Sunday, 24 February 2019 00:00

ኢትዮጵያ በጣሊያን ወራሪ መንግስት ለተፈፀመባት ዘግናኝ እልቂት ተገቢ ካሳ እንድትጠይቅ ጥሪ ቀረበ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)


- በ5 አመቱ የኢጣሊያ ወረራ ከ1 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በግፍ ተጨፍጭፈዋል
- የቫቲካን መንግስት የኢትዮጵያን ህዝብ በይፋ ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል ተብሏል
- ጠቅላይ ሚ/ር ዐብይ አህመድ በካሳ ጥያቄው ላይ ጫና እንዲያሳድሩ ተጠይቋል


ከ82 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ በወራሪው የኢጣሊያን መንግስት በተፈፀመባት ወረራ በግፍ ለተሰውት ንፁሃን ዜጐችና ለወደመባት ንብረት ተገቢ ካሳ ሊከፈላት እንደሚገባ የሚጠይቅ  አለም አቀፍ ንቅናቄ መጀመሩ ይፋ ሆነ፡፡
አለምአቀፍ ህብረት ለፍትህ የኢትዮጵያ ጉዳይ (Global alliance for justice the Ethiopian Case) የተባለው አለም አቀፍ ድርጅት ይፋ ያደረገው ይኸው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የየካቲት 12/1929 ዘግናኝ እልቂትን ጨምሮ ጣሊያን በአምስት ዓመቱ የወረራ ዘመን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያንን በግፍ የጨፈጨፈች ሲሆን ለዚህ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቷ ለኢትዮጵያ መንግስት ተገቢ ካሳ ልትከፍልና ህዝቡን በይፋ ይቅርታ ልትጠይቅ ይገባል ተብሏል፡፡
በድርጅቱ ይፋ የተደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ አገራት በተለያዩ ጊዜያት ወረራ በመፈፀም በግፍ ለጨፈጨፏቸው ንፁሀን ዜጐችና ላወደሙት ንብረት በቢሊዮኖች የሚቆጠር ካሳ እየከፈሉና ህዝቡን በይፋ ይቅርታ እየጠየቁ ይገኛሉ። በደል የተፈፀመባቸው አገራትም ሊከፈላቸው የሚገባውን የካሳ መጠን በመግለጽ፣ ጥያቄ እያቀረቡ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት ግን እስከአሁን ምንም አይነት ጥያቄ ሳያቀርብ ቀርቷል፡፡
በዚህ ምክንያትም ጣሊያን በኢትዮጵያ ላይ የፈፀመችውን ዘግናኝ እልቂት አስመልክቶ ለኢትዮጵያ ተገቢውን ካሳ እንድትከፍል ለማድረግ የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩንና የፊርማ ማሰባሰብ ሂደት በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡ አለም አቀፍ ህብረት ለፍትህ የኢትዮጵያ ጉዳይ፤ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ኢትዮጵያ በጣሊያን መንግስት ለተፈፀመባት ኢ-ሰብአዊ ወንጀል ተገቢ ካሳ እንድትጠይቅና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ጫና እንዲያሳድሩ የሚያሳሰብ ደብዳቤ መላኩም ታውቋል፡፡
ድርጅቱ ይፋ ባደረገው በዚሁ መረጃ ላይ እንደተመለከተው፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤ የጣሊያን መንግስት በኢትዮጵያውያን ላይ የፈፀመውን ዘግናኝ ግፍ እንዲመዘግብ፣ የኢጣሊያ መንግስት ተገቢውን ካሳ እንዲከፍል፤ የቫቲካን መንግስት ፋሽስት ኢ-ጣሊያን በመደገፍ በኢትዮጵያውያን ላይ ለተፈፀመው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ተባባሪ በመሆኗ የኢትዮጵያ መንግስትንና ኢትዮጵያውያንን በይፋ ይቅርታ እንድትጠይቅ፣ በቫቲካና  በጣሊያን መንግስት የተዘረፉ ንብረቶች ለኢትዮጵያ እንዲመለሱና በኢጣሊያ የተሰራው የጦር ወንጀለኛው የግራዚያኑ መታሰቢያ ሃውልት እንዲፈርስ የሚጠይቅ እንደሆነም ታውቋል፡፡
በአምስት ዓመቱ የኢጣሊያ ወረራ ዘመን ከተጨፈጨፉት ንፁሐን ዜጐች በተጨማሪ ከ14 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ከብቶች ማለቃቸውንና ለዚህ ሁሉ ኢ-ሰብአዊ ወንጀልና የግፍ ጭፍጨፋ የኢጣሊያ መንግስት ለኢትዮጵያ  የሰጠው የቆቃ ግድብ የተሰራበት 25 ሚሊዮን ዶላር ብቻ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
ኢጣሊያ በሊቢያ ላይ ለፈፀመችውና ከ30ሺ በላይ ሊቢያውያን ላለቁበት ጭፍጨፋ የኢጣሊያ መንግስት በቅርቡ አምስት ቢሊዮን ዶላር ካሳ ለመክፈል መስማማቷ ይታወሳል፡፡      

Read 6179 times