Tuesday, 26 February 2019 15:05

“እንኳን ሞት እርጅና አለ አይደለም ወይ?” አለ አንበሳ

Written by 
Rate this item
(9 votes)


ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሰው በነብሰ - ገዳይነት ተጠርጥሮ ተከሶ ፍርድ ቤት ይቀርባል፡፡
አንድ ሌላ ሰው ደግሞ በምስክርነት እዚያው ፍርድ ቤት መጥቷል፡፡
ዳኛ ለምስክሩ፤
“እሺ ያየኸውን ተናገር፡፡”
ምስክር፤
“ሰውየው በሞተ ጊዜ እዚያው አካባቢ ነበርኩኝ፡፡ የጥይት ድምፅ ስሰማ፤ ወደሰማሁበት አቅጣጫ ወዲያውኑ ሄድኩኝ፡፡ ሟቹ ጭንቅላቱን ነበር የተመታው፡፡ ትኩስ ደም እየፈሰሰው ነበር፡፡”
ዳኛ፤
“በትክክል በዐይንህ ገዳይ በጥይት ሲገለው አይተሃል?”
ምስክር፤
“አይ ከተተኮሰ በኋላ ነው የደረስኩት”
ዳኛ፤
“ገዳዩንስ አይተኸዋል?”
ምስክር፤
“አላየኹትም”
ዳኛ
“እንግዲያው ለምስክርነት አትበቃም፤ መሄድ ትችላለህ”
ምስክር ከፍርድ ቤት ሲወጣ ኮሪደሩ ላይ፤
“ወይ ዳኝነት! ወይ ዳኝነት! ወይ ዳኝነት!” እያለ ጮክ ብሎ እየሳቀ ሲሄድ፣ ዳኛው ሰምተው፣ የሥነስርዓት አስከባሪውን ልከው አስጠሩት፡፡
ዳኛ፡-
“ችሎቱን ደፍረሃል”
ምስክር፡-
“ምን አድርጌ ጌታዬ?”
ዳኛ፡-
“እየሳቅህ ተሳልቀሃል”
ምስክር፡-
“ስስቅ አይተዋል?”
ዳኛ፡-
“አላየሁም፡፡”
ምስክር
“እንግዲያው እርሶም ለምስክርነት አይበቁም!” አላቸው፡፡
***
ፍትህን የሚፈታተኑ አያሌ ጉዳዮች እንዳሉ መቼም አይረሱ! ዳኞችም ይፈተሹ፡፡ የአንድ ህዝብ ሥልጣኔ መለኪያ ናቸው ከሚባሉት ነገሮች አንዱ የትምህርት ሥልጣኔ ነው፡፡ ያ ህዝብ ምን ያህል የትምህርት ግብዓትና ጥቅም ገብቶታል እንደማለት ነው፡፡ ዱሮ፡- በመዝሙር ይገለፅ እንደነበረው፡-
“በጠቅል ጊዜ ያልተማረ
ማዘኑ አይቀርም እያደረ
ዐይናችን ታሞ ታውረን
ኃይለሥላሴ አዳኑን” ይባል ነበር፡፡
ለህዝቡ የትምህርትን ግንዛቤ ለማስጨበጥ ብርቱ ጥረት ተደርጓል፡፡ ብዙ ድካም ተደክሟል፡፡ ያ ባይሆን ዛሬ የደረስንበት ደረጃ ባልተደረሰም ነበር፡፡ ከዕቅዳችን ሁሉ ትልቁ ትምህርት ሊሆን ግድ ነው፡፡
“ዕቅድህ የአንድ ዓመት ከሆነ ጤፍ ዝራ፡፡ ዕቅድህ የአምስት ዓመት ከሆነ ባህር ዛፍ ትከል፡፡ ዕቅድህ የዘለዓለም ከሆነ ልጅህን አስተምር” የሚባለውም ለዚሁ ነው፡፡
አበው ፀሃፍትም፤
“ይህቺን ጨቅላ መጽሐፍ የምታነቡ ሁሉ
አደራ ስለእኔ ማርያም ማርያም በሉ
ከሆዴ ያለውን የትምህርት ሽል
ያለጭንቅ እንድወልድ እንድገላገል
ከሃያ ስድስቱ ወንዶች ፊደላት
አርግዣለሁና መዝገበ - ቃላት
ለትምክህት አይደለም ይህን መናገሬ
ለማስቀናት እንጂ ሰነፉን ገበሬ
ሃዋርያው ሲናገር ወደ ምዕመናኑ
ለምትበልጥ ፀጋ ይላል ቅኑ አስቀኑ”
ስለዚህ ለተሻለ ዕውቀት እንቅና እናስቀና፡፡ በዚህ መልክ አገር ትሻሻላለች፡፡ ሙያዊ ክህሎትን ማሳደግ፣ ትክክለኛው ሰው በትክክለኛው ቦታ መመደቡን ማረጋገጥ፣ የሥራ ክትትልና ቁጥጥር (Monitoring and Evaluation) ላይ ማተኮር፣ ከአፍ አልፎ በተግባር ሲፈፀም እንይ፡፡ ለዕድገት እንጓጓ፡፡ ከልምድ ለመማር እንጓጓ፡፡ እርስ በርስ ለመማማር እንታትር፡፡
ይህን በሥራ ላይ ለማዋል ጥበብ ያስፈልጋል፡፡ መላ ያስፈልጋል፡፡ ዋናው ሃሳብ እንዳያረጅብን መጣጣር ነው፡፡ “እንኳን ሞት እርጅና አለ አይደም ወይ?”
ያለው አንበሳ ወዶ አደለም፡፡ አዳዲስ ዘዴ እንፍጠር!

Read 9838 times