Sunday, 24 February 2019 00:00

የህዝብ ቆጠራ ጊዜ እንዲራዘም ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)


በመጪው ወር ይከናወናል የተባለው ሃገር አቀፍ የህዝብና ቤቶች ቆጠራ መርሃ ግብር እንዲራዘም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቀ (አብን) የጠየቀ ሲሆን የ1999 ዓ.ም ቆጠራ ውጤትም ከወዲሁ እንዲሠረዝ ጠይቋል፡፡
በ1998/99 ዓ.ም በተደረገው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ 2.5 ሚሊዮን የአማራ ህዝብን ጨምሮ የአዲስ አበባ፣ የጉራጌና የቅማንት ህዝብ ላይ የቁጥር መቀነስ ተደርጎ እንደነበር ያስታወቀው ንቅናቄው፤ ይህ የቁጥር ማቀናነስ ገለልተኛ ኮሚሽን ተቋቁሞ እንዲጣራም ጠይቋል፡፡
ዘንድሮ የሚካሄደው የህዝብ ቆጠራ የ1998/99 ቆጠራን መነሻ አድርጎ እንዲተገበር አብን አሳስቧል፡፡ ከወር በኋላ ይካሄዳል ተብሎ ለታቀደው ቆጠራ ሁለንተናዊ በቂ ዝግጅት አልተደረገም የሚል እምነት እንዳለው ያስገነዘበው ንቅናቄው፤ የቆጠራው አስተባባሪ፣ አስፈፃሚና ኮሚሽን አባላትም እንደገና እንዲመለመሉና የህዝብና ቤቶች ኮሚሽንም በድጋሚ እንዲደራጅ ጠይቋል፡፡ በ1998/99 በተደረገው ቆጠራ በኃላፊነት የተሳተፉ ግለሰቦች ከኃላፊነታቸው እንዲነሱና በህግ እንዲጠየቁም ንቅናቄው ጠይቋል፡፡
የማንነት ጥያቄ ባላቸው የወልቃይትና የራያ አካባቢዎች ቆጠራው ከመከናወኑ አስቀድሞ አካባቢዎቹ በፌደራል መንግሥቱ ሙሉ ቁጥጥር ስር እንዲሆኑን አብን ያሳሰበ ሲሆን እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ሳይፈፀሙ የሚደረግ ቆጠራና ውጤቱ ተቀባይነት የለውም ብሏል፡፡



Read 7275 times