Tuesday, 26 February 2019 14:53

ሉሲ የሠላም ጉዞዋን በአፋር ጀመረች ጉዞው ምስራቅ አፍሪካን ያካትታል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

ኢትዮጵያን የሰው ዘር መገኛና  ምድረ ቀደምት የሚል መጠሪያ እንድታገኝ ምክንያት የሆነቻት ሉሲ  በመላው ኢትዮጵያና በምስራቅ አፍሪካ አገራት

የምታደርገውን የሰላም ጉዞ፣ ጀመረች - ወደ አፋር በማቅናት፡፡
ከትናንት በስቲያ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተደረገው የሽኝት ጉዞ ላይ እንደተገፀው፤ ሉሲ በአገሪቱ ሁሉም ዋና ዋና ከተሞችና በየከተሞቹ በሚገኙ
ዩኒቨርሲቲዎች በመገኘት፣ ህዝቡ ለሠላም፣ ለፍቅርና ለኢትዮጵያዊነት በጋራ እንዲነሳ የማስተማርና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን የማጠናከር ስራን ትሰራለች፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ካሳሁን፣ በሽኝት ፕሮግራሙ ላይ እንደተናገሩት፤ አሁን በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩት ግጭቶችና
አለመግባባቶችን በማስወገድ፣ ህዝቡ የእርስ በርስ ግንኙነቱን እንዲያጠናክርና ለሰላምና ለፍቅር እንዲነሳ ለማድረግ ታስቦ ፕሮግራሙ መዘጋጀቱን ጠቁመው፣ ሁሉንም
ኢትዮጵያዊ አንድ በሚያደርግና በሚያግባባ መንገድ፣ የሰው ዘር መገኛ የሆነችውና ሉሲን በመያዝ፣ የሰላም ጉዞ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
በታላላቅ የሃይማኖት አባቶች፣ የሰላም አምባሳደሮችና በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ባላቸው የአገር ሽማግሌዎች ታጅባ፣ በየክልሉ በሚገኙ ዋና ዋና
ከተሞችና በምስራቅ አፍሪካ አገራት በምታደርገው ቆይታ፣ ህዝቡን በቅርበት ለማግኘትና ቀደምት ባህሉንና ልምዱን ጠብቆ በሰላምና በመከባበር አብሮ የመኖር
ልማዱን ለማስቀጠል የሚያስችል ታላቅ ተግባር ይከናወናል የሚል እምነት እንዳላቸው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
ይኸው የሰላም ጉዞ፤ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ በሰላም ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ ብሮድካስቲነግ ኮርፖሬት የጋራ ትብብር መዘጋጀቱም ተገልጿል፡፡   



Read 6137 times