Saturday, 16 February 2019 14:40

አልኮሆል እና እርግዝና

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(2 votes)


         የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ፌብሩዋሪ 5-6/በአዲስ አበባ አመታዊ ጉባኤውን ማካሄዱን ባለፈው እትም አስነብበናችሁዋል፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ የተለያዩ ሳይንሳዊ ጥናቶች የቀረቡ ሲሆን ከዚህም አንዱ በእርግዝና ወቅት አልኮሆልን መጠቀም ያለውን ጉዳት የሚያ ሳየው ነበር፡፡ ይህንን በሚመለከት ጥናታቸውን ያቀረቡት አቶ አባተ ዳርጌ ሲሆኑ በሳይንስ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የሰሩ ናቸው። ጥናቱም የተካሄደው በ2018/ዓም/ በሰሜን ሸዋ ዞን በደብረ ብርሀን ሆስፒታል የእርግዝና ክትትል በማድረግ ላይ የነበሩ እናቶች ላይ ነው፡፡ እንደውጭው አቆጣጠር April-May,2018/ በጥናቱ የተካተቱት እናቶች ቁጥርም በዚህ ወቅት ለእርግዝና ክትትል የመጡ በሙሉ ናቸው፡፡ አላማውም ችግሩን ለይቶ ለማወቅና ተያያዥ ምክንያቶችንም ለመጠቆም ነው፡፡ አንዳንድ መረጃዎች የሚያስነብቡትንም ጨምረን ወደአማርኛ መልሰናል፡፡                                            
በእርግዝና ወቅት አልኮሆል መመጠጣት የሚያስከትለው ችግር፡-
አልኮሆል በአካልም ይሁን በሕይወት ላይ አስጊ የሚሆንበት አጋጣሚ አለ፡፡ የሰው ሰውነት አልኮሆል ላይ ጥገኛ አለመሆኑን በአሜሪካ የተደረገ ጥናት  ያሳያል።
በ2011/በኢትዮጵያ የተደረገው ጥናት (EDHS,2011) አልኮሆልን በመጠጣቱ ረገድ ያለውን ልምድ እንደሚያ ሳየው ከሆነ፡-
45 በመቶ ሴቶች እና 53 በመቶ ወንዶች ይጠጣሉ፡፡
የመጠጡም አይነት በቤት ውስጥ የሚመረት ባህላዊ መጠጥ ጠላ ወይንም ጠጅ የመሳሰሉት እድሜና ጾታ ወይንም ማርገዝ አለማርገዝ ሳይመርጥ ለሁሉም የተፈቀደ የሚመስል መጠጥ ስለሆነ ብዙዎች ጎጂነቱን ሳያስቡ ይጠቀሙበታል።
አልኮሆል በእርግዝና ወቅት ሲጠጣ በእናትየው ደም አማካኝነት በእንግዴ ልጅ በኩል ወደተረገዘው ሕጻን ይተላለፋል፡፡ ስለዚህም እናትየው ስትጠጣ የተረገዘው ልጅም አልኮሆል ይጠጣል ማለት ነው። ይህ ደግሞ ለእናትየውም ይሁን ለጽንሱ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል እውነታው ታይቶአል።
አንዳንዶች በሚሰጡት አስተያየት ይህን ያህል መጠን ያለው ወይንም በዚህን ጊዜ አልኮሆል ቢጠጣ ይጠቅማል ሊሉ ይችላሉ፡፡ ይህንን ግን ሳይንሱ በጭራሽ አይደግፍም፡፡
በእርግዝና ወቅት በምንም መጠን አልኮሆል መውሰድ አይገባም፡፡
በእርግዝና ወቅት ጊዜን ለይቶ ወይንም መጥኖ በዚህ ጊዜ አልኮሆል መጠጣት አለበት የሚባልበት ጊዜ የለም፡፡
በእርግዝና ወቅት የትኛውም አይነት መጠጥ ለመጠጣት አይመረጥም፡፡ ሁሉም የአልኮሆል መጠጦች በእርግዝና ወቅት ጎጂ ናቸው፡፡
አልኮሆል በእርግዝና ላይ ያለውን ጽንስ ለማጥፋት እና ጉዳት ለማድረስ የሚችል ጎጂ የሆነ መጠጥ ነው፡፡
በእርግዝና ወቅት የአልኮሆል መጠጥ የሚወሰድ ከሆነ የሚወለደው ልጅ የተለያዩ ችግሮችን ሊያሳይ ይችላል፡፡
በትምህርት ወቅት ትምህርትን የመቀበል ችግር ያሳያል፡፡
ነገሮችን የማስታወስ ብቃት አይኖረውም፡፡
ትኩረት የማድረግ ችግር ይኖርበታል፡፡
ከሰዎች ጋር የመግባባት ችሎታ አይኖረውም፡፡
የመስማት ወይንም የማየት ችግር ሊገጥመው ይችላል፡፡
በእርግዝና ወቅት ከ150/ግራም በላይ አልኮሆል ከሚጠጡ እናቶች የሚወለዱ 33/ከመቶ የሚ ሆኑ ሕጻናት ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ይስተዋልባቸዋል፡፡ አልኮሆል ከሚጠጡ እናቶች የሚወለዱ ልጆች የብቃት ማነስ ችግር እና የባህርይ እንዲሁም ትምህርት የመማር ችግር ስለሚኖራቸው ሁልጊዜም እራሳቸውን ተወዳዳሪ ማድረግ ይሳናቸዋል፡፡
በተለይም፡-
እንደሂሳብ ያሉ ትምህርቶችን የመቀበል ችግር ይኖርባቸዋል፡፡
ነገሮችን ካለፉ በሁዋላ የማስታወስ ችግር አለባቸው
ነገሮችን በትክክለኛው መንገድ መፈረጅ ወይንም በአንድ ነገር ላይ ትክክለኛውን ፍርድ መስጠት፤ መወሰን ያቅታቸዋል፡፡
አንድን ነገር ፈጥኖ ለማሰብ ወይንም ለማድረግ አይችሉም፡፡  
አልኮሆል ከሚጠጡ እናቶች የሚወለዱ ልጆች የተለያዩ የጤና እውክታዎችም ሊኖሩአቸው ይችላል፡፡  
የልብ ሕመም፤
የኩላሊት ሕመም፤
የአጥንት ሕመም አንዳንዴም ከመስማት ችግር ጋር ይታይባቸዋል፡፡
በእርግዝና ወቅት አልኮሆል መጠጣት ለተረገዘው ጽንስ ብቻም ሳይሆን ለእናትየውም ጤና ችግር ማስከተሉ እሙን ነው፡፡
ሌሎች ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በእርግዝና ወቅት አልኮሆል ከሚጠጡ እናቶች የተወለዱ ልጆች የተለያዩ አካላዊ ምልክቶች ሊኖራቸው ይችላል፡፡ Dr. Kristin Daniel እንደሚሉት፤
አንዳንድ ሕጻናት አይኖቻቸው በደንብ ላይከፈቱ ይችላሉ፡፡
በአፍንጫ እና በላይኛው ከንፈር መካከል ያለው ስፍራ ጠባብ መሆን፤
የላይኛው ከንፈር ስስ መሆን፤
የጭንቅላት መጠን ትንሽ መሆን፤ የቁመት ማጠር፤ የአካል ቅጥነት፤
የመሳሰሉት አካላዊ ችግሮች ሊታዩባቸው ይችላሉ፡፡
በእርግዝና ወቅት መጠጥ የሚጠጡ እናቶች በእንግዴ ልጅ በኩል በቀጥታ ለጽንሱ መጠጡ ስለሚተላለፍ ከሚደርሰው የአካል መሙዋላት ችግር በተጨማሪ የነርቭ ስርአት ችግርም አልፎ አልፎ በልጆቹ ላይ ይታያል፡፡ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት የሆኑት ዶር/ Daniel እንደ ሚገልጹት ልጆቹ ከሰው ጋር የመተባበር ድክመት፤ በአንዳንድ የልማት ስራዎች ላይ ለስኬት መዘግየት ፤አንዳንድ የባህርይ ችግሮች እና ዝቅተኛ የሆነ የመማርና የማሰብ አቅም በእርግዝና ጊዜ ይጠጡ ከነበሩ እናቶች የተወለዱ ልጆች የሚያሳዩት ባህርይ ነው፡፡   
አልኮሆል ከሚጠጡ እናቶች የተወለዱ ሕጻናት ውለው አድረው አልኮሆል የመጠጣት ባህርይ ሊታይባቸው ይችላል፡፡ በማደግ ላይ ያለው አእምሮአቸው አልኮሆል የሚያደርስባቸውን ችግር መቋቋም ስለማይችል ሁሉንም የአእምሮ ነርቭ ስርአት ሊረብሽና በጠቅላላውም በእድገቱ ላይ ጫና ሊፈጥር ይችላል፡፡ በተጨማሪም የህጻኑ ጉበት እንደአዋቂዎቹ ጉበት አልኮሆል ሰውነትን መመረዝ እንዳይችል ለማክሽፍ አቅም የለውም፡፡ ስለሆነም ጽንሱ አልኮሆሉን እንዳለ ስለሚ ቀበል አል ኮሆሉ ከእናትየው ደም ውስጥ ቢወጣ ወይንም ቢቀንስ እንኩዋን ጽንሱ ጋ ግን እንደነበረ ይቆያል ይላል የዶ/ር Dr. Kristin Daniel ጥናት፡፡   
በአቶ አባተ ዳርጌ ጥናት ማጠቃለያ ላይ እንደተጠቆመው በእርግዝና ወቅት አልኮሆል የመጠጣት ልምድ ከፍተኛ እንደነበርና በቤተሰብ ደረጃ የአእምሮ ጤንነት ሁኔታ ወይንም ጽንስን ከማቋረጥ ፤እንደ ድብርት እና ነገሮችን መርሳት ወይንም የማህበራዊ ድጋፍ አናሳ መሆኑ የመሳሰሉት አልኮሆልን ለመጠጣት ሊገፋፉ እንደሚችሉ በጥናቱ ተደርሶበታል፡፡    
ስለዚህም በእናቶችና በሕጻናት ጤና ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎችና ክሊኒኮች አልኮሆልና እርግዝናን በተመለከተ ለይተው የሚያውቁበትና ጤናን ለመጠበቅ የሚረዱ ትምህርቶችን ለእናቶች መስጠት የሚቻልበት ሁኔታ ቢፈጠር ችግሩን ለመቀነስ እንዲሁም የተሟላ እና ጤናማ አስተሳሰብ ያለው ትውልድ ለማፍራት ይረዳል ባለሙያዎቹ በጥናት እንዳረጋገጡት፡፡
በአልኮሆል መጠጣትና በእርግዝና ምክንያት በልጆች ላይ ይታያሉ ተብለው ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች በሌሎች ምክንያቶችም ሊከሰቱ እንደሚችሉ መጠቆም እንወዳለን፡፡   

Read 4589 times