጎ የፕሬዚዳንቱ የስልጣን ዘመን ይራዘም የሚል ሃሳብ ይዘው መነሳታቸውን አስታውሷል፡፡
የህገመንግስት ማሻሻያው በአገሪቱ ልዩ የህገመንግስታዊና የህግ ጉዳዮች ኮሚቴ ከተመከረበት በኋላ ለመጨረሻ ውሳኔ ዳግም ወደ ምክር ቤቱ እንደሚላክ የጠቆመው ዘገባው፣ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ በአገር አቀፍ ደረጃ ህዝበ ውሳኔ ተደርጎበት የሚጸድቅ ይሆናል ብሏል፡፡

Read 6882 times
Administrator

Latest from Administrator